ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 12 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, October 21, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 12

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት አስራ ሁለት በዚህች ዕለት ሊቀ መላእክት #ቅዱስ_ሚካኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ #ቅዱስ_ዳዊትን በሳኦል ፈንታ እንዲሾመው ለሳሙኤል የነገረበት እና በጎልያድ ላይ ኃይልን የሰጠበት እንዲሁም የወንጌላዊው #ቅዱስ_ማቴዎስ እና #የቅዱስ_ድሜጥሮስ የዕረፍት ቀን ነው፡፡

ጥቅምት ዐሥራ ሁለት በዚች ዕለት የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ የሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። በዚችም ቀን ወደ ነቢይ ሳሙኤል እግዚአብሔር ልኮታልና የዳዊት አባት ወደሆነ በቤተ ልሔም ወደሚኖር ወደ እሴይ ቤት ይሔድ ዘንድ በቂስ ልጅ በሳኦልም ፈንታ ለእስራኤል ልጆች እንዲነግሥ ልጁ ዳዊትን ይቀባው ዘንድ አዘዘው።
ሳሙኤልም ወደ እሴይ ቤት ሔዶ ልጆችህን ሁሉንም አቅርብልኝ ብለው እሴይም ከዳዊት በቀር ሁሉንም አቀረባቸው እርሱ በእርሻ ውስጥ በጎችን ይጠብቅ ነበርና።
ሳሙኤልም የመንግሥት ቅባት ያለበትን ብልቃጥ በራሳቸው ላይ ከፍ ከፍ በአደረገ ጊዜ እግዚአብሔር አልመረጣቸውም ። ሳሙኤልም እሴይን ልጆችህ እነዚህ ብቻ ናቸውን አለው ዕሴይም በጎች የሚጠብቅ አንድ ትንሽ ልጅ አለ አለው።
ሳሙኤልም ደግሞ ዕሴይን እሱ ሳይመጣ ምሳ አልበላምና ልከህ አስመጣው አለው። እሱም ልኮ አስመጣው መልኩም ቀይ ዐይኖቹም የተዋቡ አርአያውም ያማረ ነው እግዚአብሔርም ሳሙኤልን ይህ ይበልጣቸዋልና ተነሥተህ ቅባው አለው። በዚያንም ጊዜ ሳሙኤል የመንግሥት ቅባት ያለበትን ቀንድ አምጥቶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው ከዚያችም ቀን ጀምሮ ለሁል ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ አደረበት በእስራኤል ልጆችም ላይ ነገሠ።
ደግሞ ሁለተኛ በዚች ቀን እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ሚካኤልን ወደ ዳዊት ላከው ረዓይታይ ጎልያድን እስኪገድለውና የእስራኤልን ልጆች እስከሚያድናቸው ረድቶ ኃይልን ሰጠው።
ስለዚህም የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን እናደርግ ዘንድ የቤተክርስቲያን መምህራን አዘዙን።

ዳግመኛም በዚችም ቀን ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት የአንዱ የወንጌላዊ ማቴዎስ የዕረፍቱና የምስክርነቱ መታሰቢያ ነው። ይህም እንዲህ ነው በብዙ አገሮች ውስጥ አስተምሮ ብዙዎች ሰዎችን እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ከመለሰ በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ወደ ካህናት አገር እንዲሔድ አዘዘው።
ተጒዞም ወደ ከተማው መግቢያ ደጅ በደረሰ ጊዜ አንድ ወጣት ብላቴና አገኘ ወደ ከተማው ለመግባት እንዴት እንደሚችል ጠየቀው ወጣቱ ብላቴናም እንዲህ ብሎ መለሰለት አንተ ግን ራስህንና ጽሕምህን ካልተላጨህ በእጅህም ዘንባባ ካልያዝክ መግባት አትችልም። ይህም ነገር ለሐዋርያ ማቴዎስ አስጨንቆት ሲያዝን አስቀድሞ ያነጋገረው ያ ወጣት ብላቴና ዳግመኛ በስሙ ጠራው። ሐዋርያውም ወዴት ታውቀኛለህ አለው እርሱም እኔ ጌታህ ኢየሱስ ነኝ አሁንም እንደ ነገርኩህ አድርግ እኔም ከአንተ ጋር አለሁ ከአንተም አልርቅም አለው።
ከዚህም በኋላ ጌታችን እንዳዘዘው አድርጎ ወደ ካህናት አገር ገባ ለአማልክት ካህናት አለቃቸው ከሆነ ከአርሚስ ጋር ተገናኘ ከእርሱም ጋር ስለ አማልክቶቻቸው ተነጋገረና ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ጣዖቶቻቸውን አቃጠላቸው እንዲህም አላቸው። ራሳቸውን ማዳን ያልቻሉ ሌላውን እንዴት ያድናሉ በዚያንም ጊዜ ከአርሚስ ጋር ብዙዎች ሰዎች አምነው አጠመቃቸው ከሰማይም ማዕድ አውርዶ መገባቸው።
የሀገሩም ንጉሥ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ከአርሚስ ጋር ሐዋርያውን ወደ እሳት ጨመረው ጌታችንም አዳናቸው። ከዚህም በኋላ በሚአሠቃያቸው ነገር ሲአስብ እነሆ ልጁ እንደ ሞተ ነገሩት እጅግም አዘነ። ሐዋርያ ማቴዎስም ልጅህን እንዲያስነሡት ወደ አማልክትህ ለምን አትለምንም አለው ንጉሡም የሞተ ማንሣት እንዴት አማልክት ይችላሉ ብሎ መለሰ። ቅዱስ ማቴዎስም ብታምንስ የእኛ አምላክ ልጅህን ማሥነሣት ይችላል አለው። ንጉሡም ልጄ ከተነሣ እኔ አምናለሁ አለ በዚያን ጊዜ ሐዋርያው ክብር ይገባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየና የንጉሡን ልጅ ከሞት አስነሣው።
ንጉሡም ክብር ይግባውና በጌታችን አመነ የአገር ሰዎች ሁሉም አመኑ የቀናች ሃይማኖትንም አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ካህናትንም ሾመላቸው ከዚህም በኋላ ወደ ሌሎች አገሮች ሒዶ ወንጌልን አስተማረ። ከዚህም አስቀድሞ በደመና ተነጥቆ ብሔረ ብፁዓን ገብቷል ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስን ሁል ጊዜ በየበዓላቸው ወደ እነርሱ ሲመጣ አየው ከእርሱም ጋር መቶ አርባ ሽህ ሕፃናት አሉ መላእክትም ሁሉ በዙሪያው ቁመው ያመሰግኑታል።
በብሔረ ብፁዓን ስለ ሚኖሩ ወገኖችም ድንቅ ስለሆነ ሥራቸው ሁሉ ከሐዋርያው በኋላ ወደርሳቸው የገባ ዘሲማስ ቀሲስ ምስክር ሆነ። ከዚህም በኋላ የሐዋርያው የተጋድሎውና የምስክርነቱ ፍጻሜ ሲቀርብ ወደ አንዲት ከተማ ገብቶ አስተማረ ብዙዎችንም አሳመነ አገረ ገዢውም ይዞ ከወህኒ ቤት ጨመረው። በዚያም አንድ እጅግ የሚያዝን እሥረኛ አይቶ ስለኀዘኑ ጠየቀው እርሱም ብዙ የሆነ የጌታው ገንዘብ ከባሕር እንደ ሠጠመበት ነገረው ሐዋርያ ማቴዎስም ወደ ዕገሌ ባሕር ዳርቻ ሒድ ወርቅን የተመላ ከረጢትንም ታገኛለህ ያንንም ወርቅ ወስደህ ለጌታህ ስጥ አለው።
ስለዚህም ድንቅ ተአምር ብዙዎች ክብር ይግባወና በጌታችን አመኑ። መኰንኑም በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ ቅዱስ ማቴዎስንም ራሱን እንዲቆርጡ ሥጋውንም ለሰማይ ወፎች እንዲጥሉ አዘዘ። ከከተማውም አውጥተው ቈረጡት ምእመናንም በሥውር መጥተው ወስደው በመልካም ቦታ አኖሩት።

ዳግመኛም በዚችም ቀን ንጹህ ድንግል የጠባይን ፍላጎት ድል የነሳ አባት ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ዐሥራ ሁለተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ድሜጥሮስ አረፈ።
ይህም አባት አስቀድሞ መጻሕፍትን ያልተማረ ሕዝባዊ ገበሬ ነው በወላጆቹ የወይን አታክልት ቦታዎች ውስጥ የሚሠራ ሆነ ከታናሽነቱም ሚስት አጋብተውት ከእርሷ ጋር አርባ ስምንት ዓመት ኖረ ድንግልናቸውን በንጽሕና የጠበቁ ናቸው የተሠወረውን ከሚያውቅ እግዚአብሔር በቀር ይህን የሚያውቅ የለም።
ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ዮልያኖስ ዕረፍቱ በቀረበ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት ። ከእርሱ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት የሚሆነውን በምልክት ገለጠለት እንዲህም አለው ነገ የወይን ዘለላ ይዞ ወደ አንተ የሚገባ ሰው አለ ከአንተ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት የሚሆን እርሱ ነውና ያዘው አትተወው።
በዚያችም ቀን ድሜጥሮስ ወደ አታክልቱ ቦታ ገባ ያለ ጊዜው ያፈራ የወይን ዘለላ አገኘ ያንንም የወይን ዘለላ በረከት ሊቀበልበት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮልዮስ ይዞት ሔደ። በዚያንም ጊዜ አባ ዮልዮስ ድሜጥሮስን በእጁ ይዞ ለሕዝቡ ሁሉና ለኤጲስቆጶሳት አሳልፎ ሰጠው ከእኔ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት የሚሆናችሁ ይህ ነው ስለ ርሱ ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ ነግሮኛልና ይዛችሁ ሹሙት አላቸው።
ከዚህም በኋላ አባ ዮልዮስ በአረፈ ጊዜ የጸሎቱን ሥርዓት ፈጽመዉለት ሊቀ ጵጵስና ሾሙት ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ መላበት የቤተ ክርስየቲያን የሆኑ የብሉያትና የሐዲሳት መጻሕፍትን አንብቦ ተረጐማቸው ብዙዎች ምሥጢራትም ተገለጡለት።
ከዚህም በኋላ ባሕረ ሐሳብ የተባለውን የዘመን መቊጠሪያ ሠራ ከእርሱ በፊት የነበሩ የክርስቲያን ወገኖች የመድኃኒታችን የጥምቀቱን በዓል ጥር ዐሥራ አንድ ቀን አክብረው በማግስቱ የከበረች አርባ ጾምን ጀምረው እስከ የካቲት ሃያ ሁለት ቀን ድረስ ይጾማሉ። ከዚያም በኋላ መጋቢት ሃያ ሁለት ቀን የሆሣዕናን በዓል አክብረው በማግስቱ የሕማማትን ሰሞን ጾም ጀምረው ይጾማሉ። ከሐዋርያትም ዘመን ጀምሮ እስከርሱ ዘመን እንዲህ እያደረጉ ኖሩ።
እርሱም እንዲህ ሠራ የከበረች የጌታችን ጾም መግቢያዋ ከሰኞ ቀን እንዳይፋለስ ፍጻሜውም በዐረብ ቀን ከዚህም የሆሣዕናን በዓል አያይዞ ሠራ በሚቀጥለው ሰኞ ቀን የሕማማት ጾም ተጀምሮ እንዲጾም የስቅለቱም በዓል ከዐርብ ቀን እንዳይፋለስ የከበረች የትንሣኤውና የጰራቅሊጦስም በዓል ከእሑድ ቀን የዕርገቱም በዓል ከሐሙስ እንዳይፋለስ።
እንዲሁም አዘጋጅቶ ለኢየሩሳሌም አገር ለሮሜ ሀገር ለኤፌሶንና ለአንጾኪያ ሀገር ሊቃነ ጳጳሳት ለየአንዳንዳቸው ላከላቸው። እነርሱም በደስታ ተቀብለው ሠሩበት እስከዚችም ቀን ጸንቶ ኖረ።
በቊርባን ቅደሴ ጊዜም ዘወትር ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያየው ሆነ። የሕዝቡ ኃጢአታቸው በፊቱ ግልጥ ሆነ ስለዚህም የማይገባቸውን ሥጋውንና ደሙን ከመቀበል ይመልሳቸዋል እንዲህም ይላቸዋል ሒዱ ንስሐ ግቡ ከዚያም በኋላ መጥታችሁ ሥጋውና ደሙን ተቀበሉ ።
ሰለዚህም ነገር ብዙ ሕዝቦች ኃጢአት ከመሥራት የሚጠበቁ ሆኑ ልባቸው የደነደነ ሌሎች ግን ጠሉት እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ። ይህ ሰው ሚስት አግብቶ ሚስቱም ከእርሱ ጋር ትኖራለች ሳይገባውም በወንጌላዊው ማርቆስ ወንበር ተቀምጠ ከንጹሕ ድንግል በቀር አይሾምበትም ነበርና እኛንም ኃጢአተኞች ናችሁ ብሎ ይገሥጸናል።
በአንዲት ሌሊትም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ወደርሱ መጥቶ ድሜጥሮስ ሆይ ራስህን ብቻ ማዳንን አትሻ ወገኖችህም ይጠፋ ዘንድ አትተው ነፍሱን ስለ መንጋዎቹ አሳልፎ ለሞት የሚሰጥ እርሱ ቸር ጠባቂ እንደሆነ ጌታችን በቅዱስ ወንጌል የተናገረውን አስብ አለው።
ድሜጥሮስም መልአኩን ጌታዬ የምትለኝ ምንድን ነው አለው መልአኩም በአንተና በሚስትህ መካከል ተሰውሮ ያለውን ምሥጢር ለወገኖችህ ግለጽ ብሎ መለሰለት።
ከዚህም በኋላ ሕዝቡን አሰባሰባቸው ሊቀ ዲያቆኑንም ወጥተው ወደ ቤታቸው እንዳይገቡ ሕዝቡን ንገራቸው አለው ራሱም ቅዳሴውን ቀደሰ ሁለተኛም ዕንጨቶችን ሰብስበው እሳትን እንዲአነዱ አዘዛቸው እንዳዘዛቸውም አደረጉ። ያን ጊዜ ይህ አባት ተነሥቶ ከሚነደው እሳት መካከል ገብቶ ለረጅም ጊዜ ቁሞ ጸለየ ከእሳቱም ፍም አንሥቶ በሚከናነብበት ቀጸላ አደረገ ሚስቱንም ጠርቶ መጎናጸፊያሽን ዘርጊ አላት በዚያም የእሳቱን ፍም ጨመረ በእሳቱም መካከል በአንድነት እየጸለዩ ቆሙ ሕዝቡም እጅግ ያደንቁ ነበር።
ከዚህም በኋላ ካህናቱና ሕዝቡ እንዲህ ብለው ለመኑት አባታችን ሆይ ይህን የሠራኸውን ሥራ ታስረዳን ዘንድ ከቅድስናህ እንሻለን እርሱም ይህን ሥራ የሠራሁት ከንቱ ውዳሴን ሽቼ አይደለም እናንተ እኔን አምታችሁ ስለእኔ እንዳትጐዱ እንድትድኑ ከዚች ሴት ጋር በመካከላችን ተሠውሮ ያለውን ሚሥጢር እገልጽላችሁ ዘንድ የእግዚአብሔር መልአክ ስለአዘዘኝ ነው እንጂ አላቸው።
እርሷ የአባቴ የወንድሙ ልጅ ናት በሕፃንነቷም አባቷ ሞተ በአባቴም ቤት ከእኔ ጋር አደገች አካለ መጠንም በአደረሰን ጊዜ አባቴ እርሷን አጋባኝ ወደ ጫጉላ ቤትም በገባን ጊዜ እኔ እኅትህ ስሆን ለአንተ እንዴት አጋቡኝ አለችኝ። እኔም የምትፈቅጂ ከሆነ ድንግልናችንን ጠብቀን በአንድነት እንኑር ይህንንም በመካከላችን ያለውን ምሥጢር የሚያውቅ አይኑር አልኋት በዚህም ተስማምተን በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ ዐልጋ እየተኛን አንድ መጐናጸፊያንም እየተጐናጸፍን አርባ ስምንት ዓመት ያህል ኖርን ይህን ሥራችንንም ያለ እግዚአብሔር የሚያውቅ የለም እኔም እርሷ ሴት እንደ ሆነች አላወቅኋትም እርሷም እኔን ወንድ እንደሆንኩ አታውቅም በየሌሊቱም ሁሉ በንስር አምሳል ወደ መኝታችን እየገባ ክንፎቹን አልብሶን ያድራል ሲነጋም ከእኛ ይሠወራል አላቸው።
በዚያንም ጊዜ በደላቸውን ይቅር ይላቸው ዘንድ ከእግሩ ሥር ወድቀው ለመኑት እርሱም ይቅር አላቸው አጽናናቸውም። ይህንንም ድንቅ ሥራ ያዩ ሁሉ ምስጉን እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
በዚህ አባት ዘመንም ስማቸው ቀሌምንጦስ አርጌንስ የሚባሉ ሌሎችም መናፍቃን ስዎች ተነሥተው ታዩ ሌሎችም በአንድነት ሁነው ስለሃይማኖት የፈጠራ መጽሐፍን ጻፉ እርሱም አውግዞ ከምእመናን ለያቸው።
እርሱም ሁል ጊዜ ያለ ዕረፍት ከጥዋት እስከ ማታ ምእመናንን የሚያስተምራቸው ሆነ። ሸምግሎ በደከመም ጊዜ በዐልጋ ላይ አስቀምጠው ተሸክመው ወደ ቤተ ክርስቲያን ያደርሱታል እስከማታ ድረስም ያስተምራቸዋል ሰዎችም ሁሉ ትምህርቱን ይሰሙ ዘንድ ይጨናነቃሉ መላ የሕይወቱ ዘመንም መቶ ሰባት ነው በሰላም በፍቅር አንድነትም አረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages