ቅዱስ ሩፋኤል - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, April 15, 2020

ቅዱስ ሩፋኤል


ከከበሩት ከ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ :: ጦቢት 12 : 13 እንግዲህ ከባህሪው ቅድስና ፍጥረቱን በጸጋ ቅድስና መርጦ የሚለይ እግዚአብሔር አክብሮ እንዲህ ያለ ሰማያዊ ፀጋ ከሰጣቸው ቅዱሳን መላእክት መካከል በስልጣኑ ሊቀመናብርት (የመናብርት አለቃ) የሆነ በሹመት ፈታሔ ማኅጸን (ማሕጸን የሚፈታ) ከሳቴ እውራን (የእውራንን ዓይን የሚያበራ) ሰዳዴ አጋንንት (አጋንንትን የሚያባርር) ፈዋሴ ዱያን (ድውያንን የሚፈውስ)፣ አቃቤ ኆኅት (የምህረትን ደጁ የሚጠብቅ) ተብሎ የተገለጠ ከሊቃነ መላእክቱ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ተከትሎ የሚነሳ መልአክ ራሱን እንዲህ በማለት ገለጠ « የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነት ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ» (ጦቢ.12÷15) ይህ የከበረ ታላቅ መልአክ ሰሙ የእብራይስጥ ሁለት ቃላት ጥምረት ውጤት ነው፡፡ ሩፋ ማለት ጤና፣ ፈውስ፣ መድኃኒት ማለት ሲሆን ኤል ሚለው በሌሎቹም መላእክት ስም ላይ የሚቀጠል ስመ አምላክ ነው ይህም « መልአኬን በፊትህ እሰዳለሁ….. ስሜ በእርሱ ስለሆነ . አታስመርሩት» (ዘጸ.23÷20-22) እዳለው ነው፡፡ ታዲያ ሩፋኤል የሚለው በጥምረት ከአምላክ ለሰዎች የተሰጠ ፈውስ የሚለውን ይተካል «በሰው ቁስል የተሾመ ከከበሩ ከመላእክት አንዱ ሩፋኤል ነው፡» (ሄኖ.6÷3) ይህ መልአክ እንደሌሎቹ ሊቃነ መላእክት ሁሉ የሰው ልጆችን ይጠብቃቸዋል(ዳን.4÷13 ዘጸ. 23÷20 መዝ. 90÷11-13 ) ያማልዳል፣ ከፈጣሪ ያስታርቃቸዋል፡፡(ዘካ.1÷12) በፈሪሀ እግዚአቤሔር እና በአክብሮተ መላእክት ያሉትን ድናቸዋል (ዘፍ.49÷15 መዝ.3÷37) « እግዚአብሔር ሃይሉን የሚገልጥበትን ቅጣቱን ሊያሳይ ቢወድ አስቀድሞ መርጦ በወደዳቸው ለይቅርታ የተዘጋጁ የይቅርታ መላእክትን ያመጣል» (ሮሜ.9÷22) ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀመናብርትን ድንቅ ገቢር ተአምራቱን ያዩ ምዕመናን ……የወላድ ማኅፀን እንዲፈታ ስለተሸመ ከጌታ አዋላጅ ብትኖር ባትኖርም ሐኪም ሩፋኤል አይታጣም በምጥ ጊዜ ሲጨነቁ የባላገር ሴቶች ሁሉ የመልአኩን መልክ አንግተው ማርያም ማርያም ይላሉ ማየጸሎቱን ጠጥተው ቶሎ ፈጥነው ይወልዳሉ …… እያሉ ደጅ ጠንተው ይማጸኑታል፡፡ ዜና ግብሩን ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ከተናገረለት በመነሳት በቅዱሳን ላይ ድንቅ የሆነ እግዚአብሔር በመልአኩ አድሮ ያደረጋቸውን ተግባራት አበው የበረከት ምንጭ በሆነ ድርሳኑ ላይ አኑረው የበረከቱ ተካፋይ እንድንሆን ሰጥተውናል፡፡ በጉልህ ሠፍረው ከምናገኛቸው ብዙ ድንቅ ሥራዎች መሀል ጥቂቶቹን እነሆ ~~~> በሥነ-ስዕሉ የተማጸኑ፣ በምልጃው ታምነው የጸኑ ቴዎዶስዮስንና ዲዮናስዮስን በገሃድ ተገልጾ ለንግስናና ለጵጵስና ክብር አብቅቷቸዋል፡፡ ~~~> የንጉስ ቴዎዶስዮስ ልጅም ጻድቁ አኖሬዋስም በፈጣሪው ህግ እየተመራ የሊቀ መናብርቱን መታሰቢያ ቤተ መቅደስ አሳንጾ ሲያስመርቅ ለበለጠ ክብር ልቡን አነቃቅቶ ለታናሽ ወንድሙ ለአርቃዴዋስ የነጋሢነት ስልጣኑን ትቶ መንኖ በስውርና በጽሙና እዲኖር ረድቶታል፡፡ ~~~> በሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን አባቶች ለሊቀመናብርቱ ክብር በአሣ አንበሪ ጀርባ ላይ ያሳነጹትን መታሰቢያ ቤተ መቅደስ በወደቡ አጠገብ በእስክንድሪያ ሳለች ጠላት ዲያቢሎስ አነዋውጾ ለምስጋና የታደሙትን ምዕመናን ሊያጠፉ አሣ አንበሪውን ቢያውከው ወደ ሊቀመናብርቱ ተማጽነው እርዳን ቢሉ ፈጥኖ ደርሶ በበትረ መስቀሉ (ዘንጉ) ገሥጾ ከጥፋት ታድጓቸዋል፡፡ በቅዱስ መጽሐፍም እንደተገለጠው ~~~> ሣራ ወለተ ራጉኤልን አስማንድዮስ ከተባለው የጭን ጋንኤን ሲታደጋት የጦቢያን አባት የጦቢትን ዓይን አበራለት (መጽሐፍ ጦቢት) ከዚህም አልፎ የይስሐቅን እናት ሣራን፣ የሶምሶንን እናት (እንትኩይን) ምክነታቸውን የቆረጠ ወልዶ ለመሳም ያበቃቸው ይኸው ፈታሔማኅጸን የልዑል እግዚአብሔር መልአክተኛ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ከመልአኩ ከቅዱስ ሩፋኤል ረድኤት ያሳድርብን አሜን !!!

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages