ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ:- መስቀል ከፀሐይ ይልቅ ብሩሕ ይሆናል - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, September 29, 2022

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ:- መስቀል ከፀሐይ ይልቅ ብሩሕ ይሆናል

 
በዕለተ ምጽአት ጌታችን በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት ከአእላፋት መላእክቱ ጋር ሲመጣ የሚሆነውን ሲናገር :-
"የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል" ብሎአል:: ማቴ. 24:30
የሰው ልጅ የተባለው መድኃኔዓለም ክርስቶስ በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ከመምጣቱ በፊት ፣ የምድር ወገኖች ዋይታ ከመሰማቱ በፊት አንድ ነገር ይከሰታል?
"የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል!"
ይህ የሰው ልጅ ምልክት ምንድር ነው?
"ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው" ተብሎ የተነገረለት ቅዱስ መስቀሉ ነው::
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን የወንጌል ክፍል ሲተረጉም ከጌታችን መምጣት ቀድሞ በሰማይ ስለሚታየው የሰው ልጅ ምልክት (መስቀል) እንዲህ ይላል:-
"መስቀል ከፀሐይ ይልቅ ብሩሕ ይሆናል:: ፀሐይም ትጨልማለች ብርሃንዋንም ትሰውራለች:: ከዚያም በተለምዶ በማትታይበት ሰዓት ትታያለች:: ይህም የአይሁድ ጠማማነት ይቆም ዘንድ ነው" (Homily on Matthew 24)
ጌታችን በምድር ላይ ከተመላለሰ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው መስቀል ዳግም ሊፈርድ ሲመጣ ግን መስቀሉ ሐዋርያ ሆኖ ቀድሞ በሰማይ ላይ ያበራል::
"መስቀል አብርሓ በከዋክብት አሰርገወ ሰማየ"
"መስቀል በከዋክብት ዘንድ አበራ ሰማይንም አስጌጠ" ብሎ ከቅዱስ ያሬድ ጋር መዘመር ያን ጊዜ ነው::

 
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መስከረም 17 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages