ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 18 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, October 28, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 18

 

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት አሥራ ስምንት ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ቴዎፍሎስ ያረፈበት፣ የከበረ #ቅዱስ_ሮማኖስ በሰማዕትነት ያረፈበት ነው።


ጥቅምት አሥራ ስምንት በዚህች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃያ ሦስተኛ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት ቴዎፍሎስ አረፈ። ይህም አባት ንጉሥ ቴዎዶስዮስ በነገሠ በስድስተኛ ዓመት ተሾመ በወንጌላዊ ማርቆስም ወንበር ሃያ ስምንት ዓመት ኖረ።
በዘመኑ ብዙ መጻሕፍትን የተረጎመ ከእሳቸውም የወንጌላዊ ዮሐንስን ራእይና የሐዋርያ ጳውሎስን መልእክት የተረጎመ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ተነሣ ዳግመኛም ለደሴተ ቆጵሮስ ኤጲስቆጶስ የሆነ ኤጲፋንዮስ ነበረ።
በዘመኑም ሰባቱ ደቂቅ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት ከአንቀላፉ በኋላ ተነሡ። ይህም አባት የሐዋርያዊ ሊቀ ጳጳሳት አባት አትናቴዎስ ደቀ መዝሙር ነው የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍትና ሥርዓቱን ሁሉ እየተማረ በእርሱ ዘንድ አደገ። ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጢሞቴዎስም በአረፈ ጊዜ ይህ አባት በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ አዋቂና አስተዋይም ስለሆነ ስለ ፍቅር ስለ ርኅራኄ ከንሰሐ በፊት ሥጋውንና ደሙን ከመቀበል መጠበቅ ስለ ሚገባ ስለ ሙታን መነሣትና ለኃጥአን ስለ ተዘጋጀ ስለዘላለማዊ ሥቃይ ሌሎችም ጠቃሚ የሆኑ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ።
ቅዱስ ቄርሎስም ለዚህ አባት ቴዎፍሎስ የእኅቱ ልጅ ነው እርሱም በበጎ አስተዳደግ አሳደገው የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት አስተማረው። ከዚያም በኋላ ወደ አባ ሰራብዮን ላከው አባ ሰራብዮንም መንፈሳዊ ተግባርን ሁሉ አስተማረው።
በአትናቴዎስም ዘመን አስቀድሞ እንዲህ ሆነ በጎ ዘመን ባገኝ ይህን ኮረብታ ባስጠረግሁት ነበር። ለከበሩ ለመጥምቁ ዮሐንስና ለነቢይ ኤልሳዕም ቤተ ክርስቲያን በሠራሁም ነበር ሲል ይህ አባት ቴዎፍሎስ አባ አትናቴዎስን ይሰማው ነበር። በሹመቱ ወራትም ይህን ነገር አስታውሶ የሚያዝንና ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን የሚጸልይ ሆነ።
በዚያ ወራትም ባሏ ብዙ ገንዘብ ትቶላት የሞተ አንዲት ባለጸጋ ሴት ከሮሜ አገር መጣች ሁለት ልጆቿም ከእርሷ ጋር አሉ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስንም ሲያዝን አየችውና ክብር አባት ሆይ ምን ያሳዝንሐል አለችው። እርሱም ብዙ ወርቅ በዚህ ኮረብታ ውስጥ እያለ ድኆች ይራባሉና አላት እርሷም አንተ ስለ እኔ ጸልይ እኔም አስጠርገዋለሁ አለችው።
ይህንንም ብላ ያን ኮረብታ አስጠረገችው በውስጡም በደንጊያ ሠሌዳ እየአንዳንዱ የተከደኑ ሦስት ሣጥኖች ተገለጡ። በላያቸው ቴዳ ቴዳ ቴዳ የሚል ተጽፎባቸዋል አባ ቴዎፍሎስም በአየው ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ምሥጢራቸውን አውቆ ቴዳ ማለት የጌታ ስም ነው ይህም ለድኆች ይገባል አለ ሁለተኛውም ቴዳ የንጉሥ ቴዎዶስዮስ ነው ሦስተኛውም ቴዳ ቴዎፍሎስ ማለት ነው። የእኔ ገንዘብ ስለሆነ በዚህም አብያተ ክርስቲያናትን እሠራለሁ አለ። እሊህም ሣጥኖች በመቄዶንያዊው ፊልጶስ ልጅ በንጉሥ እስክንድር ዘመን እንደ ተቀበሩ የዘመን ቊጥር ተገኘ እርሱም ሰባት መቶ ዘመናት ነው።
ከዚህም በኋላ ያን የወርቅ ሣጥን ለንጉሥ ቴዎዶስዮስ ላከለት ስለዚያም የወርቅ መዝገብ አስረድቶ ቦታውን መጥቶ እንዲያይ አሳሰበው እርሱም በመርከብ ተጭኖ ወደ እስክንድርያ አገር መጥቶ ሁሉንም አየ የዚያንም ወርቅ እኵሌታ መለሰለት አባ ቴዎፍሎስም ብዙዎች አብያተ ክርስቲያንን ሠራ።
አስቀድሞም በቅዱሳን በመጥምቁ ዮሐንስና በነቢይ ኤልሳዕ በስማቸው ቤተ ክርስቲያን ሠራ ሥጋቸውንም ከእስራኤል አገር አፍልሶ አምጥቶ በውስጧ አኖረ እርሷም የታወቀች ናት ዴማስ በሚባል ቦታ ሁለተኛም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በሀገሩ ምሥራቅ በኩል ሠራ ከዚህም በኋላ በሊቀ መላእክት ሩፋኤል ስም በደሴት ውስጥ ሠራ ሌሎችንም ብዙዎች አብያተ ክርስቲያን አሳነፀ።
ንጉሡም አብያተ ክርስቲያናትን ለመሥራት ያለውን የሊቀ ጳጳሳቱን ፍቅር አይቶ በግብጽ አገር ያሉትን የጣዖታት ቤቶችን ሁሉንም ሰጠው እርሱም ተቀብሎ አፈረሳቸውና በቦታቸው አብያተ ክርስተከያናትንና የእንግዶች ቤቶችን ሠራ ሁለተኛም ምድራቸውን ሁሉ ሰጠው።
ይህም አባት ቴዎፍሎስ የክርስትና ጥምቀትን በሚያጠምቅ ጊዜ የብርሃን በትረ መስቀል በሚጠመቁት ላይ በመስቀል ምልክት ሲያማትብ ያይ ነበር።
ይህ አባት ቴዎፍሎስና ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ልጆች በሆኑበት ጊዜ ሁለቱም በአንዲት ሌሊት አንዲት የሆነች ራእይን እነርሱ እንጨቶችን እንደሚለቅሙ አዩ። ከእነርሱም አንዱ ንጉሥ እንደሚሆን ሁለተኛውም ሊቀ ጳጳሳት እንደሚሆን ያቺን ራእይ ተረጎሟት እንዲሁም ሆነ።
ይህም አባት ቴዎፍሎስ ሊቀ ጵጵስና በተሾመባት በመጀመሪያዪቱ ዓመት ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ሃይማኖትን እናስተምራለን የሚሉ ሁሉ ሃይማኖታቸውን በመጽሐፍ ጽፈው ወደርሱ እንዲአቀርቡ አዘዛቸው እንዳዘዛቸውም አደረጉ።
ከዚህም በኋላ ንጉሡና ሊቀ ጳጳሳቱ ተነሥተው እነዚያን ጽሑፎች በመሠዊያው ላይ አድርገው ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ ጌታም ወልድ በመለኮቱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል ነው ብሎ ከሚታመን በቀር ከውስጣቸው በቀናች ሃይማኖት የጸና እንደ ሌለ ገለጠላቸው። በዚያንም ጊዜ እሊህን የመና*ፍ*ቃን መጻሕፍትን እንዲአቃጥሏቸው እነዚያንም መና*ፍ*ቃን ከሚገዛው አገር እንዲአሳድዷቸው ንጉሥ አዘዘ።
ዮሐንስ አፈወርቅም መጻሕፍትን ማንበብና መመርመር ያበዛ ነበር ስለዚህም የአውጋርዮስን መጻሕፍት አወገዘ ያወግዙ ዘንድም ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ወደዚህ አባት ወደ ቴዎፍሎስ ወደ ቆጵሮስ ኤጲስቆጶስ ወደ ኤጲፋንዮስ ወደ ኤዺስቆጶሳት ሁሉ በየሀገሩ ላከ። ከዚህም በኋላ መልካም ጒዞውን በፈጸመ ጊዜ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

ዳግመኛም በዚህች ቀን ክርስቲያኖችን በአሳደደ በመኰንን አስቅልጵያኖስ ዘመን የከበረ መነኰስ ሮማኖስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ የክርስቲያን ወገኖችን መኰንኑ እንዳሳደዳቸው በሰማ ጊዜ ከቀሳውስትና ከዲያቆናት ጋር የክርስቲያን ወገኖችን ሁሉ በአንድነት ሰበሰባቸው ስለ ክርስቶስ ሃይማኖትም መክሮ አጸናቸው።
አስቅልጵያኖስም ይህን ሰምቶ እንዲአመጡት አዘዘ በፊቱም በቆመ ጊዜ አስቅልጵያኖስ በወገን የከበርክ ሮማኖስ አንተ ነህን አለው ቅዱሱም የወገን ክብር ምን ይጠቅመኛል ክብሬ ግን ክርስቶስ ነው ብሎ መለሰለት። መኰንኑም ሰምቶ እንዲሰቅሉትና ጉንጮቹን ይሰነጣጥቁ ዘንድ አዘዘ ጉንጮቹንም ሲሰነጣጥቁት ምንም አልተናገረምና መኰንኑ ትዕግሥቱን አደነቀ።
በዚያንም ጊዜ ሮማኖስ መኰንኑን እንዲህ አለው እነሆ ስንፍናህን እዘልፍ ዘንድ ፈጣሪዬ አፌን ከፈተ እውነት ነገርን ብታውቅ ለእግዚአብሔር እንሰግድ ዘንድ ይገባ እንደሆነ ወይም ለአማልክት እንዲነግረን ሕፃን ልጅ እንዲአመጡ እዘዝ መኰንኑም ታናሽ ሕፃንን እንዲአመጡ አዘዘ መኰንኑም ሕፃኑን ስግደት ለማን እንዲገባ ዕውነቱን ንገረን አለው። ሕፃኑም ልብ የሌለህ ደንቆሮ መኰንን በአንዲት ቃል ዓለሙን ሁሉ ለፈጠረ ለሕያው እግዚአብሔር ስግደትና አምልኮ እንዲገባ አታውቅምን አለው።
መኰንኑም ሕፃኑን ይሰቅሉት ዘንድ አዘዘ የሕፃኑም እናት ልታየው መጣች ሕፃኑም እናቱን ተጠምቻለሁና ውኃ አጠጭኝ አላት። እናቱም ልጄ ሆይ ከዚህ ውኃ የለም ነገር ግን ወደ ሕይወት ውኃ ሒድ አለችው።
በዚያንም ጊዜ የሕፃኑን ራስ በሰይፍ እንዲቆርጡ የቅዱስ ሮማኖስንም ምላሱን ከግንዱ እንዲቆርጡ መኰንኑ አዘዘ። ያን ጊዜ መኰንኑን ይዘልፍ ዘንድ ለአባ ሮማኖስ ረቂቅ አንደበት ተሰጠው ሲዘልፈውም መኰንኑ ሰምቶ ምላሱ እንዳልተቆረጠ ተጠራጠረ። ወታደሩንም ጠርቶ ምላሱን ያልቆረጥክ ለምንድን ነው አለው ወታደሩም የምላሱን ቁራጭ ያመጡ ዘንድ እዘዝ አለው አምጥተውለትም አይቶ መኰንኑም ወደ ወህኒ ቤት አስገብተው በዚያ አንቀው እንዲገድሉት አዘዘ። እንዲህም ምስክርነቱን ፈጽሞ የምስክርነት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages