ነሐሴ ፳፬
ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ
እጅግ የከበረችና የተመሰገነች እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን እናመሰግናታለን። እርሷ በሁሉ ጐዳና ፍጹምነትን ያሳየች ኢትዮዽያዊት እናት ናት። ገና ከልጅነት የነበራት የትሕትናና የመታዘዝ ሕይወት እጅግ ልዩ ነበር። እናታችን ቅድስናን ያገኘችው ገና በትዳር ውስጥ እያለች ነው።
ከተባረከ ትዳሯ 12 ልጆችን አፍርታ ምጽዋትን የዕለት ተግባሯ አድርጋ ኑራለች። በዚህ ደግነቷም ሙት እስከ ማንሳት ደርሳለች። አብያተ ክርስቲያናትን አንጻ አንድ ልጇን (ዳግማዊ ቂርቆስን) አዝላ ምናኔ ወጥታልች።
በደብረ ሊባኖስ ውስጥ የቆየችው ቅድስት እናት ተጋድሎዋን የፈጸመችው ግን ጣና ሐይቅ ውስጥ ነው። በተለይ ለ22 ዓመታት ሐይቁ ውስጥ አካሏ አልቆ አሣ በሰውነቷ ውስጥ እስከሚያልፍ ድረስ ተጋድላለች። በቀኝና በግራ 12 ጦሮችን ተክላም ጸልያለች።
ብዙ ኃጥአንን አማልዳ 12 ክንፎችን አብቅላ: ከፍ ከፍ ብላለች። ከርሕራሔዋ ብዛት የተነሳ ሰይጣንን እንኩዋ ለማስታረቅ ሞክራለች። ጌታም ከሲዖል ነፍሳትን እንድታወጣ ፈቅዶላታል። ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ያረፈችው በዚህ ዕለት ሲሆን አጽሟ እስከዛሬ በራሷ ገዳም (ጣና ዳር) ይገኛል።
ቅዱስ ቶማስ ዘምርዓስ
ነሐሴ ሃያ አራት በዚች ቀን የክርስቶስ ምስክሩና ሐዋርያው የሆነ የመርዓስ ኤጲስቆጶስ ተጋዳይ ቅዱስ አባት ቶማስ አረፈ ። የዚህንም አባት ትሩፋቱንና ገድሉን ሰው ተናግሮ ሊፈጽመው አይችልም እርሱ አስቀድሞ በጾም በጸሎት በስጊድ ቀንና ሌሊትም በመራራት ተጠምዶ የሚኖር ነው ። ከዚህም በኃላ መርዓስ ለሚባል አገር ኤጲስቆጶስ ይሆን ዘንድ የክብር ባለቤት ጌታችን መረጠው መንጋውንም እንደ ሐዋርያት ጠበቀ ። ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስም በነገሠ ጊዜ ክርስቲያኖችን ያሠቃያቸው ዘንድ ከመኳንቶቹ አንዱ ወደዚያች አገር ደረሰ እርሱም ቅዱስ ቶማስን ወደርሱ ያቀርቡት ዘንድ ጭፍሪቹን ላከ እነርሱም እየደበደቡ በምድር ላይ እየጎተቱ ወሰዱት ደሙም እንደውኃ ፈሰሰ ።
ከዚህም በኃላ መኮንኑ ቅዱስ ቶማስን ለአማልክት ስገድ አለው ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት እኔ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለረከሱ ጣዖታት የሚሰግድ ሁሉ የተረገመ ነውና ።
መኰንኑም ተቆጥቶ እጅግ የበዛና ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሥቃይን አሠቃየው የነዳጅ ድፍድፍና አፍልተው በላዩ በአፉና በአፍንጫው ውስጥ ጨመሩ እንዲህም እያደረጉበት እስከ ብዙ ዘመናት ኖረ ።
የእሊህ ከሀዲያን ልባቸው እንደ ድንጊያ የጸና ስለሆነ ቅዱስ ቶማስ ቶሎ እንዲሞት አልፈለጉም ። ሌሎች ብዙዎች ሰዎችን ያሰፈሩአቸው ዘንድ የክብር ባለቤት ክርስቶስንም ይክዱት ዘንድ የሥቃዩን ዘመን አስረዘሙ እንጂ ።
እርሱ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል የጸና ነውና ማሠቃየቱን ከሀድያን በተቸነፉ ጊዜ ስለ ስሕተታቸውም ይዘልፋቸው ስለነበር ስለዚህ በጨለማ ቦታ ጣሉት በዚያም ሃያ ሁለት ዓመት ኖረ።
ከሀድያንም በየዓመቱ ወደርሱ ገብተው ከሕዋሳቱ አንዱን ይቆርጣሉ። በዚያም ቦታ አፍንጫውን ከንፈሮቹን ጆሮዎቹን እጆቹንና እግሮቹን ቆረጡ መንጋዎቹም ያረፈ መስሏቸው በየዓመቱ መታሰቢያውን ሲያደርጉ ኖሩ። ነገር ግን አንዲት ክርስቲያናዊት ሴት በጣሉት ጊዜ ስለአየችው ቦታውን ታውቅ ነበር እርሷ በሌሊት ወደርሱ ተሠውራ በመሔድ ትመግበዋለች ። ጻድቅ ቁስጠንጢኖስም እስከ ነገሠና የቀናች የክርስቶስን ሃይማኖት ክብር እስከ ገለጠ ድረስ እንዲህ ሲሠቃይ ኖረ።
ይህም ንጉሥ ክርስቶስን በመታመን የታሠሩ እሥረኞችን ሁሉ በሀገሮች ሁሉ በወህኒ ቤት ያሉትን ይፈቷቸው ዘንድ አዘዘ።
ይችም ሴት ሒዳ ስለ ቅዱስ ቶማስ ከእርሱ የሆነውን ሃያ ሁለት ዓመት ተጥሎ እንደኖረ ለካህናቱ ነገረቻቸው በውስጡ ወደሚኖርበትም ቦታ መራቻቸው። እነርሱም አንሥተው ተሸከሙት እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አደረሱት በቤተ መቅደሱም ፊት ለፊት በወንበሩ ላይ አስቀመጡት ምእመናንም ሁሉ ወደርሱ እየመጡ ከእርሱ ይባረኩና የተቆረጡ ሕዋሳቱን ይሳለሙ ነበር።
ንጉሥ ቂስጠንጢኖስም የከበሩ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳትን የአንድነት ጉባኤን በኒቅያ አገር በሰበሰበ ጊዜ ይህ የከበረ ቶማስ ከእሳቸው አንዱ ነው።
ንጉሡም ወደ እንርሱ ገብቶ ሰላምታ ሰጣቸውና ከእርሳቸውም ቡራኬ ተቀበለ። የዚህ የቅዱስ ቶማስን ተጋድሎውን በነገሩት ጊዜ ወደርሱ ቀርቦ ሰገደለት ሕዋሰቱም ከተቆረጡበት ላይ ተሳለመው አዝኖና እጅግም አድንቆ ሕዋሳቱን ዳሠሠው ፊቱንና ዐይኖቹን አሻሸው።
ከሀዲ አርዮስንም ተከራክረው ከረቱ በኃላ አውግዘው ለይተው ከወገኖቹ ጋር ከቤተ ክርስቲያን አሳደዱት። ከዚህም በኃላ መንፈስ ቅዱስ እንደ አስተማራቸውና እንደመራቸው የሃይማኖትን ትምህርት በአንደበታቸው ተናገሩ ሕግና ሥርዓትን ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍርድንም ሠሩ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቶማስ ወደ መንበረ ሢመቱ ሔደ ካህናቱንና መንጋዎቹን ሁሉ ሰብስቦ አነበበላቸው እርሱንም እንዲአስተውሉት እንዲጠብቁትም በመጠበቅም እንዲጸኑ አዘዛቸው። ጥቂት ዘመናትም ከኖረ በኃላ በሰላም በፍቅር አረፈ የሹመቱም ዘመን አርባ ዓመት ነው በዚህም እግዚአብሔርን አገለገለው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን። በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment