ስንክሳር_ዘወርኅ_ጥቅምት 28 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, November 7, 2022

ስንክሳር_ዘወርኅ_ጥቅምት 28

 

ጥቅምት 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ ይምዓታ ጻድቅ (ከተስዓቱ ቅዱሳን)
2.ቅዱሳን መርትያኖስ ወመርቆሬዎስ (ሰማዕታት)
3.አባታችን ያፌት (የኖኅ ልጅ)
 
ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክክርስቶስ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
6.ቅዱስ አባዲርና ቅድስት ኢራኢአንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ ስምንት በዚህች ቀን ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት ጻድቁ_አቡነ_ይምዓታ አረፉ፣ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ_መርትያኖስና_ቅዱስ_መርቆሬዎስ በሰማዕትነት አረፉ።

ጥቅምት ሃያ ስምንት በዚህች ቀን ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት ጻድቁ አቡነ ይምዓታ አረፉ።
ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮዽያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት። አባ ይምዓታ ከዘጠኙ (ተስዓቱ) ቅዱሳን አንዱ ናቸው። ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው።
ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው። በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር፦
1.የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ
2.ዓላማ (የእግዚአብሔር መንግስት) እና
3.ገዳማዊ ሕይወት ነው።
አባ ይምዓታን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግስት ነው። እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል። አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል።
በምናኔ ቅድሚያውን አባ ዸንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ። ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት 5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ።
በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮዽያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም። ስለዚህም በ470ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮዽያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ።
ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው። ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው። ይህች ቦታ "ቤተ ቀጢን" ትባላለች።
አባ ይምዓታና 8ቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደ ገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር። ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዛው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ። በወቅቱ በአቡነ ሰላማ፣ በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አባ ይምዓታ እንደ ገና አቀጣጠሉት።
ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት። የካደውን እየመለሱ የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ። ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ።
ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው። በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አባ ይምዓታ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማሕበር ነበር። በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር። ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም።
የነ አባ ይምዓታ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ:: ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው:: እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ:: ዸንጠሌዎን በጾማዕት፣ ገሪማ በመደራ፣ ሊቃኖስ በቆናጽል፣ አረጋዊ በዳሞ፣ ጽሕማ በጸድያ፣ ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ።
አባ ይምዓታ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ገርዓልታ (እዛው ትግራይ) ሆነ። ጻድቁ ወደ ቦታው ሲሔዱ ወንዝ (ባሕር) ተከፍሎላቸዋል። ወደ ቦታው ደርሰውም ገዳም አንጸዋል። በቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠርተው በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው፣ ለዘመናት ተጋድለው በገርዓልታ በዚህች ቀን አርፈዋል።
የአቡነ ይምዓታ ፍልፍል ዋሻ ቤተ መቅደስ ትግራይ ገርዓልታ ልዩ ስሙ ‹‹ጎሕ›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይገኛል፡፡ ቤተ መቅደሱ ሰማይን እንደ ምሰሶ ደግፈው የያዙ የሚመስሉ በጣም ረጃጅም ተራሮች መካከል በአንደኛው ጭፍ ላይ ይገኛል፡፡ ቤተ መቅደሱ ከባሕር ወለል በላይ በ2300 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ሲሆን ቤተ መቅደሱ ያለበት የተራራው ርዝመት ብቻውን 300 ሜትር ነው፡፡ ቤተ መቅደሱ በር ላይ ለመድረስ በጭንቅና በፍርሃት ሆኖ ተራራውን እንደዝንጀሮ በእጅ እየቧጠጡ መውጣት ይጠይቃል፡፡ እርሱም ቢሆን በገዳሙ አባቶች እገዛና ድጋፍ ካልሆነ መውጣት የማይቻል ነው፡፡
ቤተ መቅደሱ እጅግ የሚደንቀው በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ ብቻ አይደለም ውስጡ ያሉት የግድግዳ ላይ ሥዕሎችም እጅግ ድንቅና ጥንታዊ ናቸው፡፡ ስለዚሁ የአቡነ ይምዓታ እጅግ አስደናቂ ቤተ መቅደስ ገድለ አቡነ አረጋዊ "በሞት በዐረፉ ጊዜ የሥጋቸው ሥርዓተ ግንዘት በመላእክት እጅ ነው የተከናወነው፡፡ ይልቁንም ቁመቱና ርዝመቱ ከታላላቅ ገደል እጅግ በጣም የሚበልጥ የድንጋይ ዓምድ ከወንዝ ማዶ ዘንበል ብሎ መጥቶ ሥጋቸውን በክብር ተቀብሎ በተራራው ጫፍ ላይ እስከዛሬም ድረስ ፈጽሞ ሳይነቃነቅና ሳይናወፅ ቀጥ ብሎ ቆሞ ይገኛል በማለት ይገልጻል፡፡

ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ መርትያኖስና መርቆሬዎስ በሰማዕትነት አረፉ። እሊህም ለቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ለአባ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱ ናቸው።
ይህም እንዲህ ነው አርዮሳዊ የሆነው ሁለተኛው ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ አባ ጳውሎስን በተጣላው ጊዜ ወደ አርማንያ አጋዘውና በዚያም በሥውር በእሥር ቤት ውስጥ አንቀው እንዲገድሉት አደረገ እሊህ ቅዱሳን መርትያኖስና መርቆሬዎስ ግን የዕረፍቱን ቀን ገድሉንም ጻፉ አርዮሳዊውንም ንጉሥ ረገሙት።
አንድ ክፉ ሰውም ወደ ንጉሡ ሒዶ እነርሱ እንደረገሙት ወነጀላቸው። ንጉሡም ያን ጊዜ ከአታክልት ቦታዎች በአንዲቱ ቦታ ተቀምጦ ሳለ ወታደሮች ልኮ ወደርሱ አስቀረባቸው በሰይፍም እንዲገድሏቸው አዝዞ ገደሏቸው። በዚያም በገደሏቸው ቦታ ቀበሩአቸው እስከ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘመንም በዚያ ቦታ ኖሩ እርሱም ዜናቸውን በሰማ ጊዜ መልእክተኞችን ልኮ ሥጋቸውን ወደ ቊስጥንጥንያ በክብር አስመጣ ያመረች ቤተ ክርስቲያንንም ሠርቶላቸው ሥጋቸውን በውስጧ አኖረ በዚችም ቀን በዓልን አደረገላቸው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages