በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ
ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::
ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::
ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)
የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::
ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ::" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)
ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ::" እንዳለ ጌታ በወንጌል::
(ማቴ. 13:16, 1ጴጥ. 1:10)
ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::
ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት
¤አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት:
¤አራቱ ዐበይት ነቢያት:
¤አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና
¤ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ::
አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት ማለት:-
*ቅዱስ አዳም አባታችን
*ሴት
*ሔኖስ
*ቃይናን
*መላልኤል
*ያሬድ
*ኄኖክ
*ማቱሳላ
*ላሜሕ
*ኖኅ
*አብርሃም
*ይስሐቅ
*ያዕቆብ
*ሙሴና
*ሳሙኤል ናቸው::
አራቱ ዐበይት ነቢያት
*ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
*ቅዱስ ኤርምያስ
*ቅዱስ ሕዝቅኤልና
*ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::
አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት
*ቅዱስ ሆሴዕ
*አሞጽ
*ሚክያስ
*ዮናስ
*ናሆም
*አብድዩ
*ሶፎንያስ
*ሐጌ
*ኢዩኤል
*ዕንባቆም
*ዘካርያስና
*ሚልክያስ ናቸው::
ካልአን ነቢያት ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስና
*ኤልሳዕ . . . ሌሎችም ናቸው::
ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል)ና
*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ::
በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::
ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::
ቅዱስ ሚክያስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ.ል. ክርስቶስ በ800 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው::
አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ አሥራ አራት ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::
ሚክያስ አባቱ ሞራት (ሞሬት) ይባላል:: ሚክያስ ማለት "መኑ ከመ አምላክ - እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው!" ማለት ነው:: አንድም "መልአከ እግዚአብሔር" ማለት ነው:: የአባቶቻችን ሁሉ ስማቸው እግዚአብሔርን የሚሰብክ ነው::
ቅዱሱ ነቢይ ገና ልጅ እያለ መላእክት ያነጋግሩት ነበር:: በዚህ ምክንያት ከሰው አይቀርብም:: ትክ ብለው ሲያዩት በፊቱ ላይ ብርሃን ቦግ ቦግ እያለ ይታይ ነበር:: በወጣትነት ዘመኑ እግዚአብሔር ለትንቢት ሲጠራው በእሺታ ታዘዘ:: በሦስቱ ነገሥታት (በኢዮአታም: አካዝና ሕዝቅያስ) ዘመንም ትንቢቶችን ተናግሯል:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን: ነገሥታቱን አስተምሮ ገስጿል::
አንድ ቀን በቤተ ልሔም ሲያልፍ የዳዊት ከተማ ፈት ሁና: ዳዋ በቅሎባት ቢመለከት አዘነ:: ወዲያውም ትንቢት ተናገረላት::
"ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ: ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ: እስመ እምኔኪ ይወጽዕ ንጉሥ: ዘይርዕዮሙ ለሕዝብየ እሥራኤል::"
"አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም: የይሁዳ ነገሥታት ከነገሡባቸው ከተሞች ከቶ አታንሺም:: ወገኖቼን እሥራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ (መስፍን) ካንቺ ዘንድ ይወጣልና::" አለ::
ይኸውም አልቀረ ለጊዜው ከሚጠት በኋላ ደጉ ዘሩባቤል ነግሦባታል:: በፍጻሜው ግን የባሕርይ ንጉሠ ነግሥት ኢየሱስክርስቶስ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወልዶባታል::
ቅዱስ ሚክያስ ወገኖቹን ሲያስተምርና ሲመራ ኑሮ: ሰባት ምዕራፎች ያሉትን ሐረገ ትንቢት ተናግሮ: በመልካም ሽምግልና: በንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን ዐርፏል:: ወገኖቹ ቀብረውታል:: ጌታም በክብረ ነቢያት ከልሎታል::
ቸር አምላከ ነቢያት የነቢያቱን መከራ አስቦ ከመከራ: በእንባቸውም ከእንባ ይሰውረን:: ከተረፈ በረከታቸውም አያጉድለን::
ነሐሴ 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ
1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
3.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
4.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
5.አባ ጳውሊ የዋህ
"ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መስዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጐች: ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? . . . ሰው ሆይ! መልካሙን ነግሮሃል:: እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ: ምሕረትንም ትወድ ዘንድ: ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሔድ ዘንድ አይደለምን?" (ሚክ. ፮፥፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ
No comments:
Post a Comment