_______________________________
እኛ ለቅዱሳን ስንሰግድ፣ውዳሴ ስናቀርብ፣ ስናከብራቸው፣ፍቅራችንን ስንገልጽ፣ አማልዱን ስንል ፍጡርነታቸውን ዘንግተን እነሱን በልዑል እግዚአብሄር ቦታ ተክተን አይደለም። ስለዚህ በምንም መልኩ ድርጊታችን ባእድ አምልኮ ሊሰኝ አይችልም!!ሲጀመር ማማለድ የአምላክነት ተግባር ስላልሆነ የእነሱ ማማለድ በምንም መንገድ የጌታን የአምላክነት ግብር እንደሚጋፋ ተደርጎ መቅረብ የለበትም።
በሥጋም ይሁን በነፍስ በገነት ያሉት ቅዱሳን ፍጡራን እንደመሆናቸው መጠን በሁሉም መልኩ ውስንነት አላቸው። ከተሰጣቸው የቅድስና ጸጋ አንዱ ግን በቦታ ርቀት የማይወሰን የእውቀት ደረጃ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ማወቅ ነው! ለዚህም በሰማይ ሆነው ወይም በገነት ሆነው በምድር ያለው ነገር የማየትና የማወቅ ጸጋ ተሰጥቷቸዋል! ስለዚህ ብንጠራቸው አይሰሙም አያውቁምም የሚለው ሐሳብ መሰረተ ቢስና ይህንን ጸጋ የሰጣቸውንም መንፈስ ቅዱስንም መሳደብ መሆኑን እናስረግጣለን።
መፅሐፍ ቅዱስ ስለ ቅዱሳን አማልጅነት ይመሰክራል።
ምልጃ ማለት "ጸሎት ልመና" ማለት ለመሆኑ (ሉቃ22:32፣ 1ቆር4:12፣ ፊል4:6፣ 1ጢሞ2:1) አስረጂዎች ናቸው! ቅዱሳን ሰዎች ደግሞ ቅድስት ነፍሳቸው ከቅድስት ሥጋቸው በመለየት ወደ ገነት እንደሚገቡ፣ ሕያዋን እንጂ ሙታን እንደማይባሉም ያስረዳናል (ማቴ22:31፣ ማር12:27፣ ዮሐ14:19፣ 2ቆሮ 6:9):: እቺ የቅዱሳን ነፍስ ደግሞ በምድር ምን እየተሰራ እንዳለ የማወቅ ጸጋ ከጌታ ዘንድ እንደምትቀበል ቃሉ ይመሰክራል::
የሞቱ ቅዱሳን ከእኛ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም የምትሉ ሰዎች አላችሁ!!!እሺ ቅዱሳኑስ ይሁኑ ታዲያ መላእክት እኮ አይሞቱም!!!ስለታናናሾች የአብን ፊት ያያሉ እንጅ-በማቴ 18ቁ 10 እንደተጻፈው!በዘካርያስ 1 ቁ 13 የመልአኩ ምልጃ እንዲህ ተጽፉዋል “አቤቱ የሰራዊት ጌታ ሆይ እነዚህ 70 አመት የተቆጣሀቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተማዎች የማትምራቸው እስከመቼ ነው አለው እግዚአብሔርም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው” ታዲያ ሳንለምነው እንዲህ የሚማልድልን መልአክ ብንለምነውማ ምን ያህል ይማልድልን?ሰአሉ ለነ ሚካኤል ወገብርኤል እንበላቸውማ።
የሞቱ ቅዱሳን በክርስቶስ ህያው ስለሆኑ ከእኛ ጋር በመንፈስ እንደሚገናኙ ደግሞ ይሄው!!!የሞቱ ቅዱሳን “እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነሱ እንደማያፍር” በዕብ 11 ቁ 16 ተጽፉዋል!!!የሞቱ ቅዱሳን አላዋቂዎች ሳይሆኑ ወደፍጹምነት የተሸጋገሩ ‘ፍጹማን’ መሆናቸው በዕብ 12 ቁ 22 ሰፍሮልናል!!!ጌታም ከአመታት በፊት በሞት የተለዩትን አብርሃምን፣ይስሀቅንና ያዕቆብን ጠቅሶ “የህያዋን አምላክ ነኝ” ሲል በማቴ 22 ቁ 32 ገልጹዋል!!!ጌታችን በስጋ ስለሞተው አብርሃም በዮሀንስ 8 ቁ 56 ሲናገር፡ “አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሀሴትን አደረገ፤አየም ደስ አለው” ይላል!!!በአጸደ ነፍስ ያለው አብርሃም የጌታን ቀን አይቶ የተደሰተው በሰማይ ያሉ ቅዱሳን በምድር ካለነው ጋር ህብረት ስላላቸው ነው!! ዮሐንስ በራዕዩ ምዕራፍ 8 ቁ 3 “የዕጣኑ ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚብሔር ፊት ወጣ” ይለናል!!መላእክት ጸሎታችንን ያሳርጋሉ!!!አእርጉ ጸሎተነ የምንላቸውም ለዚሁ ነው-እንደ ቅ/ያሬድ-እንደ አባ ጎዮርጊስ ዘጋስጫ!!ሙሴስ በዘጸአት 32 ቁ 13 “በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምን፣ይስሀቅንና እስራኤልን አስብ” ብሎ በአጸደነፍስ ነፍስ ባሉ ቅዱሳን ስም ጌታውን ሲማጸን ከሞቱ ቅዱሳን ህብረት ስላለን አይደለምን?ነው እንጅ።
አብርሃም በሰማይ ሁኖ ሃብታሙ ሰውዬና ድኃው አልዓዛር በምድር የነበራቸውን ሕይወት እንደሚያውቅ "አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ" ይላል!(ሉቃ16:25) በመቀጠልም በዚያን ጊዜ አብርሃም ከሞተ ከ600 ዓመታት ብኋላ በስራኤላውያን ዘንድ "ሙሴና ነቢያቶች" እንደተነሱ ማወቁን ደግሞ "አብርሃም ግን። ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ አለው" በማለቱ እንገነዘባለን! (ሉቃ16:29)ይሄም ብቻ አይደለም በምድር ላይ ስለ ክርስቶስ ብለው በግፍ ደማቸው የፈሰሱ ሰማዕታት፤ ጌታ እነዚያን ደም አፍሳሾችን እንዳልተበቀለ ስላወቁ "ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?"ብለው ጸልየዋል! (ራእይ6:9)
አንድ ሰው ለሌላ ሰው የሚጸልይለት ወይም ደግሞ የሚያማልድለት ስለ ሁለት ምክንያት ሲሆን እነርሱም 1)ፀልይልኝ ሲለው 2)በራሱ ፍቃድና "ለጠላቶቻችሁ ጸልዩ"(ማቴ5) ስለሚል ቃሉ ነው!
ይሄን ደግሞ የሚገባን ሲኦል ውስጥ የተጣለው ሃብታሙ ሰውዬ የርሱ ዘመዶች እርሱ የገባበትን እሳት ይገቡ ዘንድ አይፈልግምና ስለነርሱም አዝኗልና "እኔ የገባሁበት እንዳይገቡ ነቢይ ላክላቸው" ብሎ ምልጃን አቅርቦ ነበር::
አዎ! ማንም ሰው ቢሆን፣ ገነት ይግባ ሲኦል፣ ስለወገኑና በምድር ስላሉ ሰዎች ያማልዳል። ምን እያሉ? በሲኦል ያሉትቀ "እባክህን እኛ ያገኘነው እንዳያገኛቸው ልቦና ስጣቸው" እያሉ!
በገነት ያሉት ደግሞ "ለኛ የሰጠሃትን ገነት ለነርሱም እንድትሆን እባክህን ልቦና ስጣቸው እርዳቸው!" እያሉ! የሁለቱ ልዩነት ግን የጌታ ጆሮዎቹ በሲኦል ወዳሉት ኃጥአን ሳይሆን በገነት ወዳሉት ጻድቃኑ መሆኑ ነው! "የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል"(1ጰጥ 3:12 መዝ33:15)
ለዚህም ነው በሲኦል የነበረው ሰውዬ ስለ ቤትሰቡ ሲያማልድ ምልጃው ተሰሚነት ባይኖረውም በገነት ሁነው ደማቸውን ያፈሰሱትን ሰዎች እንዲበቀል የጸለዩት/ያማለዱት ደግሞ ጽሎታቸው ተቀባይነት አግኝቷል "ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው ... ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው" ብሏቸዋልና (ራእይ 6:11)
ፕሮቴስታንቱ ወዳጄ ሆይ እስኪ ልጠይቅህ? አሁን አንተ (አይበለውና) ብትሞትና ገነት ብትገባ በምድር ስላለነው ሰዎች ትንሽ እንኳን አትጨነቅምም? በምድር ሁነው ክርስቶስን ስላላወቁት ሰዎች ትንሽ እንኳን አታዝንልም? "ጌታ ሆይ እባክህ በመንፈስህ ምራቸው?" እውነት የማትል ከሆነ ጨካኝ ነህ! እኔ ግን የምል ይመስለኛል! ታድያ ይሄ ምልጃ አይመስልህምን? በገነት ጸሎትና ምስጋና እንጂ ምን ያለ ይመስልሀል? እስኪ በፍቅር መልስልኝ!
ከጎረቤቱ "እባክህን ብር ስጠኝ" ብሎ የሚለምን ምስኪን ሰው፣ ከቅዱሳን በረከት ረድኤትና ምልጃ መለመን ግን ቅር የሚለው ሰው፤ ችግሩ የመጽሐፍ ሳይሆን ቅዱሳንን የመጥላትና የመጸየፍ የዘንዶው መንፈስ እንደተጠናወተው እናውቃለን! እኛ ግን ይህንን ጸጋ አብዝቶ ለሰጣቸው ለእኛም በገነትን በወረስን ጊዜ ለሚሰጠን ለመንፈስ ቅዱስ ክብርና ኣምልኮ ይሁን እንላለን!
ስለሞቱ ጻድቃን እውቀት፡በ2ኛዜና መዋእል ምእራፍ 21ቁ12እስከ14 የይሁዳ ንጉስ ኢዮራም ብዙ ሀጢኣት በመስራቱ ከአመታት በፊት በእሳት ሰረገላ ወደ ሰማይ ተወስዶ የነበረው ነቢዩ ኤልያስ የተግሳጽና የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደላከለት ተገልጹዋል!!በኤር 15ቁ1 ላይም “ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙ እንኩዋ ልቤ ወደዚህ ህዝብ አልመለስ አለ” የሚለው እነሙሴ ከሞቱ ከብዙ አመታት በሁዋላ የተነገረ ቃል, የሞቱ ጻድቃን በምድር ስላለው ህይወት እውቀት እንዳላቸውና ስለእኛ እንደሚማልዱ የሚያሳይ ነው!!!በ1ኛ ቆሮ13ቁ12 “አሁን በመስታወት እንደምናየው አይነት በድንግዝግዝ እናያለን፣በዚያን ጊዜ ግን እግዚአብሄር እኔን የሚያውቀኝን ያህል ሙሉ እውቀት ይኖረኛል” በማለት የሞቱ ጻድቃንን እውቀት ፍጹምነት ይገልጻል!!!ታዲያ በድንግዝግዝ ያለው ምድራዊ ሰው ያማልዳል ,በፍጹምነት ያሉት ቅዱሳን ግን አያማልዱልም የምትል አንተ ማነህ??እንዲህ አይነት ትምህርትስ በየትኛው ጉባኤ ተማርክ??የሞቱ ቅዱሳንን ቀርቶ ቅዱስ ዳዊት ፍጥረታቱን፣አህጉራቱን፣መላእክቱን ሁሉ እግዚአብሄርን አመስግኑት እያለ ያናግራቸው የለ!!አንብብ….እመሰ ረሳእኩኪ ኢየሩሳሌም ለትርስአኒ የማንየ….ስምዒ ወለትየ ወርዕይ ወአጽምኢ እዝነኪ….ሰብህዎ ለእ/ር ኩልክሙ መላእክቲሁ….ወዘተ ሲል ታገኘዋለህ!!
“ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢዩን ዋጋ ይወስዳል፣ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል” ተብሎ በማቴ 10ቁ40 የሰፈረው ቃልም በጥሞና ላነበበው ከበቂ በላይ ነው!!አስተውል፡ጌታ በአጸደነፍስ ያሉና የሌሉ ብሎ አልከፈላቸውም!!!እንዲያማ ቢሆን ኖሮ ‘ጻድቁን/ነቢዩን በህይወት ባለ ጻድቅ/ነቢይ ስም የሚቀበል’ የሚል አነጋገር ይጠቀም ነበር!! እነዲያውም ጌታ ይህን ቃል ሲናገር አንድም ነቢይ በአጠገቡ አልነበረም!!ስለዚህ ቃሉን የተናገረው ስለሞቱ ነቢያትና ቅዱሳን ጭምር እንደሆነ እናምናለን!!ጻድቅን በጻድቅ ‘ስም’ የሚለው ንግግር ግልጽ ነው!!ወደ ራሱ ወደጻድቁም አማልደን ብሎ በራሱ በጻድቁ ስም መጠየቅ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው!!
ይሄን ሁሉ ስንል ባለቤቱን ረስተን አይደለም!!!በቀጥታም እሱን ማረን እንለዋለን-እግዚኦ መሀረነ ክርስቶስ በምህላ-መሀረነ አብ በማስታኮት!!!ስማን፣ተማለደን፣ታረቀን እንለዋለን!!!ግን እንደሌሎቹ አማልደን አንለውም!!!ሌሎቹ የሚያማልደን ጌታ ነው እያሉ ቤዛነቱን እንደአማላጅነት ስለሚወስዱት ነው እኛ ቅዱሳንን አማልዱን ስንል አምላክ ያደረግናቸው የሚመስላቸው!!! አምላካችን አንድ ነው!!!የሃይማኖታችን መሰረትም እሱ-ለዚህም ነው ሰማይንና ምድርን በፈጠረ በአንድ አምላክ እናምናለን ስንል የሃይማኖት ጸሎታችንን የምንጀምረው።
ወስብሃት ለእግዚአብሔር ወለዘአብጽሃነ እስከዛቲ ሰዓት
Post Top Ad
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
Post Bottom Ad
Author Details
Templatesyard is a blogger resources site is a provider of high quality blogger template with premium looking layout and robust design. The main mission of templatesyard is to provide the best quality blogger templates which are professionally designed and perfectlly seo optimized to deliver best result for your blog.
No comments:
Post a Comment