ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 6 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 15, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 6

 

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ስድስት በዚህች ቀን እመ ሳሙኤል ነቢይ #ቅድስት_ነቢይት_ሐና ያረፈችበት፣ ቅዱስ አባት #አባ_ጰንጠሌዎን ያረፈበት፣ #ዕንባቆም_ነቢይ መታሰቢያው፣ የሀገረ አቴና ኤጲስቆጶስ #ቅዱስ_ዲዮናስዮስ በሰማዕትነት ያረፈበት እና የሴት ልጅ #ቅዱስ_ሄኖስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።
 
 

 
ጥቅምት ስድስት በዚህች ቀን የታላቁ ነቢይና ካህን የሳሙኤል እናት ቅድስት ነቢይት ሐና አረፈች።
ይችም ቅድስት ከሌዊ ነገድ ናት የታኅርም ልጅ ሕልቃና አገባት ፍናና የምትባልም ሌላ ሚስት አለችው እርሷም ወላድ በመሆኗ ሐና ልጅ ስለሌላት መካንም ስለሆነች ሁልጊዜ ትገዳደራት ነበር።
ሐና ግን ፈጽማ በማዘን አትበላም አትጠጣም ባሏ ሕልቃናም ያረጋጋታል ማረጋጋቱንም አልተቀበለችውም በሊቀ ካህናቱ በኤሊ ዘመንም ወደቤተ እግዚአብሔር ወጣች እያለቀሰችና እያዘነች በእግዚአብሔር ፊት ጸለየች እንዲህም ብላ ስለትን ተሳለች አቤቱ ልጅ የሰጠኸኝ እንደሆነ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለአንተ የሚያገለግል አደርገዋለሁ።
ካህኑ ኤሊም አያትና እርሷ የወይን ጠጅ ጠጥታ እንደ ሰከረች አሰበ እርሷ በዝምታ በልቧ ትጸልይ ነበርና በቊጣና በግሣጼ የወይን ጠጅ ጠጥተሽ ወደዚህ ወደ እግዚአብሔር ቤት ለምን መጣሽ አሁን ሒጂ ስካርሺን በእንቅልፍ አስወግጂ አላት።
እርሷም እንዲህ አለችው የወይን ጠጅ ከቶ አልጠጣሁም ልጅ ያጣሁ በመሆኔ በልቤ አዝናለሁ እንጂ ካህን ኤሊም አጽናናት እንዲሁም ብሎ ባረካት የእስራኤል ፈጣሪ የለመንሽውን ይስጥሽ በሰላም ሒጂ በቃሉም አምና ወደ ቤቷ ገባች።
ከዚህም በኋላ ፀንሳ ወንድ ልጅን ወለደች ስሙንም ሳሙኤል ብላ ጠራችው። ጡትንም በአስጣለችው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዛው ወጣች ወደ ካህን ኤሊም አቀረበችውና እንዲህ ብላ አስረዳችው ከአሁን በፊት ልጅን ይሰጠኝ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ስጸልይና ስለምን ያየኸኝ ሴት ነኝ ልመናዬንም ሰምቶ ይህን ልጅ ሰጠኝ አሁንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር አገልጋይ ይሆን ዘንድ አመጣሁት።
ከዚህም በኋላ ሐና እግዚአብሔርን አመሰገነችው። ልቤ በእግዚአብሔር አምኖ ጸና የሚለውን ጸሎትና ትንቢት እስከ መጨረሻው ተናገረች። ይቺም በዳዊት መዝሙር መጨረሻ ከሙሴ መኀልይ ቀጥላ ተጽፋለች።
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔርን አገልግላ በሰላም አረፈች።
 
 
 
ዳግመኛም በዚችም ቀን በዋሻ ውስጥ የሚኖር ቅዱስ አባት አባ ጰንጠሌዎን አረፈ። ይህም ቅዱስ በሮሜ አገር በንጉሥ ቀኝ ከሚቀመጡ ከከበሩ ሰዎች ወገን የተወለደ ነው ። በታናሽነቱም ጊዜ ወደ መነኰሳት ገዳም ወስደውት በበጎ ምክር ዕውቀትን እየተማረ በመጸለይና በመጾም በዚያ አደገ።
ከዚህም በኋላ ከቅዱሳን ከስምንቱ ባልንጀሮቹ ጋር ወደ ኢትዮጵያ በንጉሥ አልዓሜዳ ዘመን መጣ በአንድነትም ጥቂት ዘመናት ኑረው ከዚህም በኋላ እርስበርሳቸው ተለያዩ ቅዱስ ጰንጠሌዎንም ከታናሽ ተራራ ላይ ወጥቶ ርዝመቱ አምስት ክንድ አግድመቱ ሁለት ስፋቱ ሦስት ክንድ የሚሆን ዋሻ ለራሱ ሠራ ጠፈሩም አንድ ደንጊያ ነው ከጥቂት ቀዳዳ በቀር በር የለውም።
በውስጡም ሳይቀመጥ ሳይተኛ ያለመብልና ያለ መጠጥ አርባ አምስት ዓመት ኖረ ቆዳው ከዐጥንቱ እስከሚጣበቅ በዕንባ ብዛትም ቅንድቡ ተመለጠ። በሽተኞችን በማዳን የዕውሮችንም ዐይኖች በመግለጥ ብዙ ተአምራትን አደረገ።
በአንዲትም ቀን በማታ ጊዜ ዕንጨት ተከለ አሰከሚነጋ ድረስም አድጎ ትልቅ ዛፍ ሆነ ወዲያውም ደረቀና ደቀ መዝሙሩ ፈልጦ አነደደው ፍሙንም በልብሱ ቋጥሮ ለማዕጠንት ወሰደው።
የናግራንን አገር ያጠፋትን ምእመናኖችንም የገደላቸውን አይሁዳዊ ንጉሥ ሒዶ ሊወጋው ንጉሥ ካሌብ በአሰበ ጊዜ በጸሎቱ ይረዳው ዘንድ ይህን አባት ጰንጠሌዎንን ለመነው እርሱም በሥራው ሁሉ ላይ ችሎታ ያለው እግዚአብሔር በጠላቶችህ ላይ ድል አድራጊነትን ሰጥቶህ በደኀና በፍቅር አንድነት ትመለሳለህ አለው።
ንጉሥ ካሌብም ከናግራን ሀገር በደረሰ ጊዜ ከከሀዲው ንጉሥ ከፊንሐስ ጋር ተዋጋ ድል አድርጓቸውም ከሀድያንን ሁሉ እንደ ቅጠል እስቲረግፉ አጠፋቸው አባ ጰንጠሌዎንንም በጦርነቱ መካከል ጠላቶችን ሲአሳድዳቸው እንዳዩት ብዙዎች ምስክሮች ሆኑ።
ከዚህም በኋላ ንጉሥ ካሌብ ከድል አድራጊነት ጋር በተመለሰ ጊዜ መንግሥቱን ትቶ በዚህ አባት እጅ መነኰሰ ከዋሻ ውስጥም ገብቶ በጾምና በጸሎት እየተጋደለ ኖረ።
ይህም ቅዱስ አባ ጰንጠሌዎን ተጋድሎውን በፈጸመ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ መጣ ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን የሚያደርግ ገድሉንም ለሚጽፍ ቃል ኪዳን ሰጠው እንግዲህስ ድካም ይበቃሀል ዕረፍ ያን ጊዜም ዐጥንቶቹ ተነቃነቁ በፍቅር አንድነትም አረፈና በዚያ በዋሻው ውስጥ ተቀበረ።
 
 
በዚችም ቀን የስሙ ትርጓሜ አዋቂ የሆነ የዕንባቆም ነቢይ መታሰቢያው ነው። ይህም ቅዱስ በአንዲት ዕለት እህሉን ለሚያጭዱለት ምሳቸውን አዘጋጅቶ ተሸክሞ ሲሔድ መልአክ ተገልጾለት ይህን መብል በባቢሎን አገር በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ ላለ ለነቢዩ ዳንኤል ውሰድ አለው።
ዕንባቆምም ጌታዬ ሆይ ባቢሎንን አላየኋት ጉድጓዱንም አላውቀው አለው። የእግዚአብሔር መልአክም በራሱ ጠጉር ያዘው ምግቡን በእጁ እንደያዘ ወሰደውና ጉድጓዱ እንደተዘጋ አስገባው ምግቡንም ሰጥቶ መገበው ወዲያውኑ ዕንባቆምን ወደ ይሁዳ አገር መለሰው።
በአረጀና በሸመገለም ጊዜ የእስራኤል ልጆች ከተማረኩበት ተመልሰው ቤተ መቅደስን ሠሩ። ዕንባቆምም ኢየሩሳሌም ደርሶ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ በታላቅ ደስታም ተቀበሉት ትንቢቱንም ሊሰሙ ወደርሱ ተሰበሰቡ አፉንም ከፍቶ በመንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለ።
አቤቱ ድምፅህን ሰማሁ ሰምቼም ፈራሁ ሥራህንም አይቼ አደነቅሁ አለ። ስለ መድኃኒታችንም መውረድና በይሁዳ ክፍል በሆነች በቤተ ልሔም ስለመወለዱ ሲናገር የተመሰገነ እግዚአብሔር ግን ከፋራን ተራራ ከቴማን ከይሁዳ አውራጃ ይመጣል ብሎ እስከ መጨረሻው ተናገረ ከነቢያት መጻሕፍትም ጋራ ደመርዋት።
ከዚህ በኋላ ከእስራኤል ልጆች አንዲት ሴት ወደርሱ መጣች እያለቀሰችም እንዲህ አለችው። ሁለት ልጆች ነበሩኝ ጣዖት እንዲአመልኩ ፈለጉአቸው እምቢ በአሉ ጊዜም ገድለው በጐዳና ላይ ጣሉአቸው። ተገድለው ወደ አሉበትም አብሮዋት ሔደ ነፍሳቸውንም ይመልስላቸው ዘንድ እግዚአብሔርን ለመነው ልመናውንም ተቀበሎ በሕይወት አነሣቸው።
ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ ዘመዶቹን ጠራቸው። እንደሚሞትም ነገራቸውና አንዲት ሰዓት ያህል ወደላይ እየተመለከተ ተቀመጠ ። እነሆ እንደ ሰው ክንድ ያለች ታላቅ ክንድ የቤቱን ጣሪያ ሠንጥቃ ወረደች ወደ አፉም ተዘርግታ ነፍሱን ወሰደች ያን ጊዜም አረፈ።
በክርስቲያናዊ ንጉሥ በአንስጣስዮስ ዘመን እንዲህ ሆነ ገድሉን በአነበበ ጊዜ አድንቆ በግብጽ ደቡብ ቀርጣስ በሚባል ቦታ በስሙ ቤተ ክርስቲያን ተሠራለት።
 
 
በዚችም ቀን የሀገረ አቴና ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ዲዮናስዮስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ በአቴና አገር በእውቀቱና በመራቀቁ የከበረና ከፍ ከፍ ያለ ነው። በአቴናው ከተማ በዐዋቂዎች የመሳፍንት አንድነት ከአማካሪዎች አንዱ እርሱ ነው።
ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስም ወደዚያ በደረሰ ጊዜ ሃይማኖትን አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጥምቆ በአቴና አገር ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾመው።
ብዙ ድርሳናትንም ደረሰ ከእርሳቸውም አንዱ ክብር ይግባውና ስለ መድኃኒታችን ስቅለት የደረሰው በዕለተ ዐርብ የሚነበብ አንዱ ነው።
የእምነቱም ምክንያት እንዲህ ነው ከዕለታት በአንዱ በፍልስፍናው ቤት ተቀምጦ ሳለ የአቴናም ፈላስፎች በእርሱ ዘንድ ተሰብስበው ነበር እርሱ ለሁሉም አለቃ ስለሆነ በዐርብ ቀንም ቀትር ሲሆን ፀሐይ ጨለመ ታላቅ ንውጽውታም ሆነ አሕዛብ ሁሉ ደንግጠው እጅግ ፈሩ ቅድስ ዲዩናስዩስንም በዓለም ውስጥ የሆነውን ጌታችን ሆይ አስረዳን ብለው ጠየቁት።
አርሱም ፀሐይን ጨረቃንና ከዋክብትን መረመረ ጸጥ ብለው አገኛቸው ደግሞ ባሕሮችን ትልቁንም በዓለም ዙሪያ ያለውን የውቅያኖስን ባህር መረመረ እሱንም ጸጥ ብሎ አገኛው።
ከዚህም በኋላ አርስጣላባ የሚባል የፍልስፍና መጽሐፍን አንስቶ ሲመረምር በውስጡ እልመክኑን የሚል አገኘ ይህም ኀቡእ አምላክ ወረደ ወገኞቹም በእርሱ ላይ ተነስተው ሰቀሉት ማለት ነው በዚያችም ጊዜ ልብሱን ቀዶ ታላቅ ሀዘንን አዘነ ከበታቹ ምሁራን ያየውን ያስርዳቸው ዘንድ ለመኑት እርሱም ሁሉን ነገራቸው እነርሱም ይህን ሰምተው ታላቅ ፍርሃት ፈሩ።
ደቀ መዝሙሩ ኡሲፎስንም የሆነውን ሁሉ የዚያችንም ቀን ስሟን ሰዐቷን ወርዋን ዘመኑንም እንዲጽፍ አዘዘው ዳግመኛም በጣዖታቱ ቤቶች በደጃፋቸው እልመክኑን እያሉ እንዲጽፉ አዘዘ።
ከዐሥራ አራት ዓመትም በኋላ ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ ወደ አቴና አገረ መጣ ክብር ይግባውና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መውረዱን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከስጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ መወለዱን መከራ መቀበሉን መሰቀሉንና መሞቱን በሶስተኛው ቀን መነሳቱን ማረጉንም በሕያዋንና በሙታን ለምፍረድ ዳግመኛ መምጣቱን አስተማረ።
የአቴና ሰዎችም የሐዋርያዉን ስብከት በሰሙ ጊዜ እጅግ አደነቁ ወደ ዲዩናስዩስም ሩጠው እንዲህ ብለው ነገሩት አንድ ሰው ዛሬ ወደ አገራችን መጥቶ እኛ የማናውቀውን ወይም ከእኛ በፊት የነበሩ አባቶቻችን የማያውቁትን በአዲስ አምላክ ስም አስተማረን።
ዲዮናስዮስም ልኮ ሐዋርያ ጳውሎስን ወደርሱ አስመጥቶ በሀገራችን ውስጥ በአዲስ አምላክ ስም የምታስተምረው ምንድን ነው አለው።
ቅዱስ ጳውሎስም በአደባባያችሁ መካከል አልፌ ስሔድ በአማልክቶቻችሁ ቤቶች በደጃፋ ላይ እልመክኑን የሚል ጽሑፍ አየሁ ይህም የማይመረመር አምላክ ወረደ ማለት ነው እኔም ለእናንተ የምሰብከው ይህንኑ ነው ብሎ መለሰ።
በዚያንም ጊዜ ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት ያጻፈውን ያን መጽሐፍ ያመጣው ዘንድ ኡሲፎስን አዘዘው ሁለተኛም ጊዜውንና ወራቱን ሐዋርያውን ጠየቀው እርሱም በመጋቢት ወር በሃያ ሰባት ዓርብ ቀን በስድስት ሰዓት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርሶቶስ ያን ጊዜ እንደ ተሰቀለ ፀሐይም እንደ ጨለመ ምድርም እንደተናወጠች አስረዳው።
የአቴና ሰዎችም ይህን በስሙ ጊዜ ከቅዱስ ዲዮናስዮስ ጋር ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ዲዮናስዮስንም በእነርሱ ላይ ኤጲስቆጶስን አድርጎ ሾመው የቤተ ክርስቲያንንም ሥርዓት የተረጐመ እርሱ ነው።
ከዚህም በኋላ በባሕር አቅራቢያ ወደ አለ አገር በመሔድ በሐዋርያት ዘመን አስተማረ ብዙ ወገኖችንም ክብር ይግባውና በጌታችንም አሳመነ ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራትን አደረገ።
ከሀዲ ንጉሥ ጠማትያኖስም ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሰቃየው ከዚያም የከበረች ራሱን በሰይፍ ቆረጠው የተቆረጠች ራሱንም በእጁ ይዞ ሁለት ምዕራፍ ያህል ጐዳና ተጓዘ ሁለተኛም የደቀ መዛሙርቱን የኡሲፎስንና የኡርያኖስን ራሳቸውን ቆረጠ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።
 
 
በዚችም ቀን የሴት ልጅ የሄኖስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው የእግዚአብሔርንም ስም መጥራት የጀመረ ይህ ሄኖስ ነው። ሄኖስም መቶ ዘጠና ዓመት ኖረ ቃይናንም ወለደው ቃይናንንም ከወለደው በኋላ ሰባት መቶ አሥራ አምስት አመት ኖረ ወንዶች ልጆችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ በቅዳሜ ቀንም አረፈ። መላ ዕድሜውም ዘጠኝ መቶ አምስት ነው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages