ማቴዎስ ወንጌል 1፤ 19 እስከ ፍጻሜ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, April 25, 2020

ማቴዎስ ወንጌል 1፤ 19 እስከ ፍጻሜ


ወእንዘ ዘንተ ይሄሊናሁ አስተርአዮ መልአከ እግዚአብሔር ለዮሴፍ በህልም  
 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክፍል ሁለት ማቴዎስ 1፤19-25

 ወእንዘ ዘንተ ይሄሊ ናሁ አስተርአዮ መልአከ እግዚአብሔር ለዮሴፍ በህልም
  ሕልም ከሦስት ወገን ነው
1) ከሐሞት
2) ከመልአክ
3) ከሰይጣን የሚገኝ ነው።

 ከሐሞት የሚገኝ በልቀም፤ ደም፤ ሳፍራ፤ ሳውዳ የሚባሉ ሐሞታት አሉ።
 በልቀም====እሳታዊ ደም=====ማያዊ ሳፍራ====ነፍሳዊ ሳውዳ====መሬታዊ ነው።

 እኒህ በሰለጠኑ ጊዜ በየኅብራቸው ሲያሳዩ ያድራሉ
  ከሰይጣን የሚገኝ እንደ ሄሮድስ በስደቷ ጊዜ ከዚህ ዋለች ከዚያ አደረች እያለ ይነግረው ነበር
  ከመልአክ የሚገኝ እንደ ዮሴፍ እንደ ፈርዖን እንደ ናቡከደነፆር።
 እንዘ ይብል ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት ኢትፍራህ ነሲኦታ ለማርያም ፍኅርትከ።
 ኦ ቃለ አክብሮ ቃለ አኅስሮ ቃለ አራህርሆ ይሆናል። ቃለ አኅሥሮ ኦ ሐናንያ ኦ አብዳን ሰብዓ ገላትያ ቃለ አክብሮ ኦ ጳውሎስ ምንት ትቤ ኦ አኃውየ ፍቁራን ቃለ አራኅርሆ ኦ ድንግል አዘክሪ ኦ ዮሴፍ ያለው ይህ ነው። የሩህሩህ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ እህትህ ናትና ራራላት።  አንድም፤ የጥቡዕ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ ከካህናት እጅ እንደ ተቀበልህ ከእደ መንፈስ ቅዱስ መቀበልን አትፍራ። ንሲዖታ ባለው አዕርጎታ አውፅዖታ አቂቦታ ተል እኮታ ይላል። እስመ አምፍሬ ከርሥከ አነብር ዲበ መንበርከ ያለው ትንቢት እንደተፈጸመ ለማጠየቅ ዳዊትን አነሣው።

እስመ ዘይትወለድ እምኔሃ እመንፈስ ቅዱስ ውእቱ ። ከእሷ የሚወለደው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነውና።
ማቴዎስ እመንፈስ ቅዱስ ያለውን ሉቃስ መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ያለውን ኢሳይያስ መንፈሰ እግዚአብሔር ዘላዕሌየ ዘበእንቲአሁ ቀብዓኒ ያለውን ሊቁ ዛቲመ ትርጓሜሃ ለቅብዓት እስመ መንፈስ ቅዱስ አንጽሐ ሥጋሁ ለአዳም ብሎ ወስዶታል።
ንጽሐን ክብር የሚል ወዴት አለ ቢሉ ወሠዓርኮ እምንጽሑ ይላል።  ወትወልድ ወልደ ወንድ ልጅ ትወልዳለች ወትሰምዮ ስሞ ኢየሱስሃ ስሙንም ኢየሱስ ትለዋለች እስመ ውእቱ ያድኅኖሙ ለህዝቡ እምሃጣውኢሆሙ ወገኖቹ እስራኤልን በሃጢአት ከመጣባቸው ፍዳ ያድናቸዋልና፤ ወዝንቱ ኩሉ ዘኮነ ከመ ይትፈጸም እምኀበ እግዚአብሔር በነቢይ እንዘ ይብል ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ እመቤታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ትፀንሳለች በግብረ መንፈስ ቅዱስ ትወልዳለች ብሎ መል አኩ ለዮሴፍ መንገሩ ነቢዩ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ብሎ የተናገረው ይደርስ ይፈጸም ዘንድ ነው። ወይሰመይ ስሙ አማኑኤል ዘበትርጓሜሁ እግዚአብሔር ምስሌነ ስሙም አማኑኤል ይባላል። ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው ወተንሲኦ ዮሴፍ እምንዋሙ ገብረ በከመ አዘዞ መል አከ እግዚአብሔር ዮሴፍም ከእንቅልፉ ተነስቶ መል አኩ ያዘዘውን እንዳዘዘው አደረገ ወኢያእመራ እስከ አመ ወለደት ወልደ ዘበኩራ የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ የግብር እውቀት አላወቃትም። ከወለደች በኋላስ አወቃት ማለት ነውን ቢሉ? ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው። ኢተመይጠ ቋዕ እስከ አመ ነትገ ማየ አይኅ ኢወለደት ሜልኮል እስከ አመ ሞተት። ሜልኮል ከሞተች በኋላ ወለደች ማለት ነውን ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው።

 አንድም
 አምላክን የወልደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልናዋ ጸንታ የኖረች የአምላክ እናት ናት እንጂ ሌሎች መናፍቃን እንደሚሉት ልጆችን የወለደች አይደለችም። የተመረጠችው ለአምላክ እናትነት ብቻ ነውና።
 በክርስቶስ አምላክነት አምነን ክርስቲያን ነን ብለን እስካልን ድረስ የባህርይ አምላክ መሆኑን መጠራጠር የለብንም የባህርይ አምላክ ነውና። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ተወልዶልናልና ስለዚህ እመቤታችን ወላዲተ አምላክ የአምላክ እናት ናት ብሎ ማመን ግዴታችን ነው ማለት ነው።

  የመስቀል ሥር ስጦታችንን፤ እናታችንን፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከተለዩ የተለየች ከከበሩት የከበረች የሚያደርጋት ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ አምላክን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና መውለዷ ነው።

 እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታን ከመጽነሷ በፊት፤ በጸነሰች ጊዜ፤ ከጸነሰች በኋላ ከመውለዷ በፊት፤ በወለደች ጊዜ ከወለደች በኋላ ድንግል ናት።  ነቢዩ ሕዝቅኤል የተመለከተው ራዕይም እመቤታችን እናትና ድንግል መሆኗን ነው። ሕዝ 44፤3

  እመቤታች ከሌሎች ሴቶች ተለይታ እግዚአብሔር ከፈጠራት ጀምሮ በሃሳብ በመናገርና በመስራት ንጽሐ ጠባይዕ ያላደፈባት ንጽህት ድንግል ናት።  እመቤታችን የዘለዓለም ድንግል ናት (መኃ 4፤15)

  በተጨማሪም ለእመቤታችን ቅድስት ማርያም፤ ድንግል የሚለው ቃል በእርግጥ ቅድስናዋን ንጽሕናዋን ብቻ ሳይሆን ልዩ መሆንዋን ያመለክታል፤ ምክንያቱም ልዩ የሆነች እናት ናትና፤ ብጽእት ናትና፤ ቅድስት ናትና፤ ፍጽምት ናትና፤ የመዳናችን ምክንያት ናትና

 በዓለም ከነበሩና ከሚኖሩ ሴቶች እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ድንግልና ከእናትነት እናትነትን ከድንግልና ጋር አስተባብራ የተገኘች ሴት የለችም። ፈጽሞም ሊኖር አይችልም፤ የአምላክ እናት ናትና።

አንድም
 ነቢዩ ኢሳይያስ እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ብሎ ስሟን እስከ ግብሯ ድንግል ብሏታል

 ቅዱስ ሉቃስም ቅዱስ ገብር ኤል ወደ አንዲት ድንግል ተላከ የዚያችም ድንግል ስሟ ማርያም ነው በማለት ስለ ድንግልናዋ ተናግሯል ሉቃ 1፤27

 የቅድስት ኤልሳቤጥ ምስክርነት እንዲህ የሚል ነበር፤ አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ የማህጸንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፤ የጌታየ እናት ወደ እኔ ትመጭ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል። ሉቃ 1፤41

  ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች ልጅንም ትወልዳለች ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆነ።

 ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም እንዲህ ብሏል፤ ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከልን እርሱም ከሴት ተወለደ ለሕግም ታዛዥ ሆነ። ገላ 4፤4 አንዳንድ አላዋቂ መናፍቃን ያወቁ እየመሰላቸው የእመቤታችንን ክብር ሲያዋርዱ ይስተዋላሉ። እናቱን ጠልቶ ልጁን እወድሃለሁ ማለት ምን ይሉታል እብደት ካልሆነ በቀር። በማቴዎስ ወንጌል 1፤20 ላይና በሉቃስ 1፤27 ላይ እመቤታችን የዮሴፍ እጮኛ ስትባል ከቆየች በኋላ በማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ ሁለት ላይ የዮሴፍ እጮኛ መባል ቀርቶ ሕጻኑን ከእናቱ ጋር መባል ተጀመረ።
ለምን ቢሉ? አረጋዊው ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወደ ቤቱ የወሰዳት ወይም በመልአኩ ዘንድ እንዲወስዳት የታዘዘው እንዲጠብቃት እንጂ እንዲያገባት አይደለምና። መናፍቃን ሆይ ይህን አስተውሉ። በፈጣሪያችሁ ላይ አትዘባበቱ። ያመለካችሁ እየመሰላችሁ በፈጣሪ ላይ አትዘባበቱ። እመቤታችንን ሌላ ልጅ ወልዳለች እያላችሁ አምላክን አታስቀይሙ። የት እንዳመጣችሁት ራሳችሁን ፈትሹ።  መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ሲያበስራት እንኳ እመቤታችን የሰጠችው መልስ ድንግል ነኝ ይህ እንዴት ይሆናል ብላ ነው የተናገረች፤ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተዋልና በፍጹም መንፈሳዊነት እናንብብ። አለበለዚያ አወዳደቃችን የከፋ ነው የሚሆነው። አምላክ ታግሎ የጣለ የለምና እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ። የብርሃን እናቱ ስለሆነችው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክነት፤ ዘለዓለማዊ ድንግልና ስናነሳ ብዙ አህዛብና መናፍቃን የሚያነሱት ጥያቄ አለ። በእርግጥ መናፍቃኑ ራሱን ክርስቲያን ነኝ ብሎ በድፍረት ሲናገር ሳይ ይገርመኛል። ምክንያቱም እናቱን እያዋረዱ ልጁን እናመልካለን ማለት ራሱ የሚያመልኩት ጌታ ከተዋረደች እናት የተወለደ ነው እያሉ እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል። እግዚአብሔር አምላክ ልቦናችሁን ይመልስላችሁ ሌላ ምን ይባላል። በተለይ በሉቃስ ወንጌል 2፤17 ላይ ያለውን ቃል ስንመለከት የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ የሚል ቃል አለ።
 ይህን ቃል አጣመው በመተርጎም መንፈሳዊ ሳይሆን ዓለማዊ ትርጉም ሰጥተው የአምላክን እናት ከሌላ እንደወለደችና ጌታችን በሥጋ ወንድሞች እንዳሉት አድርገው የሚዘባርቁ እኩይ መናፍቃን አሉ። ለዚህም የሚሰጡት መረጃ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ወንድም ወንድሞች ተብሎ የተጠቀሰውን በመውሰድ ጥሬ ቃሉን በቀጥታ በመተርጎም ሲሰናከሉበት እናያለን ይከራከራሉም ነገር ግን ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን እንዴት ያየዋል በመጨረሻው በክፍል ሦስት እመለስበታለሁ። ይቆየን…………..

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages