ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 18 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, May 2, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 18

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሚያዝያ ዐሥራ ስምንት በዚህች ቀን የቅዱስ ሱስንዮስ አገልጋይ ቅዱስ_አውሳብዮስ በሰማዕትነት አረፈ፣ የአባ ብሶይ ወንድም አባ_ጴጥሮስ በሰማዕትነት አረፈ።




ሚያዝያ ዐሥራ ስምንት በዚህች ቀን የቅዱስ ሱስንዮስ አገልጋይ ቅዱስ አውሳብዮስ በሰማዕትነት አረፈ፡፡
ዲዮቅልጥያኖስም ቅዱስ ሱስንዮስን በሚያሠቃየው ጊዜ ንጉሥ ሆይ አውሳብዮስ የሚባል አገልጋይ አለው፣ እርሱም በፍጹም ልቡ እንደ ጌታው ክርስቶስን ያመልከዋል፡፡ የአንተን አማልክ አያመልክም አሉት፡፡ አምጡት አለ፡፡ ወደ እርሱ በቀረበ ጊዜ ስለ ሃይማኖቱ ጠየቀው፡፡ እርሱም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ፡፡ ንጉሱም ብዙ አባበለው አማልክቶቹን ማምለክ በመተው ገሰጸው፡፡ ቅዱሱም የዕውነተኛ አምላክ የአግዚአብሔርን አምልኮ በመተው ንጉሡን መልሶ ገሰጸው፡፡
ስለዚህም ንጉሡ ቁጣን ጨመረ ሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ፡፡ ይህም ቅዱስ ከጌታ ከሱስንዮስ ቀድሞ የሰማዕትነትን አክሊል በመንግስተ ሰማያት ተቀበለ፡፡

በዚችም ዕለት የአባ ብሶይ ወንድም አባ ጴጥሮስ በሰማዕትነት አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ሲድራቅ የእናቱ ስም ማርያም ነው። ይህንንም ቅዱስ በወለዱት ጊዜ ከርሳ የምትባል የእናቱ እኅት ወስዳ ከልጅዋ ጋራ አሳደገችው። ሰባት ዓመትም በሆናችው ጊዜ ወደ መምህር ወሰደቻቸውና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሕጉንም ተማሩ በጾም በጸሎትም ሲጋደሉ ኖሩ።
የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ተገለጠላቸው ስለ ክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም ምስክር እንደሚሆኑ ነገራቸው።
ከጥቂት ወራትም በኋላ ሰይጣን ዲዮቅልጥያኖስን አስቶት ለጣዖት በሰገደ ጊዜ እሊህን ቅዱሳን ክርስቲያኖች እንደሆኑ ነገር ሠሩባቸው። የእንዴናው ገዥ አርያኖስም ወደርሱ አስቀርቦ ለጣዖት እንዲሰግዱ ግድ አላቸው እምቢ በአሉትም ጊዜ ደማቸው እስኪፈስ ከባላ ላይ ሰቅለው እንዲገርፉአቸው አዘዘ።
ከጾምና ከስግደት የተነሣ ሥጋው ስለደከመ የሥቃዩ ሕማም ለጴጥሮስ ታወቀው ያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ከሕማሙ ፈወሰው። አርያኖስም አይቶ ጴጥሮስን ወደ ምሥራቅ ሀገር ወስደው በዚያ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡት አዘዘ።
አባ ብሶይም በእሥር ቤት እያለ መልአክ ነጥቆ ወደ ወንድሙ ወደ ጴጥሮስ አደረሰው፡፡ እርስ በርሳቸውም ተቃቅፈው ተሳሳሙ በሰማያዊት ኢየሩሳሌምም እንዲሰበስባቸው ወደ ጌታችን ጸለዩ እነሆ ወደ እርሳቸውም ከሰማይ ቃል መጣ። እንዲህ የሚል ተጋዳዮች ሆይ በሰማያት በብዙ ጉባኤ መካከል ትኖራላችሁና ሰላም ይሁንላችሁ ሥጋችሁም በምድር አይለያይም። ከዚህም በኋላ መልአክ አባ ብሶይን ወደ እሥር ቤት መለሰው።
ጭፍሮችም ኃያል ድል አድራጊ አባ ጴጥሮስን ራሱን ቆረጡ ሥጋውንም በዕንጨት ላይ ሰቀሉ። አባ ብሶይም በጭልታ ይሰደው ዘንድ የእሥር ቤት ጠባቂውን ለመነው ሒዶም የአባ ጴጥሮስን ሥጋ ዋጀው በሽቱ አድርጎ ገንዞም በሥውር ቦታ ቀበረ።
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages