ጻድቁ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 15, 2022

ጻድቁ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ

 


‹‹የለመንከኝን ሁሉ አደርግልህ ዘንድ ቃል ኪዳንን ሰጥቼሃለሁ››
ለሰማንያ ዓመት በጫካ ውስጥ ከአንበሶችና ከነብሮች እንዲሁም ከአራዊት ጋር መኖርን ሳይፈሩ እስከ ሞት ድረስ የታገሡ እንዲሁም በዝቋላ ተራራ ባለው ባሕር ውስጥ መቶ ዓመት ተዘቅዝቀው ለኢትዮጵያ ሰዎች ምሕረትን የለመኑ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቃል ኪዳን የተቀበሉበትን ጥቅምት አምስት ቀን እናከብር ዘንድ ይገባል፡፡
በሀገረ ግብጽ የተወለዱት ጻድቁ አባት የእግዚአብሔር ትእዛዝ ሆኖ ስለ ኢትዮጵያ ይለምኑና ይማልዱ ዘንድ ፈቃዳቸውም ስለነበር ቤተሰቤ፣ ሕዝቤ ወይንም ሀገሬ ሳይሉ ወደ ሀገራችን በመምጣት በጭንቅላታቸው ተዘቅዝቀው ደማቸው ፈሶ እስኪያልቅና ሥጋቸውም አልቆ አጥንቶቻው እንደበረዶ እስኪሆን ድረስ የጸለዩ ታላቅ አባታችን ናቸው፡፡
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በተወለዱበትም ቤት አልኖሩምና እናት አባታቸው የሥጋ ዘመዶቻቸውም አላወቋቸውም፡፡ በበረሃ ብቻቸውን ኖሩ እንጂ፡፡ ነገር ግን ሰማያውያን ሁሉ ወዳጆቻቸው ሆኑ፤ እመቤታችን ወዳጄ ትላቸዋለች፡፡ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ወገናችን ይሏቸዋል፡፡ መላእክትም ወዳጃችን እያሉ በክንፋቸው ያቅፏቸዋል፡፡ የአባታችን መዓዛቸው ጫካውን ይሞላው ነበር፡፡ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል ወደፈለጉት ቦታ በፍጥነት እንደወፍ ይበራሉ፡፡ ስለተሰጣቸውም ጸጋ የበረሃ እንስሳት (አንበሳና ነብር) ሁሉ ያገለግሏቸዋል፡፡ አባታችን ሁልጊዜ እንዲህ ይሉ ነበር፡፡ ‹‹የሚጣፍጥ ምግብን መውደድ ኃጢአትን ያመጣል፤ ሞትን ያስከትላል፡፡ ክንፍ ያላቸው የሰማይ ወፎች እንኳን በመብል ምክንያት ይጠመዳሉ፤ ምግብ በመሻት ከምድር ላይ ይወድቃሉ፤ በወጥመድም ይያዛሉ፡፡ የሰው ልጅም ምግብን በመውደድ በኃጢአት ይወድቃልና እኔስ ለሰውነቴ ምግብ መጠጥን አልፈልግም፤ ልብስም አልሻም፤ ዕራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን እንደወጣሁ እንዲሁ ዕረቁቴን ወደ መቃብር እመለሳለሁ እንጂ፡፡ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም በሞት በተለየሁ ጊዜ መብል መጠጥንና ልብስን ማን ያስከትልልኛል?›› አሉ፡፡
ዳግመኛም ‹‹ሰው ሊደርስ በማይችልበት በረሃ እኖራለሁ፣ ነጣቂ ተኩላዎችና አራዊቶች ባሉበት እነርሱ እንዲበሉኝ ሥጋዬን እጥላለሁ፤ ዳዊት በመዝሙር ‹‹የጻድቃን ሥጋቸው ለዱር አራዊት ነው›› እንዳለ እኔ ክፉ አውሬዎች፣ ተናዳፊ እባቦችና ዘንዶዎች ወዳሉበት እገባለሁ፤ ምግብም እሆናቸው ዘንድ እወዳለሁ›› በማለት አባታችን ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ይሰጡ ነበር፤ ነገር ግን አራዊቱ ሁሉ እየሰገዱላቸው ይገዙላቸው ከእግራቸውም በታች ይተኙ ነበር፡፡ እንደሚታዘዝ ደቀ መዝሙርም ይታዙላቸው ነበር፤ ለጸሎትም በሚቆሙበት ጊዜ አብረዋቸው ይቆማሉ፡፡ በፊታቸውም ይጫወታሉ፡፡ በአንደኛው ዕለት አባታችን ጸሎታቸውን እንደጨረሱ ሰማይ ተከፍቶ የእሳት ድንኳን ተገልጦ አርባእቱ እንስሳ የእግዚአብሔርን ዙፋን ተሸክመው ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ ማዕጠንት ይዘው፣ ቅዱሳን መላእክትና አለቆቻቸው በየነገዳቸው በዙሪያው ቆመው ጌታችን ለአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአንድነት በሦስትነት እንዳለ ተገለጠላቸው፡፡ አባታችንም ይህንን ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተውና ደንግጠው መሬት ላይ ወደቁ፡፡ ጌታችንም ካጸናቸውና ካበረታቸው በኋላ ‹‹ዮሐንስ ቀለምሲስእኔን እንዳየኝ አንተም እኔን ማየት የምትችልበትን ኃይል እሰጥሃለሁ፤ ወዳጄ ሆይ
ምን ትሻለህ? የምትጠይቀኝስ ነገር ምንድነው? ልይህ ብለህ በለመንከኝ ጊዜ ተገልጥኩልህ፡፡ ሰማንያ ዓመት በጫካ ኖርክ፤ በረሃዎችን ዞርክ፤ ከአንበሶችና ነብሮች ከአራዊትም ጋር መኖርን አልፈራህም፤ ጨክነህ እስከ ሞት ድረስ ታገሥህ፡፡ የመረጥኩህ ወዳጄ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ምን አደርግልህ ዘንድ ትወዳለህ?›› አላቸው፡፡ አባታችንም ይህንን ቃል ከጌታችን ሲሰሙ ‹‹አምላኬ ሆይ ይህን ልታደርግልኝ አይገባኝም፡፡ በፊትህስ ሞገስን ካገኘሁ የገቦታን ሰዎች ማርልኝ፤ እነርሱ ኃጥአን ናቸውና አንተ ንስሓን ለማይሹ ጻድቃን አልመጣህምና ኃጥአንን ወደ ንስሓ ልትመልስ ነው እንጂ›› አሉት፡፡ ዳግመኛም ‹‹አቤቱ እንደ ክረምት ውኃ እንባቸውን እያፈሰሱ ጥርሳቸውን እያፋጩ በደይን የሚኖሩትን አስባቸው፤ ሰይጣን አስቷቸዋልና፤ በማወቅ ባለማወቅ በሠሩት ማራቸው፤ ይቅር በላቸው›› እያሉ ለመኑት፡፡ ጌታችንም ‹‹ወዳጄ ሆይ የለመንከኝን አልከለክልህም፣ እንደቸርነቴም ስምህን የጠሩትን መታሰቢያህን ያደረጉትን ኃጥአንን ምሬልሃለሁ፤ የለመንከኝንም ሁሉ አደርግልህ ዘንድ ቃል ኪዳንን ሰጥቼሃለሁ›› አላቸው፡፡ አባታችንም እጅግ ደስ ብሏቸው በግንባራቸው መሬት ላይ ወድቀው ጌታችንን ሲያመሰግኑት ቅዱሳን መላአክትና ሰማያውያን ቅዱሳን ሁሉም አብረው ተደስተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡
አባታችንም ይህንን ቃልኪዳን ሲቀበሉ ዕድሜአቸው ሦስት መቶ ዓመት ነበር፡፡ ጌታችንም የመላእክት አለቆችን ‹‹ስለ ወዳጄ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምልጃ ወደ ገሃነም ሂዱና የኃጥአንን ነፍስ አውጡ፤ ከእስራታቸውም ፍቱአቸው›› አላቸውና እነርሱም የገቦታ ሰዎችን ሦስት ሺህ ነፍሳት ከደይን አውጥተው ወደ ገነት አገቧቸው፡፡ ዳግመኛም እግዚአብሔር አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ‹‹እንደ አንተ ካሉት ሰዎች በቀር በዓለም ያሉ ሰዎች እንዳያውቁህ አደርጋለሁ፤ መላእክት ይጎበኙሃል እንጂ ከካህናት፣ ከመነኮሳት፣ ከምእመናንም ወገን ቢሆን ምንም ያለ ፈቃድህ አያይህም፡፡ ወደጄ ሆይ እንደ ወደድህም እኔን አባቴንና መንፈስ ቅዱስን በሦስትነቴ አየኸኝ፡፡ አሁንም ወደ ኢትዮጵያ ሂድ፤ በዚያም ከደይን የምታወጣቸው ነፍሳት አሉ›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹አምላኬ ሆይ ወደዚያች አገር ማን ያደርሰኛል?›› አሉት፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹እኔ በሥልጣኔ አደርስሃለሁ›› ካላቸው በኋላ ከእርሳቸው ተሰወረ፡፡
አባታችንም የገቦታ ሰዎች ምሕረትን ሲያገኙ አይተው እጅግ ተደሰቱ፡፡ በሌላም ጊዜ አባታችን አራት ሺህ እልፍ እየሰገዱ፣ ሦስት መቶ) ጊዜ የቀኝ ሦስት መቶ ጊዜ ደግሞ የግራ ፊታቸውን በድንጋይ እየመቱ፣ መዝሙረ ዳዊትን እየደገሙ፣ ዐሠራ አምስቱን መኅልየ ነቢያት፣ መኅልየ ሰለምንንና ውዳሴ ማርያም እየጸለዩ ለኃጥአን ምሕረትን ሲለምኑ ዕንባቸው እንደ ውኃ ይፈስ ነበር፡፡ ጌታችንም ‹‹በተወለድሁባት፣ በተጠመቅሁባትና ከሞት በተነሣሁባት ዕለት እልፍ እልፍ ነፍሳትን እምርልሃለሁ›› አላቸው፡፡
ከዚህም በኋላ አባታችን ስድሳ አንበሶችና ስድሳ ነብሮች እየተከተሏቸው ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ብርሃናዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ከእነዚሁ ተከታዮቻቸው ጋር በነፋስ ሠረገላ ጭኖ ምድረ ከብድ አደረሳቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹ደብር ቅዱስ›› ወደሚባለው ወደ ዝቋላ ወሰዳቸው፡፡ አባታችን በባሕሩ ቁሞ ምሥራቁን፣ ምዕራቡን ሰሜኑን፣ ደቡቡን ዐራቱን ማዕዘን ተመለከተ፡፡ የኢትዮጵያ ሰዎች የሚሠሩትን ኃጢአታቸውን በዐይኖቹ ፊት የተፈለጠ ሆኖ አየ፡፡ በራሱም ተዘቅዝቆ ተወርውሮ ወደ ባሕሩ ውስጥ ገባ፤ ‹‹እነዚህን የእጅህ ፍጥረቶች የሆኑትን ካልማርካቸው ከዚህ ባሕር እንዳልወጣ በእግሮቼም እንዳልቆም በሕያው ስምህ እምላለሁ›› እያለ ማለ፤ እንዲህም ሆኖ ዐርባ ቀን ዐርባ ሌሊት ኖረ፡፡ ‹‹ስምህን የጠራውን መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ›› የሚል ቃል በመልአክ አማካኝነትም ወደ አባታችን መጣ፡፡ አባታችንም መልአኩን ‹‹መላውን የኢትዮጵያ ሰው ካልማረልኝ ከዚህ ባሕር አልወጣም›› አለው፡፡ መልአኩም ከአጠገቡ ሄደ፤ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስም በዚያ ባሕር ውስጥ መቶ ዓመት ኖረ፤ሥጋው ሁሉ አለቀ፤ ደሙም በባሕሩ ውስጥ ፈሰሰ፤ አጥንቶቹም እንደ በረዶ ነጭ ሁነው ታዩ፡፡ አጋንንትም ከዐራቱ ማእዘን በየቀኑ ሰባት መቶ ሺህ ሦስት መቶ ሽህ እየሆኑ በመምጣት በቀስታቸው ይነድፉታል፤እስከ መቶ ዓመትም አጥንቶቹን በሻፎ ድንጋይ ይፍቁታል፤ይህን ሁሉ መከራ በትዕግሥት ሲቀበል ኖረ፡፡
ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ መጥቶ ከባሕሩ ዳር ቆመ፤ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስንም ‹‹መላውን የኢትዮጵያን ሰው ምሬልሃለሁና ተነሥተህ ውጣ›› አለው፡፡ ያንጊዜም ወጣ፤ አጥንቶቹም እንደ ወንፊት ቀዳዳ የተበሳሱ ሁነው ተገኙ፤ጌታም ዳሠሠውና ጠነኛ አደረገው፤ ወደ ምዳረ ከብድም ሰደደው፡፡
ከዚያ በኋላ ወደ ላይ ወጥቶ ከፀሐይ በላይ ከሰማይ በታች እስከ ሰባት ዓመት ኖረ፡፡ ዳግመኛም ወደ ምድረ ከብድ ተልኮ እንደ ዓምድም የተተከለ ሆኑ ሳባት ዓመት ቁሞ ኖረ፡፡ ወደ ሰማይም ሲመለከት ቅንድቦቹን አልከደነም፤ራሱንም ወደ መሬት ዝቅ አላደረገም ነበር፤ እጆቹም ወደ ሰማይ ያንጋጠጡ ሁነው አገኛቸው፤ በራሱ ላይም ተቀምጦ ሁለቱን ዐይኖቹን አንቊሮ አሳወረው፡፡ እርሱ ግን ምንም ሳያጓድል እንደ ቀድሞው በመትጋት ሲጸልይ ኖረ፡፡
ከዚህ ዓለም የሚለይበት በቀረበ ጊዜ እነሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነሆ ተገለጠለት፡፡ ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውንም ለሚያደርግ እስከ ዐሥራ አምስት ትውልድ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡የዕድሜውም ዘመናት አምስት መቶ ስድሳ ሁለት ሲሆን በሰላም በፍቅር ዐረፈ፤ጌታችንም ነፍሱን ተቀበለ፤ አቅፎም ሳማት፤ በመላእክትና በቅዱሳን ሁሉ ምስጋና አሳረጋት፡፡
 
ጥቅምት 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ
2.ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ (ዻዻስ ወሰማዕት)
3.ቅድስት ሐና ሰማዕት (እናቱ)
4.ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
5.አባ ዻውሎስ ሰማዕት (አርዮሳውያን አንቀው የገደሉት አባት)
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
3.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
4.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
5.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)
 
 ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት: እኔም
ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ
መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ:: በክርስቶስ
ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ
ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና::  (ገላ. 6:14)
       
               ወስብሐት ለእግዚአብሔር
 
የጻድቁ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤አሜን፡፡
ምንጭ፡ – ገድለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ተስፋ ገብረሥላሴ ፲፱፻፺፪ዓ.ም

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages