የሰሚት ኆኅተ ምሥራቅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተጠናቆ በድምቀት ተከበረ!! - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, October 28, 2022

የሰሚት ኆኅተ ምሥራቅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተጠናቆ በድምቀት ተከበረ!!

 

የሰሚት ኆኅተ ምሥራቅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተጠናቆ በብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት በቅብዓ ሜሮን ከብሮ ቅዳሴ ቤቱ በድምቀት ተከበረ!!


(ጥቅምት ፲፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ)
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የሚገኘውና ለዓመታት ሲገነባ የነበረው የሰሚት ኆኅተ ምሥራቅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ከ፳፻፮ ዓ.ም መገንባት የተጀመረ ሲሆን ለ፱ ዓመታት ሲገነባ ቆይቶ ጥቅምት ፲፫ /፳፻፲፭ ዓ/ም ከሰዓት በኋላ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አማካኝነት በቅብዓ ሜሮን ከብሮ ቅዱሱ አገልግሎት ተጀምሮበታል፡፡
በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትና የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች፣ የቦሌና የለሚ ኩራ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል እና የዚሁ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሥራ ሓላፊዎች፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የደብሩ ሰ/ ተማሪዎችና በረከቱን ከቅርብም ከሩቅ የጠራቸው ምዕመናንና ምዕመናት በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል፡፡
ከብሉይ ኪዳን አገልግሎት በተለየ መልኩ የሐዲስ ኪዳን ቤተ መቅደስ የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ደም የሚቀርብበት፣ በረከት የሚፈሥበት መሆኑን የመሠከሩት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትና የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለዚህ በመብቃቱም እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ አድስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው ውብ የሆነ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ያሰበን ልብ፣ ለግንባታው እጁን የዘረጋውን፣ በጉልበቱን ያገዘውንና በመልካም አስተዳደር የመሩትን አካላት ያማሰገኑ ሲሆን በቀጣይ ለሚሠራው የሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውንም የሚበረታታ አግልግሎት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት የሁልጊዜ ናፍቆታቸው እንደነበረ የሚገልጹት የደብሩ ታሪክ ፰ኛ አስተዳደሪ የሆኑት መልአከ ፀሓይ መኮንን ፍስሓ ይህን በማየታቸው እጅግ እንዳስደሰታቸው አብራርተዋል፡፡
በተለይ ያሳለፍነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽ፣የሀገራችን ከፍተኛ የሰላም እጦት ችግርና አሁን ያለንበት የኑሮ ውድነት ሸክም ፈተና ቢሆንም ሁሉም የእግዚዘብሔር ነው እሱ ሲባርከው ነው የሚቀደሰው ብሎ የሚምን ምእመን በመኖሩ ያን ሁሉ አልፈን ለዚህ ደርሰናል ብለዋል የሕንጻ ኮሚቴው ምክትል ሰበሳቢ ኢንጅነር ዘላለም ተስፋዬ።
በመጨረሻ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎችን የያዘው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ቢጠናቀቅም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ሥራዎች የሚቀሩ መሆናቸውን የጠቆሙት የደብሩ ዋና ጸሓፊ የሆኑት ሊቀ ልሳናት ተስፋ ሚካኤል ታደሰ ምዕመናን ታሪክ የመሥራት ልማዳቸውን እንዲቀጥሉበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘገባው:- የኢኦተቤ ቲቪ ነው።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages