________________________________
እኛስ ሥላሴ ባልን ጊዜ ስለ አብ ስለ ወልድ ስለ መንፈስ ቅዱስ እንና ገራለን።
(ቅዱስ ባስሊዮስ)
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ (ሊቀ ጳጳስ)
________________________________
ምስከረም ፯ በ451 ዓ.ም በጉባዔ ኬልቄዶን ላይ ተገኝቶ ልዮንን የረታውና ያወገዘው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በዓለ ልደቱና ዕረፍቱ ነው፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት 25ኛው ነው፡፡ ስለ ቀናች ሃይማኖት ታላቅ ተጋድሎን ከፈጸመ በኋላ በተሰደደበት በደሴተ ጋግራ መስክረም 7 ቀን ዐርፏል፡፡ ንጉሡ መርቅያኖስ በጠራው ጉባዔ በጠሩት ጊዜ በቦታው ሲገኝ 636 ጉባኤተኞች ተሰብስበው ደረሰ፡፡ ‹‹ምን ጉድለት ተገኝቶ ነው ይህ ሁሉ የተጠራው?›› ሲላቸው ‹‹በንጉሡ ትእዛዝ ተጠርተን ነው›› አሉት፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም ‹‹ይህ ጉባኤ ስለ ጌታችን ክብር ቢሆን ኖሮ እኔ ተቀምጨ እግዚአብሔር በሰጠኝ በአንደበቴ እናገር ነበር ነገር ግን የጉባኤው መሰብሰብ በንጉሡ ትእዛዝ ከሆነ ንጉሡ እንዳሻው ይምራው›› አላቸው፡፡
ከዚህም በኋላ የክርስቶስን ባሕርይ ለሁለት የሚከፍለው የክህደትን ቃል በውስጡ የያዘውን የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ልዮን የላከውን ደብዳቤ ቀደደው፡፡ ለጉባኤውም ርትእት የሆነች ሃይማኖትን ገለጸ፡፡ የተዋሕዶንም ምሥጢር በነፍስና በሥጋ እንዲሁም በእሳትና ብረት እየመሰለ አስዳ፡፡ ጌታችን ሰው እንደመሆኑ ወደ ሠርግ ቤት ተጠርቶ ሄደ፣ አምላክ እንደመሆኑ ውኃውን ለውጦ ወይን አደረገው›› እያለም በብዙ ምሳሌዎች ሲያስረዳቸው ከጉባኤው ሊከራከረው የደፈረ ማንም አልነበረው፡፡ ነገር ግን ክፉዎች ጉባኤውን በከሃዲው በልዮን ምክር ወዳዘጋጀው ንጉሡ መርቅያንና ወደ ሚስቱ ንግሥት ብርክያል መልዕክት ልከው ከዲዮስቆሮስ በቀር እነርሱ ያዘዙትን ሃይማኖትንና ትእዛዝ የሚቃወም እንደሌለ በመናገር ነገር ሠሩበት፡፡ ነገር ግን በጉባኤው ውስጥ ንስጥሮስን ያወገዙ አባቶችም ነበሩበት፡፡
ንጉሡም ቅዱስ ዲዮስቆሮስን አስጠርቶት ከሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት ጋር እስከ ማታ ድረስ ሲከራከሩ ዋሉ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ እንዳልተመለሰላቸው ባዩ ጊዜ ንግሥቲቷና ንጉሡ በእርሱ ተቆጥተው ክፉኛ አስደበደቡት፡፡ ጽሕሙን ነጭተው ጥርሱንም አስወለቁት፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም የተነጨ ጽሕሙንና የወለቀ ጥርሱን ሰብስቦ ወደ እስክንድርያ በመላክ ‹‹እነሆ የቀናች ሃይማኖት ፍሬ ይህ ነው›› አላቸው፡፡ ለጉበኤው የተሰበሰቡ ኤጲስ ቆጶሳትም በቅዱስ ዲዮስቆሮስ ላይ የደረሰውን ዐይተው ፈሩና ከከሃዲው ንጉሥ መርቅያኖስ ጋር ተስማሙ፡፡ ክብር ይግባውና ‹‹ለክርስቶስ ሁለት የተለያዩ ባሕርያት አሉት›› ብለው በንጉሡ መዝገብ ላይ በእጆቻቸው ጽፈው ፈረሙ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም እነርሱ የጻፉለትን መዝገብ እንዲልኩለት ሲጠይቃቸው ላኩለት እርሱም ጽፎ የሚፈርምበት መስሎአቸው ነበርና፡፡ እርሱ ግን አባቶቻችን ሐዋርያት ካስተማሯት ከቀናች ሃይማኖት በኒቅያ የተሰበሰቡ ሃይማኖታቸው የቀና የ318 ኤጲስ ቆጶሳት አባቶቻችን ከሠሯት ሕግ የሚወጣውን ሁሉ በደብዳቤው ግርጌ ጽፎ አወገዘ፡፡
መናፍቁ ንጉሥም ይህን ጊዜ እጅግ ተናዶ ጋግራ ወደምትባል ደሴት እንዲያግዙት አዘዘ፡፡ የሀገረ ቃው ኤጲስ ቆጶስ አባ መቃርስ አብሮት ተሰደደ፡፡ ሌሎቹ ግን ሸሹ፡፡ ከዚህም በኋላ እነዚያ የካዱ 636 ኤጲስ ቆጶሳት ተቀምጠው በኬልቄዶን ለራሳቸው መመሪያ የሚሆናቸውን ሥርዓት ሠሩ፡፡ በጋግራ ደሴት ያለው ኤጲስ ቆጶስም ከንጉሡ ጋር የተባበረ ነበርና አቡነ ዲዮስቆሮስ ላይ ብዙ መከራ አደረሰበት፡፡ የደሴቱ ሰዎች ግን በቅዱስ ዲዮስቆሮስ እጅ የሚፈጸሙ ተአምራትን እያዩ እጅግ ያከብሩት ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ አባ መቃርስን ወደ እስክንድርያ ሄዶ ሰማዕት እንደሚሆን ትንቢት ነገረውና ከነጋዴዎች ጋር ላከው፡፡ እንደተናገረውም አባ መቃርስ በእስክንደርያ ሰማዕት ሆኖ ዐረፈ፡፡ አቡነ ዲዮስቆሮስ ግን በዚያቹ በጋግራ ደሴት ሰማዕትነቱን ፈጽሞ በክብር ዐርፏል፡፡ ምእመናንም ሥጋውን በዚያው አኖሩት፡፡ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን አሜን።
አቡነ ሳዊርያኖስ፡-
_______________
መስከረም ፯ በዚህ ዕለት በአካል መሄድ ሳያስፈልጋቸው ደብዳቤ በመጻፍ ብቻ በንጉሡ ልጅ ላይ ያደረውን ሰይጣን ያስወጡትና በሀገርም ላይ የመጣውን የጠላትን ጦር በመርታት ድል ያደርጉ የነበሩት አቡነ ሳዊርያኖስ ዕረፍታቸው ነው፡፡
የግሪክ አቴናን ፍልስፍናና ጥበብ ጠንቅቀው የተማሩ ናቸው፡፡ ምግባር ሃይማኖታቸው የሰመረ፣ ትሩፋት ተጋድሏቸው የቀና ነው፡፡ ብሉይን ከሐዲስም አጠናቀው ተምረዋል፡፡ ወላጆቻቸው ያወረሷቸውን እጅግ የተትረፈረፈ ንብረት ሸጠውና ለጦም አዳሪዎች መጽውተው ለድኆች ማደሪያና ለእንግዶች ማሪፊያ ቤት ሠርተው ነዳያንን ይንከባከቡ ጀመር፡፡ ይህንንም የጽድቅ ሥራቸውን የሮሜው ጻድቁ ንጉሥ አኖሬዎስ ሲሰማ እጅግ ደስ ተደስቶ አስመጥቶ ከእርሱ ጋር በቤተ መንግሥቱ አማካሪና አባቱ አድርጎ አኖራቸው፡፡ ከንጉሡም ጋር አብረው ሁልጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ሌሊቱን በሙሉ ለጸሎት ቆመው ያድራሉ፡፡
ጻድቁ የገብላው አገር ንጉሥ ሴት ልጁን ሰይጣን ይዟት ሳለ ደብዳቤ በመጻፍ ልከው በልጅቷ ላይ ያደረውን ሰይጣን በደብዳቤአቸው ብቻ አስወጥተውታል፡፡ አቡነ ሳዊርያኖስ ደብዳቤ በመጻፍ ብቻ በሀገር ላይ የመጣ የጠላትንም ጦር እያሸበሩ ድል ያደርጉ ነበር፡፡ ይኸውም የቍስጥንጥንያው ንጉሥ አርቃዴዎስና አኖርዮስ በገብላ አገር ኤጲስቆጶስነት ከሾሟቸው በኋላ የፋርስ ሰዎች እነዚህን ደጋግ ነገሥታት ሊወጓቸው ሽተው በኃይል በመጡባቸው ጊዜ ወደ አባ ሳዊርያኖስ መልአክትን ላኩ፡፡ አባታችንም ለቅዱሳን ነገሥታቱ ‹‹እኛ የክርስቶስ ከሆንን መንግሥታችንም የክርስቶስ ነው፣ እንዲህም ከሆነ የጦር መሣርያ የጦር ሠራዊትም አንሻም…›› ብለው ደብዳቤ ጽፈው እንደላኩ ነገሥታቱ ያለ ምንም ጦርነት የፋርስን ሀገር ሰዎች አሸንፈው ወደ ሀገራቸው መልሰዋቸዋል፡፡
አቡነ ሳዊርያኖስ በገብላ አገር ኤጲስቆጶስነት ከተሾሙ በኋላ የሙሴን ሕግ በማወቁ የሚመካ አንድ ስሙ ስቅጣር የሚባል አይሁዳዊ ወደ እርሳቸው መጥቶ ተከራከራቸው፡፡ የጻድቁንም ቃላቸውን ሊሰማቸው አልቻለም ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታችን ለአቡነ ሳዊርያኖስ ተለጠላቸውና ‹‹እኔ ካከበርኳቸው ወገኖች ይሆናል›› በማለት እንደሚያምን ነገራቸው፡፡ ያም አይሁዳዊ ወደቤቱ በገባ ጊዜ ወገኖቹ አይሁድ ሲኦል ውስጥ ሆነው ሲሠቃዩ በራእይ ተመለከተ፡፡ ‹‹ከሃዲዎች ዘመዶችህን እነሆ እይ›› የሚል ድምንም ሰማ፡፡ በማግሥቱም ይህ አይሁዳዊ ወደ አቡነ ሳዊርያኖስ መጥቶ ከእግራቸው ሥር ወድቆ እንዲያስተምሩትና የክርስቶስ ወገን እንዲያደርጉት ለመናቸው፡፡ እርሳቸውም አስተምረው ከሀገሩ ሰዎች ጋር አንድ ላይ አጠመቋቸው፡፡ የቀሩት ብዙ አይሁድም በጌታችን አምነው ተጠመቁ፡፡ አቡነ ሳዊርያኖስ ሥራየኛ ጠንቋዮችን ሁሉ እያሳመኑ አስተምረው አስጠምቀዋቸዋል፡፡
አቡነ ሳዊርያኖስ ስለ ዮሐንስ አፈወርቅ ስደትና እንግልት ያለችበት ድረስ ሄደው ንግሥት አውዶክስያን ቢመክሯትና ቢገሥጹዋትም በክፋቷ ጸንታ አልሰማቸው ብትል ተመልሰው ወደ አገራቸው ሄደዋል፡፡ አቡነ ሳዊርያኖስ ተአምራታቸው ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በጣም ብዙ ድርሳናትን ደርሰዋል፡፡ 100 ዓመት በሆናቸው ጊዜ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ከ10 ቀን በኋላ በሞት እንደሚያርፉ ነገራቸው፡፡ ሕዝቡንም ጠርተው በሃይማኖት እንዲጸኑ ከመከሯቸውና ከተሰናበቷቸው በኋላ መስከረም ፯ ቀን በሰላም ዐርፈዋል፡፡ ይኸውም ዕረፍታቸው የተከናወነው ኤጲፋንዮስ ባረፈ በ2ኛ ዓመቱ ዮሐንስ አፈወርቅ ባረፈ በዓመቱ ነው፡፡ ጌታችን የብርሃን ሰረገላ ሰጥቷቸዋል፣ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን አሜን፡፡
ሰማዕታቱ ቅድስት ራፊቃ እና አራት ልጆቿ
__________________________________
መስከረም ፯ በዚች ዕለት ቅድስት ራፊቃ እና አራት ልጆቿ ቁልቁል ተሰቅለውና አንገታቸውን በመሰየፍ ሰማዕትነታቸውን በድል ፈጸሙ፡፡
ለቅድስት ራፊቃ እና ለአራት ልጆቿ ማለትም ለአጋቶን፣ ለጴጥሮስ፣ ለዮሐንስና ለአሞን ጌታችን ለሁሉም በራእይ ተገልጦላቸው በስሙ መስክረው ሰማዕት እንሚሆኑ ነገራቸው፡፡ አስቀድሞም ታላቁ አጋቶን በአገሩ ተሹሞ በሥልጣን ሆኖ ነበር፡፡ የጌታችንንም የሰማዕትነት ጥሪ ተቀብለው ከላይኛው ግብጽ ከቁስ አውራጃ ተነሥተው በከሃዲው መኮንን በዲዮናስዮስ ፊት ስለ ጌታችን አምላክነት መሰከሩ፡፡ መኮንኑም ብዙ ሥቃዮችን አደረሰባቸው፡፡ ጌታችንም በተአምራት ከመከራቸው ሲያድናቸው ያየ ብዙ ሰዎች ሲያምኑ መኮንኑ እጅግ ተቆጥቶ ጽኑ ሥቃይ አደረሰባቸው፡፡ ማሠቃየትም በሰለቸው ጊዜ ወደ እስክንድርያው ገዥ አርማንዮስ ዘንድ ላካቸው፡፡ ከሃዲው አርማንዮስም ሥጋቸውን ቆራርጦ በመንኮራኩር ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ነገር ግን ጌታችን ጤነኛ አድርጎ ፈወሳቸው፡፡ ዳግመኛም ዘቅዝቀውም ሰቀሏቸው፡፡ አሁንም ጌታችን አዳናቸው፡፡ በተአምራተቸውም ብዙዎች በጌታችን አመኑ፡፡ በመጨረሻም ራሶቻቸውንም በሰይፍ ቆርጠው ሥጋቸውን ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ ቅድስት ራፊቃና አራት ልጆቿም ሰማዕትነታቸውን በዚሁ ፈጸሙ፡፡ የታዘዘ መልአክም መጥቶ ለአንዱ ባለጸጋ የቅዱሳኑን ሥጋ ያለበትን ነግሮት እንያወጣውና በክብር እንዲያስቀምጠው ነአዘዘው፡፡ ባለጸጋውም የቅዱሳኑን ሥጋቸውን ከባሕሩ አወጥቶ የመከራ ዘመን እስኪያልፍ በክብር አኖረው፡፡ ከሥጋቸውም ብዙ ተአምራት ተገልጠው ታዩ፡፡ የሰማዕታቱ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን አሜን።
ቅድስት ሐና እማ ለእግዝእትነ ማርያም
________________________________
መስከረም ፯ የብርሃን እናቱ የሆነች ድንግል ወላዲተ አምላክን የወለደቻት ቅድስት ሐና ልደቷ ነው፡፡ ሐና ማለት ‹‹ጸጋ›› ማለት ነው፡፡ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እናት ናት፡፡ እርሷም ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት ልጁ ናት፡፡ የቅድስት ሐና አባት ማጣትና እናቷ ሄርሜላ ከእርሷ በተጨማሪ ሶፍያና ማርያም የሚባሉ ሌሎች ሁለት ሴት ልጆችን ወልደዋል፡፡ ቅድስት ሐና ከይሁዳ ነገድ የሆነውን ጻድቅ ኢያቄምን አግብታ ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደች፣ ድንግል ማርያምም መድኃኔዓለም ክርስቶስን ወለደች፡፡ ሶፍያ ኤልሳቤጥን ወለደች፣ ኤልሳቤጥም መጥምቁ ዮሐንስን ወለደች፡፡ ከሦስቱም ታናሽ የሆነችው ‹‹ማርያም›› የተባለችው የማጣትና የሄርሜላ ልጅ ደግሞ ሰሎሜን ወለደቻት፡፡
ይኽችም ታላቅ እናት ቅድስት ሐና አምላክን በድንግልና ሆና በሥጋ ለወለደችው ለቅድስት ድንግል ማርያም ወላጇ ትሆን ዘንድ የተገባት ሆናለችና ከሴቶች ሁሉ እንደምትበልጥና እንደምትከብር እንረዳ፡፡ ለዓለም ሁሉ ድኅነት የተደረገባትን ልዩ ስጦታ የሆነች ድንግል ማርያምን እርሷ አስገኘቻት፡፡ ለክብር ባለቤት ለጌታችን ለአምላችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ አያቱ ሆናለችና ምን ያህል ክብርት እንደሆነችና እግዚአብሔር የመረጣት ንጽሕት ቅድስት እንደሆነች በዚህ ይታወቃል፡፡ ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን፡፡
ተአምር
_____
መስከረም ፯ ቀን በበዓለ ልደቷ ታስባ የምትውለው ዓለማትን ለፈጠረ ለአምላክ አያቱ ትሆን ዘንድ የተመረጠች ቅድስት ሐና ያደረገችው ተአምር ይህ ነው፡- ክፉዎች አይሁድ መካን ሆና ስለኖረች ቅድስት ሐናን በነቀፌታና በስድብ "...ቢወልዷት እንጂ የማትወልድ፣ ማኅፀኗ የተዘጋ፣ በቅሎ..." እያሉ በመስደብ በእጅጉ ያሳዝኗት ነበርና እግዚአብሔር ጎብኝቷት አያቱም ትሆነው ዘንድ መርጧታልና ክብርት እመቤታችንን ከወለደቻት በኃላ ቅድስት ሐና ለክፉዎች አይሁድ "...የልጄ ልጅ አምላኬ ኢየሱስ ክስቶስ ለአብርሃምና ለዘሩ ሁሉ እስከዘለዓለሙ ምሕረትን አድርጎ ሕይወትን ሰጥቷልና ከእኔም ስድቤን አርቋልና የከበረ ቅዱስ ስሙ የተመሰገነ ይሁን...የነቢያት ሁሉ የአባቴም የዳዊት ትንቢት በእኔ ላይ ተፈጸመ" አለቻቸው፡፡ ሐናም እመቤታችንን ከወለደች በኃላ የእስራኤል ልጆችም ከሐና ልጅ ከክብርት እመቤታችን ከድንግል ማርያም ክርስቶስ እንደሚወለድ ባወቁ ጊዜ በቁጣ በሐና ላይ ተነሡባት፡፡ በመናቅና በማቃለል "በእውነት ልጄ እግዚአብሔርን ትወልደዋለች እኔም በሥጋ አያቱ እባላለሁ አልሽን? " የዚህ ነገር መጨረሻው የከፋ እንዳይሆን ሐናንም ሆነ ልጇን በድንጋይ ወግረን እንገድላቸው ዘንድ አንድ ሆነን ጽኑ መሐላን ኑ እንማማል"ተባባሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን ቅድስት ሐናን ከክፉዎች አይሁን ክፋት ሁሉ በረድኤትና በተአምራት ይጠብቃት ነበር፡፡
ቅድስት ሐናም እመቤታችንን ገና በማኅፀኗ ይዛት ሣለ ብዙ ተአምራትን አድርጋለችና ክፉዎች አይሁን ይቀኑባትና ይሰድቧት የነበረው ገና ከፀነሰች ጊዜ ጀምሮ ነበር፡፡ ቅድስት ሐና ክብርት እመቤታችንን ከፀነሰቻት በኋላ አይሁድ ቀንተው ተነሱባቸው፡፡ ቅናቱ እንዴት ነው ቢሉ ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ከአጎቱ ቤት ሄዶ ሞተ፡፡ እነርሱም እንቀብራለን ብለው ባልጋ ይዘው ሲሄዱ ከመንገድ አሳረፉት፡፡ ቅድስት ሐናም የአጎቷ ልጅ ነበርና ለማልቀስ ብትደርስ ዘመዶቿ ሁሉ ተሰብስበው ሲላቀሱ ቆዩአት፤ እርሷም አብራ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ብድግ ብሎ ተነሥቶ ‹‹ስብሃት ለኪ ማርያም እሙ ለፀሐየ ጽድቅ ለአብ ሙሽራው ለወልድ ወላዲቱ ለመንፈስ ቅዱስ ጽርሃ ቤቱ ተፈስሂ ደስ ይበልሽ" ብሎ ሰገደላት፡፡ አይሁድም ይህ ተአምር ሲደረግ ከዚያው ነበሩና ‹‹ምነው ሳሚናስ ምን አየህ? ምን ትላለህ?›› ቢሉት እርሱም ‹‹ከዚህች ከሐና ማኅፀን የምትወለደው ሕፃን ‹ሰማይን ምድርን አየርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች› እያሉ መላእክት ሁሉ ሲያመሰግኗት ሰማሁ›› አላቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹እኔንም ያነሣችኝ የፈወሰችኝ ያዳነችኝ እርሷ ናት›› አላቸው፡፡ አይሁድም ‹‹በል ተወው ሰማንህ›› ብለው ቅናት ጀመሩ፡፡ ቅድስት ሐና በእርጅናዋ ጊዜ መፀነሷን የተመለከቱ ዘመዶቿና ያገሯ ሰዎች ተገርመው እየመጡ ይጠይቋት ነበር፡፡ እመቤታችን ማርያም በፅንስ እያለች ብዙ ታምራትን አድርጋለች። ከእነዚህም መካከል ዐይነ ስውር የነበረችው የአርሳባን ልጅ ወደ ሐና መጥታ እውነትም ሐና መፀነሷን ለማረጋገጥ ሆዷን ዳሰሰቻት፡፡ እርሷም ሳታስበው ዐይኗን ስትነካ ዐይኗ በራላት፡፡ እመቤታችንም በተፀነሰች በ9 ወር ከአምስት ቀን የግንቦት መባቻ ዕለት ግንቦት 1 ተወለደች፡፡
ክቡራን የሆኑ ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱ፤ ሰማይ የተባለች ክብርት እመቤታችንም እውነተኛውን የጽድቅ ፀሓይ ክርስቶስ ኢየሱስን ወልዳለችና ዓለማትን ለፈጠረ ለአምላክ አያቱ ትሆን ዘንድ የተመረጠች የቅድስት ሐና ረድኤት በረከቷ ይደርብን!
ዳግመኛም በዚኽች ዕለት ከቅዱስ ፋሲለደስ ጋር ማኅበርተኞቹ የሆኑ ሁለት ሺህ ሰባት ሰዎችም በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ የመጥምቁ ዮሐንስ እናት የቅድስት ኤልሳቤጥም የመታሰቢያዋ በዓል ነው፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን አሜን።
ምንጭ፡- ስንክሳር ዘወርኅ መስከረም
ድርሳነ ኢያቄምና ወሐና
ከገድላት አንደበት
ዝክረ ቅዱሳን
Post Top Ad
Saturday, October 2, 2021
Tags
# ነገረ ቅዱሳን
Share This
About አትሮንስ ሚዲያ
ነገረ ቅዱሳን
Labels:
ነገረ ቅዱሳን
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
Post Bottom Ad
Author Details
Templatesyard is a blogger resources site is a provider of high quality blogger template with premium looking layout and robust design. The main mission of templatesyard is to provide the best quality blogger templates which are professionally designed and perfectlly seo optimized to deliver best result for your blog.
No comments:
Post a Comment