ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 4 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, July 24, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 4

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሐምሌ አራት በዚህች ቀን የቅዱሳን አቡቂርና ዮሐንስ የሥጋቸው ፍልሰት ሆነ፣የነቢዩ ሶፎንያስ እረፍት ነው፣ የዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት መታሰቢያቸው ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የቅዱሳን አቡቂርና ዮሐንስ
ሐምሌ አራት በዚች ቀን የቅዱሳን አቡቂርና ዮሐንስ የሥጋቸው ፍልሰት ሆነ። ይህም እንዲህ ነው እሊህ ቅዱሳን የካቲት ስድስት ቀን ሰማዕታት ሆነው በሞቱ ጊዜ ምእመናን ሥጋቸውን ተሸክመው ወስደው በእስክንድርያ ከተማ በስተሰሜን ባለች በቅዱስ ወንጌላዊ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሥውር አኖሩዋቸው እስከ ሊቀ ጳጳሳት ቄርሎስ ዘመንም በዚያ ኖሩ።
የእግዚአብሔር መልአክም ለቅዱስ ቄርሎስ ተገለጸለት ወደ ወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያንም ሔዶ የቅዱሳን የአቡቂርንና የዮሐንስን ሥጋቸውን አውጥቶ እንዲሸከም አዘዘው። እርሱም ተነሥቶ ሔደ ከእርሱም ጋራ ብዙ ሕዝቦች ነበሩ በደረሱም ጊዜ ጸለዩ ምድሩንም ሲቆፍሩ ሥጋቸው በውስጡ ያለበት ቦታ ተገለጠላቸው በባሕር ዳርቻ ወደ አለች ወደ ሌላዪቱም የቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ክብር የቅዱሳኑን ሥጋቸውን ተሸክመው አድርሰው በዚያ አኖሩ።
በዚያም ቤተ ክርስቲያን ሠሩላቸው በዚችም ቀን ታላቅ በዓል አደረጉ ከሥጋዎቻቸውም ድንቆች ተአምራት ተገለጡ አረማውያንም ተሰበሰቡ ይህንንም ድንቅ ተአምር በአዩ ጊዜ ጣዖቶቻቸውን ትተው ክርስቲያኖች ሆኑ። በዚያቺም የጣዖቶች ቤት አሸዋ በላይዋ ተከመረባት ታላቅ ኮረብታም ሆነ። የቅዱሳንም ሥጋቸው ታምራትንና ለበሽተኞች ታላቅ ፈውስን ያደርጋል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የነቢዩ ሶፎንያስ
በዚህችም ቀን ደግሞ የአማርያ ልጅ፣ የሴዴቅያስ ልጅ፣ የጎዶልያ ልጅ፣ የኩሲ ልጅ የሶፎንያስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። እርሱም በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ዘመን ትንቢት ተናገረ። እንዲህም አለ እግዚአብሔር ከዚህ ዓለም ፈጽመው ይጠፋሉ አለ ከብቶችና ሰዎች ያልቃሉ። የባሕር ዓሣዎችና በሰማይ የሚበሩ አዕዋፍም ያልቃሉ።
ዳግመኛም ስለሞአብ እንዲህ አለ ስለዚህ ሞአብ እንደ ሰዶም ትሆናለች የአሞንም ልጆች እንደ ገሞራ ልጆች ይሆናሉ ደማስቆም እንደ እህል ታልቃለች። እርሱ እንደ ተነበየው እነዚያ አገሮች በናቡከደነጾር ምርኮ ይጠፋሉና።
ዳግመኛም ስለ ፋርስና ስለ ነነዌ ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ የፋርስን ሰዎች አጠፋቸዋለሁ ነነዌንም ፍርስራሽና ውኃ እንደሌለባት ምድረ በዳ አድርጋታለሁ መንጋዎችም በመካከሏ ይሠማሩባታል። ይህቺም ከተማ በመቄዶናዊው እስክንድር እጅ ጠፍታለች።
ዳግመኛም ስለ ክርስቶስ መምጣት እንዲህ ተናገረ። ያን ጊዜም ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ይጠራ ዘንድ በአንድ ሕግም ይገዙልኝ ዘንድ የአሕዛብን ሁሉ አንደበት ወደ ሕግ እመልሳለሁ። ደግሞም እንዲህ አለ ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ መሥዋዕቴን ያመጡልኛል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ደቂቀ ነቢያት
ዳግመኛም በዚች ቀን ስለ ክርስቶስ ትንቢታቸውን እንደ ፈሳሽ ውኃ ያጐረፉ የዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት መታሰቢያቸው ነው።
ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነው፡፡ 12ቱ ቅዱሳን ደቂቀ ነቢያት የሚባሉት፡- ሆሴዕ፣ አሞጽ፣ ሚክያስ፣ ኢዩኤል፣ አብድዩ፣ ዮናስ፣ ናሆም፣ እንባቆም፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ዘካርያስ እና ሚልክያስ ናቸው፡፡
ሌሎቹ ዋና (ዓበይት) ነቢያት የሚባሉት አራት ሲሆኑ እነርሱም ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ናቸው፡፡ ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ድረስ ያሉት ነቢያት ‹‹ደቂቀ ነቢያት›› የተባሉት ምክንያት አንድም የነቢያት ልጆች በመሆናቸው ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የጻፏቸው ትንቢቶቻቸው ዓበይት ነቢያቱ ከጻፏቸው ጋር በንፅፅር ሲታይ አነሥተኛ ስለሆነ ነው፡፡
'ነቢይ' ማለት እግዚአብሔር የመረጠውና የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ የሚያስተላልፍ ብሎም የተሠወረውንና የሚመጣውን ሁሉ በግልጽ የሚመለከት ማለት ነው፡፡ ነቢያት ሲባሉ በአጠቃላይ ምግባር ሃይማኖታቸው ያማረ፣ ትሩፋት ተጋድሎአቸው የሰመረ ነውና አካሄዳቸው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ነው፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶቻችን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages