መስከረም ፰ ቀን ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 2, 2021

መስከረም ፰ ቀን ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ

____________________ መስከረም ፰ በዚች ቀን ከግብጻዊው ፈረኦናዊ ቤተ መንግስት ወጥቶ ወደ ምድያም አገር ማለትም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የካህኑን የዮቶርን ልጅ አግብቶ ሁለት ልጆችን ወለዶ በኢትዮጵያ 40 ዓመት ከኖረ በኋላ የዮቶርን በጎች እየተበቀ ሳለ እግዚአብሔር በቁጥቋጦ ውስጥ በታላቅ ራእይ ተገልጦለት እስራኤልን ከግብጽ እንዲያወጣ ነግሮት ሄዶ በ10 መቅሰፍታት እስራኤላውያንን ነጻ ያወጣቸው ሊቀ ነቢያት ሙሴ ዕረፍቱ ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴን የፈርዖን ሴት ልጅ ‹‹ከውኃ አውጥቼዋለሁና›› ስትል ሕፃኑን ሙሴ ብላ ጠርታዋለች፡፡ ዘጸ 2፡10፡፡ እስራኤላውን በግብፅ ባርነት እየተገዙ ባለበት ወቅት ፈርዖን እስራኤላውያን ወንድ ልጅ ሲወልዱ እንዲገደል በአዋጅ አስነገረ፡፡ የሙሴም እናት ልጇ በፈርዖን ትእዛዝ መሠረት እንዳይገደልባት ስለ ፈርዖን ትእዛዝ ፍራቻ ልጇን በቅርጫት አድርጋ ወንዝ ውስጥ ጣለችው፡፡ ተርሙት የምትባለው የፈርዖን ሴት ልጅ በወንዝ ገላዋን ልትታጠብ ወርዳ ሳለ በዚያ ቅርጫት አግኝታ ብትከፍተው የሚያሳሳ ውብ ልጅ አገኘት፡፡ ‹‹ይህንንስ አሳድገዋለሁ›› ብላ ወደ ቤቷ ወሰደችውና ሙሴ በንጉሡ በፈርዖን ቤት አደገ፡፡ የሙሴም እናት ተንከባካቢ ሞግዚቱ ሆና ተጥሎ የተገኘውን ልጇን እንድታሳድግ ከፈርዖን ሴት ልጅ ጋር በድብቅ ተስማምታ በንጉሡ ቤት ገባች፡፡ እናቱም ልጇን ሙሴ የፈርዖን ልጅ እንዳይባል ሃይማኖቱን፣ ማንነቱን፣ ታሪኩን፣ ባሕሉን ጠንቅቃ እያስተማረች አሳደገችው፡፡ ሙሴ 40 ዓመት በሆነው ጊዜ አንዱ ግብፃዊ ዕብራዊውን ሲገድለው አይቶት ለወገኑ ተበቅሎ ግብፃዊውን ገደለው፡፡ በማግስቱ ደግሞ ሁለት ዕብራውያን እርስ በእርሳቸው ሲጣሉ አያቸው፡፡ ሊያስታርቃቸው ፈልጎ ወደ እነርሱ ጠጋ ቢል አንደኛው ዐመፀኛ ዕብራዊ ‹‹ትናንት ግብፃዊውን እንደገደልከው ልትገድለን ትሻለህን?›› አለው፡፡ ሙሴም ‹‹በድብቅ አደረኩት ያልኩት ለካ ታውቆብኛል›› ብሎ ፈርዖንን ፈርቶ ወደ ምድያም አገር ሸሽቶ ሄደ፡፡ የምድያም አገር ካህን የሆነውን የዮቶርን (በሌላ ስሙ ራጉኤል ይባላል) ሴት ልጁን ሲፓራን አግብቶ 40 ዓመት በምድያም ተቀምጦ ሁለት ልጆችንም ወለደ፡፡ ይህችውም ምድያም የተባለች አገር ቅድስት ኢትዮጵያ ናት፡፡ የዚህም ምስክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ዘጸ 2፡1-25፣ ኦሪት ዘኁልቅ 12፡1-12፡፡ ሕዝበ እስራኤል ከግብፅ ሳይወጡ በኋለኛውም ዘመን ጌታችን ከመወለዱም ከብዙ ዘመን በፊት በቅድስት አገር ኢትዮጵያ ውስጥ እግዚአብሔርን የሚያገለግል ካህን እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሰክረው ሐቅ ነው፡፡ ሙሴ በምድያም አገር ማለትም በኢትዮጵያ በዱር ሆኖ የኢትዮጵያዊውን ካሁን የዮቶርን በጎች እየጠበቀ ሳለ በቁጥቋጦ ውስጥ ታላቅ ራእይ አየ፡፡ ነበልባል ከሐመልማል ጋር ሐመልማልም ከነበልባል ጋር ተዋሕዶ ነበልባሉ ሐመልማሉን ሳያቃጥለው፣ ሐመልማሉም ነበልባሉን ሳያጠፋው ተመልክቷል፡፡ ይህንንም ምሥጢር ለመረዳት ጠጋ ሲል ከቁጥቋጦው ውስጥ እግዚአብሔር ድምፅ አውጥቶ ጠራው፡፡ የቆመባት ስፍራ የተቀደሰች ስለሆነች ጫማውንም ከእግሩ እንዲያወልቅ ነገረው፡፡ ዘጸ 3፡5፣ ሐዋ 7፡30-34፡፡ ለጊዜው ሐመልማል የእስራኤል፣ ነበልባሉ ደግሞ የመከራቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሐመልማሉ ነበልባሉን ያለመጥፋቱ እስራኤልም መከራውን ግብር ገብተን ቀኖና ይዘን እናርቀው ያለማለታቸው ምሳሌ ሲሆን ነበልባሉ ሐመልማሉን ሳያቃጥል ማየቱ የግብጽ መከራ እስራኤልን ጨርሶ ያለማጥፋቱ ምሳሌ ነው፡፡ ፍጻሜው ግን ሙሴ ያየው የነበልባልና የሐመልማል ተዋሕዶ የመለኮትና የትስብእት ተዋሕዶ ምሳሌ ነው፡፡ ነበልባሉ ሐመልማሉን እንዳላቃጠለው ሁሉ ሐመልማሉም ነበልባሉን እንዳላጠፋው ሁሉ መለኮት ምልአቱን ስፋቱን ርቀቱን ሳይተው ሥጋም ግዙፍነቱን ሳይተው የመዋሐዳቸው አንድ አካል አንድ ባሕርይ የመሆናቸው ምሳሌ ነው፡፡ እንዲሁም ነበልባሉ የጌታችን ምሳሌ ሲሆን ሐመልማሉ ደግሞ የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ ይኸውም ነበልባሉ ሐመልማሉን እንዳላቃጠለው ሁሉ እሳተ መለኮት ጌታችንም 9 ወር ከ5 ቀን በማኅፀኗ ባደረ ጊዜ እመቤታችንን ባሕርየ መለኮቱ አላቃጠላትም፤ ሐመልማሉም ነበልባሉን እንዳላጠፋው ሁሉ ጌታችንም ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ቢሆንም ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠም፡፡ ይህንንም ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ምስጋናው ላይ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡- ‹‹መለወጥ የሌለባት ድንግል ማርያም ሙሴ በበረሐ በነደ እሳት ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ያያት ዕፅን ትመስላለች፣ የአብ ቃል በእርሷ ሰው ሆኗልና እሳተ መለኮቱ አላቃጠላትምና፤ ከወለደችው በኋላ ድንግልንናዋ አልተለወጠምና፤ ሰውም ቢሆን መለኮቱ አልተለወጠም በእውነት አምላክ ነውና፣ በእውነት አምላክ የሆነ እርሱ መጥቶ አዳነን፡፡›› የደማስቆው ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ዕፀ ጳጦስ የአምላክ እናት አምሳል ነበረች፤ ሙሴ ወደ እርሷ በተጠጋ ጊዜ እግዚአብሔር ‹አንተ የቆምክባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ› አለው፡፡ እንግዲህ ሙሴ የወላዲተ አምላክን ምሳሌ ያየባት መሬት የተቀደሰች ከሆነች ምሳሌዋ ራሷ ምን ያህል የተቀደሰች ትሆን? እርሷ ቅድስት ብቻ ሳትሆን ቅድስተ ቅዱሳን ናት›› በማለት ስለ እመቤታችን አስተምሯል፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ሕዝበ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት እንዲያወጣቸው ላከው፡፡ ሙሴም ወደ ግብፅ አገር ሄዶ 10 የተለያዩ መቅሰፍቶች አመጣ፡፡ መጀመሪያ ውኃውን ወደ ደምንት ለወጠው፡፡ 10ኛው የበኩር ልጆቻቸው ሞቱ፡፡ በተአምራቱም ሕዝቡን ይዞ ከግብፅ ወጣ፡፡ የኤርትራን ባሕር በበትሩ ለሁለት ከፍሎ አሻገራቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ሕዝበ እስራኤልን በምድረ በዳ 40 ዓመት ሙሉ መና ከሰማይ እያወረደ መገባቸው፣ ከአለትም ላይ ውኃ እያፈለቀ አጠጣቸው፡፡ እራኤል ግን እጅግ ክፉዎች ነበሩና በክፋ ይነሱበት ነበር፡፡ በድንጋይ ሊወግሩት ያሉበት ጊዜም ነበር፡፡ እርሱ ግን ፍጹም በመታገስ በኃጢአታቸው እንዳይሞቱ ወደ እግዚአብሔር ይማልድላቸው ነበር፡፡ ሙሴ ሰው ከወዳጁ ጋር እንደሚነጋገር ከእግዚአብሐር ጋር 570 ጊዜ ቃል በቃል ተነጋግሯል፡፡ 40 ቀን 40 ሌሊት ከጾመ በኋላ ዓሥሩን ትእዛዛት የተጻፉባቸውን ጽላት ተቀበለ፡፡ እስራኤላውያን ባዩት ጊዜ እንዳይሞቱ ፊቱን እስኪሸፍንላቸው ድረስ ፊቱ እንደ ፀሐይ የሚያበራበት ጊዜም ነበር፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ 120 ዓመት በሆነው ጊዜ እግዚአብሔር ሕዝቡን ለአገልጋዩ ለነዌ ልጅ ለኢያሱ እንዲያስረክበው ስላዘዘው ለኢያሱ አስረክቦታል፡፡ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው በምስክሩ ድንኳን ውስጥ የሚሠራውን ሁሉ ሠርቶ ካዘጋጀ በኋላ በተራራ ውስጥ ዐረፈ፡፡ በዚያም በመልእክት እጅ በሥውር ተቀበረ፡፡ የእስራኤል ልጆችም ወስደው እንዳያመልኩት እግዚአብሔር የሙሴን ሥጋ ሰወረ፡፡ ሰይጣንም የሙሴን ሥጋ ለእስራኤል ሊገልጥላቸው በወደደ ጊዜ ሐዋርያው ይሁዳ በጻፈው መጽሐፉ ላይ እንደመሰከረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ገሠጸው፣ ከዚህም ሥራ ከለከለው፡፡ የእስራኤልም ልጆች ለሙሴ 40 ቀን አልቅሰውለታል፡፡ ጌታችን ስለ ሙሴ ሲናገር ከእስራኤል ልጆች ውስጥ እንደ ሙሴ ያለ ደግ የዋህ ቅን ነቢይ እንደማይነሳ መስክሮለታል፡፣ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ አሜን። መስከረም ፰ በዚች ዕለት የመጥምቁ ዮሐንስ አባት የበራክዩ ልጅ ካህኑ ዘካርያስ በሰማዕትነት አረፈ፡፡ __________________________________ የመጥምቁ ዮሐንስ አባት የበራክዩ ልጅ ካህኑ ዘካርያስ፡- የበራክዩ ልጅ ካህኑና ነቢዩ ዘካርያስ- ይህም ነቢይ ዘካርያስ በንጉሥ ሄሮድስ እጅ መስከረም 8 ቀን በሰማዕትነት ያረፈ ሲሆን የመጥምቁ ዮሐንስ አባት ነው፡፡ ስለ ልጁ ዮሐንስ መወለድ ቅዱስ ገብርኤል ባበሰረው ጊዜ አምኖ ባለመቀበሉ ልጁ ዮሐንስ እስኪወለድ ድረስ ዲዳ ሆኗል፡፡ ልጁ በተወለደም ጊዜ ‹‹ስሙን ዮሐንስ በሉት›› ብሎ በእጁ ሲጽፍ አንደበቱ ተከፍቶለታል፡፡ እርሱና ሚስቱ በእግዚአብሔር ሕግ ያለነቀፋ የጸኑ ደጎች እንደሆኑ ቅዱስ ወንጌል ይመሰክርላቸዋል፡፡ ‹‹በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ›› ተብሎ ነው በወንጌል ጽድቃቸው የተነገረላቸው፡፡ ሉቃ 1፡5-6፡፡ ንጉሥ ሄሮድስ ጌታችንን የሚያገኝ መስሎት 144 ሺህ ቤቴልሔም ሕፃናትን በግፍ ሲጨፈጭፍ እመቤታችን ልጇን ጌታችንን ይዛ ወደ ግብጽ ስትሰደድ ዮሐንስንም እናቱ ቅድስት አልሳቤጥ ይዛው ወደ ሲና በረሃ ገባች፡፡ ኤልሳቤጥ ከመሄዷ በፊት ግን ከባሏ ከዘካርያስ ጋር ሲሰነባበቱ የሚሆነውንም ሁሉ እርሱ ቀድሞ ያውቅ ነበርና ‹‹ሕፃኑን ልጄን ሲያጡ እኔን ይገድሉኛል፣ አንቺ ግን ወደ በረሃው ይዘሽው ሂጂና በዚያ ሸሽጊው›› ብሎ መክሯታል፡፡ ኤልሳቤጥም ከሄደች በኋላ የርጉም ሄሮድስ ጭፍሮች ዮሐንስን ባጡት ጊዜ ወደ ዘካርያስ መጥተው ‹‹ልጅህን ወዴት አድርሰኸው ነው? ወዴትስ ደበቅኸው? አሁን ከደበቅህበት አምጥተህ ፈጥነህ አስረክበን›› በማለት የፍጥኝ አስረው አሠቃዩት፡፡ ሄሮድስም ዘካርያስ ዘንድ ሄዶ ሕፃኑን ልጅ ዮሐንስን ካልሰጠው እንደሚገድለው ነገረው፡፡ ካህኑ ዘካርያስም የንጉሡን ዛቻ ባለመፍራት አገልግሎቱን ቀጠለ፡፡ በመጨረሻም ንጉሡም ወታደሮቹን ልኮ በቤተ መቅደሱና በመሠዊያው መካከል አስገደለው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር የቅዱስ ዘካርያስን ሥጋውን ሰወረው፣ ደሙ ግን እንደ ድንጋይ ሆነች፡፡ ሕዝቡም እንደ ልማዳቸው ለጸሎት በመጡ ጊዜ ከካህናት አንዱ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ የረጋ የዘካርያስን ደም አገኘ፡፡ ከመሠዊያውም እንዲህ የሚል ድምፅ ተሰማ፡- ‹‹እነሆ የበራክዩ ልጅ ዘካርያስ ተገደለ፣ የሚበቀልም እስኪመጣ ድረስ ደሙ ስትጮህ ትኖራለች›› የሚል ድምፅ ተሰማ፡፡ ይህንንም አንዳንዶች በማሳሳት ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ስለሆነው ስለ በራክዩ ልጅ ነቢዩ ዘካርያስ የተነገረ ነው ይላሉ ግን አይደለም፡፡ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ የሆነው የበራክዩ ልጅ ነቢዩ ዘካርያስ የእርጅና ዘመኑ ደርሶ ኡረት በሚባል አገር ሞተ፡፡ ሥጋውም ያለጥፋት በዚያ ተገኝቶ ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለታል፡፡ የዚህኛው የካህኑና የመጥምቁ አባት ዘካርያስ ግን ሥጋው አልተገኘም፡፡ ስለመገደሉ የደሙ ድምፅ ምስክር ሆነ እንጂ፡፡ ጌታችንም ለተረገሙ አይሁድ ስለእርሱ ሲናገር ‹‹የገደላችሁት የዘካርያስ ደም በላያችሁ ይደርሳል›› ብሏቸዋል፡፡ የዘካርያስም ደም እስከ ሰባት ዓመት ድረስ እየፈላ ደሙ ሲካሰሳቸው ከኖረ ገዥው ጥጦስ ገዳዮቹን በሰይፍ ሲገድላቸው ደሙ መፍላቱን አቁሟል፣ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ አሜን። ሰማዕቱ ቅዱስ ዲማድዮስ _____________________ ይኸውም በሃይማኖትና በምግባር ያጌጠ ስለነበር ጌታችን ተገልጦለት ሄዶ በስሙ ሰማዕት ይሆን ዘንድ አዘዘው፡፡ ከደቡባዊ ግብጽ ተነሥቶ እናት አባቱን ትቶ ወጥቶ ወደ አትሪብ በመሄድ በከሃዲው መኮንን ፊት ስለ ጌታችን መሰከረ፡፡ ከሃዲውም ገዥ ጽኑ ሥቃይ ካደረሰበት በኋላ ወደ እስክንድርያ ላከው፡፡ የእስክንድርያም መኮንን ሉክያኖስ በተራው አሠቃየው፡፡ ነገር ግን ጌታችን ዲማድዮስ ተገልጦለት አረጋጋው፡፡ በኋላም መኮንኑ ዲማድዮስን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ራሱን በሰይፍ አስቆረጠውና የሰማዕትነቱ ፍጻሜ ሆነ፣ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ አሜን። ___________ እንዲሁም በመስከረም ፰ ቀን ከሃዲው መኮንን በእጅጉ ካሠቃየው በኋላ አንገቱን በሰይፍ የሰየፈው ሰማዕቱ ቅዱስ ሉክዮስ ዕረፍቱ መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሰዋል፡፡ ዳግመኛም በዚች ዕለት መስከረም ፰ ምግቡ የአጋዘን ወተት የሆነ በዕረፍቱም ጊዜ ብዙ ተአምራትን ያደረገ የከበረ ገዳማዊ ቂርቆስ ዕረፍቱ መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሰዋል፡፡ ምንጭ :- ስንክሳር ዘወርኅ መስከረም

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages