አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሰኔ ሃያ አምስት በዚች ቀን ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የፀራቢው ዮሴፍ ልጅ ሐዋርያው ይሁዳ በሰማዕትነት ሞተ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ጴጥሮስ አረፈ፣ ሰማዕቱ መስፍኑ ጲላጦስ መታሰቢያው ነው፡፡
ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
ሰኔ ሃያ አምስት በዚህች ቀን ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የፀራቢው ዮሴፍ ልጅ ሐዋርያው ይሁዳ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ሐዋርያ በብዙ አገሮች ሰበከ ወደ አንዲት ደሴትም ገብቶ በውስጧም ሰበከ ሰዎቿንም በጌታ አሳመናቸው ቤተ ክርስቲያንም ሠራላቸው በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው።
ከዚያም ወደ ሮሃ ሀገር ሒዶ የሮሃ ንጉሥ አውጋንዮስን ከደዌው ፈወሰው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቀው ከዚያም ደግሞ ሐራፒ ወደሚባል አገር ሒዶ በውስጧ ሰበከ ከሰዎቿ ብዙዎቹን አጠመቃቸው ቤተ ክርስቲያንም ሠራላቸው።
የዚያችም አገር ገዥ ይዞ ጽኑዕ ሥቃይ አሠቃየው ችንካር ያለው ጫማ በእግሮቹ ውስጥ አድርጎ አንድ ምዕራፍ ያህል አስሮጠው ከዚህም በኋላ ሰቅሎ በፍላፃ ነደፈው ክብር ይግባውና በጌታችን እጅ ነፍሱን ሰጠ።
ከመከራውም አስቀድሞ ለምእመናን መልእክትን ጽፎ ላከ እርሷም ከሐዋርያት መልእክቶች ሰባተኛ የሆነች ምሥጢርን የተመላች ናት በእርሷም ብዙዎች አረማውያንን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማመን አስገባቸው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት
ዳግመኛም በዚህች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጰሳት አርባ አራተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ጴጥሮስ አረፈ። ይህም አባት ከመሾሙ በፊት የማርቆስ መንበር ያለ ሊቀ ጳጳሳት ለብዙ ዘመናት ኖረ የእስላሞች ንጉሥና መኳንንቶቹ አልፈቀዱላቸውም ነበርና።
ከዚህም በኋላ ሃይማኖቱ የቀና ደግ መኰንን በእስክንድርያ ከተማ ላይ ተሾመ ያንጊዜም የአገር ሽማግሌዎች ወደ ርሱ ተሰብስበው ሊቀ ጳጳሳት እንደ ሌላቸው ኀዘናቸውን ነገሩት። እርሱም ደብረ ማሕው ወደሚባለው ወደ ደብረ ዝጋግ ወጥተው እንዲጸልዩ ለራሳቸውም ሊቀ ጳጳሳት እንዲሾሙ አዘዛቸው። በዚህም ነገር ደስ ብሏቸው ቀሲስ አባ ጴጥሮስን ወስደው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በእርሱም ደስ አላቸው።
በዚያም ወራት የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስ ሞተ የአንጾኪያ አገርም ያለ ሊቀ ጳጳሳት ትኖር ነበር የአንጾኪያ ምእመናንም ለእስክንድርያ ከተማ አባ ጴጥሮስ እንደ ተሾመ በስሙ ጊዜ እነርሱም የተማረ ደግ ሰው ለአንጾኪያ ሾሙ ስሙም ታውፋንዮስ ይባል ነበር ። እርሱም ከአባ ጴጥሮስ ጋራ ተስማማ እነርሱም ስለ ቀናች ሃይማኖት በመልእክቶቻቸው ይገናኙ ነበር።
ከእነርሱም እያንዳንዱ በባልንጀራው ምክር በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜ ይሰብክ ነበር ወደ አገራቸውም መግባት አልተቻላቸውም ነበርና አባ ጴጥሮስም በግብጽ ደቡብ በአንባንያ ገዳምና በዝጋግ ገዳም ይኖር ነበር አባ ታውፋንዮስም ከአንጾኪያ ከተማ ውጭ በአፍቆንያስ ገዳም ይኖር ነበር።
በዚያም ወራት ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ ሰባት መቶ ገዳማትና ሃይማኖታቸው የቀና ምእመናንም ያሉባቸው ሠላሳ ሁለት መንደሮች ነበሩ በግብጽ አውራጃ ሁሉና በላይኛው ግብጽ በአስቄጥስ ገዳማት የሚኖሩ መነኰሳት እንዲሁም ኖባና ኢትዮጵያ በዚህ በአባ ጴጥሮስ ስልጣን ሥር ነበሩ። እኒህ ሁሉ ሃይማኖታቸው የቀና ነበር። በትእዛዙም ጸንተው ይኖሩ ነበር። እርሱም በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ወደእርሳቸው መልእክቶችን መጻፍ አያቋርጥም ነበር። የእስክንድርያን ገዳማት ሁሉና መንደሮችንም እየዞረ ያስተምራቸውና ይመክራቸው ያጽናናቸውም ነበር።
ከእርሱ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት የሆነ ቅዱስና ዐዋቂ የሆነ ደቀ መዝሙር ነበረው እርሱም በሊቀ ጵጵስናው ሥራ ሁሉ ይራዳው ነበረ። ይህም አባት ጴጥሮስ አንዳንድ ጊዜ ወደ እስክንድርያ ከተማ ይገባ ነበር የሰዎቿንም ሥራቸውን ተመልክቶ ያስተምራቸውና በሃይማኖት ያጸናቸው ነበር።
በዐሥራ ሁለቱ ዓመት የሹመቱ ዘመን እንደ ሐዋርያት መንጋዎቹን እየጠበቀ እንዲህ በሹመቱ ኑሮ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ሰማዕቱ ጲላጦስ መስፍን
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ሰማዕቱ ጲላጦስ እና የሚስቱ ቅደስት አብሮቅላም መታሰቢያ ነው፡፡ ብዙዎቻችን መስፍኑን ዺላጦስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌታችን እንዳይሰቀል ከአይሁድ ጋር ሲከራከር እናውቀዋለን። የጌታችን ሞቱ በፈቃዱ ነበርና አይሁድ እንቢ ሲሉት የክርስቶስን ንጽሕና መስክሮ: እጁንም ታጥቦ ሰጥቷቸዋል። የዺላጦስ ታሪክ ግን እዚህ ላይ አያበቃም።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከተነሳ በሁዋላ ትንሳኤውን በራዕይ ገልጦለት አይሁድን ተከራክሯቸዋል። ውሸታም ወታደሮችንም ቀጥቷል። በመጨረሻ ግን በሮም ቄሳር ተጠርቶ ከእሥራኤል እስከ ሮም ድረስ ሰብኮ በሮም አደባባይ አንገቱ ተሠይፏል።
ቅድስት እናታችን አብሮቅላም የዺላጦስ ሚስት ስትሆን ቁጥሯ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ነው። ጌታችንን ተከትላ ቤቷን ለሐዋርያት አስረክባ ቤተ ክርስቲያንንም በዘመኗ አገልግላ ዐርፋለች። ዛሬ ሁለቱም ቅዱሳን ይታሠባሉ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ
No comments:
Post a Comment