በመምህር ገብረ መድኅን እንየዉ
ከዚህ ውጪ ምን ሊጥሱ ኑረዋል?
ቀኖና ማለት ፦ ሥርዓት፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ልክ፣ ድ ንበር፣መሰን ፣ ግዝት፣ደንብ፣መለኪያ ማለት ነው።
ቀኖና በሁለት ይከፈላል ፦
የቁጥር ቀኖና በሐዋርያት እና ሐዋርያትን መስለው በተቀበሉ በሠለስቱ ምእት ጉባኤ የተቆጠረ የተሠራ ሰማንያ አንድ መጽሐፍ ቅዱስን ቁጥር የምንለካበት ነው።
"ሊቀበሏቸው የታዘዙ አምላካውያት መጻሕፍት ሰማንያ አንድ ናቸው" ፍት ነገ አን.2 እንዲል። ቀኖና መጻሕፍት አነሰ ብሎ መጨመርም በዛ ብሎ መቀነስም አይቻልም ። ከዚህ ቁጥር ውጪ የሆኑ ሌሎችን ምንም በምሥጢር የተካከሉ ቢሆኑም አዋልድ ተብለው ይጠራሉ። 81ዱ ግን አሥራው ይባላሉ።
ቀኖናውም ሐዋርያዊ ቀኖና ይባላል ።ቤተ ክርስቲያንንም ሐዋርያዊት ያሰኛታል።
2ኛ) ሥርዓታዊ ቀኖና ነው ባጠቃላይ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ይመለከታል፦ ይህ ቀኖና በአምስት ይከፈላል።
1ኛ) የመጀመሪያ መሠረቱ የሐዋርያት ሲኖዶስ ጉባኤ ነው ሐዋርያት አባቶቻችን ከነቅዕ ከክርስቶስ ተምረው ዓለም አቀፍ አምሳለ ሰማይ የሆነ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ሠርተዋል ። ሥርዓቱንም በግዝት እና ያለ ግዝት አስተቀምጠውታል ። በግዝት የሠሩትን መቀበል፣መጠበቅ መስጠት ብቻ ነው የሚቻለው።ግዘታቸው ሐዋርያዊ ግዝት ስለሆነ ፣ቀኖነቸውም ሐዋርያዊ ቀኖና ይባላል።
ከሐዋርያት በኋለ የተነሱ አበው በዚህ መንገድ ብቻ ነው የተጓዙት።
2ኛ) በዓለም አቀፍ ጉባኤያት የተሠራ ሐዋርያዊ ፍጹማዊ ቀኖና ነው።
ይህ ቀኖና፦ሐዋርያት በሠሩት ቀኖና ላይ በሦስቱ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት በመላው ዓለም የትሰበሰቡ ቅዱሳን አበው በግዝት የሠሩት ያስቀመጡት ነው። ይህ ቀኖና ዓለም አቀፉ ጉባኤ እስካልተሰበሰበ ድረስ እና ዳግም ከሐዋርያት ጉባኤ ማሳለፊያ እስካልመጣ ድረስ ፈጽሞ አይሻሻልም።ለምሳሌ፦ጳጳስ መነኩሴ ይሁን ይላል፦ ከብዶናል ዓለማዊ ይሁን ብሎ መወሰን እና ማሻሻል አይቻልም።የትም ተነሥቶ ሥርዓትኮ ነው እያለ መናድ አይችልም ያ ጉባኤ የግድ መገኘት አለበት ።ቀኖና የጣሰውን የእኛ ዘመን ባያወግዘውም እንኳን ሲኖዶሱ (ያ ዓለም አቀፍ ጉባኤ)ያወግዘዋል።
በዚህ ሰሞን የምንሰማቸው ቀኖና ነው ይሻሻላል የሚሉ ንግግሮች ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያንን ከሰንሰለቷ የሚቆርጥ ነው።
በዚህ ቀኖና ውስጥ ዘእንበለ ግዘት (ከውግዘት ነጻ) የሆኑ ብያኔዎች እና ሥርዋጾች ትርጉም ሊሰጣቸው ይችላሉ።
3ኛ) አህጉር አቀፍ ቀኖና ነው፦በጉባኤ ቅርጣግና ፣ ሎዶቅያ፣ሥርድቅያ እና በመሳሰለው ጉባኤ የተወሰነው ቀኖና ነው፦ ይሄም ቀኖና በግዝት እና ዘእንበለ ግዘት የተሠራ ሥርዓት ነው ። ጉባኤው በቅብብሎሽ የተቀበለውን ቀኖና ጠባቂ አስጠባቂ ነው። በዚህ በግዘት የተሠራውን የትም ተነሥቶ ሥርዓትኮ ነው እያለ መናድ አይችልም የእኛ ዘመን ባያወግዘውም ሲኖዶሱ (ያ አህገር አቀፉ ጉባኤ)ያወግዘዋል።
4ኛ) ሀገር አቀፍ ቀኖና ነው። ይህ ቀኖና በአንድ ፓትርያሪክ ሥር ያለው ሲኖዶሳዊ ጉባኤ የሠራው ነው ። ሀገር አቀፉ ጉባኤ ፦ ሐዋርያዊ፣ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ፦ የሆነውን የግዝት ቀኖናን ማሻሻል አይችልም። የዚህ ጉባኤ ተግባሩ ፦መቀበል፣መጠበቅ፣ መስጠት ብቻ ነው። ዘእንበለ ግዘት በሆነው ላይ ግን ብያኔ ሊሰጥ ይችላል።
በግዝት የሠሩትን አፈርሳለሁ ቢል ግን የሐዋርያት ሲኖዶስ፣ የሦስቱ ዓለም አቀፍ ሲኖዶስ፣ የአህጉር አቀፍ ሲኖዶስ ይለየዋል።
ከዚህ ውጪ ግን ክህነትን ያህል ነገር ቀኖና ነው ይቻላል ማለት ግን ፈጽሞ የተወገዘ ነው ።
ቀኖና አልጣስንም የሚሉ ሰዎች ከዚህ ውጪ ምን ሊጥሱ ኑረዋል?
No comments:
Post a Comment