ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 30 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 23, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 30

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። 

ነሐሴ ሠላሳ በዚች ቀን ከዐሥራ ስድስቱ ነቢያት አንዱ ታላቅ ነቢይ ሚልክያስ ያረፈበት እና ጌታ ባሕር ውስጥ ለሐዋርያ እንድርያስ በሊቀ ሐመር አምሳል ተገልጦ ድንቅ ተአምር ያደረገለት ቀን ነው።



ነቢዩ ሚልክያስ
ነሐሴ ሠላሳ በዚች ቀን ከዐሥራ ስድስቱ ነቢያት አንዱ ታላቅ ነቢይ ሚልክያስ አረፈ። ይህም ነቢይ የእስራኤል ልጆች ከተሰደዱበት ከባቢሎን ሀገር በተመለሱ ጊዜ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፋቸው ገሥጿቸዋል።
ሁለተኛም ነቋር ስለሆነ መሥዋዕት ስለ አሥራትና በኵራት ገሥጿቸዋል። በዚህ ነቢይ አንደበት እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሯልና ርኅራኄ አድርጋችሁ ምጽዋትን መጽውቱ፣ ዐሥራቴንና በኵራቴንም አስገቡና እስቲ ፈትኑኝ እኔ ከሰማይ ዝናሙን ባላወርድላችሁ በረከትንም አስቲበቃችሁ ባልጨምርላችሁ የምድራችሁንም ፍሬ ነቀዝና መሰክ እንዳይበሉት እከለክላለሁ።
ዳግመኛም ከክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አስቀድሞ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ መምጣቱ ስለ ነቢዩ ኤልያስም ተናገረ። ደግሞ ስለ አይሁድ የሥርዓተ ክህነት ፍጻሜ ተናገረ በአሕዛብም አገር ውስጥ ለእግዚአብሔር የሚቀበላቸውን መሥዋዕት የሚያሳርጉ ዕውነተኞች ንጹሐን ካህናት እንዳሉ ገለጠላቸው።
በበጎ ተጋድሎውም እግዚአብሔርን ከአገለገለ በኋላ ከዚህ ዓለም በመፍለስ በሰላም አረፈ።
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ
በዚችም ቀን ጌታችን በባሕር ውስጥ ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ በሊቀ ሐመር አምሳል ተገልጦ ድንቅ ተአምር አደረገለት።
እንድርያስም ጌታችንን በመርከብህ አሳፍረን ነገር ግን የምንከፍልህ የመርከብ ዋጋ የለንም አለው። በሊቀ ሐመር የተመሰለ ጌታችንም ስለምን የላችሁም አለው እንድርያስም በከረጢታችን ወርቅን፣ ብርን እንዳንይዝ ስለአዘዘን ነው አለው። ጌታችንም እንዲህ ከሆነ ወደ መርከቤ ወጥታችሁ ተሳፈሩ አላቸው ያንጊዜም ወደ መርከብ ወጥተው ተሳፈሩ።
ከዚህም በኋላ ጌታችን እንድርያስንና ደቀ መዛሙርቱን ከባሕሩ ማዕበል የተነሣ መታገሥ እንድትችሉ ተነሥታችሁ እንጀራ ብሉ አለ። አንድርያስም አድንቆ እንዲህ አለው በመንግሥተ ሰማያት የሕይወት እንጀራ እግዚአብሔር ይስጥህ። ደቀ መዛሙርቱ ግን በባሕር ላይ ጉዞ ስለአልለመዱ ከባሕሩ ማዕበል ፍርሀት የተነሣ መብላት መነጋገርም ተሳናቸው ።
ጌታችንም እንድርያስን ደቀ መዛሙርትህን ወደ ምድር እንዲወርዱ እዘዛቸው ሲፈሩ አያቸዋለሁና ይህ ካልሆነ እንዳይፈሩ አንተ የኢየሱስ ደቀ መዝሙሩ ከሆንክ ጣዕም ባለው ቃል አስተምራቸው እነሆ ከየብስ ርቀናልና አለው። ጌታችንም መርከቡን መቅዘፍ ጀመረ እንድርያስም ማስተማርና ማጽናናት ያዘ በልቡም ጸለየ ያን ጊዜም ከባድ እንቅልፍን አንቀላፉ ስለተኙለትም እንድርያስ ደስ አለው።
እንድርያስም ወደ ጌታችን ተመልሶ እንዲህ አለው ዐሥራ አራት ጊዜ በባሕር ላይ ጒዞ አድርጌአለሁ እንዳንተ የሚቀዝፍ አላገኘሁም። ጌታም መልሶ እንዲህ አለው እኛስ በባሕር ላይ ስንጓዝ ሁል ጊዜ እንቸገራለን። ነገር ግን አንተ የክብር ባለቤት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደሆንክ ባሕር ስለአወቀችህ ማዕበሏን በአንተ ላይ አላነሣችም እንድርያስም በታላቅ ቃል እንዲህ ብሎ ጮኸ። የክብር ባለቤት ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግንሃለሁ ከሚያከብርህ ሰው ጋር ተገናኝቼ ተነጋግሬአለሁና።
ከዚህም በኋላ ጌታችን እንድርያስን እንዲህ አለው አንተ የክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ ነህና ንገረኝ። አይሁድ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ስለምን አላመኑም የሠራውን ብዙ ድንቅ ተአምርን ሰምተናልና አለው። እንድርያስም እንዲህ አለው አዎን ወንድሜ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ገልጦልናል አንካሶችንም በትክክል እንዲሔዱ አድርጓልና፣ ደንቆሮዎችንም አሰምቷልና፣ ዲዳዎችንም አናግሮአልና፣ ለምጻሞችንም አንጽቷልና፣ ውኃውንም ወይን አድርጓልና፣ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣን አንሥቶ ያዘ ሕዝቡንም በመስክ ሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ ሣሩም እንጀራ እስቲለብስ ድረስ በልተው ጠገቡ የተረፈውንም በብዙ ቅርጫቶች አነሣን ይህም ሁሉ ሲሆን አላመኑም።
ጌታ ኢየሱስም እንዲህ አለው ይህን ያደረገ በግልጥ ነው ወይስ በሥውር። እንድርያስም እንዲህ አለው ይህንስ በግልጥ ነው ያደረገ በሥውር ያደረገውም አለ ግን የምትፈትነኝ መሰለኝ ጌታችንም እንዲህ አለው ወንድሜ ሆይ ልቤን ደስ ስለሚላት ነውና ንገረኝ።
እንድርያስም እንዲህ አለው ልጄ ሆይ በጎ ሥራህን ሀሉ እግዚአብሔር ይፈጽምልህ አሁንም ስማ ጌታችን ያደረገውን ተአምር እኛ ዐሥራ ሁለታችን ሐዋርያቶቹ ከእርሱ ጋራ ስንጓዝ ከሊቃነ ካህናትና ከሕዝቡ ብዙዎች አሉ። ወደ ምኵራብም ደረስን ጌታችንም እንዲህ አለ በሰማይ ባሉ በኪሩቤልና በሱራፌል አምሳል በምድር ላይ ሰው የሠራትን ይቺን የተቀረጸች ሥዕል ታያላችሁን።
ከዚህም በኋላ ወደሥዕሊቱ ተመልሶ ብልህ ሰው የተጠበበብሽ የሰማያውያን መልክን ያደረግሽ አንቺን እላለሁ ከቦታሽ ተነቅለሽ ውረጂ የካህናት አለቆችንም ወቀሻቸው እኔም ዕሩቅ ብእሲ ወይም እግዚአብሔር እንደሆንኩ መስክሪ አላት። ወዲያውኑ ከቦታዋ ተነቅላ ወረደች እንደሰውም በመናገር እንዲህ አለች እናንተ የደነቆራችሁ አይሁድ የራሳችሁ መደንቆር ያልበቃችሁ ሌሎችንም ለማደንቆር የምትሹ ለድኅነታችሁ ሰው የሆነ እግዚአብሔርን እንዴት ዕሩቅ ብእሲ ትሉታላችሁ አስቀድሞ ሰውን የፈጠረው በንፍሐት ልጅነትንም የሰጠው ይህ ነው።
አብርሃምን የተናገረው፣ ይስሐቅንም ከመታረድ ያዳነው፣ ያዕቆብንም ወደ አገሩ ያስገባው ይህ ነው ለሚፈሩት በረከትን የሚሰጥ ለማይታዘዙለት ቅጣትን የሚያዘጋጅ ይህ ነው ።
እውነት እነግራችኋላሁ እናንተ ስለምትክዱት ሕጉንና ሥርዓቱንም ትለውጣላችሁና ስለዚህ እነሆ መስዋዕታችሁ ይሻራል ምኵራቦቻችሁም በዋሕድ ወልደ እግዚአብሔር ስም አብያተ ክርስቲያናት ይሆናሉ። ይህንንና የሚመስለውን ተናግራ ዝም አለች።
እኛም የካህናት አለቆችን መልሰን እንዲህ አልናቸው እነሆ ቅርጺቱ ሥዕል ተናግራ ወቀሰቻችሁ ታምኑ ዘንድ ይገባችኋል። የካህናት አለቆችና አይሁድም እንዲህ አሉን ይህ የሚያናግረው በሥራይ ነው አብርሃምን በወዴት አገኘው ከሞተ ዘመኑ ብዙ ነውና።
ጌታ ኢየሱስም ወደ ቅርጺቱ መለስ ብሎ እንዲህ አላት አብርሃምን እንዳነጋገርኩት አላመኑምና ሔደሽ እንዲህ በይው። አስቀድሞ አዳምን የፈጠረው፣ አንተንም ወዳጁ ያደረገህ፣ አንተ ልጆችህ ይስሐቅና ያዕቆብን ይዘህ ተነሥ ከመቃብርም ወጥተህ ወደዚህ ኑ የካህናት አለቆችን ትወቅሱአቸው ዘንድ እኔ የማውቃችሁና የተነጋገርኳችሁ መሆኔን አስረዷቸው። ቅርጺቱም ሥዕል ይህን ሰምታ እያየናት ሔደች ወደ አብርሃምም መቃብር ደርሳ በውጭ ቁማ ጠራቻቸው። ወዲያውኑ ከሦስቱ አርእስተ አበው ጋር ዐሥራ ሁለቱ ወጡ ከእኛ ውስጥ ወደ ማን ነው የተላክሽ አሏት። ቅርጺቱም እንዲህ ብላ መለሰች ወደ ሦስቱ የአባቶች አለቆች ነው እናንተ ግን እስከ ትንሣኤ ሙታን ድረስ ተኙ ያን ጊዜም ወደ መቃብራቸው ተመለሱ።
እሊህ ሦስቱ አባቶችም የካህናት አለቆችና እኛ ወደ አለንበት ከቅርጺቱ ሥዕል ጋር መጥተው ወቀሷቸው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነም ነገሩአቸው።
ከዚህም በኋላ ጌታችን አባቶችን ወደቦታችሁ ሒዱ አላቸው ወዲያው ተመለሱ ቅርጺቱንም ወደቦታሽ ተመለሽ አላት እርሷም ወደ ቀደመው አኗኗርዋ ተመለሰች ይህንንም አይተው የካህናት አለቆች አላመኑም ሌላም ብዙ አለ ብነግርህ መወሰን አትችልም ነገር ግን ለብልህ ጥቂት ቃል ትበቃዋለች ለሰነፍ ግን ቢነግሩት በቁም ነገር ላይ አይታመንም።
ከዚህም በኋላ ጌታችን ማነጋገሩን ገታ ራሱንም እንደሚያንቀላፋ አደረገ እንድርያስም አንቀላፋ እንድርያስንና ደቀ መዛሙርቱን እንዲሸከሙአቸውና ሊገቡበት ወደሚሹት አገር በውጭ እንዲአኖሩዋቸው መላእክትን አዘዛቸው።
ከዚህም በኋላ እንድርያስ በነቃ ጊዜ ዐይኖቹን ገለጠ የከተማውንም በር ተመለከተ በየብስም ላይ እንዳለ አውቆ ደነገጠ አደነቀም። ደቀ መዛሙርቱንም አነቃቸውና እንዲህ አላቸው ጌታችንን በባሕር ላይ ሳለን ያላወቅነው ምን አደረገብን ሲፈትነን መልኩን ለውጦ እንደ ሰው ሁኖ ታይቶናልና።
ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉት እኛም በጌትነቱ ዙፋን ላይ ሁኖ የመላእክት ሠራዊት ሁሉ በዙሪያው ሁነው ጌታችንን አየነው አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብንም ቅዱሳንን ሁሉ አየናቸው ንጉሥ ዳዊትም በመሰንቆ ይዘምር ነበር። እናንተንም ዐሥራ ሁለት ሐዋርያት በፊቱ ቁማችሁ ዐሥራ ሁለቱንም የመላእክት አለቆች በፊታችሁ ሌሎች መላእክት በኋላችሁ ሁነው አየናችሁ። እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስንም መላእክትን እንዲህ ብሎ ሲያዛቸው ሰማነው የሚሉአችሁን ሁሉ ሐዋርያትን ስሟቸው።
እንድርያስም በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው ይህን ድንቅ ምሥጢር ያዩ ዘንድ ደቀ መዛሙርቱ የሚገባቸው ሆነዋልና። ከዚህም በኋላ እንድርያስ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ እንዲህ ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከእኛ ከባሮችህ ሩቅ እንዳልሆንክ አወቅሁ። ነገር ግን በመርከብ ላይ እኔ እንደማስተምረው ሰው መስለኸኝ በድፍረት ተናግሬሃለሁና ጌታዬ ይቅር በለኝ ።
በዚያንም ጊዜ የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእንድርያስ ዳግመኛ ተገለጠለት እንዲህም አለው። አዎን እኔ ነኝ በሊቀ ሐመር አምሳል በባሕር ውስጥ የተገለጥኩልህና መርከቡን የቀዘፍኩልህ። አትፍራ አትደንግጥ እኔ ከአንተ ጋራ እኖራለሁ ይህንንም ብሎ ወደ ሰማያት በክብር ዐረገ እንድርያስም መንገዱን ሄደ።

 ነሐሴ 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ሚልክያስ ነቢይ
3.አባ ሙሴ ዘሃገረ ፈርማ

 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
2.አባ ሣሉሲ ክቡር
3.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
4.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
5.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት


"ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ:: ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል:: 'መፋታትን እጠላለሁ' ይላል የእሥራኤል አምላክ: የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር::" (ሚል. ፪፥፲፭)

 "ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃቹሃል:: እናንተም 'የሰረቅንህ በምንድን ነው?' ብላቹሃል:: በአሥራትና በበኩራት ነው:: እናንተ: ይህ ሕዝብ ሁሉ እኔን ሰርቃቹሃልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ::" (ሚል. ፫፥፰)
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጌቶቻችን ሐዋርያት በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages