ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ: ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 22, 2022

ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ: ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም

ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ


 
ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም

አዲስአበባ -ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚያካሂድ ይታወሳል፡፡ይኸውም በወርኃ ጥቅምትና ግንቦት ነው፡፡ በእነዚህ ወራት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምልዓተ ጉባኤውን በማካሔድ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁለንታዊ ጉዳዩች ወይም መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ላይ በመምከር ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ ይታወቃል።
ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያካሒዳቸው እነዚህ ጉባኤያት በተረጋጋ፣ በሰከነና በተሳካ መልኩ መካሔድ ይችላሉ ዘንድ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተለይም በተለምዶ ጉባኤው በሚካሔድበት ወቅት ልዩ ልዩ አቤቱታዎችን ሕጋዊውን አሠራር ባልጠበቀ መልኩ በግልና በቡድን በመሆን በቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትና በብፁዓን አባቶች ማረፊያ ቤት በመገኘት ማቅረብ ሕጋዊነት የሌለው ተግባር ከመሆኑም በላይ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤን የሚያውክ ነው፡፡ በዚህም የተነሣ ፍጹም ተቀባይነትን የሌለው ተግባር መሆኑን ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡
አቤቱታና ጥያቄዎች ካሉም በሕጋዊው የቤተ ክርስቲያናችን አሠራር መሠረት መዋቅራዊ አሠራርን በጠበቀ መልኩ ማቅረብ ተቀባይነት ያለውና ሕጋዊ አሠራር ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ሕጋዊ አቤቱታና ጥያቄ ያለው ግለስብም ይሁን ተቋም ይህንን አሠራር መሠረት በማድረግ ጥያቄና አቤቱታውን ማቅረብ ይችላል። ይህም የሚሆነው ግን የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሚካሔድበትን ወቅት ጠብቆ መሆን የለበትም።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጉባኤውን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሚያካሒደው በቀኖና ቤተ ክርስቲያንና በሕጋዊው አሠራር በተቀረጹ አጀንዳዎች መሠረት መሆኑ ይታወቃል፡፡ቅዱስ ሲኖዶሱ የመወያያ ነጥቦች ብሎ በሚያጸድቃቸው የስብሰባ አጀንዳዎች ላይ ብቻ መሆኑን መረዳትም ያስፈልጋል፡፡ እናም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በሕግና በሥርዓት የሚካሔደውን ጉባኤ ሊያውክ ከሚችል ተግባራት ራሱን በማራቅ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በተሳካ መልኩ እንዲከናወን በጸሎት ፈጣሬ ዓለማትን በመለመን ሊተጋ ይገባዋል።
ይህንን መሠረት በማድረግም የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ሰኞ ጥቅምት ፲፬ ቀን ፳፻ ፲ ወ ፭ ዓ.ም መካሔድ የሚጀምረውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን ተከትሎ የሚከተሉትን መመሪያዎች አውጥቷል።
፩ኛ. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሚካሔድባቸው ቀናቶች ሁሉ ማንኛውም አቤቱታ አቀርባለሁ የሚል አካል ልዩ ልዩ ጽሑፎችን፣ በግልና በቡድን ሆኖ ማቅረብ የማይቻል መሆኑን ተገንዝቦ የምናቀርበው አቤቱታ አለን የሚል አካልም ደረጃውን ጠብቆ ለሚመለከተው አካል እንዲያቀርብ።
፪ኛ. ማንኛውም ሰው በአቤቱታ ሽፋን ለአድማ የተዘጋጁ ጽሑፎችና ማመልከቻዎችን ይዞ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤትም ሆነ በጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።
፫ኛ. አቤቱታ እናቀርባለን በሚል ሰበብ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን ይዞ በግልም ሆነ በቡድን ብፁዓን አባቶች ቤት በመገኘት ወረቀቶችን መበተን በበር ሥር ማስገባትና አላስፈላጊ ቅስቀሳ ማድረግ በጥብቅ የተከለከለ ከመሆኑም በላይ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤ የሚያውክ ተግባር በመሆኑ ይህን ድርጊት የሚፈጽሙ ሁሉ ከአድራጎታቸው እንዲታቀቡ ከወዲሁ እናሳስባለን።
፬ኛ. ጉባኤው በሚካሔድበት ወቅት ለሥራ ጉዳይ እንዲንቀሳቀሱ ከተፈቀደላቸው የሥራ ኃላፊዎች ውጪ ያለምንም ሥራ በጉባኤው አዳራሽና አካባቢው እንዲሁም ብፁዓን አባቶት ለእረፍት በሚወጡበት ጊዜ ብፁዓን አባቶችን ተከታትሎ ማረፊያ ቤታቸው መሄድና ማወክ የተከለከለ ነው።
፭ኛ. የጉባኤው ውሎን በተመለከተ አንዳንድ የመገኛኛ ብዙኀን ተቋማት መሠረተ ቢስ መረጃዎችን በመዘገብ ሕዝበ ክርስቲያኑን ከማደናገር እንዲቆጠቡ እያሳሰብን፤ የጉባኤውን ውሎ በማስመልከት አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ አማካኝነት በቤተ ክርስቲያናችን መገናኛ ብዙኀን የሚገለጽ ስለሆነ ትክክለኛውን መረጃ ከቤተ ክርስቲያናችን መገናኛ ብዙኀን ማግኘት የሚቻል መሆኑን እንገልጻለን።
፮ኛ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሰከነና በተረጋጋ መልኩ ተከናውኖ እስከሚጠናቀቅ ድረስ መላው ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ምዕመናን በጸሎት በመትጋት ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ጥሪውን ያስተላልፋል ።
በመጨረሻም ይህ የቤተ ክርስቲያናችንን መንፈሳዊ ፣ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶችና ቀጣይ መከናወን የሚገባቸውን ተቋማዊ ጉዳዩችን በመመልከት ውሳኔ የሚተላለፍበት ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ መከናወን ይችል ዘንድ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ መላው ሕዝበ ክርስቲያንና ወጣቶች በጸሎት ከምታደርጉት ትጋት በተጨማሪ ለጉባኤው መሳካትና ውጤታማነት እንዲሁም ለዚህ መመሪያ መከበር የሚጠበቅባችሁን ሁሉ እንድታበረክቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት መልእክቱን ዳግም ያስተላልፋል።
"ልዑል እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክልን፤"
አሜን
የኢ /ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት
ጥቅምት ፲፩ቀን ፳፻፲ወ፭ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages