የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ ባለሟል በነበረው በገዛ አባቱ እጅግ ተሠቃይቶ ምስክርነቱን የፈጸመው ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦር ዕረፍቱ ነው፡፡ ኅርማኖስ የተባለው ወላጅ አባቱ የክርስቲያኖችን ደም እንደ ውኃ ያፈስ የነበረው የዲዮቅልጥያኖስ ልዩ አማካሪና የሠራዊቱ አለቃ ነበር፡፡ እናቱ ማርታ ግን በክርስቶስ አምና የተጠመቀች ክርስቲያን ነበረች፡፡ እንዲያውም ልጇን ቅዱስ ፊቅጦርን ከመውለዷ በፊት የአምላክ እናት የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ወዳለበት ሄዳ ‹‹እመቤቴ ማርያም ለኢየሱስ ክርስቶስ ደስ የሚያሰኘውን ልጅ ስጪኝ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ደስ የማያሰኝ ልጅ ከሆነ ግን ማኅፀኔን ዝጊልኝ›› ብላ በጸለየችው ጸሎት ነው ቅዱስ ፊቅጦርን ያገኘችው፡፡
ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር በዓለም ላይ ያሉ በክርስቶስ ያመኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ በግፍ ያስገድል በነበረበት ወቅት የተገኘ ታላቅ ሰማዕት ነው፡፡ ፊቅጦርን ገና 15 ዓመት እንደሆነው ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ ‹‹ከፍ ባለ ስልጣን አስቀምጥሃለሁ፣ እጅግ ብዙ ወርቅና ንብረትም እሰጥሃለሁ፣ በእስክንድርያም ላይ ገዥ አድርጌ እሾምሃለሁ ክርስቶስን ማመንህን ተውና ወደ ቤተ መንግሥቴ ግባ›› ቢለውም ቅዱስ ፊቅጦር ግን ብዙ መከራንና ሥቃይን ተቀብሎ ሰማዕት መሆንን መረጠ፡፡ ቅዱስ ፊቅጦርም ዲዮቅልጥያኖስን ‹‹ክርስቶስን በምታፈቅረው ጊዜ አፈቀርኩህ ወደ አንተም መጣሁ፤ ክርስቶስን በጠላኸው ጊዜ ግን እኔም ጠላሁህ፣ ቤትህንም ጠላሁ›› ብሎታል፡፡
ከብዙ ጊዜም በኋላ ዲዮቅልጥያኖስ ቅዱስ ፊቅጦርን በመንግሥቱ ውስጥ ሦስተኛ ማዕረግ አድርጎ ሾመው፡፡ እርሱ ግን ይጾማል ይጸልያል እንጂ በንጉሡ ቤት አይበላ አይጠጣም ነበር፡፡ ዕድሜውም 27 ብቻ ነበር፡፡ አባቱንም ከጣዖት አምላኪነቱ እንዲመለስ ቢመክረው ሄዶ ለንጉሡ ከሰሰው፡፡ ፊቅጦርም ‹‹ለአንተ ለጣዖት አምላኩ አገልጋይ አልሆንም›› በማለት በንጉሡ ፊት ትጥቁን ፈቶ ጣለ፡፡ የቅዱስ ፊቅጦር ወላጅ አባቱ ኅርማኖስ የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ የቅርብ እንደራሴና መስፍን ስለነበር ልጁ ፊቅጦርን የንጉሡን ሹመትና ልመና እንዲቀበል ብዙ ሲያግባባው ነበር፡፡ አባቱም ልጁ በሀሳቡ እንዳልተስማማለት ሲያውቅ ከዲዮቅልጥያኖስ ጋር ተማክሮ ልጁን ቅዱስ ፊቅጦርን ወደ እስክንድርያና ወደ ተለያዩ ሀገሮች በግዞት ተልኮ በዚያም ተሠቃይቶ እንዲሞት ፈደበት፡፡
ወደ ግብፅም ልከው በዚያ እጅግ አሠቃዩት፡፡ መልአክም ነጥቆ ወስዶ በሰማያት የሰማዕታትን ክብር አሳይቶት ወደ ምድር መለሰው፡፡ ክፉዎቹም በብረት አልጋ አስተኝተው ከሥሩ እሳት አነደደዱበት፡፡ በሌላም ልዩ ልዩ በሆኑ ማሠቃያዎች እጅግ አሠቃዩት፡፡ መልአክም ተገልጦ ፈወሰው፡፡ ወደ እንዴናም አጋዙትና በዚያም ብዙ አሠቃዩት፡፡ ምላሱን ቆረጡት፤ በችንካርም ጎኖቹን በሱት፤ ቁልቁል ሰቅለውም ቸነከሩት፤ በእሳትም ውስጥም ጨመሩት፤ ዐይኖቹን አወጡት፤ እሬትና መራራ ሐሞትንም አጠጡት፡፡ ደግመውም ዘቅዝቀው ሰቀሉት፡፡ ጌታችንም ተገልጦ ካጽናናው በኋላ ፈወሰውና ፍጹም ጤነኛ አደረገው፡፡ ፊቅጦር፣ ፋሲለደስ፣ ቴዎድሮስ በናድልዮስ፣ አውሳብዮስና መቃርዮስ እነዚህ ሰማዕታት በአንድነት በአንድ ዘመን አብረው ኖረው ተሰውተው ሰማዕት የሆኑ የሥጋም ዝምድና ያላቸው የነገሥታት ልጆች ናቸው፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም የቅዱስ ፊቅጦርን ዐይኑን አስወለቀው፣ ነገር ግን የታዘዘ መልአክ መጥቶ የዓይኑን ብርሃን መልሶለታል፡፡ ሰማዕቱ በመዝለል ባሕር የሚሻገር እንደ አሞራ የሚመስል ፈረስ ነበረው፡፡ ከዚህም በኋላ ማሠቃየቱ ቢሰለቻቸው ሚያዝያ 27 ቀን አንገቱን ሰይፈው በሰማዕትነት እንዲያርፍ አድርገውታል፡፡
ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር አንድ የሚነገር ትልቅ ታሪክ አለው፡፡ እርሱም በሰማዕትነት ካረፈ ከብዙ ዘመን በኋላ በራእይ ተገልጦ በ8ኛው ሺህ ዘመን በሀገራችን በኢትዮጵያና በግብፅ እንዲሁም በቁስጥንጥንያና በሮም ወደፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ በግልጽ የተናገረ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ስለ ሃይማኖት ቅዱስ ፊቅጦር ያየው ራእይ›› የሚል መጠሪያ ያለው ይህ ራእይ በሀገራችን ጎጃም ደብረ ጽሞና ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህንን በተመለከተ ቅዱስ ፊቅጦር የተናገረውንና ቅዱስ ገድሉ ላይ የተጻፈውን ቀጥሎ እንመለከተዋለን፡-
‹‹…በእስላሞችም ጊዜ በግብፅ ሀገር ሁሉ የክርስቶስ ሕግ አይቋረጥም፡፡ የጾም፣ የጸሎትና የቍርባን እምነት ይኖራል፡፡ ከእስላሞች ጋር እየኖሩ የሃይማኖት ጽናት ትበዛለች፤ በማርቆስ መንበርም የሊቀ ጳጳሳት መሾምም አይቋረጥም፤ በሊቀ ጳጳሳት እጅ በየደረጃው የጳጳሳት፣ የኤጲስ ቆጶሳት፣ የቀሳውስትና የዲያቆናት ሹመትም አይቋረጥም፡፡ የእስላሞችም መንግሥት ጥቂት ዘመናት ናቸው፡፡ ከጥቂት ዘመናት በኋላ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ ሀገር ክርስቶስን የሚወድ ቅዱስ ሰው ያነግሣል፡፡ ዐረማውያንም በእርሱ እጅ ይደመሰሳሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ግብፅ ሀገር ሄዶ እስላሞችንና መንግሥታቸውን ሁሉ ያጠፋል፡፡ እግዚአብሔር በቍስጥንጥንያ እርሱን የሚወድ ስሙ ትውልደ አንበሳ የተባለ ሰው ያነግሳል፡፡ ከኢትዮጵያ ንጉሥ ጋር ይገናኝ ዘንድ ይመጣል፡፡ በግብፅ መሀል ቦታ ላይ ይገናኛሉ፡፡ ከእርሱ ጋርም የእስክንድሪያ ሊቀ ጳጳሳትና የቍስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ይገናኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሥ ሠራዊቱን በደቡብ በኩል ትቶ የቍስጥንጥንያም ንጉሥ ሠራዊቱን በሰሜን በኩል ትቶ ሁለቱ ነገሥታትና ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ተገናኝተው እርስ በእርሳቸው ሰላምታ ይሰጣጣሉ፤ ሊቃነ ጳጳሳቶቹ በመንበራቸው ላይ ተቀምጠው ነገሥታቱን ‹በየመንበራችሁ ላይ ተቀመጡ› ይሏቸዋል፡፡ የቍስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ‹የእኛ ሃይማኖት ትበልጣለች› ይላል፡፡ የእስክንድሪያውም ሊቀ ጳጳሳት ‹እግዚአብሔር የሰጠኝን ቃል እኔ እነግራችኋለሁ› ይላል፡፡ ሁለቱ ነገሥታትም ‹አባታችን በል ንገረን› ይሉታል፡፡ ‹የአባ ሲኖዳ ወደምትሆን ወደዚህች ታላቅ ቤተክርስቲያን ገብተን በአንዲት ታቦት ላይ እኔ እቀድሳለሁ፣ ይህ ባልደረባዬ ሊቀ ጳጳሳት በአንዲቷ ታቦት ላይ ይቀድስ፤ ሁሉም ሕዝብ ሠራዊቶቻችሁም መጥተው ይመልከቱ› ይላል፡፡ ‹መንፈስ ቅዱስ እያያችሁት ከሁለታችን በአንዱ ቁርባን ላይ ከወረደ በዚያ ሃይማኖት ሁላችን እንሂድ፣ ሃይማኖቷም ትታወቃለች ቀንታለችና› ይላቸዋል፡፡ ሁለቱ ነገሥታት ‹እሺ በዚህ ቃል ተስማምተናል፣ የእግዚአብሔር ምክር ናትና› ይሉታል፡፡ ያን ጊዜ ሁለቱ ነገሥታትና ሊቃነ ጳጳሳት ሠራዊቶቻቸውም ሁሉ ካህናቶቻቸውም፣ ሕዝቡም ወደዚህች ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ይገባሉ፡፡ ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳትም በሁለቱ ታቦታት ላይ ይቀድሳሉ፡፡ በዚያ ያሉ ሁሉ እያዩ መንፈስ ቅዱስ በነጭ ርግብ አምሳል ከብርሃን ጋር የእስክንድሪያው ሊቀ ጳጳሳት በቀደሰው ቍርባን ላይ ይወርዳል፡፡ ያን ጊዜ የኢትዮጵያ ንጉሥ ይደሰታል፣ የእርሱም ሊቀ ጳጳሳት ነውና፡፡ በእግዚአብሔር ፊትም የእርሱ የሃይማኖት ሕግ የተወደደ ይሆናል፡፡ የሮም ንጉሥ ግን ከሕዝቦቹ ጋራ ያዝናል፡፡ መጻሕፍቶቻቸውን ሁሉ ሰብስበው ወደ ባሕር ይወረውሯቸዋል፡፡ ሃይማኖታቸውንም ስለአጠፋና መናፍቃን ስላደረጋቸው የቀድሞውን ሊቀ ጳጳሳቸውን ሊዎንን ይረግሙታል፡፡ ሁሉም ወደ አንዲት የእስክንድሪያ ሊቀ ጳጳሳትና የኢትዮጵያ ንጉሥ ሃይማኖት ይመለሳሉ፡፡ ሮምም፣ ግብፅም፣ ኢትዮጵያም ሁሉም የተስማሙ ይሆናሉ፤ በመካከላቸውም ጽኑ ፍቅር ይሆናል፡፡ ሁሉም ሃሌ ሉያ እያሉ እግዚአብሔርን ፈጽመው ያመሰግኑታል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሥና የሮም ንጉሥ እርስ በእርሳቸው እጅ መንሻንና ሰላምታን ተሰጣጥተው ወደየሀገራቸው ይመለሳሉ፡፡ ቅዱስ ፊቅጦርም ለእናቱ የሚነግራትን ይህንን ሁሉ ትንቢት ከጨረሰ በኋላ ‹እናቴ ማርታ ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን› ብሎ ከእርሷ ተሰወረ፡፡››
የሰማዕት የቅዱስ ፊቅጦር ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!
No comments:
Post a Comment