አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሦስት በዚህች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ አረፈ፣ የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ክልስቲያኖስ አረፈ።
ቅዱስ ቄርሎስ
ሐምሌ ሦስት በዚህች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃያ አራተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ቄርሎስ አረፈ። ይህም ቅዱስ የእናቱ ወንድም በሆነው በአባ ቴዎፍሎስ ዘንድ አደገ ጥቂት ከፍ ባለ ጊዜም ወደ አስቄጥስ ወደ መቃርስ ገዳም ላከው በዚያም አምላ*ካውያት የሆኑ መጻሕፍትን ተማረ እግዚአብሔርም መጽሐፍን አንድ ጊዜ አንብቦ እስከሚአጸናው ድረስ ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጠው።
ከዚህም በኋላ ደግሞ ያስተምረው ዘንድ ለአባ ሰራብዮን ሰጠው ከእርሱም ዘንድ ያለውን ትምህርቱን በፈጸመ ጊዜ ወደ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ መለሰው። እርሱም እጅግ ደስ ተሰኘበት እግዚአብሔርንም አመሰገነው። ከዚህም በኋላ ሁልጊዜ መጻሕፍትን እንዲያነብና ሕዝቡን እንዲያስተምር በሊቀ ጵጵስና ሥራ ውስጥ ሾመው።
ከትምህርቱም ጣዕም የተነሣ ዝም ይል ዘንድ ማንም አይወድም ነበር። አባ ቴዎፍሎስም ከአረፈ በኋላ በእስክንድርያ ከተማ ላይ ይህን አባ ቄርሎስን ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በዘመኑም በትምህርቱ ቤተ ክርስቲያን በራች። ይኸው አባት ቄርሎስ የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት የነበረው ንስ*ጥሮስ በካደ ጊዜ በንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ ማኅበርን በኤፌሶን ከተማ ሰበሰበ።
ይህን አባት ቄርሎስንም መርጠው ሊቀ ጉባኤ አደረጉት። ንስጥ*ሮስንም ተከራከረው ስሕተ*ቱንም ገለጠለት። ከስሕ*ተቱም ባልተመለሰ ጊዜ አውግ*ዘው ከመንበረ ሢመቱ አሳደ*ዱት። ይህም አባት ቄርሎስ ዐሥራ ሁለት አንቀጾችን ደረሰ በውስጣቸውም የቀናች ሃይማኖትን ገለጠ ከእነርሱ በኋላ ግን ብዙዎች ድርሳናትን ተግሣጻትንና መልእክቶችን ደረሰ።
እሊህም በሁሉ ቦታ በምእመናን እጆች ይገኛሉ። ይህም አባት ቄርሎስ እግዚአብሔር ቃል ከትስብእቱ ጋራ ከተዋሐደ በኋላ በሥራው ሁሉ በምንም በምን የማይለያይ አንድ አካል አንድ ባሕርይ እንደሆነ አስረዳ። ይህም አባት ቄርሎስ ሃይማኖታቸው ከቀና ከሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶች ሃይማኖት ወጥተው ክርስቶስን ወደ ሁለት የሚከፍሉትን መናፍ*ቃንን ሁሉንም አው*ግዞ ለያቸው።
በወንጌላዊ ማርቆስ መንበር ላይ ሠላሳ ሁለት ዓመት ኖረ መልካም የሆነ ሥራውንም ፈጽሞ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ክልስቲያኖስ
በዚህችም ቀን ከእርሱ በፊት ለነበረው ሊቀ ጳጳሳት ዮናክንዲኖስ ደቀ መዝሙሩ የነበረ የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ክልስቲያኖስ አረፈ። ይህ አባ ዮናክንዲኖስ በሚያርፍበት ጊዜ በእርሱ ፈንታ አባ ክልስቲያኖስን ሊቀ ጵጵስና እንዱሾሙት አዘዘ እርሱንም አባ ክልስቲያኖስን በሮሜ አገር ነጣቂ ተኩላዎች አሉና ልጄ ሆይ ተጠበቅ ብሎ አዘዘው። ከዚህም በኋላ አባ ዮናክንዲኖስ ባረፈ ጊዜ ይህን አባት ክልስቲያኖስን በእርሱ ፋንታ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።
በዚያን ወራት ደግ ንጉሥ አኖሬዎስ ነበረ። ከርሱም በኋላ ዐመ*ፀኛ ሉልያኖስ ነገሠ ። እርሱም ክልስቲያኖስን ከመንበሩ አሳድዶ መና*ፍቁ ንስ*ጥርስን ሊቀ ጵጵስና ሾመው የከተማ ሰዎች ግን አባረሩት እንጂ አልተቀበሉትም በከሀዲው ንጉሥም ልብ በክልስቲያኖስ ላይ ቂም ነበረ ሊገድ*ለውም ይሻ ነበር።
እርሱ አባ ክልስቲያኖስ ግን በሮሜ ከተማ ከሚገኙ ገዳማት በአንዱ ገብቶ ኖረ እግዚአብሔርም ብዙ ድንቆችንና ተአምራቶችን በእጆቹ ያደርግ ነበር። ከዚህም በኋላ ከሀዲው ንጉሥ ወደ ጦርነት ሔደ የእግዚአብሔር መልአክ የመላእክት አለቃ ሩፋኤልም ለክልስቲያኖስ ተገለጠለት ወደ አንጾኪያ ከተማ ወደ ሊቀ ጳጳሳት ድምትርያኖስ ይሔድ ዘንድ አዘዘው በዚያም ኑር አለው።
ንጉሡ ከጦርነት እንደተመለሰ ይገድ*ልህ ዘንድ በልቡ አስቧልና። ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ከዚያ ገዳም ወጣ ከእርሱ ጋራም ሁለት መነኰሳት ነበሩ። ወደ እንጾኪያም ከተማ ደርሶ ቅዱስ ድምትርያኖስን አገኘው ከዐመፀኛው ንጉሥም የደረሰበትን ሁሉ ነገረው እርሱም በአንጾኪያ ከተማ ከሚገኙ ገዳማት በአንዱ ገዳም አኖረው።
ከዚህም በኋላ ቅዱሳን ሊቃነ ጳጳሳት አግናጥዮስና ዮናክንዲኖስ በሌሊት ራእይ ለንጉሡ ተገለጡለት ከእርሳቸውም ጋር የነበረው አንዱ እጅግ የሚያስፈራና ግሩም ነበረ። እርሱም ንጉሡን እንዲህ አለው ሊቀ ጳጳሳቱን ክልስቲያኖስን አገሩን ለምን አስተውከው እነሆ እግዚአብሔር ነፍስህን ከአንተ ይወስዳል በጠላቶችህም እጅ ትሞታለህ።
ንጉሥም ጌታዬ ምን ላድርግ አለው እነዚያም ሁለቱ አባቶች በእግዚአብሔር ልጅ ሕማም በመቀበሉ ታምናለህን ብለው መለሱለት እኔ አምናለሁ አላቸው ዳግመኛም መልእክትን ልከህ ልጃችን ክልስቲያኖስን ወደ መንበሩ መልሰው አሉት። ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ መልእክትን ጽፎ ወደ ድምትርያኖስ እንዲህ ብሎ ላከ ስለ ሊቀ ጳጳሳት ክልስቲያኖስ በእኔ ላይ አትዘን ወደ መንበረ ሢመቱ ይመልሱት ዘንድ ሊቀ ጳጳሳት ክልስቲያኖስ ያለበትን ለመልእክተኞቼ ታመላክታቸውና ታደርሳቸው ዘንድ እለምንሃለሁ።
መልክተኞችም በሔዱ ጊዜ አገኙትና መለሱት ሕዝቡም በታላቅ ክብርና በብዙ ደስታ ተቀበሉት። በዚያም ወራት ንጉሡ ከጦርነት በደኅና ተመለሰ ቤተ ክርስቲያንም በዕረፍትና በሰላም ኖረች። የንስጥሮስም ክህ*ደቱ በተገለጠ ጊዜ በእርሱ ምክንያት አንድነት ያላቸው ማኅበር ተሰበሰቡ። ይህ አባት ክልስቲያኖስም በደዌውና በእርጅናው ምክንያት ወደጉባኤው መምጣት አልተቻለውም ነገር ግን ንስ*ጥሮስን ከሚያወግዝ ደብዳቤ ጋራ ሁለት ቀሳውስትን ላከ።
ክብር ይግባውና ጌታችንም ከዚህ ኃላፊ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው በፈቀደ ጊዜ ዮናክንዲኖስና አትናስዮስ ተገለጡለት እንዲህም አሉት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕይወት ጠርቶሃልና አንተ ወደ እኛ ስለምትመጣ አስጠንቅቃቸው አሉት። ከእንቅልፉ ነቅቶ ወገኖቹን ጠራቸው እንዲህም አላቸው ተኵላዎች ወደዚች ከተማ ይገቡ ዘንድ አላቸውና ተጠንቀቁ።
ይህንም ከተናገረ በኋላ ዳግመኛ እንዲህ አለ እንነሣና እንሒድ እነሆ ቅዱሳን ይሹኛልና ሁለቱ ሌሎች ናቸው። በዚችም ሰዓት ከዚች ዓለም በአንድነት እንወጣለን እነርሱም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቄርሎስና የፃን ሀገር ኤጲስቆጶስ ሉቅያስ ናቸው። ይህንንም ብሎ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶቻችን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ
No comments:
Post a Comment