ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 29 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 23, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 29

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

 ነሐሴ 29 በዚችም ቀን የአባ ዮሐንስ ሐጺር ፍልሰት እና ኤጲስ ቆጶስ አትናቴዎስ ከእርሱም ጋር ገርሲሞስና ቴዎዶጦስ በሰማዕትነት ያረፉበት ቀን ነው።

አባ ዮሐንስ ሐጺር
በዚችም ቀን የአባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ አስቄጥስ ገዳም የሥጋው ፍልሰት ሆነ ። ይህም የአባ እንጦንዮስ በሆነ በቊልዝም ገዳም ከአረፈ በኋላ ነው። ለእስክንድርያ አባ ዮሐንስ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ስምንተኛ የሆነ ነው። እርሱም ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ የከበሩ መነኰሳትም እንዲህ አሉት የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ በዚህ በቤተ ክርስቲያኑ ቢሆን እኛም ሥጋው በአለበት ለፈጣሪያችን እግዚአብሔር እንሰግድ ዘንድ እንሻ ነበር።
ያን ጊዜ የእግዚአብሔር ቸርነት አነሣሣችውና ስሙ ቆዝሞስ ለሚባል ለአንድ አበ ምኔት መልእክትን ጻፈ ከእርሱም ጋር የቊልዝም አገር የሆነ አረጋዊ አለ በደረሱም ጊዜ በዚያን ሰዓት ሥጋውን መውሰድ አልተቻላቸውም። የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ የኬልቄዶንን ጉባኤ በተቀበሉ መለካውያን ዘንድ ይጠበቅ ስለነበረ ነገር ግን ቦታውን አወቁ ተረዱ ወደ ቦታቸውም ተመልሰው ሃይማኖታቸው የቀና ምእመናን ሰዎችን አገኙ እነርሱም በዚያች አገር የሚኖሩ ናቸው ስለርሱ የመጡበትን ነገሩአቸው።
ከጥቂት ቀኖች በኋላም ከታላላቅ ዐረቦች ወገን ለቊልዝም አገር መኰንን ተሾመ እርሱም ለኤጲስቆጶስ አባ ሚካኤል ወዳጁ ነው ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስም ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ ወደ ኤጲስቆጶሱ መልእክትን ጻፈ፤በመልእክቱም የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋ ከከሐድያን መለካውያን እጅ እስከ አፈለሱት ድረስ መልእክተኞች አእሩግ መነኰሳትን ምክንያት ፈልጎ እንዲረዳቸው በማሳሰብ አዘዘው።
ኤጲስቆጶሱም በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለው ሒዶም ወዳጁ ለሆነ ለመኰንኑ ጸሐፊ ነገረው። ጸሐፊውም ለመኰንኑ ነገረው። እነሆ መኰንኑም ከመነኰሳቱ ጋራ ሔደ ጸሐፊውም መነኰሳቱ ወደዚያ ቦታ እንዲገቡ ምክንያት እንዴት እናገኛለን አለ ። መኰንኑም በልብሶቻቸው ላይ የዓረቦችን ልብሶች ያልብሱአቸውና ከእኔ ጋራ ወደዚያ ቦታ ይምጡ አለ እንዲሁም እንዳላቸው አደረጉ።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ ሔደ ከእርሱም ጋራ ብዙ ፈረሰኞች ሰዎች ብዙ ሕዝብም የአስቄጥስ ገዳም የከበሩ አረጋውያን አሉ ወደቊልዝም ገዳምም ደረሱ። መኰንኑም በዚያ የሚኖራውን የመለካውያን ኤጲስቆጶስ እንዲህ ብሎ አዘዘው ያንተን ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስወጣቸው በዚች ሌሊት እኔ በውስጧ አድራለሁና ያ መለካዊም መኰንኑ እንዳዘዘው አደረገ።
መነኰሳቱም እንስሶቻቸውን ከከተማ ውጭ አዘጋጅተው በሌሊት ወደዚያ ገብተው የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋ ይዘው ወደ ምስር ደረሱ ከዚያም ወደ አስቄጥስ ገዳም ደረሱ የአባ መቃርስ ገዳም መነኰሳትም መስቀሎችን፣ ወንጌሎችን፣ ማዕጠንቶችንና መብራቶችን በመያዝ እየዘመሩና እያመሰገኑ ተቀበሏቸው ወደ አባት መቃርስ ሥጋም አቀረቡትና ከእርሱ ተባረኩ በላዩም ብዙ ሽቱዎችን ነሰነሱ የቊርባን ቅዳሴንም ቀደሱ የከበረ ወንጌልም በሚነበብ ጊዜ ታላቅ ድንቅ ተአምር ተገለጠ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለመናዋ በሰማያዊ ብርሃን በራች ። ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ በጎ መዓዛ ሸተተ ታላቅ ደስታም ሆነ በዚያም ቦታ ሰባት ቀን ኖረ።
ከዚህም በኋላ ወደ ራሱ ቤተ ክርስቲያን ተሸክመው ወሰዱት ዕብራውያንም በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እያሉ መድኃኒታችንን እንደተቀበሉት ልጆቹ መነኰሳት ተቀበሉትና ወደ ቦታው አኖሩት ከእርሱም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።
ከዚህም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስ በወጣ ጊዜ ወደ አባ ዮሐንስ ሐጺር ቤተ ክርስቲያን ገባ። ከእርሱም ጋር ብዙዎች ኤጲስቆጶሳትና የእስክንድርያ አገር ታላላቆች ከግብጽ አገር ሁሉ አሉ። የአባ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ የተጠቀለለበትን ሰሌን ገልጦ ከእርሱ ተባረከ መሪር ልቅሶንም አለቀሰ ያን ጊዜ ሥጋው ሲገለጥ መብረቅና ነጐድጓድ ሆነ። በቤተ ክርስቲያኑም ውስጥ ያሉት ሁሉም ደንግጠው ወደቁ ሊቀ ጳጳሳቱም ሰሌኑን መልሶ በፍጥነት ሥጋውን ጠቀለለ በሽብሸባ እየዘመሩና እያመሰገኑ እንደቀድሞው ሸፈነው።
ከዚህም በኋላ ዳግመኛ እንዲህ እያሉ ሊያመሰግኑ ጀመሩ ፈጣን ደመና ሁነህ የመንፈስ ቅዱስን ዝናም የተሸከምክ ሠለስቱ ደቂቅ ወዳሉበት ወደ ባቢሎን የሔድክ በላይህ በአደረ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ እስከንድርያ አገር የተመለስክ ሁለተኛም ወደ ቊልዝም የሔድክ የጣዖታትን ቤቶች አፍርሰህ ሃይማኖትን የሰበክ በሽተኞችን የፈወስክ አጋንንትን ያስወጣህ ወደርስትህም የተመለስክ አንተ የበረከት ማደሪያ ነህና። የአባ ዮሐንስ ሐጺር የሥጋው ፍልሰት ከንጹሐን ሰማዕታት ዘመን በአምስት መቶ ሃያ ዓመት ሆነ።
ቅዱስ አትናቴዎስ ሰማዕት እና ሁለቱ አገልጋዮች (ገርሲሞስና ቴዎዶጦስ)
ዳግመኛም በዚችም ቀን ኤጲስቆጶስ አትናቴዎስ በሰማዕትነት ሞተ ከእርሱም ጋር ስማቸው ገርሲሞስና ቴዎዶጦስ የሚባል ሁለት አገልጋዮች በሰማዕትነት አረፉ።
ይህንንም ቅዱስ አትናቴዎስን የእንጦኒቆስን የጭፍራ አለቃውን ልጅ እርሱ እንዳጠመቃት በንጉሥ ዘንድ ወነጀሉትና ንጉሥ አርስያኖስ ያዘው እርሱም ክርስቲያን እንደሆነ ታመነ ብዙ ሥቃይንም አሠቃየው።
በሃይማኖቱም ጸና እንጂ ሃይማኖቱን ባልካደ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ እንዲሁም እሊህን ሁለቱን አገልጋዮች ገርሲሞስንና ቴዎዶጦስን በግርፋትና በስቅላት ከቀጣቸው በኋላ ራሶቻቸውን በሰይፍ አስቆረጠ ሦስቱም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።
አማንያን ሰዎችም መጡ ለወታደሮችም ገንዘብ ሰጥተው የቅዱሳኑን ሥጋቸውን ወሰዱ በአማሩ ልብሶችም ገንዘው በሣጥን ውስጥ አኖሩአቸው ከሥጋቸውም ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።
ነሐሴ 29 ቀን የሚከበሩ
👉
ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐጺር (ፍልሠቱ)
2.ቅዱስ አትናቴዎስ ሰማዕት
3.ቅዱሳን ገርሲሞስና ቴዎዶጦስ (ሰማዕታት)
4.አባ ባስልዮስ ጻድቅ (ዘትግራይ)
👉
ወርኀዊ በዓላት
1.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
2.ቅድስት አርሴማ ድንግል
3.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
5.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
6.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)
"እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ 'የማንጠቅም ባሪያዎች ነን: ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል' በሉ::" † (ሉቃ. 17:10)
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን። በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages