ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 11 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, October 21, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 11


 
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ዐሥራ አንድ በዚችም ቀን ገድለኛዋ #ቅድስት_ጲላግያ እና የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባት_ያዕቆብ አረፉ፤ የውቅሮው #አቡነ_ኤልያስ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡

ጥቅምት ዐሥራ አንድ በዚችም ቀን ገድለኛዋ ቅድስት ጲላግያ አረፈች። ይቺም ከአንጾኪያ አገር የሆነች ናት ወላጆቿም ከሀድያን ናቸው እርሷም አስቀድማ ከረከሰ ሃይማኖቷ ጋር በረከሰ ሥራ ጸንታ መኖርን ገንዘብ አደረገች። እርሷም በመሸታ በጨዋታ ቤት በመዋል ስትሣለቅና ስታመነዝር ስትዘፍንም ትኖራለች።
በአንዲት ቀንም የገሀነም እሳትና የዘላለም ሥቃይ እንደሚጠብቃቸው እያሳሰበ ዝንጉዎችንና አመንዝራዎችን ሲገሥጻቸው ኤጲስቆጶስ ጳውሎስን ሰማችው ምክሩም በልቧ አደረ። ከዚህም በኋላ ወደርሱ ሒዳ የሠራችውን ሁሉ ተናዘዘች እርሱም አጽናንቶ የቀናች ሃይማኖትን አስተማራትና አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃት።
በቀደመው ሥራዋም እየተጸጸተች በጾም በጸሎት በስግደት ሰውነቷን ማድከም ጀመረች ከዚህም በኋላ የወንድ ልብስ ለብሳ ወደ ኢየሩሳሌም ሒዳ በከበሩ ቦታዎች ሁሉ ሰግዳ ሁሉንም ቦታዎች ተሳለመች ወደ ኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሳትም ተመለሰች። እርሱም ከኢየሩሳሌም ከተማ ውጭ ከደናግል ገዳማት ወደ አንዱ ላካት የምንኵስናንም ልብስ ለብሳ በጽኑዕ ገድልም ተጠምዳ ሠላሳ ዓመት ያህል ኖረች እግዚአብሔርንም አገልግላ በሰላም አረፈች።

ዳግመኛም በዚህች ቀን የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ያዕቆብ አረፈ። ይህም ቅዱስ ብዙ መከራ ደርሶበታል ስለ ቀናች ሃይማኖቱ አርዮሳውያን አሳደውት በደሴት ብዙ ወራት ኖረ።
ከዚህም በኋላ የአንጾኪያ ምእመናን ሰዎች ተሰብስበው መከሩ። መልእክትም ልከው ወደ እነርሱ መልሰውት ጥቂት ቀኖች ኖረ። ከዚህም በኋላ ሁለተኛ አርዮሳውያን ተነሡበት አሳደዱትም በስደትም ውስጥ ሰባት ዓመት ኑሮ በዚያው አረፈ።

ዳግመኛም በዚህች ቀን የውቅሮው አቡነ ኤልያስ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡ አቡነ ኤልያስ ዘውቅሮ የትውልድ ሀገራቸው አክሱም ነው፡፡ የአቡነ አረጋዊ 3ኛ የቆብ ልጅ ናቸው፡፡ አባታቸው ውቅሮ የሚገኘው የጥንታዊው የአብርሃ ወአጽብሓ ቤተ መቅደስ አጣኝ ነበሩ፡፡ ይህ ጻድቅ የሚታወቁበት አንድ ትልቅ ገድል አላቸው፡፡ በቀን 548 ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን እየጸለዩ 666 ጊዜ ይሰግዱ ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድ ዓባይ የሀገራችንን አፈርና ዛፉን ሁሉ ጠራርጎ ሲወስድ ቢመለከት ድምጹን ከፍ አድርጎ ኦ አባይ አይቴ ተሐውር ወለመኑ ተሐዲጋ ለኢትዮጵያ ብሎ ሲዘምር ዓባይ ቀጥ ብሎ ቆሟል፡፡ መልአኩም ወዲያው መጥቶ ‹‹ለምን ትደክማለህ? ለምንስ ተፈጥሮን ትከለክላለህ? ሕጉን አታፍርስ›› ሲለው ቅዱስ ያሬድ ደንጎጦ ‹‹አጥፍቻለሁ ዓባይ ሆይ ሂድ የተፈጥሮ ግዴታህን ፈጽም›› ብሎ አሰናብቶታል፡፡ የኢትዮጵያ ብርሃኗ ቅዱስ ያሬድ በዜማው ዓባይን ቀጥ አድርጎ እንዳቆመው ሁሉ አቡነ ኤልያስ ዘውቅሮም በጸሎታቸው ዓባይን ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ አድርገውት ነበር፡፡
ታቦተ አብርሃ ወአጽብሓን ይዘው ከኢትዮጵያ ጠረፍ ዳር ኑብያ ሄደው ድንጋይ ከዓባይ ዳር ደርድረው ታቦቱን አስቀምጠው ሥዕለ ማርያምን አድርገው መሥዋዕት ሰውተው ‹‹ዓባይ ከኢትዮጵያ እንዳትወጣ ገዝቼሃለሁ›› ሲሉት ዓባይም ተመልሶ ቆሟል፡፡ ዓባይ ምድረ ኑብያን ሲያጥለቀልቃት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ ‹‹ለምን የእግዚአብሔርን ስነ ፍጥረት ታስጨንቃለህ?›› ብሎ ተቆጣቸው፡፡ ጻድቁም ‹‹ውኃው ይሂድ ግን ዛፉን አፈሩን ይዞ ከኢትዮጵያ አይውጣ›› ብለው መልአኩን ጠየቁት፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ‹‹ውኃ ሲሞላ ዛፉን ቅጠሉን ይዞ መጓዙን እንዴት ትረሳዋለህ? የጸሎት ጊዜህ ደርሷልና ወደ በዓትህ ተመለስ›› ብሎ በቁጣ የእሳት ሰይፉን ሲያዛቸው ግዝታቸውን አንሥተው ታቦታቸውን ይዘው ወደ በዓታቸው ውቅሮ ተመልሰዋል፡፡ አባቶቻችን እንዲህ ናቸው እንኳን ሃይማኖት፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ስብዕና ማንነታችንን ይቅርና የሀገራችንን አፈር እንኳን ለባዕድ አሳልፈው የማይሰጡ ቅዱሳን ጻድቃን ነበሩ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages