ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 7 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, May 20, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 7

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ግንቦት ሰባት በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃያኛ የሆነ የከበረ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_አትናቴዎስ_ሐዋርያው አረፈ፣ ቅዱስ አባት የባሕታውያን አለቃ የሆነ መስተጋድል አባ_ሲኖዳ ልደቱ ነው፡፡


ግንቦት ሰባት በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃያኛ የሆነ የከበረ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አትናቴዎስ አረፈ።
ይህም ቅዱስ ሐናፊ ከሚባል የእስ*ላም ነገድና ከአረማ*ውያን ተወላጅ ነው ይባላል። እርሱም ከመምህር ከሚማሩ ሕፃናት ጋራ እያለ እርስ በርሳቸው በመጫወት ሥርዓተ ቤተክርስቲያን እየሠሩ ከእነርሱ ውስጥ ዲያቆናትን ኤጲስቆጶሳትንም ሲያደርጉ እሊያን የክርስቲያንን ልጆች አይቶ ጨዋታቸው ደስ ስለአለው ከእሳቸው ጋራ በጨዋታቸው አንድ ይሆን ዘንድ የክርስቲያንን ልጆች ለመናቸው። እነርሱም አንተ አረ*ማዊ ነህና ከእኛ ጋራ አትደመርም ብለው ከለከሉት እርሱም ክርስቲያን እሆናለሁ አላቸው እነርሱም ደስ ተሰኙበት።
ያን ጊዜም ወስደው በሊቀ ጳጳሳት አምሳል አደረጉት ከበታቹም ወንበር አድርገው ይሰግዱለት ጀመር። በዚያን ጊዜም ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስ በዚያ አለፈ የክርስቲያን ልጆች ሲጫወቱ በአያቸው ጊዜ አብረውት ላሉ ይህ ሕፃን ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች ሹመትን ይሾም ዘንድ አለው አላቸው።
አባቱም በሞተ ጊዜ ወደ አባ እለእስክንድሮስ መጣ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቀው። ከዚህም በኋላ የአባቱን ገንዘብ ሁሉ ወስዶ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጥቶ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርትና ሕግ ሥርዓትንም ከአባ እለእስክንድሮስ ዘንድ እየተማረ ኖረ እርሱም ተወዳጅ ልጅ አደረገው።
ከዚህም በኋላ ዲቁና ሾመው የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ የተመላ ሆነ። የከበረ አባት እለእስክንድሮስም በአረፈ ጊዜ ይህን አባት አትናቴዎስን በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት። ከዚህ አስቀድሞ ግን የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ በተደረገ ጊዜ አባ እለእስክንድሮስ ከዚህ ዓለም ሳይለይ ይህም አትናቴዎስ ከእሳቸው ጋራ ተሰብስቧል። የጉባኤውም ጸሐፊ አድርገውት በኒቅያ ከተማ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ከእሳቸው ጋራ ሠራ።
ጻድቁ ቈስጠንጢኖስ በሞተ ጊዜ አርዮ*ሳዊ ልጁ ሁለተኛው ቈስጠንጢኖስ ነገሠ አርዮ*ሳውያንም በዙ ይህንንም አባት አርዮ*ሳዊው ንጉሥ ከመንበረ ሢመቱ አሳደደው በእርሱም ፈንታ ጊዮርጊስ የተባለ ከሀዲ ሰው ሾመ።
ከዚህም በኋላ ብዙ ጊዜ ሲአሳድዱትና ሲመልሱት ኖረ። በስደቱም በአንዲት ምዕራባዊት አገር በአለ ጊዜ በዚያ የጣዖት ቤት አለች። በዚያችም የጣዖት ቤት ብዙ ሕዝቦች በውስጧ ይሰበሰባሉ። ለዚያችም የጣዖት ቤት በውስጧ የሚሠሩ ብዙ የሰይጣን ሥራዎች አሏት። እርሱም የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነው ያቺንም የጣዖት ቤት አፍርሶ የአገር ሰዎችን ሁሉ እግዚአብሔርን ወደማወቅ መለሳቸው።
ይህንንም አባት አምስት ጊዜ አሳደዱት የሹመቱም ዘመን አርባ ሰባት ሲሆን ዐሥራ አምስቱን ዓመት በስደትና በእሥራት ነው ያሳለፈው። ይህንንም አባት ብዙ መከራና ድካም መሰደድም ስለደረሰበት ሐዋርያዊ ተብሎ ተጠራ።
በሚሞትበትም ጊዜ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን ባገኝ ይህን የጣዖት ቤት ያፈርስ ዘንድ በፊቱ እኔ እየሰገድኩ እለምነዋለሁ። ይህም አባት ከአረፈ በኋላ ንጉሥ ልኮ ያንን የጣዖት ቤት አስፈረሰው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ታላቁ_አባ_ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ አባት የባሕታውያን አለቃ የሆነ መስተጋድል አባ ሲኖዳ ልደቱ ነው።
ይህም ቅዱስ በግብጽና በአክሚም አውራጃ ስሟ ስንላል ከምትባል ሀገር ከላይኛው ግብጽ ነበር። ስለእርሱም የመላእክት አምሳል የሆነ አባ ሐርስዮስ ትንቢት ተናገረለት። እርሱም ስለ ገዳም አገልግሎት ከመነኰሳት ጋር ሲሔድ የዚህን የቅዱስ ሲኖዳን እናት ውኃ ለመቅዳት ወጥታ አገኛት: ወደርሷ ሒዶ ሦስት ጊዜ ራሷን ሳማትና እንዲህ አላት ዜናው በዓለሙ ሁሉ የሚሰማ የስሙ መዓዛ ከሽቱ የሚጥም የሆነ የሆድሽን ፍሬ እግዚአብሔር ይባርክ።
እነዚያ መነኰሳትም በአዩት ጊዜ አድንቀው አባታችን አንተ የሴት ፊት ማየት ከቶ አትሻም ነበር ዛሬ ግን ከሴት ጋራ ትነጋገራለህ አሉት። ልጆቼ ሆይ ሕያው እግዚአብሔርን የእግዚአብሔርን ምሕረት ተስፋ የሚያደርግ ዓለሙ ሁሉ የሚጣፍጥበት ከዚች ሴት የሚወጣ የጨው ቅንጣት አለ አላቸው።
አንድ በገድል የጸና ጻድቅ ሰው መነኰስ ነበረ እርሱም መልሶ አባ ሐርስዮስን እንዲህ አለው እግዚአብሔር ሕያው ነው አንተ ራሷን ትስም ዘንድ ወደዚያች ሴት በቀረብክ ጊዜ በእጁ የእሳት ሰይፍ የያዘ የእግዚአብሔርን መልአክ በዙሪያዋ አየሁት፡፡ ራሷንም በሳምካት ጊዜ ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጁ ሆይ ሰላምታ ይገባሃል ሲልህ ደግሞም ከዚች ሴት የሚወለደው የተመረጡ ቅዱሳንን ሁሉ ልባቸውን ደስ ያሰኛል ወልደ እግዚአብሔርም ከርሱ ጋር ብዙ ጊዜ ይነጋገር ነበር ሲል ሰማሁት አለ።
በግንቦት ሰባት ቀን ይህ ቅዱስ አባ ሲኖዳ ተወለደ በአደገም ጊዜ አባቱ በጎች ስለነበሩት ለልጁ ለሲኖዳ እንዲጠብቃቸው ሰጠው ይህ ሲኖዳም ምሳውን ለእረኞች ሰጥቶ እስከ ማታ ድረስ ይጾም ነበር። በሌሊትም ከውኃ ዐዘቅት ውስጥ ወርዶ በዚያ ቁሞ እስቲነጋ ድረስ ሲጸልይ ያድር ነበር። በክረምትም ሆነ በቊር ሰዓት እንዲሁ ያደርግ ነበር።
አባቱም የሲኖዳ እናት ወንድም ወደ ሆነው ወደ አባ አብጎል እጁን በላዩ ጭኖ ይባርከው ዘንድ ወሰደው። አባ አብጎልም በአየው ጊዜ የሕፃኑን እጅ አንሥቶ በራሱ ላይ አድርጎ ሲኖዳ ሆይ ባርከኝ ለብዙ ሕዝብ ታላቅ አባት ትሆን ዘንድ የሚገባህ ሁነሃልና አለው: አባቱም በአባ አብጎል ዘንድ ተወው።
ከዕለታትም በአንዲቱ ቀን አባ አብጎል እንዲህ የሚል ቃል ከሰማይ ሰማ እነሆ ሲኖዳ ለዓለሙ ሁሉ አርሲመትሪዳ የባሕታውያን አለቃ ሁኖ ተሾመ። ይህም ሲኖዳ ለዓለሙ ሁሉ ብርሃን እስከሚሆን በበጎ አምልኮ ያለ ማቋረጥ በጾምና በጸሎት በስግደትና በመትጋት ታላቅ ተጋድሎ መጋደልን ጀመረ።
ከዚህም በኋላ በአንዲት ቀን ለአባ አብጎል የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና የኤልያስን አስኬማ የሠለስቱ ደቂቅን ቆብና የመጥምቁ ዮሐንስን ቅናት አመጣለት። እንዲህም አለው እንድትጸልይና የምንኵስና ልብስ ለሲኖዳ እንድታለብሰው እማዚአብሔር አዝዞሃል። ያን ጊዜም አባ አብጎል ተነሥቶ ጸለየ የምንኵስና ልብስንም አለበሰው።
ከዚህም በኋላ ተጋድሎውን አበዛ፡፡ ለመነኰሳት፣ ለመኳንንት፣ ለሕዝባውያንና ለሴቶች ለሰዎች ሁሉ መመሪያ የሚሆን ሥራትን ሠራ። በኤፌሶንም የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ ስለ ከሀዲው ንስጥሮስ በተደረገ ጊዜ ከማኅበሩ አባት ከሊቀ ጳጳሳት ቄርሎስ ጋራ ወደ ጉባኤው ሔደ ንስጥሮስም ከክህደቱ ባልተመለሰ ጊዜ አውግዘው ለይተው አሳደዱት።
ከዚህ በኋላም ወደ ሀገራቸው በመመለሻቸው ጊዜ መርከበኞች ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋራ አትሳፈርም ብለው አባ ሲኖዳን ከለከሉት እርሱም ወደ እግዚአብሔር በጸሎት ማለደ። ወዲያውኑም ደመና መጥታ ተሸከመችውና አባ ቄርሎስ በመርከቡ ውስጥ እያለ በበላዩ በአንጻሩ አደረሰችው። አባቴ ሆይ ሰላም ለአንተ ከአንተ ጋራ ላሉትም ይሁን ብሎ ሰላምታ አቀረበ፡፡ በመርከብ ያሉት ሁሉም ላንተም ሰላም ይሁን በጸሎትህም አትርሳን አሉት። እጅግም አደነቁ ለሚፈሩት ይህን ይህል ጸጋ የሚሰጥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
ወደ ገዳሙም ደርሶ ከልጆቹ መነኰሳት ጋራ የመንፈቀ ሌሊትን ጸሎት አደረገ። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ብዙ ጊዜ ወደርሱ እየመጣ ያነጋግረው ነበር። እርሱም የመድኃኒታችንን እግሩን ያጥበው ነበር እጣቢውንም ይጠጣ ነበር ጌታችንም ብዙ ምሥጢራትን ገለጠለት ትንቢቶችንም ተናገረ።
ከዚህም በኋላ ፈጽሞ በአረጀ ጊዜ ሐምሌ ሰባት ቀን ተኛ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መጥቶ እያረጋጋው በእርሱ ዘንድ ተቀመጠ። ብፁዕ አባ ሲኖዳም ጌታችንን እንዲህ አለው ጌታዬ ፈጣሪዬ ልዩ ሦስትነትህንና ጌትነትህን ስለሚነቅፉ ከሀድያን ወደ ጉባኤው እሔድ ዘንድ እንዲጠሩኝ ሊቀ ጳጳሳቱ ወደ እኔ ልኳልና እንደቀድሞው ታጸናኛለህን።
ጌታችንም በጸጋና በጥዑም ቃል እንዲህ ብሎ መለሰለት ወዳጄ ሲኖዳ ሆይ ሌላ ዕድሜ ትሻለህን። እነሆ ዕድሜህ ሁሉ መቶ ሃያ ዓመት ከሁለት ወር ሁኖሃል ዕድሜህ ዘጠኝ ዓመት ሲሆን አስኬማን ለበስኽ ከዚያ በኋላ መቶ ዐሥራ አንድ ዓመት ከሁለት ወር ኖርኽ አሁንስ ድካምህ ይብቃህ ይህንንም ብሎ ጌታችን በክብር ዐረገ።
በዚያንም ጊዜም የቅዱሳን አንድነት ማኅበር ወደርሱ መጡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ዳግመኛ አየው ልጆቹንም ክብር ይግባውና ለጌታዬ ለኢየሱስ ክርስቶስ እሰግድ ዘንድ አንሱኝ አላቸው አንሥተውትም ሰገደለት። ከዚህም በኋላ ዳግመኛ እንዲህ አላቸው ወደ እግዚአብሔር አደራ አስጠብቅኋችሁ ነፍሴም ከዚህ ከደካማው ሥጋዬ የምትለይበት ጊዜ ደርሷል እኔም ለአባታችሁ ለዊዳ እንድትታዘዙ አዝዛችኋለሁ ከእኔ በኋላ ጠባቂያችሁ እርሱ ነውና አላቸው።
ለልጆቹም ይህን በተናገረ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመረጥሁህ ሲኖዳ ሆይ ብፁዕ ነህ ቸርነቴም ይደረግልሃል በሕይወትህ ዘመን ሁሉ አንተ የምወደውን ሥራ ሠርተሃልና እንግዲህ ወደ ዘለዓለም ተድላ ታርፍ ዘንድ ወደእኔ ና አለው። ሐምሌ 7 ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎትና ምልጃ ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages