“መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ” - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 2, 2021

“መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ”

___________________________________ ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በዘመኑ ፍጻሜ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ፣ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ተሰቅሎ በመሞት በክቡር ደሙ ዓለምን ለዋጀበትና ለመላው የሰው ዘር ሰላምን ላደረገበት ለመስቀል የምትሰጠው ክብርና ልዕልና ከሌላው ዓለም የላቀና የተለየ ነው፡፡ ከቀደሙት የሀገሪቱ መሪዎች እነ ዐፄ ዳዊት ከኢየሩሳሌም የመጣውን ግማደ መስቀሉን ከእስክንድርያ ለማምጣት ስናር ላይ ተሠውተውበታል፡፡ የግብጽ ሡልጣኖች በመስቀሉ ፈንታ በ፲፪ እልፍ ወቄት ወርቅ ሊደልሏቸው ቢሞክሩም ለሀገራቸው ሰላም፣ በረከትና ጤንነት ሲሉ መስቀሉን ነው የመረጡት፡፡ በኋላም ልጃቸው ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በነገሡ ጊዜ የአባታቸውን ክርስቲያናዊ ፈለግ በመከተል፣ ስናር ላይ የነበረውን ግማደ መስቀል ከአባታቸው ከዐፄ ዳዊት ዐፅም ጋራ ወደ ኢትዮጵያ አምጥተው፣ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” ማለት “መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ” የሚለውን በራእይ የተነገረውን አምላካዊ ቃል በተግባር በመተርጐም በተፈጥሮ አቀማመጧ የመስቀል ቅርፅ ባላት በግሸን ደብረ ከርቤ ተራራ ላይ ቤተ ክርስቲያን አሳንፀው እንዲሠለስብት፣ እንዲቀደስበት አድርገው አስቀምጠውበታል፡፡ ከዚያም ወዲህ እስከ ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. ድረስ የተነሡት የሀገሪቱ መሪዎችና ሕዝቦች ለመስቀሉ የሚሰጡት ክብርና ልዕልና እጅግ በጣም ከፍ ያለ ነበር፡፡ በየዓመቱ መስከረም ፲፮ እና ፲፯ ቀን የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በሚገኝበት በመላ ኢትዮጵያ አስደናቂ በኾነ ድምቀት ይከበራል፡፡ በተለይ በዐዲስ አበባ፣ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን፣ በቅዱስ ላሊበላ እና በጎንደር የሀገሪቱ መሪዎች፣ የየክልሉ ባለሥልጣናትና ዓለም አቀፍ የሀገር ጎብኚዎች በሚገኙበት፣ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ እጅግ በሚያስገርምና በሚያስደምም ኹኔታ ነው ሲያከብረው የኖረው፡፡ በይበልጥም በዐዲስ አበባ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል፣ የሀገሪቱ የጦር ኃይልም የኃይሉን መጠን የሚለካበትና የሚያሳይበት ልዩ በዓል ነበር፡፡ የሚገርመው፣ የስድስት ኪሎ አንበሶችም ጭምር ሳይቀሩ ከጦር ኃይሉ ጋራ አብረው ያከብሩት ነበር፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል፣ በቤተ ክርስቲያን አማካይነት በዓመት ውስጥ ለአምስት ጊዜያት ያኽል በዐደባባይ ትዘክረዋለች፤ ታከብረዋለች፡፡ በመስከረም ወር ብቻ ለዐራት ጊዜ ያኸል ይከበራል፡፡ መስከረም ፲ ቀን፦ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ከስናር ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡበት ዕለት ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. በፊት የዐፄ መስቀል በዓል ተብሎ በቤተ መንግሥት በታላቅ ሥነ ሥርዓት ይከበር ነበር፡፡ ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. ወዲህ ግን በቤተ ክርስቲያን ብቻ ይከበራል፡፡ መስከረም ፲፮ ቀን፦ ንግሥት ዕሌኒ በዕጣን ጢስ አመልካችነት አስቈፍራ ከተቀበረበት ያስወጣችበት የመታሰቢያ ዕለት የደመራ በዓል ተብሎ በዐደባባይ ሕዝበ ክርስቲያን በሚገኙበት በመላ ኢትዮጵያ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ በማግስቱ መስከረም ፲፯ ቀንም፣ ቅዳሴ ቤቱ በዝማሬ፣ በማሕሌት፣ በሥርዐተ ንግሥ በቤተ ክርስቲያን ይከበራል፡፡ መስከረም ፳፩ ቀን ደግሞ፣ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም የገባበት ዕለት፣ ስፍር ቁጥር የሌለው ሕዝበ ክርስቲያንና በርካታ ዓለም አቀፍ የሀገር ጐብኚዎች በሚገኙበት በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም በታላቅ በዓለ ንግሥ ይከበራል፡፡ መጋቢት ፲ ቀንም፣ ንግሥት ዕሌኒ በመጀመሪያ መስቀሉን ያገኘችበት ዕለት በውዳሴ፣ በቅዳሴ፣ በሥርዐተ ንግሥ ደረጃ በቤተ ክርስቲያን ይከበራል፡፡ ከዚያም ባለፈ፣ የቀደሙት የሀገር መሪዎችና ሕዝቦች፣ “መስቀለ ኢየሱስ፣ መስቀለ ክርስቶስ፣ መስቀል ክብራ” በሚል ስያሜ በመስቀሉ ስም ገዳማትን እየገደሙ፣ አብያተ ክርስቲያናትን እየተከሉ መንፈሳዊውን አገልግሎትና በረከት ሲያገኙበት፣ ሃይማኖታቸውን ሲያጠናክሩበት፣ አንድነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን ሲቀዳጁበት ኖረዋል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በበኩሉ፣ ለመስቀሉ ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሣ፣ ወንድ ወንዱ ወልደ መስቀል፣ ገብረ መስቀል፣ ኃይለ መስቀል፣ ብርሃነ መስቀል በመባል፤ ሴት ሴቱ ደግሞ ወለተ መስቀል፣ አመተ መስቀል በመባል የራሱን ስም በመስቀል እየሰየመ፤ ሰውነቱን በመስቀል ቅርጽ እየተነቀሰ፤ በመስቀል ቅርጽ የተቀረጸ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ወይም የመዳብ ጌጣጌጥ በጆሮው በማንጠልጠል፣ በአንገቱ በማሰር፣ በጣቱ በማጥለቅ፣ በልብሱና በቤቱ ጉልላትም ላይ የመስቀል ቅርጽ በማሠራት በኹለንተናዊ መልኩ መስቀልን ከማሰብና ከመዘከር አቋርጦ አያውቅም፡፡ ሌላው ቀርቶ በግንባራቸው ላይ የመስቀል ምልክት ያለባቸውን እንስሳትም ጭምር፣ ወንዱን በሬ ወይም ወይፈን – መስቀል፤ ሴቷን ላም ወይም ጊደር – መስቀሌ ብለው በመጥራት በእንስሳቱም ስም ላይ ሳይቀር መስቀልን በማስታወስ ለመስቀሉ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅርና ክብር ይገልጣሉ፡፡ ለመስቀሉ ካላቸው ጽኑ ፍቅር የተነሣ፣ በየዓመቱ በመስቀል አካባቢ የምትታይ “የመስቀል ወፍ” ብለው የሚጠሯት የሰማይ ወፍም አለች፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት አንድ ጥንታዊ የቅኔ ሊቅ፣ ይህችኑ የመስቀል ወፍ ግማደ መስቀሉ ከተቀበረበት ከግሸን ደብረ ከርቤ መስቀለኛ ተራራ ጋር አመሳስሎና አመሥጥሮ፡- “ወበበመዓት ትትረአይ ወአኮ ዘዘልፍ ደብረ ከርቤ ዘመስቀል ዖፍ፡፡” የሚለውን ኅብር ቅኔ ተቀኝቶባታል፡፡ በደፈናው ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በመስቀሉ ኃይል፣ ዳር ድንበሯ ታፍሮና ተከብሮ፣ ሰላሟ ተጠብቆ የኖረችና ለመስቀሉ ልዩ ፍቅር ያላት ሀገረ መስቀል ለመኾኗ ከዚኽ በላይ በዝርዝር የተጠቀሱት በመስቀል ቅርጽ የተሠሩት ጌጣጌጦችና የሰዎቹም፣ የእንስሳቱም፣ የወፏም ስሞች በቂ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ኾኖም ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. ወዲህ የተነሣው እግዚአብሔር አልባ ትውልድ ግን፣ ይህ ዓለም በመስቀሉ ያገኘውን ፈወስና ሰላም ዘንግቶ፣ በተለይም ሀገራችን ኢትዮጵያ ተጠብቃ የኖረችው በመስቀል ኃይል መኾኑን ረስቶ ለመስቀሉ ደንታ ስላልነበረው፣ በዓለ መስቀሉ ይከበርበት የነበረው ቦታ ተከልክሎ የመስቀሉ ክብርና ልዕልና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ(ለዓመታት) ተቀብሮ ይኖር ነበር፡፡ የሰላም ባለቤት የኾነው መስቀሉም በበኩሉ፣ ክብሩና ልዕልናው ለዓመታት እንዲቀበር ያደረጉትን ወገኖች በውጭ ኃይል ሳይኾን በውስጥ ኃይል ድል እንዲነሱና ሰላምን እንዲያጡ አደርጎአቸዋል፡፡ ዛሬም ቢኾን የመስቀሉን ክብርና ልዕልና የሚጋፋና “እኔ ነኝ የበላይ” የሚል አካል ካለ፣ መስቀሉ አኹንም እንደዚያው እንደበፊቱ ኃይሉን የሚያሳይ መኾኑን በጥልቀት ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ በዚያም ኾነ በዚህ፣ ባለፈው ዓመት በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ፣ ለክርስቲያኖች አንድ ደስ የሚል ነገር ታይቷል፡፡ ይኸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በዐዲስ አበባ በመስቀል ዐደባባይ በሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ብቻ ነበር የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ወይም የመንግሥት ተወካይ የሚገኙት፡፡ ባለፈው ዓመት በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ግን፣ ያለመስቀል ሰላም እንደማይገኝ በተግባር አምነውበት፣ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙት የክልል መንግሥታት ባለሥልጣናት በየክልሉ በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ተገኝተው እንደ ጥንቱ መስቀልን አክብረዋል፤ መልእክትም አስተላልፈዋል፡፡ ይህም ለሀገራችን ታላቅ የምሥራች ነው፤ አንዱ የሰላም ምልክትም ነው፡፡ በዓለም ላይ ከክርስቶስ መስቀል በስተቀር ሌላ ሰላም አስገኚ ነገር ስለሌለ፣ “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ” እንዲሉ ወደፊትም በዚኹ መቀጠል ይገባቸዋል፡፡ በመስቀሉ ክብርና ልዕልና ዙሪያ፣ ባለፈው ዓመት፣ ሌላም ደስ የሚል ነገር በሀገራችን ተከሥቷል፡፡ ይኸውም፣ የመስቀል በዓል፥ በዐዲስ አበባ፣ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን፣ በቅዱስ ላሊበላና በጎንደር እንደሚሰጠው ክብርና ልዕልና፤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ርእሰ መስተዳድሩና ሹማምንቱ፣ ከየአቅጣጫው የተሰባሰቡ በርካታ ምእመናንና ዓለም አቀፍ የሀገር ጐብኚዎች በብዛት በተገኙበት ሰማይ ጠቀስ የመስቀል ተከላ በተደረገበት በዓዲ ግራት ተራራ ላይ በታላቅ ድምቀት መከበሩ ነው፡፡ በቀጣዩም በመቐለ በጮምአ ተራራ ላይ በተመሳሳይ ኹኔታ የመስቀልን በዓል ለማክበር ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መስከረም ፲፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.፣ በ52 ሜትር ከፍታ በከፍተኛ ወጪ የተገነባውን መዘክረ መስቀል መርቀው መክፈታቸው ደግሞ ሌላ አስደሳች ዜና ነው፡፡ በአጠቃላይ በአኹኑ ጊዜ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ከመስቀሉ ጋራ ጥላቻን አስወግዳ ዕርቅን እየፈጠረች ስለኾነ፣ ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያዪቱ የቆሮንቶስ መልእክቱ፣ “አወቅን ብለን መስቀሉን እንዳንሽረው ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፤ የመስቀሉ ነገር በሚጠፉት ወገኖች ዘንድ እንደ ስንፍና የሚቈጠር ሲኾን፤ በእኛ በዳንበት ዘንድ ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና፤” ብሎ ባስተማረው መሠረት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በመስቀሉ ኃይል ተጠብቃ እንደኖረች ኹላችንም ኢትዮጵያውያን ካመንና እንደ ጥንቱ ለመስቀሉ ክብርና ልዕልና መስጠት ከጀመርን፣ መጪው ጊዜ ለሀገራችን ለኢትዮጵያና ለእኛ ለመላው ሕዝቦቿ፥ የሰላም፣ የጤና፣ የስምምነትና የልማት ጊዜ እንደሚኾን ወይም የልማት እንጂ የጥፋት ጊዜ እንደማይኾን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር መስቀሉን በዓመት ለ5 ጊዜ በአደባባይ ትዘክረዋለች፤ ታከብረዋለች፤ በመስከረም ብቻ ለአራት ጊዜ ይከበራል፤ “መስቀለ ኢየሱስ፣ መስቀለ ክርስቶስ፣ መስቀል ክብራ” እያለች ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት… ወንዱ፥ ወልደ መስቀል፣ ገብረ መስቀል፣ ኃይለ መስቀል፣ ብርሃነ መስቀል በመባል፤ ሴቷን፥ ወለተ መስቀል፣ አመተ መስቀል በማለት በመስቀል ስም እየሰየመ፤ በግንባሩ መስቀል ያለበትን በሬ/ወይፈን – መስቀል፤ ላሟን/ጊደሯን – መስቀሌ በየዓመቱም “የመስቀል ወፍ” አለች።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages