የኢትዮጵያ ትንሳኤ ዋዜማ ላይ የደረስን ይመስላል? - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 2, 2021

የኢትዮጵያ ትንሳኤ ዋዜማ ላይ የደረስን ይመስላል?

------------------------------------------------------------ ቅዱስ ዳዊት "ኢትዮጵያ ታበጽህ እደዊ ሀበ እግዚአብሔር፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ታነሳለች/ ታቀርባለች" እጆች የተባሉ ጳጳሳት፣ እጆች የተባሉ ካህናት ፣ እጆች የተባሉ ነገስታት እጆች የተባሉ ሕዝቦቿ ምዕመና ናቸው።(መዝ ፷፯፣፴፩) ብዙዎቻችን የኢትዮጵያ ትንሳኤ ሲባል እንዲሁ ከሰማይ የሚወርድ ድንገተኛ ክስተት አድርገን እናስበዋለን። ነገሩ ግን እንደዛ አይደለም ለኢትዮጵያ ትንሳኤ የእያንዳንዳችን የእጅ አሻራ ያስፈልገዋል በተለይ የአባቶች ካህናት መነሳት ግድ ይላል። ኢትዮጵያ ትንሳኤዋ እንደ ምፅአት በተስፋ የምንጠባበቀው አይደለም ኢትዮጵያን የምናነሳት እኛው ነን ሁላችንም ፊታችንን ወደ ምዕራባውያን ፊታችንን አዙረን ፈረንጅ ብቻ ነው ልክ ብለን እያሰብን ፈረንጅን ብቻ እያመንን ተስፋ እያደረግን እየኖርን የኢትዮጵያን ትንሳኤ መጠበቅ ዘበት ነው። የኢትዮጵያ ታላቅነትና ጥበብ ስልጣኔ እንኳን የፈረንጅ ገረድ ለሆንን ለኛ ለራሳቸው ለፈረንጆቹም እንቆቅልሽ የሆነ ነው። መቼ ና እንዴት ተብሎ ቢጠየቅ ሊመለስ በማይችል ሁኔታ ግን የኢትዮጵያዊነት እንቅስቃሴ እነደ ቆመ ቀርቷል። ኢትዮጵያ ተኝታለች አንቀላፍታለች ይህን ያላወቁ ልጆቿ ግን ሞተች ብለው ትብያና ቆሻሻን ደፍተው ቀብረዋታል ታድያ ዛሬ ትብያዋን አራግፎላት የሚቀሰቅሳት ልጆቿን ትጠብቃላች የሚቀሰቅሳት ልጆቿን ያላገኘች እንደሆነ ግን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ኃይል ካላነሳት በቀር ኢትዮጵያ እንደተኛች መቅረቷ ነው። ውድ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተሰቦች ብዙዎቻችሁ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ናፋቂና የሀገር ፍቅር ያላችሁ እንደሆናችሁ አልጠራጠርም እንደምታዩት አሁን ያለንበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ጭራሽ ቀብሮ የሚያስቀራት ይመስላል ። ይህን ለመረዳት በተለያየ ቦታ በተግባር የምናየውን ታሪካው የዘመን ጥቀርሻ ጥፋትን መመልከት በቂ ነው። የኢትዮጵያ ትንሳኤ ምንም እንኳ ለሁሉም ቢሆንም መሠረቷ ግን ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እንደሆነች የማይካድ ሐቅ ነው። እነሆ ዛሬ የኢትዮጵያ ትንሳኤን ለማየት እኛ ልጇቿ እጅ ለእጅ ልንያያዝና ኢትዮጵያን ልንቀሰቅሳት ይገባል። የኢትዮጵያ ትንሳኤ መሠረት የሆነው ፍቅር መተሳሰብ ይሉኝታ አዛኝነት ከታመመ ዘመናት አለፉ። የትንሳኤያችን የጥበባችን የስልጣኔያችንን የአባቶቻችን ውርስ እንደያዘ የመጥፋት አደጋ ተጠንስሶለት እሱም ተመልሶ ላይመጣ እያንቀላፋ ነው። ክብራችንም የኢትዮጵያዊነት ቁልፉን እንደያዘ እስከመጨረሻው ሊያሸልብ አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ደርሷል። አባቶቻችን ኢትዮጵያን ከከፍታ ማማ ያደረሱበት የመላዕክት ልሳን የሆነው ግዕዝ ቋንቋችን ከእንግዲህ ላንሰማው ላናየው ሊሰናበተን ከጫፍ ደርሷል። ጠበብት አባቶቻችን ሊቃውንት የግዕዝ ምሁራኖቻችን ካህናት የኢትዮጵያን ትንሣኤ ከዛሬ ነገ ለኮሱልን ስንል ባዕዳን የዘረኝነት ችቦ ለኩሰው ሰተዋቸው ተማሪዎቻቸውን የሚረዳቸው በማጣታቸው በዘመን አመጣሽ ችግር በትነዋቸው ቅኔ ቤቶች የግዕዝ ቤቶች ከተዘጉ ኢትዮጵያዊነት ከነወዙ መክሰም ከጀመረ ቀናቶች አለፉ። ትንሳኤውን ለኳሻ ቤተክርስቲያን አነሆ ደጇቿ ከተከረቸሙ ወራት ተቆጠሩ። የኢትዮጵያን ትንሳኤ ስንሻ ኢትዮጵያዊነት እራሱ ከነወዙ ከዳን። ግን ዛሬ የኢትዮጵያን ትንሳኤ የሚያሳይ ጭላንጭል እየታየኝ ነው እውነት እላችኋለው እየታየኝ ነው እንወያይ እንመካከር። ከታች የምትመለከቱት ሊቃነ ጳጳሳት ትላንት ኢትዮጵያውያን በዚህ ሥፍራ ኃያላኑን ደጅ እንዳልጠኑ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ በሊቃነ ጳጳሳት ልጆቿ በኩል እጇን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ ኃያላኑን ተው እያለች ነው። ቃል ያለው ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ የትንሳኤውን ችቦ ለመለኮስ እያኮበኮበ ነው። ዛሬ ላይ ከመንግስት ተስፋ የለንም የኢትዮጵያ ትንሳኤ ከመንግስት ይመጣል ማለት ቢወቅጡት እንቦጭ ነው። የኢትዮጵያ ትንሳኤ ኢትዮጵያዊነትን እራሱ የመሠረተችው ቅድስት ተዋህዶ ናት እራሷ የምትለኮሰው ኢትዮጵያን የመሠረተቻት ኢትዮጵያን ልታነሳት እጆቿን የዘረጋች ይመስለኛል። ይህ ምልክት ከዚህ በፊት ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ አዲስ ነገርን ይዞ መቷል። ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ሊያነሷት ስላልቻሉ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ኢትዮጵያን ዳግም ልታነሳት ታጥቃ ተነስታለች። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ያቅርብልን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages