ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 11 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 11

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ዐሥራ አንድ በዚች ቀን የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት #ቅዱስ_በላትያኖስ በሰማዕትነት ሞተ፣ ተጋዳዩ ባለ አንበሳው #ቅዱስ_አውሎግ አረፈ፣ የአባ ስልዋኖስ ረድእ #ቅዱስ_አባ_በትራ አረፈ።


የካቲት ዐሥራ አንድ በዚህች ቀን የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት በላትያኖስ በሰማዕትነት ሞተ።
ይህም ቅዱስ ብልህና አዋቂ የሆነ ታላቅ ተጋድሎን የሚጋደል ነው በሮሜ ሀገርም ሊቀ ጵጵስና ተሹሞ በቅዱስ ጴጥሮስ ወንበር ላይ ዐሥራ ሁለት ዓመት በሰላም ኖረ። ሕዝቡን የቀናች ሃይማኖትን እያስተማራቸው ሳለ መኰንኑ ፊሊጶስ በንጉሥ ቀላውዴዎስ ላይ ተነሥቶ በገደለው ጊዜ በርሱ ፈንታ ነገሠ በምእመናንም ላይ ታላቅ መከራን አመጣ በዚህ በንጉሥ ዳኬዎስ እጅ ብዙዎች በሰማዕትነት ሞቱ።
በዘመኑም ሰባት ሰዎች ከእርሱ ሸሹ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት ተኝተው ነቁ እርሱም በኤፌሶን ከተማ መስጊድ ሠርቶ በውስጡ ጣዖታትን አኖረ ሰዎችን ሁሉ ለጣዖታት እንዲሠዉ አስገደዳቸው ለጣዖታት ያልሠዉትንም ገደላቸው።
ይህ የከበረ በላትያኖስም የጣዖታት አምልኮን እንደሚቃወም ሕዝቡም በክብር ባለቤት በክርስቶስ ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ እንደሚያስተምር ንጉሥ በሰማ ጊዜ ወደ ሮሜ አገር ልኮ ወደ ኤፌሶን ከተማ አስመጣውና ለጣዖታት እንዲሠዋ ለመነው።
እርሱ ግን ቃሉን አልሰማም ተሣለቀበት አማልክቶቹንም ረገመ እንጂ። ንጉሡም ተቆጣ አንዲት ዓመት ያህልም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ በሰይፍ ራሱን ቆረጠው የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ተጋዳዩ ባለ አንበሳው አውሎግ አረፈ፡፡ የዚህ ቅዱስ ወላጆች ከሀገረ ንጽቢን የሆኑ በበጎ ሥራ ፍጹማን በወርቅና በብርም የበለጸጉ ናቸው። ለልጃቸውም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ አስተማሩት ከጥቂት ቀኖች በኋላ ወላጆቹ ብዙ ገንዘብን ትተውለት ሞቱ።
በአንዲትም ዕለት አውሎግ ያለህን ገንዘብህን ሁሉ ሽጠህ ለድኆች ሰጥተህ መከራ መስቀልህን ተሸክመህ ና ተከተለኝ የሚለውን የከበረ የወንጌልን ቃል አሰበና ወዲያውኑ ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች በትኖ ወደ አባ አውሎጊን ሔደ እርሱም በደስታ ተቀበለው።
ስለ ርሱ እንዲህ የሚለውን ራእይ አይቶ ነበር እነሆ ወዳንተ ጐልማሳ ይመጣል ተቀበለውና ከሚያገለግሉ መነኰሳት ጋር ቀላቅለው እየፈተነውም ሦስት ዓመት ያህል ኖረ ፍጹም የሆነ ቅድስናውንም በአየ ጊዜ የምንኵስናን ልብስ የመላእክትንም አስኬማ አለበሰው።
ከሰንበትም እስከ ሰንበት እየጾመ በብዙ ተጋድሎ ኖረ ምግቡም እንጀራና ጨው ነበረ በቀንና በሌሊትም ሰባት መቶ ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን ከስግደት ጋር ይጸልያል በዚህም ተጋድሎ አርባ ዓመት ኖረ።
ከዚህም በኋላ ያሰናብተው ዘንድ መምህሩ አባ አውሎጊንን ማለደውና ወደ በረሀ ሔደ ከአንዲት ታናሽ ዋሻ ውስጥም ገብቶ እየተጋደለ ኃምሳ ዓመት ኖረ። ለፍላጎቱም የሚያገለግሉት ሁለት አንበሶችን እግዚአብሔር ሰጠው በአንዲትም ዕለት ታመመ አንበሶቹንም እጠጣ ዘንድ የሞቀ ውኃ እሻለሁ አላቸው። አንዱ አንበሳም ወደ ተራራ ሒዶ እረኛ አግኝቶ ወደ አባ አውሎግ አመጣው በአየውም ጊዜ ሰገደለትና አባቴ ሆይ ምን ትሻለህ አለው። እርሱም የሞቀ ውኃ ታጠጣኝ ዘንድ እሻለሁ አለው እንዳለውም አደረገለት ከዚህም በኋላ አንበሳው እረኛውን ወደቦታው መለሰው።
ያም እረኛ ለእግሩ ተረከዝ ዓለሙ ሁሉ መጠኑ የማይሆን ጻድቅ ሰውን አገኘሁ ብሎ ለሰው ሁሉ ተናገረ በሰሙ ጊዜም ሰዎች ሁሉ ወደርሱ ተሰበሰቡ በሽተኞችንም ሁሉ አመጡለትና ፈወሳቸው።
በዚያ ወራትም መምህሩ አባ አውሎጊን ጣዖትን የሚያመልኩ የፋርስ ሰዎችን ወደ ቀናች ሃይማኖት ለመመለስ ወደ ፋርስ ሀገር ሊሔድ ፈለገ ዳግመኛም ልጁ አውሎግን ከእርሱ ጋር ሊወስደው ወደርሱ መልእክተኛ ሊልክ ሽቶ ሳለ መንፈስ ቅዱስ አንበሳውን አስገነዘበውና አጽፉንና ወንጌሉን አንሥቶ ተሸከመ። አባ አውሎግንም ጕዞን አመለከተው ተነሥቶም አንበሳውን ተከትሎ ወደ መምህር አውሎጊን ደረሰ እርሱም በደስታ ተቀበለው።
ሲጓዙም ከጤግሮስ ወንዝ ደረሱ ውኃውም ተከፍሎላቸው ተሻገሩ ወደ ሀገሩም ውስጥ በደረሱ ጊዜ አስተማሩአቸው ወደ ቀናች ሃይማኖትም መለሷቸውና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው።
በአንዲትም ዕለት ደግሞ ቅዱሳን በተራቡ ጊዜ ምግባቸውን ይፈልጉላቸው ዘንድ አባ አውሎግ አንበሶችን አዘዘ ሒደውም እንጀራ በአህያ ላይ ጭኖ የሚጓዝ ሽማግሌ አገኙ ሕፃንም ከእንጀራው ጋር አለ ።
አህያውንም ወደ ቅዱሳን አመጡት ከድንጋጤም የተነሣ ብላቴናው ሞተ ቅዱሳንም ጸልየው ሕፃኑ ድኖ ተነሣ ቅዱሳንም ተመገቡ አንበሶችም አህያውን ከእንጀራውና ከሕፃኑ ጋር ወደ ሽማግሌው መለሱት። ከዚህም በኋላ አባ አውሎግ ወደ በዓቱ ተመለሰና ጥቂት ታሞ አረፈ በታላቅ ክብርም ተቀበረ እነዚያ አንበሶችም መቃብሩን እየጠበቁ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖሩ ከዚያም በኋላ ወደ ዱር ገቡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የአባ ስልዋኖስ ረድእ አባ በትራ አረፈ። ይህም ቅዱስ በደብረ ሲና ካለች በዓቱ በነበረ ጊዜ ትርኅምትን ይጠብቅ ነበር በራትም ጊዜ ለሥጋው የሚያሻውን ይመገባል።
ፈርኑ በሚባል አገር ላይ ኤጲስቆጶስ በአደረጉት ጊዜ ትርኅምትን በማብዛት ሰውነቱን እጅግ አደከመ ደቀ መዛሙርቱም አባታችን ሆይ በገዳም በበኣትህ በነበርክ ጊዜ ትርኅምትን እንዲህ አላበዛህም ነበር አሉት ይህም አባት እንዲህ አላቸው "ያን ጊዜ በገዳም በችግር ውስጥ ነበርኩ ዛሬ ግን ከብዙዎች መካከል በአንድነት አለሁ የምሻውም ሁሉ ብዙ አለኝ ነገር ግን ሥጋዬን ቀጥቼ ብገዛው ይሻላል እንዲህም እየተጋደለ ኖረ ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages