አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ባልዋ ስቅራጥስም እኔ የክርስቲያንን ሃይማኖት እወዳለሁ የንጉሡን ሥቃይ ከመፍራት በቀር ክርስቶስን በልቤ አልካድኩትም ይላት ነበር። እንደዚህም ስትኖር ሁለት ልጆችንም ወለደች በአንጾኪያም አገር የክርስትና ጥምቀትን ልታስጠምቃቸው አልተቻላትም። አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተዋልና ጠፍተዋልምና ሰውን ወዳድ ክርስቶስን ብዙ ስለመውደዷ ልጆቿን ታስጠምቃቸው ዘንድ ታላቅ ተጋድሎ አደረገች ወደ እስክንድርያ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጴጥሮስ ልትሔድ ወዳ አሽከሮቿን አስከትላ ሁለቱን ልጆቿን ይዛ በመርከብ ተሳፈረች።
የክብር ባለቤት ጌታችንም የሃይማኖቷን ልዕልና ለመጪው ትውልድ ሊገልጥ ወዶ ያቺ መርከብ ለመሥጠም እስከምትደርስ በባሕር መካከል ጥቅል ነፋስን አስነሣ። ይቺ ቅድስትም ልጆቿ ሳይጠመቁ እንዳይሞቱ ፈራች ተነሥታም ጸለየች ከዚያም ምላጭ አንሥታ ጡቷን የቀኙን በጣች ከደሟም ወስዳ ፊታቸውን በመስቀል ምልክት ቀባች በደረታቸውና በጀርባቸውም ላይ እንዲሁ አደረገች በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በባሕሩ ውስጥ አጠመቀቻቸው ያን ጊዜም ታላቅ ጸጥታ ሆነ።
ወደ እስክንድርያ አገርም በደረሰች ጊዜ ከሀገር ልጆች ጋራ ያጠምቃቸው ዘንድ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጴጥሮስ ልጆቿን አቀረበች በዚያን ጊዜም ከሀገር ልጆች አጠመቀ። ወደልጆቿም ደርሶ ሊአጠምቃቸው ወሰዳቸው ያን ጊዜ ውኃው ረጋ እነርሱን ትቶ ከአገር ልጆች አጠመቀ ውኃውም ተፈትቶ ወረደ ደግሞ ሊአጠምቃቸው ወደ ልጆቿ ተመለሰ አሁንም እንደቀድሞው ውኃው ረጋ እንዲሁም ሦስት ጊዜ አደረገ ውኃውም ይረጋል አደነቀ። እናታቸውንም አቅርቦ ጠየቃት እርሷም ፈርታ ተንቀጠቀጠች ከእርሷም የሆነውን በባሕር መካከል ዐውሎ ነፋስ እንደተነሣባት ጡቷን በጥታ ደሟን እንደ ቀባቻቸውና በባሕር ውስጥ እንዳጠመቀቻቸው ነገረችው ስለ አደረገችውም ድፍረት በፊቱ ሰግዳ ይቅር ይላት ዘንድ ለመነችው።
አባ ጴጥሮስም ሴትዮ አትፍሪ ሃይማኖትሽ ፍጹም ነው አንቺ በባሕር ውስጥ በአጠመቅሻቸው ጊዜ በመለኮታዊት እጁ ያጠመቃቸው ባለቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና አይዞሽ አላት።ማጥመቁንም በፈጸመ ጊዜ ሥጋውን ደሙን አቀበላቸው ይቺም ቅድስት ወደ አንጾኪያ ቤቷ ተመለሰች።
ባሏም በአያት ጊዜ ይህን በማድረጓ ተቆጥቶ ወደ ንጉሡ ሒዶ ከሰሳት ያደረገችውንም ነገረው። ንጉሡም ወደርሱ ያቀርቧት ዘንድ አዘዘ ስትቀርብም ወደ እስክንድርያ ለምን ሔድሽ ከክርስቲያን ወገኖች ጋራ ልታመነዝሪ ነውን አላት። እርሷም እንዲህ ብላ መለሰችለት ክርስቲያኖች አያመነዝሩም እንደናንተ የረከሰ ጣዖትን አያመልኩም ከእንግዲህ ደግሞ ከእኔ ቃልን አትሰማም የወደድከውን አድርግ ሁለተኛም በእስክንድርያ ካንቺ የሆነውን ንገሪኝ ብሎ ጠየቃት ምንም ምን አልመለሰችለትም ።
ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም እጆቿን የኋሊት አሥረው ሁለቱንም ልጆቿን በሆድዋ ላይ አድርገው ሦስቱንም በእሳት ያቃጥሉአቸው ዘንድ አዘዘ። ፊቷንም ወደ ምሥራቅ መልሳ ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ጸለየች ከዚያም ከልጆቿ ጋራ አቃጠሉዋት የድልና የሕይወት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ለዘላለም ይማረን አሜን።
No comments:
Post a Comment