ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም 30 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, October 9, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም 30

 

 
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሠላሳ በዚህች ቀን #በአባ_አትናቴዎስ ላይ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ነው፣ #የቅዱስ_አባ_ሣሉሲ እና #የደብረ_ክሳሄው_አቡነ_አብሳዲ ዕረፍታቸው ነው። ዳግመኛም #አባ_ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ መታሰቢያ ነው።


መስከረም ሠላሳ በዚህች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በሆነ በከበረና በተመሰገነ በአባ አትናቴዎስ ላይ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ሆነ።
ይህም ሁለተኛም ቁስጠንጢኖስ ወደ ረከሰች የአርዮስ ሃይማኖት በገባ ጊዜ የእስክንድርያውን ሊቀ ጳጳሳት አባ አትናቴዎስን አሳድዶ ከሀዲውን ጊዮርጊስን በእስክንድርያ መንበር ላይ ሾመው። የአርዮስንም ሃይማኖት እንዲአጠናክር የረከሰ የአርዮስን ሃይማኖት የማይቀበሉትን ግን ሁሉንም ይገድላቸው ዘንድ አዘዘው ብዙዎች ፈረሰኞች ጦረኞችን ለእርሱ ሰጥቶታልና። ስለዚህም ከእስክንድርያ ሰዎች ቁጥር የሌላቸውን ብዙዎች ምእመናንን ገደላቸው።
ቅዱስ አትናቴዎስም በተሰደደበት ስድስት ዓመት ኖረ። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔርን ልጅ የካደው ታናሹ ቁስጠንጢኖስ ወደአለበት ወደ ቁስጥንጥንያ ተነሥቶ ሔደ ንጉሡንም እንዲህ አለው ወደ ተሾምሁበት መንበሬ ትመልሰኝ እንደሆነ መልሰኝ ይህ ካልሆነ የምስክርነት አክሊልን እንድቀበል ግደለኝ።
ንጉሡም ይህን ነገር ከእርሱ በሰማ ጊዜ በታናሸ መርከብ አድርገው ያለ ቀዛፊና ያለ መብልና መጠጥ በባሕር ውስጥ እንዲተዉት አዘዘ ንጉሡም በስጥመት ወይም በረኃብና በጥም እንደሚሞትለት አስቦ ነበርና የቀናች ሃይማኖትንም ስለመለወጡ እንዳይዘልፈው ከእርሱ ያርፍ ዘንድ እንዲሁም ንጉሡ እንዳዘዘ በቅዱስ አትናቴዎስ ላይ አደረጉበት። ንጉሡም እንጀራና ውኃ ባይሰጠው ከሰማይ ለእርሱ የወረደ እንጀራ ስለርሱ የፈለቀ ውኃም አለው። የመርከብም ቀዛፊ ቢከለክለው እነሆ ዓለሙን ሁሉ በቃሉ የሚጠብቅ የሚመራ ከእርሱ ጋር ነበር። ስለዚህም ቅዱስ አትናቴዎስ በውስጧ የተቀመጠባት ያቺ መርከብ መላእክት እየቀዘፏት በጸጥታና በሰላም ተጓዘች በሦስተኛውም ቀን ከእስክንድርያ ወደብ ደረሰ።
የምእመናን ወገኖችም ደግ ጠባቂያቸው እንደ ደረሰ በሰሙ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው መብራቶችንም በመያዝ በምስጋና እየዘመሩ ሊቀበሉት ወጡ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገቡት። ከሀዲው ጊዮርጊስም ከወገኖቹ ጋር ወጥቶ ሔደ።
በዚያችም ቀን ቅዱስ አትናቴዎስ ለእግዚአብሔር ታላቅ በዓልን አከበረ የእስክንድርያም ሰዎች እስከ ዛሬ ድረስ ያከብሩ አታል።


በዚችም ቀን ቅዱስ አባ ሣሉሲ አረፈ። ይህም ቅዱስ መስጋድል ሲሆን ራሱን እንደ እብድ አደረገ እርሱም በሥውር ይጸልያል ይጾማልም በሰው ፊት ግን ምንም ምን አይጸልይም አይጾምም በየጥዋቱ ሁሉ የሚመገበውን የሣር ፍሬ አድርጎ በሰው ፊት ያላምጣል በምሽት ጊዜ ግን ከውንድሞች መነኰሳት ጋር ምንም ምን አይቀምስም።
አበ ምኔቱ አባ ይስሕቅና መነኰሳቱ ሁሉ ከሥራው የተነሣ ያደንቃሉ ይህንንም ልማዱን ሊአስጥሉት ይሻሉ ነገር ግን ልቡን እንዳያሳዝኑት ያስባሉ።
በአንዲትም ዕለት የገዳማቸው በዓል ሆነ አበ ምኔቱ አባ ይስሐቅም መነኰሳቱን እንዲህ አላቸው ቅዱስ ቁርባንን ከመቀበሉ በፊት እህልን እንዳይቀምስ አባ ሣሉሲን ጠብቁት። እነርሱም ጠበቁት የሚበላበትም ጊዜ ሲደርስ ከእነርሱ ሊለይ ወደደ መነኰሳቱም ከለከሉት እርሱም በረኃብ እንዳልሞትና በእናንተ ላይ በደል እንዳይሆንባችሁ ልቀቁኝ ብሎ ጮኸባቸው።
ባልተውትም ጊዜ በዚያን ወቅት ቆቡን ከራሱ ላይ አውልቆ እመቤቴ ማርያም ሆይ ከእሊህ መነኰሳት እጅ አድኝኝ ብሎ የቤተ ክርስቲያኑን ግድግዳ በቆቡ መታበት ሕንፃውም ተሠንጥቆለት በዚያ ወጥቶ ሔደ የግድግዳውም ግምብ ተመልሶ እንደቀድሞው ሆነ።
የተሰበሰቡትም ይህን ድንቅ ተአምር በአዩ ጊዜ ሦስት መቶ ጊዜ ኪርያላይሶን እያሉ ጮኹ በዚያንም ጊዜ ያቺን ቆብ ወድቃ አገኙአት በታላቅም ክብር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩዋት ድውያንንም በመፈወስ ከእርሷ ብዙ ተአምራት ተደረገ።
ሊቀ ጳጳሳቱም በሰማ ጊዜ ከእርሷ ሊባረክ ወዶ ያቺን ቆብ ሊወስዳት ፈለገ በየጊዜውም ሲወስዳት ወደቦታዋ ወደዚያ ገዳም ትመለሳለች እንዲህም ሦስት ጊዜ ሆነ ከዚህም በኋላ መውሰዱን ተወ።
ከብዙ ወራትም በኋላ እንደ ዛሬው ሁሉ በዚች ቀን አባ ሣሉሲ በዚሁ ገዳም በአረፈበት ቦታ ተገልጾ ተገኘ በክብርም ገንዘው ቀበሩት።


አቡነ አብሳዲ አጽፋቸውን እንደጀልባ ተጠቅመው የኢያሪኮን ባሕር የተሻገሩት የታላቁ ጻድቅ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባሕር ደቀ መዝሙር ናቸው፡፡ የደብረ ክሳሄው አቡነ አብሳዲ ገድላቸውን የፈጸሙት ኤርትራ ውስጥ ነው፡፡
አቡነ ኤዎስጣቴዎስን ጌታችን በቃሉ ጠርቶ ‹‹በላይህ ላይ ያለውን ቅዱስ መንፈስ በወዳጅህ በልጅህ አብሳዲ ላይ አሳድር፣ ሙሴ የራሱን መንፈስ በነዌ ልጅ በኢያሱ ላይ እንዳሳደረ፣ ኤልያስም በረድኡ በኤልሳዕ ላይ እንዳሳደረ›› አላቸው፡፡ ምክንያቱም ልጆቻቸውን ትተው ወደ ኢየሩሳሌም ከዚያም ወደ አርማንያ እንዲሔዱ ነግሯቸዋልና ነው፡፡ አባታችንም ልጃቸውን አቡነ አብሳዲን ሦስት ጊዜ ‹‹አብሳዲ አብሳዲ አብሳዲ›› ብለው ጠሩት፡፡ እርሱም አባቱን ‹‹አቤት ጌታዬ እነሆ ጠርተኸኛልና›› አለው፡፡ አባታችን ኤዎስጣቴዎስም ‹‹እነሆ በረከት ከሰማይ ለአንተ ተሰጠች፣ ይህችንም በረከት ብርንና ወርቅን የማይወዱ ራሳቸውንም ወደ ጠባብ በር ያስገቡ እንደ አንተ ካለ ጻድቃንና ከተመረጡት በቀር መቀበል የሚችል የለም፤ እነርሱም ሥጋቸውን አሳልፈው ለጻዕር ለጭንቅ የሰጡ ናቸው፤ ከተወለዱም ጀምሮ ጣፋጭ የሆኑ የምድር ምግቦችን ያልወደዱ ናቸው፣ ራሳቸውንም እንደምታልፍ ነፋስ ያደረጉ ናቸው፡፡›› አባታችን ኤዎስጣቴዎስም ይህንን ተናግረው በአብሳዲ ራስ ላይ እጃቸውን ጫኑ፡፡ ሙሴ በኢያሱ እንደጫነ፣ ያዕቆብም በይሁዳና በሌዊ ላይ እጁን ጭኖ ለመንግሥትና ለክህነት እንደባረካቸው ዮሴፍም ልጆቹን ኤፍሬምና ምናሴን ይባርካቸው ዘንድ ወደ አባቱ እስራኤል አምጥቷቸው እርሱም የተባረከና ቅዱስ ሕዝብ ያድርጋችሁ ብሎ እንደባረካቸው እንደዚሁም ሁሉ አባታችን ኤዎስጣቴዎስ ልጃቸውን አብሳዲን እንዲህ እያሉ ባረኩት፡- ‹‹የቀደሙ አባቶች በረከት፣ የነቢያትና የሐዋርያት በረከት፣ ድል የሚነሡ የሰማዕታት በረከትና በተጋድሎ የጸኑ የጻድቃን በረከት፣ የቅዱሳን መላእክት በረከት፣ ማኅበረ በኩር የተባሉ የሁሉም ቅዱሳን በረከት፣ አምላክን የወለደች የቅድስት ድንግል ማርያም በረከት፣ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ በረከት በአንተ ላይና በልጆችህ ላይ ይደር፤ መታሰቢያዬንና መታሰቢያህንም በሚያደርጉ ላይ ይደር ለዘለዓለሙ አሜን›› ብለው መባረክን ከባረኩት በኋላ አብሳዲን ግንባሩን ቀብተው አተሙት፡፡
አቡነ አብሳዲ ገዳማትንና ምንኵስናን ለማስፋፋት ብዙ የደከሙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ቀንና ሌሊት ሳያርፉ ምእመናን በማስተማር አባታቸው ኤዎስጣቴዎስ እንዳስተማሯቸው
ገዳማትንና ምንኵስናን በኤርትራና በኢትዮጵያ በማስፋፋት ለገዳማዊ ምናኔ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሐዋርያ ናችው፡፡ በመንፈስ የወለዷቸው በርካታ መነኵሳት ልጆቻቸው አማካኝነት በኢትዮጵያና በኤርትራ የተገደሙት ገዳማት ከ120 በላይ ናቸው፡፡
በልጆቻቸው አማካኝነት በኤርትራ ከተገደሙት ገዳማት ውስጥ፦ ደብረ ኮል አቡነ ብሩክ (መራጉዝ)፣ የአቡነ ዮናስ ገዳማት (ደብረ ድኹኻን ቆሓይን፣ ደብረ ጽጌ ትምዛእ፣ ደብረ ሣህል ዛይዶኮሎም)፣ ደብረ አቡነ ሙሴ (ማይ ጎርዞ)፣ ደብረ ሲና አቡነ ድምያኖስ፣ ምድሪ ወዲ ሰበራ፣ ደብረ ሐዋርያት አቡነ ሴት (ዓዲ ቂታ)፣ ደብረ ማርያም (ዓይላ) እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ እነኚህን እንደ ምሳሌ ጠቀስን እንጂ በኢትዮጵያም የአቡነ አብሳዲ ልጆች የመሠረቷቸው በርካታ ገዳማት አሉ፡፡
አባታችን የረጅም ዘመን ተጋድሏቸውን በፈጸሙ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኹለተኛ ጊዜ ተገልጦላቸው ‹‹በሰሜን ያለች ይኽችን ገዳም ባርኬልሃለውና ከልጆችህ ጋር በእርሷ
ኑር›› ካላቸው በኋላ ቃልኪዳን ገብቶላቸው ተሰወረ፡፡ ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ይኽችም ለአባታችን የተሰጠቻቸው ገዳም ደበረማርያም (ደብረ ክሳሄ) ናት፡፡
ከዚኸም በኋለ ቅዱስ አባታችን አብሳዲ ደከመኝ ልረፍ ሳይሉ መላ ዘመናቸውን ሐዋርያዊ ተልዕኳቸውን ፈጽመው ከእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ተቀብለው በ101 ዓመታቸው መስከረም 30 ቀን 1383 ዓ.ም ዐርፈው ቆሓይን በምትገኘው ገዳማቸው ደብረ ክሳሄ ደብረ ማርያም ገዳም ተቀበሩ፡፡

አቡነ ገሪማ የተወለዱት በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሮም ውስጥ ነው። ወላጆቻቸው መስፍንያኖስ እና ሰፍንግያ እግዚአብሔርን የሚወዱ የሮም ከተማ ንጉሥና ንግሥት ነበሩ። ልጅ በማጣታቸው እመቤታችንን ለመኑ።
እመ ብርሃንም ደግ ፍሬ ሰጠቻቸው። ስሙን ይስሐቅ ብለው አሳደጉት። ገና በልጅነቱ አባቱ ድንገት በመሞቱ ይስሐቅ በዙፋኑ ተተክቶ ነገሠ። ለሰባት ዓመታት ሕዝቡን በፍትሕ እያስተዳደረ መጻሕፍትንም እያጠና ኑሯል።
አንድ ቀን ግን ከግብጽ በርሃ የተላከ ደብዳቤ ደረሰው። ላኪው አባ ጰንጠሌዎን ሲሆኑ መልዕክቱ "ምድራዊ ንግሥና ምን ያደርግልሃል? ይልቁኑስ በሰማይ ለዘላለም እንድትነግሥ ወደ በርሃ ና!" የሚል ነበር።
ንጉሥ ይስሐቅ አላመነታም ሌሊት ተነስቶ ወደ ፈጣሪው ጸልዮ በለበሳት ልብስ ብቻ ዙፋኑን ጥሎ መነነ። ድንገት ግን ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ በቀኝ ክንፉ ነጥቆ ግብጽ አባ ጰንጠሌዎን በዓት ላይ አኖረው።
እርሳቸውም ተቀብለው ፍኖተ አበውን አስተምረው አመነኮሱትና ዘጠኝ ሁነው ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ተስዓቱ ቅዱሳን በሃገራችን ብዙ ሲሰሩ አንዱና ታላቁ አባ ይስሐቅ (ገሪማ) ናቸው። ሰውነታቸውን በገድል ቀጥቅጠውት ቆዳና አጥንታቸው ተጣብቆ ነበር።
አንድ ቀን አባ ይስሐቅ በልቶ ቀደሰ ብለው ነግረዋቸው አባ ጰንጠሌዎን አዘኑ። ልምከር ብለው "ልጄ ይስሐቅ የሰማውብህ ነገር አለና ሰዎችን አርቅልኝ።" አሉ። አባ ይስሐቅ ግን "ሰዎች ብቻ አይደሉም፤ ዛፉም እንጨቱም ገለል ይበል።" ቢሉ የቤተ ክርስቲያኑ አጸድ አንድ ምዕራፍ (ሁለት መቶ ሜትር) ተጠራርጎ ሸሸ።
ይህንን የተመለከቱት አባ ጰንጠሌዎን "ወልድየ ይስሐቅ ገረምከኒ (ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ)።" አሏቸው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮም "አቡነ ገሪማ" ተብለው ቀሩ።
አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሲሔዱ እነዚያ የሸሹ ዛፍና ድንጋዮች "ገሪማ ለእኛም ግሩም ነህ።" እያሉ በዝማሬ ተከትለዋቸዋል። ይህም የተደረገው በዚህች ዕለት መስከረም ፴ ቀን ነው።
ጻድቁ ወንጌልንና ገዳማትን ከማስፋፋት ባለፈ ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል፦
፩. ስንዴ ጧት ዘርተውት በዘጠኝ ሰዓት ያፈራ ነበር። "በጽባሕ ይዘርዕ ወበሠርክ የአርር" እንዲል።
፪. ጧት የተከሉት ወይን በዘጠኝ ሰዓት ያፈራ ነበር።
፫. አንድ ቀን ምራቃቸው ቢወድቅ ጠበል ሆኖ ዛሬም አለ።
፬. ብዕራቸው ወድቃ አብባ አፍርታለች።
፭. አንድ ቀን ድርሳን እየደረሱ ሊመሽ በመሆኑ ፀሐይን አቁመዋታል።
ከእነዚህ ሁሉ ዘመናት በኋላ ጌታችን ተገልጦ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ሰጣቸው። "ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገ እስከ አሥራ ሁለት ትውልድ እምርልሃለሁ። አንተ ግን ሞትን አትቀምስም።" ብሏቸው ተሰወረ። ያን ጊዜ መላእክቱ በሠረገላ ጭነው እየዘመሩ ብሔረ ሕያዋን አድርሰዋቸዋል።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages