ቅድስት አርሴማ ድንግል ማን ናት? - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, June 7, 2019

ቅድስት አርሴማ ድንግል ማን ናት?


እናታችን ቅድስት አርሴማ እግዚአብሔርን በቅንነት ያገለግሉ ከነበሩ ከከበሩ ካህናት ወገን ከሆኑ ከቅዱስ ቴዎድሮስና ከእናቷ ቅድስት አትናሲያ በስዕለት ተወለደች፡፡
ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ብሉይን ሐዲስን ተምራ እያነበበች እንዲሁም በተግባር እየተረጎመች ዘወትርም በጸሎት ትተጋ እንደነበር ገድሏ ይተርካል፡፡ በዚህ ዘመን ድርጣድስ የሚባል በአርመን የነገሠ አረማዊ ንጉሥ ለጣዖት የሚሰግድ' ፀሐይንም የሚያመልክ' ክርስቲያኖችንም እኔ ለማመልከው አምላክ መስገድ አለባችሁ በማለት መከራ ያጸናባቸው ነበር፡፡

እናታችን ቅድስት አርሴማም ተጋድሎዋን የጀመረችው የዚህ ጨካኝ ንጉሥ አገልጋይ ወይም ሹም ፳፯ ክርስቲያኖችን እንደልማዱ እየደበደበ' እየገረፈና ልዩ ልዩ ስቃይ እያደረሰባቸው ሲወስዳቸው በማየቷ ነበር፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘‘ለእነርሱና ለአሕዛብ ምስክር እንዲሆን ስለኔ ወደገዢዎችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ፡፡’’ (ማቴ. ፲፡፲፮፡፲፱)፡፡ ያለውን በማሰብ ቅድስት አርሴማም ገና በሃያ ዓመቷ የዚህን ዓለም ንጉሥ እኩይ ግብሩን በመንቀፍ ስለ ክርስቶስ ከሚሰቃዩ ወገኖቿ ጋር ግንባር ቀደም በመሆን ትመሰክር ጀመር፡፡ የንጉሡም አገልጋይ በደም ግባቷና በንግግሯ ማማር ተደንቆ በዚች በፈቃዷ ልትሠዋ በወደደች ሴት ምንም ሊያደርግባት ስላልወደደ ወደ ንጉሡ ወደ ድርጣድስ ከሃያ ሰባቱ ክርስቲያኖች ጋር ወሰዳት፡፡ ንጉሡም ብዙ የተነገረላትን ወጣት ሲያይ በውበቷና በንግግሯ ተማርኮ ለዓለማዊ ደስታውና ፍላጎቱ ተመኛት፡፡ ለእርሱም ሙሽራ እንድትሆን ብዙ ወተወታት፡፡ ቅድስት አርሴማ ግን ናቀችው ‘‘እኔ የሰማያዊው ንጉሥ የክርስቶስ ሙሽራ እንጂ የዚህን ዓለም አላፊ ጠፊ የሆነውን ገንዘብና ደስታ የምሻ አይደለሁም፡፡’’ በማለትም መለሰችለት፡፡

ንጉሡም ይህንን ከእርሷ በመስማቱ እጅግ ተቆጣ፤ በመናቁም ተበሳጨ፤ አሽከሮቹንም ጠርቶ በቤተ መንግሥቱ የታሰሩትን አንበሶች እንዲለቀቅባቸው አዘዘ፡፡ አንበሶቹ ግን ይደሰቱ ነበር፡፡ በኋላም ፊታቸውን ወደ ንጉሡና አገልጋዮቹ በማዞር ሩጠው እስኪደበቁ ድረስ አሳደዷቸው፡፡ ንጉሡ ይበልጥ ነደደው ክርስቲያኖቹ በረሃብ እንዲያልቁ እንዲታሰሩ አዘዘ፡፡ እግዚአብሔርም በአምስተኛው ቀን በብርሃን ቤቱን ሞልቶት የሚበሉትን በመሶብ የሚጠጡትን በጽዋ ከሰማይ አወረደላቸው፡፡ ንጉሡም ይህንን በማየቱ ከዚያ አውጥቶ በእሳት ውስጥም አስገባቸው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅን የጠበቀ አምላክ እነርሱንም አዳናቸው፡፡ በሌላም በብዙ መንገድ ሊያጠፋቸው እንደሞከረ ገድሏ ይተርካል፡፡ በመጨረሻም ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ በሰይፍ እንዲያልቁ ይወስናሉ፡፡

እያንዳንዳቸውን ተራ በተራ ሲሰይፋቸው ቅድስት አርሴማ ለሚሰየፉት ሁሉ የድል አክሊል ከሰማይ ሲወርድላቸው ትመለከት ስለነበር የእርሷን ተራ በጉጉት ትጠብቀው ነበር፡፡ በመደሰቷም እየጸለየች አይዟችሁ ጽኑ ትላቸው ነበር፡፡

በመጨረሻም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽናቷን ተመልክቶ ቃል ኪዳን ይገባላታል፡፡ ንጉሡም ሌሎቹን አሰይፎ ሲያበቃ ወደሷ ዞሮ በቁጣ እየጮኸ አንቺን እንደ ባልንጀሮችሽ በቀላሉ አልገልሽም ስቃይሽን አጸናብሻለሁ ብሎ ለአገልጋዮቹ ትእዛዝ በመስጠት አይኗን አስወጥቶ በእጇ ያሲዛታል፤ ጡቷን ያስቆርጣል፤ በኋላም አንገቷን ያሰይፋታል በዚሁ ሁኔታ እናታችን ሰማዕትነትን ተቀበለች፡፡

ይህንን ሁሉ መከራ ስለአምላኳ ስትል እራሷን አሳልፋ የሰጠች ድንቅ ሰማዕት ናት፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ‘‘ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ’’ (መዝ.) እንዳለ ለእናታችንም የገባላት ቃል ኪዳን ‘‘በእኔ ስም አምነሽ የዚህ ዓለም ተድላና ደስታ ሳያታልልሽ አንገትሽን ለሰይፍ ሰጥተሽ ተሰይፈሻል፤ የሰማዕትነት ተጋድሎ ፈጽመሻልና ስምሽን የጠራ፤ በዓልሽን ያከበረ፤ ዝክርሽን የዘከረ፤ ገድልሽን የጻፈና ያጻፈ፤ የሰማና ያሰማም እስከ ፲፪ ትውልድ ድረስ እምርልሻለሁ’’ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶላታል፡፡ በዚህም መሠረት በሷ አማላጅነት አምኖ እገዳሟም ሄዶ በጸሎት የተማጸናት ሁሉ ለችግሩ መፍትሄ አግኝቶ እንደሚመለስ እሙን ነው፡፡ የቅድስት አርሴማ ረድኤት በረከት ጸሎትና ምልጃ ከእኛ ጋር ይኑር፡፡

 አሜን ::


ስንክሳር  " ታኅሣሥ 6 "
 
እንኩዋን "ለድንግልና ሰማዕት ቅድስት አርሴማ" : "አባ አብርሃም" እና "ቅዱስ ስምዖን ጫማ ሰፊው" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ 

 ቅድስት አርሴማ ድንግል 
 እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው:: መድኃኒታችን ክርስቶስ በወንጌል እንዳለው "በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትምና" (ማቴ. 5:11) የሰማዕቷ ሕይወት በፊታችን እንደ ብርሃን ተገልጦ ይታያል::
*ቅድስት አርሴማ እንደ ልጅ ወላጆቿን በመታዘዝ ደስ ያሰኘች ቡርክት ናት::
*ቅድስት አርሴማ ይሕ ቀረሽ የማይሏት ውብ ናት::
*ቅድስት አርሴማ ድንግል ናት::
*ቅድስት አርሴማ ባሕታዊት ጻድቅ ናት::
*ቅድስት አርሴማ ኃያል ሰማዕት ናት::
¤ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:
+አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ከሆነ ቅዱሱ ጐርጐርዮስ የታላቁዋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው:: በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት:-
1.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት
2.ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት
3.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት::
+ቅዱሱ 3ቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ:: ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት:: መከራው ገፍቶ እስከ መጣበት ጊዜ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ: ይጾሙ: ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር::
+ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ ጻድቃን የምንላቸው:: በሁዋላ ግን ማሕደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኩዋ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ::
+በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ:: ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው:: የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ::
+በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ:: በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር:: መከራው ግን አለቀቃቸውም:: ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው::
+ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት:: ድንግሊቱ ግን "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ: አይሆንም" አለችው:: ሊያስፈራራት ሞከረ:: ዐይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው::
+አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው:: እጅግ ስላፈረ አስገረፋት: አሰቃያት: ዐይኗንም አወጣ:: በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት::
+ከነገር ሁሉ በሁዋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው::
+የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ:: የንጉሡ እህት ስታለቅስ በራዕይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን-ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም" አላቸው:: ወዲያውም ቆፍረው አወጡት::
+ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም:: ለ15 ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው::
ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው::
+የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ አጽም በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ከሌሎች ሰማዕታት አጽም ጋር ኢትዮዽያ እንደ መጣ አባቶቻችን በትውፊት ነግረውናል:: ለዚህም ይመስላል ቡርክቷ እናታችን ከሌሎች ሃገራት ለይታ ለኢትዮዽያውያን ልዩ ፍቅር ያላት:: በዋናው ገዳሟ (ወሎ /ኩላማሶ/ : ስባ : ውስጥ የሚገኝ ነው) ጨምሮ ስሟ በተራበት ሁሉ ኃይልን ታደርጋለችና::
+ነገር ግን ወንድሞቼና እሕቶቼ በቅድስቷ እናታችን ስም የሚነግዱ ሥጋውያን ሰዎች በዝተዋልና እንጠንቀቅ:: የሰማዕቷ ክብር ብዙ ነውና በሕልም ላይ ብቻ አንታመን:: አባ እንጦንስ እንዳሉት "በሕልሙ የሚታመን ሰው ከንቱ ነውና::" (መዝ. 75:5)
+በዚህ ዕለት ከሰማዕቷ ጋር የመንፈስ እናቷን ቅድስት አጋታን ልናስባት ይገባናል:: ይህች እናት እመ-ምኔት ስትሆን ቅድስት አርሴማን ታስተምራት: ታጸናት: ከጐኗም ትቆምላት ነበር:: ረሃቧን: ጥሟን: ስደቷን: መከራዋንም ሁሉ አብራት ተሳትፋለች:: በፍጻሜውም አብራት ተሰይፋለች::
 
ይህች ዕለት ለቅድስት አርሴማና ለተከታዮቿ ሰማዕታት የፍሰትና የቅዳሴ ቤት መታሰቢያ ናት:













No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages