ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 19 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, October 28, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 19

 

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት አስራ ዘጠኝ በዚህች ቀን ደግ ንጉሥ #ቅዱስ_ይምርሃነ_ክርስቶስስ እረፍቱ ነው፣ #ቅዱስ_በርቶሎሜዎስና_ሚስቱ በሰማዕትነት አረፉ፣ ስለ #ጳውሎስ_ሳምሳጢ በአንጾኪያ አገር የቤተ ክርስቲያን የአንድነት ስብሰባ ተደረገ፣ የጸይለም አገር የከበረ አባት #ቅዱስ_ዮሐንስ አረፈ።

ጥቅምት አስራ ዘጠኝ በዚህች ቀን ደግ ንጉሥ፣ ፃድቅ ካህን፣ቤተ መቅደሱን በባህር ላይ ያነፀ መሀንዲስ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስስ
እረፍቱ ነው።
ልክ እንደ አቡነ ተክለሃይማኖትና እንደነ አቡነ ዜና ማርቆስ እርሱም ሲወለድ ወደ ምሥራቅ ዞሮ አምላኩን ያመሰገነ ሲሆን ቤቱም በብርሃን ተሞልቶ ታይቶ አዋላጆቹን ሁሉ አስገርሞ ነበር፡፡ ገና በእናቱ ማህፀን ሆኖ አጎቱ ጠንጠውድም በንግሥና ላይ ሳለ "ከአንተ በኋላ የሚነግሠው ይምርሃነ ክርስቶስ የሚባል የወንድምህ ልጅ ነው" የሚል ንግርት ይሰማ ነበርና ‹‹ይምርሃነ ክርስቶስ›› መወለዱን ሲያውቅ ‹‹የወንድሜን ልጅ ዐየው ዘንድ አምጡልኝ›› ብሎ ላከ፡፡ ባየውም ጊዜ ደም ግባቱ እጅግ ያምር ስለነበር ‹‹ይህስ መንግሥቴን ይውረስ፣ በእውነት ልጄ ነው›› ብሎ ባረከው፡፡
ከእርሱ ጋር ስምንት ቀን ተቀምጦ በወለዳቸው ልጆቹ መካከል ሆኖ ሲጫወት በተመለከተው ጊዜ ግን በልቡ ሰይጣን አደረበትና በቅናት ሆኖ ‹‹እርሱ ነግሦ ልጆቼ ወታደሮቹ ሊሆኑ ነውን›› በማለት ይገድለው ዘንድ አሰበ፡፡ ሆኖም አማካሪዎቹ ‹‹ለጊዜው ምንም ስለማይረዳ ተወው ለወደፊቱም የንግሥና ምሥጢር እንዳያውቅ ወደ እናቱ ዘንድ መልሰውና በዚያ ከብት ሲያግድ ይደግ››ስላሉት ወደ እናቱ ላከው፡፡ እርሷ ግን በጥበብና በብልሃት አስተዋይ አድርጋ አሳደገችው። ይህንንም ሲሰማ ሊገድለው አሽከሮቹን ላከ፡፡ እናቱም የተላኩትን አሽከሮች ተቀብላ ምግብ አቅርባ አስተናገደቻቸው። ነገር ግን እግዚአብሔር የንጉሡን ተንኮል ስለተገለጠላት ልጇን ደበቀችው፡፡ በስውርም ወስዳ ከጳጳሱ ዘንድ ዲቁና እንዲቀበል ካደረገችው በኋላ ‹‹ልጄ ሆይ! አጎትህ ሊገድልህ ይፈልግሃልና በፊቴ ከሚገድልህ ርቀህ ብትሄድ ይሻላል፣ ያዕቆብን ከኤሳው የጠበቀ አንተንም ይጠብቅህ›› ብላ ሸኘችው፡፡ ይምርሃነ ክርስቶስም ወደ በጌምድር ተሰደደ፡፡ (ገድሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ በዚያም የሌዋውያን ወገን የምትሆን ቅድስት ሕዝባን አግብቶ ቅስናም ተቀብሏል ይላል።) ያም ሆነ ይህ ቅዱሱ በስደቱ ወቅት ሥጋዊውንና መንፈሳዊውን ጥበብ ተምሮ እንዳጠናቀቀና በኋላም ወንጌልን እየሰበከ፣ በተአምራቱም ሕመምተኞችን እየፈወሰ እግዚአብሔርንም እያገለገለ እንደኖረ ታሪኩ ያወሳል፡፡
በዚህ አይነት ሁኔታ ዓመታት ሲያልፉ እግዚአብሔር አምላክ ንጉሥ አጎቱ ጠንጠውድም መሞቱንና በዙፋኑም እርሱ እንደሚነግሥ ነገረውና በመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል መሪነት ወደ ሀገሩ ተመልሶ መጥቶ በላስታ ወረዳ ሳይ (ዛሬ ሸጐላ ማርያም) ከምትባል ቦታ ላይ ወንጌልን እያስተማረ፣ ድውያንን እየፈወሰ እንዲቀመጥ አደረገው፡፡ ትምህርቱንና ተአምራቱን ያዩት የአካባቢው ሰዎችም ‹‹ነፃነትና ፍቅር የሚገኝብህ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! እኛ ሰላማዊ ብርሃናዊ ብለን ስም አወጣንልህ፣ ያንተ ግን ስምህ ማን ይባላል ንገረን›› አሉት፡፡ እርሱም ‹‹ስሜ ይምርሃነ ክርስቶስ ነው›› አላቸው ይህኔ ሕዝቡ ሁሉ በሹክሹክታ ‹‹ይምርሃነ ክርስቶስ የሚባል ሲነግሥ ሃይማኖት ይቀናል፣ ፍርድ ይስተካከላል›› እያሉ አባቶቻችን ሲናገሩ ሰምተናል አሉ፡፡
ከጠንጠውድምም ሞት በኋላ ማንም እንዳልነገሠ ሲያረጋግጡ የማን ልጅ እንደሆነ እንዲነግራቸው በእግዚአብሔር ስም ለመኑትና የጠንጠውድም ታናሽና የዣን ስዩም ታላቅ ወንድም የሆነው የግርማ ስዩም ልጅ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ እነርሱም ‹‹የተነገረው ትንቢት ደርሷልና ሳንዘገይ እናንግሠው›› ብለው ሥርዓተ መንግሥቱን ፈጽመው በዙፋን ላይ አስቀመጡት፡፡
ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ በትረ መንግሥቱን ከያዘ በኋላ ሁሉም ሰው በተለያዩ እንቅስቃሴዎቹ ውስጥ እንደ ወንጌሉ ቃል እንዲኖር በግዛቱ ሁሉ አወጀ፡፡ እግዚአብሔርም የሚመሰገንበትን ቤት መሥራት አሰበና የተፈቀደለትን ቦታ እንኪያገኝ ድረስ ዛዚያ በምትባል ልዩ በሆነች ስፍራ ድንኳን ተክሎ እንደ ሙሴ አምላኩን ማገልገል ጀመረ፡፡ በዚህም ቦታ ሕዝቡን ከሰማይ በወረደለት መስቀል እየባረከና እርሱ ለቅዳሴ በሚገባበት ጊዜ ከአምላኩ የሚሰጠውን ሰማያዊ ኅብስትና ጽዋ እያቆረበ ለ22 ዓመት በድንኳኗ ውስጥ ኖረ፡፡ ከነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ተገለጠለትና እንዲህ አለው፡- ‹‹ወዳጄ ይምርሃነ ክርስቶስ ይህን ሥፍራ (ዛዚያን) ልቀቅ፣ ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ቦታ ሰማያዊ ኅብስትና ሰማያዊ ጽዋ አይወርድልህም፡፡ ወደማሳይህ ቦታ ተነሥተህ ሂድ፣ በዚያም እስከ ዕረፍትህ ቀን ድረስ ሰማያዊ ኅብስትና ሰማያዊ ጽዋ ይወርድልሀል፡፡ ይህን ዓለም ለማሳለፍ እስከምመጣበት እስከ ዕለተ ምፅዓት ድረስ የእኔ ጌትነት የአንተም የቅድስና ሕይወት የሚነገርበት፣ የሥጋህ የዕረፍት ቦታ የሚሆንበት፣ ለምትሠራው መቅደስ ክዳን የሚሆን ሣር የማትፈልግበት ሰፊ ዋሻ እሰጥሀለው ፣ በዚያ ቤተ መቅደሴን ሥራ፣ እኔ በምትሠራው ቤተ መቅደስ ከአንተ ጋር ለዘለዓለም ቃልኪዳኔን አቆማለሁ፡፡ በምታንጸው ቤተ መቅደስ ውስጥ ‹አቤቱ የይምርሃነ ክርስቶስ አምላክ ሆይ! ስለወዳጅህ ስለ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ብለህ ይቅር በለኝ› እያለ ‹አባታችን ሆይ!› የሚለውን ጸሎት የሚጸልይ ዕለቱን እንደተጠመቀ አደርገዋለሁ፡፡ ነገ ማለዳ ተነሥተህ ወግረ ስሂን ወደሚባለው የዕረፍትህ ቦታ ወደሚሆነው ዋሻ ሕዝብህን አስከትለህ ሂድ፤ በዚያም ቤተ መቅደሴን አንጽ›› ብሎ ቃልኪዳን ሰጠው።
ይምርሃነ ክርሰቶስም ሕዝቡን ይዞ ተነሳና አሁን ከቅዱስ ላሊበላ ቤተ መቅደሶች 42 ኪ,ሜ ርቀት ላይ ወደሚገኘውና ጥቁር አለታማ ተራራ ሥር ወዳለው የውግረ ስሂን ዋሻ አመራ። ሲደርስም ቦታው የሰዎች ይዞታ ሆኖ ስላገኘው እኔ ንጉሥ ነኝ ብሎ እነርሱን በግፍ ሳያስለቅቅ ካሳ ከፍሎ ስፍራውን ተረከባቸው። ውስጡ ግን ውሀ የቆመበት ባህርና ርኩሳት መናፍስት የሞሉት ስለነበር መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል መናፍስቱን አባሮ በባሕሩ ላይ ቤተ መቅደሱን እንዴት እንደሚያንጽ ገለጠለት። እርሱም በተነገረው መሠረት ለግንባታው የሚያስፈልጉ እቃዎችን ከኢየሩሳሌም አስመጥቶ ማነጽ ጀመረ። የውሀውን ክፍል እንጨት ረብርቦ አፈር እየበተነ ደለደለው። ሰዎች በባህር ላይ መሠራቱን እንዳይጠራጠሩም አነስተኞ መስኮትነገር አበጀለት። (በዚህችም አሁን ድረስ በክንድ ርቀት ያህል ከሥር ያለው ውሀ ይነካል።) ከበላዩም ስስ ሆነው የተፈለጡ ድንጋዮችን በኖራ እያቦካ በማያያዝ በእኩል መጠን እየገነባ በመሀከላቸው እንደ መቀነት የተጠረቡ እንጨቶችን በማስገባት አሳምሮ አነፀው። ውስጡንም በሦስት ቤተ መቅደሶች ከፈለው በየመስኮትና በየበሮቹም ላይ እንደ ዐይነ እርግብ ሆነው የተፈለፈሉ ሐረጎችን አደረገበት ጣሪያውንም በሰባቱ ሰማያት ምሳሌ ምስጢር ባላቸው የተለያዩ ቅርፆች አስዋበው።ይህን አድርጎ ሥራውን ከጨረሰ በኋላም የቅዱስ ገብርኤልን የእመቤታችንንና የቅዱስ ቂርቆስን ታቦታት አስገባበት። በድጋሚም ቤተ መንግሥቱን በዛው ዋሻ ውስጥ አነጸና በአስተዳደሩ ደሀ ሳይበድል ፍርድ ሳያጓድል ሕዝቡን በክህነቱም ንፁህ ሆኖ እግዚአብሔርን እያገለገለ ኖረ።በስተመጨረሻም ፍጥረት ሆኖ ከመሞት ሰው ሆኖ በመቃብር ከመዋል የሚቀር አይኖርምና ንጉሣችንና አባታችን ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስም የእረፍት ዘመኑ ሲደርስ እግዚአብሔር አምላክ ቃል ኪዳኑን ለዘላለም እንደሚያፀናለት ነግሮት በዚህች በተባረከች #በጥቅምት_19 ቀን በክብር አሳረፈው።
መቃብሩንም አስቀድሞ እነደነገረው በዛው በተቀደሰ ዋሻ ውስጥ አደረገለት። እናም ዛሬ ድረስ ቦታው በክብር ተጠብቆ ይኖራል። ምእመናንም ቃል ኪዳኑን በማሰብ "ማረኝ ይምርሐ" እያሉ መቃብሩን ይዞራሉ። ያንን ከሰማይ የወረደለትን መስቀልም በቤተመቅደሱ የሚያገለግሉት ካህናት አባቶች ቦታውን ለመሳለም የሚመጣውን ሕዝበ ክርስቲያን በበዓል ቀን ይባርኩበታል፡፡

ዳግመኛም በዚህች ቀን በከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን ቅዱስ በርቶሎሜዎስና ሚስቱ በሰማዕትነት አረፉ።
እሊህ ቅዱሳንም የግብጽ ምዕራብ ከሆነ ፍዩም ከሚባል አገር ናቸው ክርስቲያኖችም እንደሆኑ በመኰንኑ ዘንድ ወነጀሏቸው መኰንኑም ልኮ አስቀረባቸውና ስለ ሃይማኖት ጠየቃቸው እነርሱም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊቱ ታመኑ።
መኰንኑም ጥልቅ ጒድጓድ እንዲቆፍሩላቸው በዚያም እንዲጨምሩአቸውና በሕይወታቸው እንዲደፍኑባቸው አዘዘ። መኰንኑም እንዳዘዘ አደረጉባቸው በዚህም ምስክርነታቸውን ፈጽመው የሰማዕትነት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ ።

በዚችም ቀን ስለ ጳውሎስ ሳምሳጢ በአንጾኪያ አገር የቤተ ክርስቲያን የአንድነት ስብሰባ ተደረገ። ይህ ጳውሎስም ከአንጾኪያ አገሮች በአንዲቱ አገር ኤጲስቆጶስነት በተሾመ ጊዜ ክፉ ዘርን ሰይጣን በልቡ ውስጥ ዘራበት አካላዊ ቃልን አካል እንደሌለ የክርስቶስም ጥንት መገኛው ከማርያም እንደሆነ እርሱም አለምን ያድንበት ዘንድ እግዚአብሔር የፈጠረው እንደሆነ ከመለኮትም ጋር ያልተዋሐደ በላዩ ወርዶ በእግዚአብሔር ፈቃድ አደረበት እንጂ ብሎ የሚያምን ሆነ በወልድም ቢሆን በመንፈስ ቅዱስም ቢሆን የሚያምን አልሆነም።
ስለዚህም ኤጲስቆጶሳት አንድነት ተሰበሰቡ የእስክንድርያ አባ ዲዮናስ የሮሜ አባ ዲዮናስዮስ እሊህ ሊቃነ ጳጳሳት ስለ እርጅናቸው ከዚያ ደርሰው ከእርሳቸው ጋር ሊሰበሰቡ አልቻሉም ነገር ግን መልእክትን ጻፉ።
የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዲዮናስም እንዲህ የሚል መልእክትን ጻፈ። የእግዚአብሔር ልጁም ቃሉም የሆነ ክርስቶስ በመለኮቱም ከእርሱ ጋር ትክክል የሆነ እርሱም ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ ስለእኛ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ ዘር ስጋንና ነፍስን ነሥቶ ፍጹም ሰው የሆነ በመለኮቱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል ሲሆን እንደእኛ ፊጹም ሰው ሁኗል ከተዋሕዶውም በኋላ ያለ መለያየትና ያለ መቀላቀል ሁለቱ ባሕርያት አንድ ሁነዋል ከብሉይና ከሐዲስ መጻሕፍት ምስክሮችን ጠቅሶ እያስረዳ ጽፎ ይቺንም መልእክት ከሁለት ምሁራን ቀሳውስት ጋር ላካት።
በዚያንም ጊዜ አሥራ ሦስቱ ኤጲስቆጶሳትና እሊህ ሁለቱ ቀሳውስት ጉባኤ አድርገው ይህን ጳውሊ ሳምሳጢን አቅርበው የአባ ዲዮናስን መልእክት በፊቱ አነበቡ። ዳግመኛም ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጁም ቃሉም የሆነ የጌትነቱ ነጸብራቅ ነው የሚለውን የሐዋርያ ጳውሎስን ቃል በመጥቀስ እርሱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በትክክልነት እንደሚኖር አስረዱት እርሱ ግን ቃላቸውን አልተቀበለም።
ከዚህም በኋላ በእርሱ ትምህርት የሚያምኑትን ሁሉ አው*ግዘው ከምእመናን ለይተው አሳደዱት። ለምእመናንም ሥርዓትን ሠሩ።

በዚችም ቀን የጸይለም አገር የከበረ አባት ዮሐንስ አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ከሀገሩ ታላላቆች ወገን ናቸው የአባቱም ስም አብርሃም የእናቱም ስም ሣራ ነው እነርሱም ልጆች ስለ ሌሏቸው ብዙ ዘመን ወደ እግዚአብሔር እየለመኑ ኖሩ።
በአንዲትም ዕለት ሁለት መነኰሳት ወደ እነርሱ እንግድነት መጡ እነርሱም በክብር ተቀብለው አሳደሩአቸው። እሊህ መነኰሳትም አብርሃምን ልጅ የለህምን አሉት እርሱም እንባውን እየአፈሰሰ አባቶቼ ልጅ የለኝም አሁንማ እኔ አረጀሁ የሚስቴም የልጅነቷ ወራት አለፈ ብሎ መለሰላቸው። እሊህ መነኰሳትም ስለ እርሳቸው ጸለዩላቸው ባርከዋቸውም ጎዳናቸውን ተጓዙ።
ከጥቂትም ቀን በኋላ ሳራ ፀነሰች ደስ የሚያሰኝም ልጅን ወለደች ስሙንም ዮሐንስ ብለው ሰየሙት በእርሱም ደስ አላቸው የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት እየአስተማሩ አሳደጉት።
ዐሥራ ሰባት ዓመትም በሆነው ጊዜ ወደ መምህሩ ቤት መነኰሳት መጡ ዮሐንስም ከእርሳቸው ጋር እንዲወስዱት ለመናቸው እነርሱም አባትህን እንፈራለንና እኛ አንወስድህም አሉት። መነኰሳቱም ወደቦታቸው እየሔዱ ሳሉ ወደ መረጠው ጎዳና ይመራው ዘንድ ዮሐንስ ተነሥቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ከመምህሩም ቤት ወጥቶ ሊደርስባቸው ወዶ መነኰሳቱን በኋላቸው ተከተላቸው ወደ ታላቅ ወንዝም ደረሰ ብቻውንም መሻገር ፈርቶ ቆመ ከዚያም ሳለ ዓረቦች ከግመሎቻቸው ጋር መጡ ያሻገሩትም ዘንድ ለመናቸው እነርሱም ከእርሳቸው ጋር አሻገሩት አንወስድህም ወደአሉት መነኰሳት ወደ ገዳማቸው በእግዚአብሔር ፈቃድ ደረሰ።
ከእርሳቸውም አንዱ አባ ስምዖን የሚባለው ዮሐንስን ወስዶ ደቀ መዝሙሩ አድርጎ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር አኖረው።
አባ ስምዖን የሚሞትበት ጊዜ እንደቀረበ በአወቀ ጊዜ ልጆቹን ጠርቶ ከሞትኩ በኋላ በእናንተ ላይ የሚሆነውን እግዚአብሔር ያሳየኝን እነግራችሁ ዘንድ ልጆቼ ኑ አላቸውና ከእናንተ አንዱን ጅብ ነጥቆ ይወስደዋል። ሁለተኛው ወደ ዓለም ተመልሶ ይባክናል። የሦስተኛው ግን ዜናው በዓለሙ ሁሉ ይሰማል አላቸው።
ከዚህም በኋላ አረጋዊው ስምዖን ወደ ዮሐንስ ተመልክቶ ልጄ ሆይ በክርስቶስ ፍቅር ጽና ለብዙዎች አባት ልትሆን እርሱ መርጦሃልና አለው። አባ ስምዖንም ከአረፈ በኋላ በሦስተኛው ቀን አንዱ ረድዕ ወደ ዓለም ተመልሶ ሚስት አገባ ሁለተኛው ወዴት እንደ ደረሰ አልታወቀም። አባ ዮሐንስም ብቻውን ቀረ ፈጽሞ አዘነ በልቡ እንዲህ አለ የጓደኞቼን ወሬ እጠይቅ ዘንድ ከገዳም ወጥቼ ልውረድ ይህንንም ብሎ ከገዳሙ ወጥቶ ሲወርድ የጸይለም ጦረኞች ተቀበሉት ደም ግባታቸው ከሚአምር ከሁለት ሴቶች ጋር አሥረው ወሰዱት በጒዞም ላይ እያሉ ለእንስሶቻቸውና ለራሳቸው የሚጠጡት ውኃ አጡ። አባ ዮሐንስም ከዚህ በረሀ ውስጥ ፈጣሪዬ ውኃን ቢአወጣላችሁ ትለቁኛላችሁን አላቸው አዎን አሉት። በዚያንም ጊዜ አባ ዮሐንስ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብሎ በምድር ላይ አማተበ ውኃም ፈልቆላቸው ጠጥተው ረኩ።
የከበረ ዮሐንስም ቃል ኪዳን እንደ ገባችሁልኝ አሰናብቱኝ አላቸው እነርሱም እንዳንተ ያለ አናገኝምና ከቶ አንለቅህም አሉት። ይህንንም ብለው ወደ አገራቸው ወደ ጸይለም አደረሱት።
በዚያንም ወራት በጸይለም አገር ታላቅ መቅሠፍት ወረደ የአበ ዮሐንስም ጌታው ከቤተሰቦቹ ሁሉና ከልጆቹ ጋር ሞተ ሚስቱም ከአንዲት ልጅዋ ጋር ብቻዋን ቀረች። የጌታውም ሚስት ቅዱስ ዮሐንስን መሠርይ እንደ ሆነ አሰበች በማደሪያውም ውስጥ እያለ ሊአቃጥሉት እሳት ለቀቁበት እግዚአብሔርም ከእሳት ውስጥ በደኅና አወጣው የጸይለም ሰዎችም ይህን ድንቅ ተአምር አይተው ሴቶችም ወንዶችም በጌታችን አምነው በእጆቹ ተጠመቁ።
ከዚያም ተነሥቶ ወደ ሌላ አገር ሔደ። የአገር ሰዎችም ዛፎችን ሲያመልኩ አግኝቷቸው እርሱም ከክህደታቸው እንዲመለሱ አስተማራቸው ባልሰሙትም ጊዜ ምሳር ይዞ በሌሊት ወደ ዛፎቹ መካከል ገብቶ ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ምሳሩንም አንሥቶ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እቆርጣችኋለሁ አለ። ወዲያውኑ በአንዲት ምት ዐሥር ሽህ ዛፎች ወደቁ የሀገር ሰዎችም ይህን ድንቅ ተአምር አይተው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ሁሉም ከሴቶችና ከልጆች ጋር ተጠመቁ።
ከዚያም ዳግመኛ ወደ ሌላ አገር ሔደ ሰዎችንም እሳትን ሲያመልኩ አገኛቸው እርሱም ይህን ደንቊርናቸውን ይተዉ ዘንድ አስተማራቸው ገሠጻቸውም እነርሱም በእርሱ ላይ ተቆጥተው ከእሳት ጨመሩት። እርሱም በደኅና ወጣ ሦስት ጊዜም ጨምረውት በደኅና ወጣ ውኃቸውንም ደም አደረገባቸው የሚጠጡትም አጥተው በተጨነቁ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ሁሉም አመኑ። አራት መቶ ሽህ ሰዎችም በእጁ ተጠመቁ ቤተክርስቲያንም ሠራላቸው አስተምሮም በቀናች ሃይማኖት አጸናቸው ቁጥር የሌላቸው ድንቆች ተአምራትንም አደረገ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም በፍቅር አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages