የ፳፻፲፭ (2015) ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዘመን አቆጣጠር (ባሕረ ሐሳብ ) - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, September 15, 2022

የ፳፻፲፭ (2015) ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዘመን አቆጣጠር (ባሕረ ሐሳብ )

የ፳፻፲፭ (2015) ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዘመን አቆጣጠር (ባሕረ ሐሳብ )
የዘመነ ሉቃስ የ፳፻፲፭ ዓ.ም የአጽዋማትና የበዓላት ማውጫ ስሌት።
ዓመተ ዓለም = ዓመተ ምሕረት + ዓመተ ኩነኔ (ፍዳ) = 2015+ 5500 =7515
ወንጌላዊ፦ በዓመቱ የሚሾም ወንጌላዊ ማለት ነው፡፡
ዓመተ ዓለም፥4
7515 ÷ 4 = 1878
1878 ፦ መጠነ ራብዒት ይባላል፡፡
7515 - 4×1878= 3
ቀሪው ' 1 ' ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ማቴዎስ
ቀሪው ' 2 ' ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ
ቀሪው ' 3 ' ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ሉቃስ
ቀሪው ' 0 ' ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ዮሐንስ ይሆናል።
ስለዚህ ቀሪው '3' ስለሆነ የዘንድሮው ወንጌላዊ ሉቃስ ሲሆን ዘመኑ ዘመነ ሉቃስ ይባላል።
•••
ዕለተ ቀመር፦ መስከረም አንድ የሚውልበት ቀን ነው፡፡
ዕለተ ቀመር= ዓመተ ዓለም + መጠነ ራብዒት÷7
= 7515 + 1878 =9393
= 9392 ÷ 7 = 1341 ቀሪ 5
ቀሪው '0 'ከሆነ ሰኞ
ቀሪው '1' ከሆነ ማክሰኞ
ቀሪው '2 'ከሆነ ረቡዕ
ቀሪው '3 'ከሆነ ሐሙስ
ቀሪው '4 'ከሆነ ዓርብ
ቀሪው '5 'ከሆነ ቅዳሜ
ቀሪው '6 'ከሆነ እሁድ መባቻ ይሆናል። በመሆኑም ዘንድሮ ቀሪው '6' ስለሆነ ዕለተ ቀመር እሁድ ይሆናል።
•••
መደብ = ዓመተ ዓለምን በ19 በመግደፍ እናገኛለን። = 7515፥19=395 ደርሶ 10 ይቀራል። ስለዚህ መደብ 10 ይሆናል፡፡
•••
• ወንበር = ከመደብ አንድን ለዘመን በመተው ወንበርን እናገኛለን።
ወንበር =10 - 1= 9 ይሆናል።
• አበቅቴ ፦ጥንተ አበቅቴን በወንበር አባዝተን በ30 ገድፈን እናገኛለን።
አበቅቴ =11*9=99
99፥30= '2' ደርሶ ቀሪው '9' ሲሆን ዘንድሮ አበቅቴ '9' ይሆናል።
አበቅቴን ለማግኘት ሌላው አማራጭ ጥንተ አበቅቴ ላይ 11 በመጨመር ነው። ይህም ማለት የ2014 ዓ.ም አበቅቴ 28 ነበር፤ ስለዚህ የ2015 ዓ.ም አበቅቴን ለማግኘት 28+11= ይህን በ30 ገድፈን ቀሪው 9 ስለሆነ አበቅቴ '9' ይሆናል ማለት ነው።
• መጥቅዕ፦ ጥንተ መጥቅዕን በወንበር አባዝተን ለ30 በመግደፍ(በማካፈል) እናገኛለን።
መጥቅዕ = 19×9 = 171
171 ÷ 30= 5 ቀሪው '21 'ስለሆነ መጥቅዕ ዘንድሮ '21 'ይሆናል።
መጥቅዕንን ለማግኘት ሌላው አማራጭ ጥንተ መጥቅዕ ላይ 19 በመጨመር ነው። ይህም ማለት የ2014 ዓ.ም መጥቅዕ 2 ነበር፤ ስለዚህ የ2015 ዓ.ም መጥቅዕን ለማግኘት 2+19=21  ስለዚህ የ2015 መጥቅዕ '21' ይሆናል ማለት ነው።
“አበቅቴ ወመጥቅ ክሌሆሙ ኢይበዝሁ እም30 ወኢይኅዱ እም 30 ወትረ ይከዉኑ 30 ፤ አበቅቴ ቢበዛ መጥቅ ቢያንስ መጥቅ ቢበዛ አበቅቴ ቢያንስ ከ30 አይበዙም አያንሱም” ይህም ማለት በሌላ አገላለጽ መጥቅዕና አብቅቴ ተደምረዉ ዉጤቱ ከ30 መብለጥና ማነስ የለበትም፤ ሁሌ 30 ይሆናል፡፡ የዘንድሮዉ የ2015 ዓ.ም = 9+21= 30
መጥቅዕ ከ14 በላይ ከሆነ በመስከረም  ይዉላል፤
መጥቅዕ ከ14 በታች ከሆነ በጥቅምት  ይዉላል፤
መጥቅዕ በመስከረም ቢዉል ጾመ ነነዌ  በጥር፣ መጥቅዕ በጥቅምት ቢዉል ጾመ ነነዌ በየካቲት ይብታል።
ስለዚህ በዚህ ዓመት መጥቅዕ 21 ሲሆን ከ14 ይበልጣል፤ ስለዚህም መጥቅዕ በመስከረም ይዉላል፤
•••
ስለዚህ የ2015 መጥቅዕ መስከረም 21 ሲሆን ዕለተ መጥቅዕ ቅዳሜ ይሆናል፡፡
•••
መባጃ ሐመር፦ መጥቅዕንና የባለመጥቅዕን ተውሳክ በመደመር በ30 በመግደፍ እናገኛለን፡፡ ከዕለተ መጥቅዕ ጀምረን እስከ ነነዌ ጾም መግቢያ ስንቆጥር 128 ቀን ይሆናል፡፡ በ30 ብንገድፈዉ 4 ቀሪ 8 ይሆናል፡፡ ይህም የቅዳሜ ተውሳክ ነው። ልብ ይበሉ የዕለት ተውሳክ ከቅዳሜ ይጀምራል፡፡
• ቅዳሜ፡ 128፥30= 4 ቀሪ 8
• እሁድ፡127፥30= 4 ቀሪ 7
• ሰኞ፡ 126፥30=4 ቀሪ 6
• ማግሰኞ፡ 125 ፥30= 3 ቀሪ 5
• ረቡዕ፡124 ፥30=  2 ቀሪ 4
• ሐሙስ፡ 123፥ 30= 2 ቀሪ 3
• ዓርብ፡122፥ 30= 2 ቀሪ 2
ስለዚህ የዕለታት ተውሳክ ቀሪዎቹን በመያዝ ይታወቃል። ይህም የቅዳሜ 8፣ የእሁድ 7፣ የሰኞ 6፣ የማግሰኞ 5፣ የረቡዕ 4፣ የሐሙስ 3 እንዲሁም የዓርብ 2 ይሆናል ማለት ነው። መባጃ ሐመርን ለማግኘት መጥቅዕንና በዓለ መጥቅዕ የዋለበትን ዕለት ተውሳክ መደመር ነው።
መባጃ ሐመር= 21+8=29
መባጃ ሐመር ከ30 ስለሚያንስ ራሱ 29 ይያዝና መጥቅዕ በመስከረም ስለዋለ ጾመ ነነዌ በጠቅላላው ጥር 29 ቀን በዕለተ ሰኞ ይውላል ማለት ነው።
• ጾመ ነነዌ፦ መጥቅዕና የዕለቱን ተውሳክ
በመደመር በ30 ገድፈን እናገኛለን፡፡ይህ ጾም ሕጸፅ የለውም፡፡ ሌሎችን አጽዋማት ተውሳኩን ከነነዌ ደምረን ከ30 ከበለጠ ለ30 እያካፈልን እናገኛለን።
•••
፩፥ ከነነዌ ጾም እስከ ዐቢይ ጾም 14 ቀናት አሉ። ስለዚህ የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14 ይሆናል፡፡
፪፥ ከነነዌ እስከ ደብረዘይት 41 ቀኖች አሉ፡፡
41 ÷ 30 = 1 ደርሶ ቀሪው 11 የደብረዘይት ተውሳክ ይሆናል፡፡
፫፥ ከነነዌ እስከ ሆሣዕና 62 ቀኖች አሉ፡፡
62 ÷ 30 = 2 ደርሶ ቀሪው 2 የሆሣዕና ተውሳክ ይሆናል፡፡
፬፥ ከነነዌ እስከ እስከ ስቅለት 67 ቀኖች አሉ፡፡
67 ÷ 30 = 2 ደርሶ ቀሪው 7 የስቅለት ተውሳክ ይሆናል፡፡
፭፥ ከነነዌ እስከ ትንሣኤ 69 ቀኖች አሉ፡፡
69 ÷ 30 = 2 ደርሶ ቀሪው 9 የትንሣኤ ተውሳክ ይሆናል፡፡
፮፥ ከነነዌ እስከ ርክበ ካህናት 93 ቀኖች አሉ፡፡
93 ÷ 30=3 ደርሶ ቀሪው 3 የርክበ ካህናት ተውሳክ ይሆናል፡፡
፯፥ ከነነዌ እስከ ዕርገት 108 ቀኖች አሉ፡፡
108 ÷ 30 = 3 ደርሶ ቀሪው 18 የዕርገት ተውሳክ ይሆናል፡፡
፰፥ ከነነዌ እስከ ጰራቅሊጦስ 118 ቀኖች አሉ፡፡ 118 ÷ 30 = 3 ደርሶ ቀርው 28 የጰራቅሊጦስ ተውሳክ ይሆናል፡፡
፱፥ ከነነዌ እስከ ጾመ ሐዋርያት 119 ቀኖች አሉ፡፡ 119 ÷ 30 =3 ደርሶ ቀሪው 29 የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ ነው፡፡
፲፥ ከነነዌ እስከ ጾመ ድኅነት 121 ቀኖች አሉ፡፡ 121 ÷ 30 = 4 ደርሶ ቀሪው 1 ሲሆን የጾመ ድኅነት ተውሳክ 1 ይሆናል፡፡
•••
ከዚህ ተነስተን አጽዋማትንና በዓላትን ተውሳኮቻቸውን ከነነዌ ጋር እየደመርን እናገኛለን፡፡ ስለዚህ የ2015 የነነዌ ጾም መግቢያ ጥር 29 ቀን ይሆናል፡፡
21+8= 29 ስለሆነ ነው፡፡
★ ዓብይ ጾም ተውሳኩ 14 ነው
= 14 +29= 43 ይህን በ30 ገድፈን ቀሪው 13 ሲሆን ስለዚህ ዘንድሮ በዘመነ ሉቃስ ዓብይ ጾም በየካቲት 13 ይገባል ማለት ነው፡፡
* ደብረ ዘይት፡ ተውሳኩ 11 ነው፡፡
11+29 = 40 ይህን በ30 ገድፈን ቀሪው 10 ይሆናል፡፡ የካቲትን ስላለፍን በመጋቢት 1ዐ እሁድ ደብረዘይት ይሆናል።
★ ሆሣዕና ተውሳኩ 2 ነው፡፡
= 2+29 =31 ይህን በ30 ገድፈን ቀሪው 1 ስለሆነና መጋቢትን ስላለፍን ሆሳዕና ሚያዚያ 1 ቀን በዕለተ እሁድ ይሆናል፡፡
★ ስቅለት ተውሳኩ 7 ነው፡፡
7+29= 36 ይህን በ30 ገድፈን ቀሪው 6 ሲሆን ዘንድሮ በሚያዝያ 6 ዓርብ ስቅለት ይሆናል፡፡
★ ትንሣኤ ተውሳኩ 9 ነው፡፡
9 +29 = 38 ይህን በ30 ገድፈን ቀሪው 8 ሲሆን ሚያዝያ 8 በዓለ ትንሣኤ ይውላል።
★ ርክበ ካህናት ተውሳኩ 3 ነው፡፡
3 +29 = 32 ይህን በ30 ገድፈን ቀሪው 2 ስለሚሆንና በሚያዝያ ስላለፍን በግንቦት 2 ረቡዕ ርክበ ካህናት ይሆናል።
★ ዕርገት ተውሳኩ 18 ነው፡፡
18 +29 = 47 ይህን በ30 ገድፈን ቀሪው 17 ሲሆን ዘንድሮ ግንቦት 17 ሐሙስ በዓለ ዕርገት ይሆናል።
በነገራችን ላይ "ተውሳክ" ማለት ተጨማሪ ማለት ነው።
★ ጰራቅሊጦስ ተውሳኩ 28 ነው፡፡
28 +29= 57 በ30 ገድፈን ቀሪው 27 ስለሆነ በግንቦት 27 እሁድ በዓለ ጰራቅሊጦስ ይውላል።
★ ጾመ ሐዋርያት ተውሳኩ 29 ነው፡፡
29 +29=58 ይህን በ30 ገድፍን ቀሪው 28 ሲሆን በግንቦት 28 ሰኞ የሐዋርያት ጾም ይገባል።
★ፆመ ድህነት ተውሳኩ 1 ነው፡፡
= 1 + 29 =30 በመሆኑም ጾመ ድህነት(የረቡዕና ዓርብ ጾም) ግንቦት 30 ይገባል።

የአጽዋማትና የበዓላት ኢይወርድ ኢይዓርግ(ገደብ)
➛ጾመ ነነዌ ከጥር 17 በታች አይወርድም ፤ ከየካቲት 21 በላይ አይወጣም።
➛ ዐቢይ ጾም ከየካቲት 1 በታች አይወርድም ፤ ከመጋቢት 5 በላይ አይወጣም።
➛ ደብረዘይት ከየካቲት 28 በታች አይወርድም ፤ ከሚያዝያ 2 በላይ አይወጣም።
➛ ሆሣዕና ከመጋቢት 19 በታች አይወርድም ፤ ከሚያዝያ 23 በላይ አይወጣም።
➛ ስቅለት ከመጋቢት 24 በታች አይወርድም ፤ ከሚያዝያ 28 በላይ አይወጣም።
➛ ትንሣኤ ከመጋቢት 26 በታች አይወርድም ፤ ከሚያዝያ 30 በላይ አይወጣም።
➛ ርክበ ካህናት ከሚያዝያ 20 በታች አይወርድም ፤ ከግንቦት 24 በላይ አይወጣም።
➛ ዕርገት ከግንቦት 5 በታች አይወርድም ፤ ከሰኔ  9 በላይ አይወጣም።
➛ ጾመ ሐዋርያት ከግንቦት 16 በታች አይወርድም ፤ ከሰኔ 20 በላይ አይወጣም።
➛ ጾመ ድኅነት ከግንቦት 18 በታች አይወርድም ፤ ከሰኔ  22 በላይ አይወጣም።

• ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ አይወጡም።
• በዓለ ደብረዘይት፣ ሆሣዕና፣ ትንሣኤና ጰራቅሊጦስ ከእሁድ አይወጡም፡፡
• ዕርገት ከሐሙስ
• ስቅለት ከዓርብ አይወጣም።
• ርክበ ካህናትም ከረቡዕ አይወጣም።

የዘመናት ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ ፣ ከ2014 ዓ.ም ወደ 2015 ዓ.ም በሰላም በጤና ያሻግረን፤ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages