ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 18 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, July 25, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 18

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሐምሌ ዐሥራ ስምንት የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ያዕቆብ በሰማዕትነት ሞተ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ በከሀዲው በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ሞተ፣ ሰማዕት የሆኑ የቅዱስ ኤስድሮስ ማኅበርተኞች መታሰቢያቸው ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ያዕቆብ
ሐምሌ ዐሥራ ስምንት የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ የጌታችን ወንድም የሚባለው ቅዱስ ያዕቆብ በሰማዕትነት ሞተ።
ይህም ቅዱስ የጠራቢው የዮሴፍ ልጅ ነው። እርሱም ከልጆቹ ሁሉ የሚያንስ ነበር። እርሱም ንጹሕ ድንግል ነበር ከጌታችንም ጋራ አደገ ስለዚህም ክብር ይግባውና የጌታችን ወንድም ተባለ። ከጌታችን ዕርገትም በኋላ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ላይ ኤጲስቆጶስ አድርገው ሾሙት። ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አስተምሮ ብዙዎችን ወደ ቀናች ሃይማኖት መለሳቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው።
እግዚአብሔርም በእጆቹ ታላላቅ ድንቆችንና ተአምራቶችን አደረገ። በአንዲት ዕለትም በጐዳና ሲጓዝ አንድ ሽማግሌ አገኘ። ቅዱስ ያዕቆብም ሽማግሌ ሆይ በቤትህ ታሳድረኛለህን አለው። አረጋዊውም እሺ እንዳልክ ይሁን አለ በአንድነትም ሲጓዙ ጋኔን ያደረበት ሰው አገኘው በአየውም ጊዜ የክርስቶስ ሐዋርያ ሆይ እኔ ካንተ ጋር ምን አለኝ ልታጠፋኝ መጣህን ብሎ ጮኸ ሐዋርያውም በናዝሬቱ ኢየሱስ ስም ተጠጋ ከሰውዬውም ውጣ አለው። ወዲያውም ያ ጋኔን ከሰውዬው ላይ ወጣ።
ያ ሽማግሌም ይህን ድንቅ ተአምር አይቶ ደነገጠ ከሐዋርያው እግር በታችም ወድቆ እንዲህ አለው። ወደ ቤቴ ልትገባ አይገባኝም ነገር ግን እድን ዘንድ ቤተሰቦቼም ሁሉ ይድኑ ዘንድ ምን ላድርግ አለ ያን ጊዜም ሐዋርያው አቤቱ ጌታዬ ሆይ መንገዴን አሳምረህልኛልና አመሰግንሃለሁ ብሎ ጌታችንን አመሰገነው። ወደ ሽማግሌውም ተመልሶ የድኅነትን ነገር ነገረው ክብር ይግባውና ስለ ጌታችን ሰው መሆን ስለ መከራው ስለ ሞቱና ስለ መነሣቱ አስተማረው።
ከዚህም በኋላ ያ ሽማግሌ ሐዋርያውን ወደ ቤቱ አስገባው ቤተሰቦቹም ሁሉ ወደርሱ ተሰበሰቡ ቅዱስ ያዕቆብም አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው። ሥጋውንና ደሙንም አቀበላቸው።
የከተማው ሰዎችም በሰሙ ጊዜ በሽተኞችን ሁሉ ወደርሱ አመጡ ሁሉንም አዳናቸው ለእነርሱም ሃይማኖትን አስተምሮ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው። ቀሳውስትንና ዲያቆናትንም ሾመላቸው ያንን ሽማግሌም ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾመው ክብር ይግባውና የጌታችንንም ወንጌል ሰጣቸው ከዚህም በኋላ ያስተምር ዘንድ ወደ ሌሎች አገሮች ወጥቶ ሔደ።
አንዲት መካን ሴት ነበረች እግዚአብሔር ልጅን ይሰጣት ዘንድ ስለርሷ እንዲጸልይላት ቅዱስ ያዕቆብን ለመነችው። እርሱም ጸለየላትና ወንድ ልጅን ወለደች ስሙንም ያዕቆብ ብላ ጠራችው ልጅዋንም ተሸክማ ወደ ሐዋርያው መጥታ ሰላምታ አቀረበችለት ከልጅዋም ጋር ከእርሱ ተባረከች ።
ከዚህም በኋላ በአንዲት ቀን ብዙዎች አይሁድ ወደርሱ ተሰበሰቡ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስም የማን ልጅ እንደሆነ ይነግራቸው ዘንድ ጠየቁት እነርሱ እርሱ ጌታን የዮሴፍ ልጅ እንደሆነ እርሱም ወንድሙ እንደሆነ እንደሚነግራቸው አስበው ነበርና።
ቅዱስ ያዕቆብም በሦስተኛ ደርብ ላይ ወጥቶ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነም ከአብ ጋራም ትክክል እንደሆነ ይገልጽላቸው ጀመረ።
ይህንንም በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቄጡ ከደርቡ ላይ አውርደው የጸና ግርፋትን ገረፉት ከእነርሱም ውስጥ የልብስ ማጠቢያ የዕንጨት ገበታ የያዘ አንድ ሰው መጣ በዚያ ዕንጨትም ቅዱስ ያዕቆብን ራሱ ላይ መታው ያን ጊዜም ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።
ስለ እርሱም ወይን እንዳልጠጣ፣ ደም ካለው ወገን እንዳልበላ፣ በራሱም ላይ ምላጭ እንዳልወጣ፣ በውሽባ ቤት እንዳልታጠበ፣ ሁለት ልብስንም እንዳልለበሰ፣ ሁልጊዜም እንደሚቆምና እንደሚሰግድ ተጽፎአል። ከመቆም ብዛት የተነሣም እግሮቹ አብጠው ነበር ከዚህም በኋላ አረፈና በቤተ መቅደሱ ጐን ቀበሩት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አትናቴዎስ
በዚህችም ቀን ከቍልዝም ከተማ ቅዱስ አትናቴዎስ በከሀዲው በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ ከነገሥታት ወገን ነበረ በሃይማኖቱም የጸና ነበረ። እኒህ ከሐዲያን ነገሥታት ዲዮቅልጥያኖስና መክስምያኖስ የጣዖታትን አምልኮ በዓወጁ ጊዜ ይህን አትናቴዎስን ለግብጽ አገር ገዥ አድርገው ሾሙት አብያተ ክርስቲያናትንም እንዲአፈርስ አዘዙት።
እርሱ ግን ወደ ግብጽ በደረሰ ጊዜ ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ ሒዶ በረከትን ተቀበለ እርሱም ክርስቲያን እንደሆነ ነገረው በእርሱም ደስ አለው። ንጉሡም በሰማ ጊዜ ይዞ ይመረምረው ዘንድ ሌላ መኰንን ላከ።
መኰንኑም በደረሰ ጊዜ ተገናኘውና የአማልክትን ፍቅር ለምን ተውክ አለው። አትናቴዎስም እንዲህ ብሎ መለሰለት እኔ ከታናሽነቴ ጀምሬ ክብር ይግባውና የክርስቶስ ነኝ የቀናች ሃይማኖቴንም አልተውም።
መኰንኑም የንጉሥን ትዕዛዝ የሚለውጥ ሁሉ ቅጣት እንዲአገኘውና በጽኑ ሥቃይ እንዲሠቃይ አታውቅምን አለው። ቅዱስ አትናቴዎስም እንዲህ አለው አንተ ሰነፍ በአንተ ላይና በንጉሥህ ላይ ቸር ሕይወት ሰጭ እግዚአብሔርን በሚጠላ በአባትህ ሠይጣን ላይ የሚመጣው የዘላለም ሥቃይን እስከምታይ ጥቂት ታገሥ አለው።
መኰንኑም በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ ራሱንም በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። ቅዱስ አትናቴዎስም ነፍሱን ከቅዱሳኑ ጋራ እንዲያሳርፍ ከቤተ ክርስቲያንም መከራን እንዲያርቅ የሮምንና የአኲስምን የክርስቲያን መንግሥት እንዲአጸና ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ጸሎቱም በፈጸመ ጊዜ በርከክ ብሎ ሰገደ ጭፍሮችም ራሱን በሰይፍ ቆረጡ። ምእመናንም ሥጋውን ወስደው ቀበሩት። ከመቃብሩም ቁጥር የሌላቸው ተአምራት ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የቅዱስ ኤስድሮስ ማኅበርተኞች
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የቅዱስ ኤስድሮስ ማኅበርተኞች የሆኑ ዘጠኝ ሺህ ሰማዕታት በዓመታዊ በዓላቸው ታስበው ይውላሉ፡፡ ይኸውም ሰማዕት ኤስድሮስ ጌታችን 5 ጊዜ ከሞት እያስነሣውና ስለ ስሙ ምስክር የሆነለት የ12 ዓመት ሕጻን ነው፡፡ ከእርሱም ጋር ማኅበርተኞቹ የሆኑ 8 መቶ 5 ሺህ ሰባት ሰዎች በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ በዚህች ዕለትም ማኅበርተኞች የሆኑ ዘጠኝ ሺህ ሰማዕታት በዓመታዊ በዓላቸው ታስበው ይውላሉ፡፡
(የዕረፍታቸውን ዕለት ግንቦት 19ን ይመለከቷል፡፡)
ሕጻኑ ሰማዕት ቅዱስ ኤስድሮስ ሀገሩ እስክንድርያ ሲሆን አባቱ በድላዖን እናቱ ሶፍያ ከቤተ መንግሥት ወገኖች ናቸው፡፡ አባቱ የዲዮቅልጥያኖስ መኰንን ነበር፡፡ ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ በክርስቲያኖች ላይ እጅግ አሠቃቂ መከራ ባደረሰ ጊዜ አባቱ በድላዖን ምስፍናውን ትቶ ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ገዳም ገባ፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም ጭፍሮቹን ልኮ አስመጣውና እምነቱን እንዲክድ ጠየቀው፡፡ በድላዖንም ‹‹ክርስቶስን በተውከው ሰዓት እኔም አንተን ተውኩህ›› አለው፡፡ ወዲያም አንገቱን በሰይፍ አስቆረጠው፡፡ ቅዱስ ኤስድሮስም ገና የ12 ዓመት ሕፃን ልጅ ነበርና ይመለስ ይሆናል በሚል በእሥር ቤት እንዲቆይ ተደረገ፡፡ በማግሥቱም ‹‹ክርስትናህን ትተህ የንጉሡን ሃይማኖት ተቀበል›› ብለው ሲያባብሉት እምቢ አላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ በንጉሡ ፊት አቅርበው ደሙ እንደ ውኃ እስኪወርድ ድረስ አሠቃቂ ግርፋትን ገረፉት፡፡ እናቱ ሶፍያም የሕፃኑን ልጇን ደም በዲዮቅልጥያኖስ ፊት ላይ እረጭታ እረገመችው፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም በንዴት ከሴት ልጇ ጋር ከወገባቸው ላይ ከሁለት አስቆረጣቸውና ሰማዕትነታቸውን ፈጽመው የክብር አክሊል ተቀዳጁ፡፡
ቅዱስ ኤስድሮስንም ቸንክረው ሰቀሉት፡፡ ሕጻኑም ተሰቅሎ ሳለ በእናቱና በእኅቱ የሆነውን ነገር ይመለከት ነበር፡፡ ሆዱን ሰንጥቀው በመቅደድ አንጀቱን አውጥተው ወስደው በተራራ ላይ ጣሉት፡፡ ጌታችንም ከሞት አሥተነስቶት እንደ ቀድሞው ሕያውና ፍጹም ጤነኛ አደረገው፡፡ ቅዱስ ኤስድሮስም ተመልሶ ሄዶ ከከሃዲው ንጉሥ ፊት ቆመ፡፡ አሁንም በብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ከሥር እሳት አነደዱበት፡፡ ሁለተኛም በብረት ላይ አስተኝተው ፈጩት፡፡ ነገር ግን ጌታችን አሁንም ከሞት አስነሣው፡፡ በዚህም ብዙዎች ‹‹በኤስድሮስ አምላክ አምነናል›› እያሉ በምስክርነት ዐረፉ፡፡ ዳግመኛም በእርሱ አምላክ ካመኑት ከሰምንት መቶ ነፍሳት ጋር ሰቀሉት፡፡ አሁን ጌታችን አድኖ አሥነሳው፡፡ በሥቃይም ብዛት አልሞት ቢላቸው አንገቱን በሰይፍ ቆረጡት ነገር ግን አሁንም ጌታችን ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት አሥነሣው፡፡
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ኤስድሮስን ትልቅ ድንጋይ በአንገቱ ላይ አስረው ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ከባሕሩ ውስጥ አውጥቶ በንጉሡ ፊት አቆመው፡፡ ዳግመኛም ወደ ከተማ ወስዶ ሰቅሎ ገደለው፣ ጌታችንም ለ4ኛ ጊዜ ከሞት አሥነሣው፡፡ ለተራቡ አንበሶች ሲሰጡት እነርሱም ምንም ሳይነኩት ቀሩ ይልቁንም አክብረው ሲሰግዱለት ቢመለከቱ በንዴት ሰውነቱን ቆራርጠው ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ ጌታችንም ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ተገልጦለት ለ5ኛ ጊዜ ከሞት አሥነሣው፡፡ ንጉሡም እጅግ አፈረና የሚያደርገው ቢያጣ በግዞት ወደ ሰሎንቅያ ሀገር ላከው፡፡ በዚያም ብዙ ካሠቃዩት በኋላ ወደ ንጉሡ መለሱት፡፡ ንጉሡም በእሥር ቤት አሥሮ በርሃብ እንዲሠቃይ አደረገው፡፡ በመጨረሻም ቅዱስ ኤስድሮስ ግንቦት 19 ቀን የሰማዕትነት ፍጻሜው ሆነና ተሰቅሎ ዐረፈ፡፡ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀዳጀ፡፡ ቅዱስ ኤስድሮስ የኖረበት ዘመን 12 ዓመት ነው፡፡ በቅዱስ ኤስድሮስ ምክንያት በጌታችን አምነው ከኤስድሮስ ጋር አብረው በሰማዕትነት የሞቱት ሰዎች ብዛት 8 መቶ 5 ሺህ ሰባት ሰዎች ናቸው፡፡ ጌታችንም ለሕፃኑ ሰማዕት ለቅዱስ ኤስድሮስ አስደናቂ ቃል ኪዳን ገብቶለታል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages