ዶግማ ፣ ቀኖና ፣ሥርዓት ክፍል ሁለት - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, June 3, 2021

ዶግማ ፣ ቀኖና ፣ሥርዓት ክፍል ሁለት

ዶግማ ፣ ቀኖና ፣ሥርዓት ክፍል ሁለት (ከመምህር ዘለዓለም ገጽ የተወሰደ)
ከዚህ በፊት ዶግማና ሥርዓት እንዲሁም ቀኖና የማይሻሻሉ መሆናቸውን አይተናል አሁን ደግሞ ቀኖናና ሥርዓት ይሻሻላሉ የሚሉትን ሰዎች ማስረጃ እንመለከታለን ፡፡ ሥርዓት ይሻሻላል የሚሉ ሰዎች እንደማስረጃነት የሚጠቅሱትን ምሳሌ ስንመለከት ቀሳውስትና ዲያቆናት በብዛት በሌሉበት ቦታ አንድ ካህንና አንድ ዲያቆን ብቻቸውን ይቀድሳሉ ይህ ሊሆን የቻለው ቀኖናው ሥርዓቱ መሻሻል ስለሚችል ነው ሥርዓት የማይሻሻል ቢሆን ኑሮ በአንድ ዲያቆንና በአንድ ቄስ ብቻ መቀደስ ባልተቻለ ነበር ብለው የሚሞግቱ ሰዎች አሉ ፡፡ በመሠረቱ ተሻሻለ የምንለው የነበረው ሥርዓት ውድቅ ሁኖ የተሻለ ሥርዓት ሲመጣ ነው ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን በድን የዳሰሰ ሰው እስከ ምሽት ድረስ ርኩስ ነው የተቀደሰውን ነገር ከመንካት ይከለከላል ከርኵሰቱ የሚነጻም በውሃ ገላውንና ልብሱን አጥቦ ነው ዘሌዋ 11 ÷24 በሐዲስ ኪዳን ግን ይህ ሥርዓት ስለተሻሻለ በድን የዳሰሰ ሰው ቅዱስ እንጅ ርኩስ አይባልም ምክንያቱም ብድን የነካ ርኩስ ነው የሚለው ሥርዓት ተሻሽሏልና ፡፡ ስለዚህ አንድ ካህንና አንድ ዲያቆን ብቻቸውን መቀደሳቸው በችግር ምክንያት እንጅ ቀኖናውና ሥርዓቱ ስለተሻሻለ አይደለም እንደዚህ ዓይነቱን የሥርዓት መሻሻል የምንለው ከሆነ ደግሞ ካህናት በብዛት ባሉበት ቦታም በአንድ ካህንና በአንድ ዲያቆን ብቻ ለምን አልተቀደሰም የሚል ጥያቄም ያስነሣል ፡፡ ሌላ ምሳሌም እንውሰድ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በቅዳሜና በእሑድ በበዓለ ሃምሳ በልደት በጥምቀት ካልሆነ በስተቀር የቅዳሴ መውጫ ሰዓት ዘጠኝ ሰዓት መሆን እንዳለበት ተወስኗል አሁን አሁን ግን በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ጾም ባልሆነበት ቀን ጠዋት መቀደስ ልምድ እየሆነ መጥቷል ይህንም ብዙ ሰዎች የሥርዓትና የቀኖና መሻሻል አድርገው ይወስዱታል ይሄ የሚሆነው የሥርዓትየቀኖና መሻሻል ተደርጎበት ሳይሆን ጾማቸውን ውለው ሥጋውንና ደሙን መቀበል የማይችሉ ሰዎች ሥጋውንና ደሙን መቀበል እንዲችሉ፣ ውለው ማስቀደስ የማይችሉትም ጠዋት አስቀድሰው ክብር እንዲያገኙ ለማድረግ እንጅ ሥርዓቱ ስለተሻሻለ አይደለም የሥርዓት መሻሻልማ ቢሆን በገጠር ባሉ አብያተ ክርስቲያናትና በገዳማት በከተማም ባሉ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ጠዋት በተቀደሰ ነበር ውለው ባልቀደሱም ነበር በመሠረቱ መሥዋዕት በየቀኑ የሚሠዋበት ዋናው ዓላማም ምእመናን ሥጋውን ደሙን እንዲቀበሉ ነውና ጾም ባልሆነበት ወቅት ጠዋት ቢቀደስ ዓላማውን ማሳካት እንጅ ሥርዓቱን ማሻሻል አይደለም ፡፡ ጠዋት መቀደሱም ሥርዓትን እንደመሻርና ቀኖናውን እንደማፍረስ ሊታይ አይገባውም ሠለስቱ ምዕትም በፍትሐ ነገሥት ለሞት የደረሰ ሰው ቢኖር በጾም ወቅት ዓርብም ሆነ ረቡዕ ጠዋት ቀድሰው ሥጋውን ደሙን ያቀብሉት ብለው ሥርዓት ሠርተዋል ስለዚህ በጾም ወቅት ጠዋት ስለበሽተኛው ተብሎ መቀደስ ከተቻለ በፍስክ ወቅት ጠዋት ቀድሶ ውለው መቀበል የማይችሉትን ሰዎች ሥጋውን ደሙን ማቀበል የቆየ እንጅ አዲስ የመጣ የተሻሻለ ሥርዓት ስላልሆነ የሥርዓት መሻሻል ተብሎ ሊወሰድ አይገባውም ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ቢሆን በሐዋርያትና በሠለስቱ ምዕት እንዲሁም በሌሎች ሊቃውንት የተሠሩ ሥርዓቶችንና ቀኖናዎችን የማሻሻል ሥልጣን የለውም እነሱ የሚሻሻለውን አሻሽለው የማይሻሻለውን ቋሚ አድርገው ሠርተዋልና የሲኖዶደሱ ኃላፊነት በሐዋርያት ሲኖዶስም ሆነ በሠለስቱ ምዕት በሌሎችም ሊቃውንት ሲኖዶስ ውሳኔ ያላገኘ ውሳኔ የሚያስፈልገው ጉዳይ ካለ ሊቃውንትን ሰብስቦ መወሰን ነው በሚወስንበትም ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን በመጥራት ስለጉዳዩ ከመጻሕፍት የሚገኘውን መረጃ በማሰባሰብ ሱባዔ ተይዞበት መሆን እንዳለበት የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥርዓት መጻሕፍት ይናገራሉ ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉም ይዳረስልን ዘንድ ጸልዩልን ፪ኛ ተሰሎንቄ ፫ ÷ ፩

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages