ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 10 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 10

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ዐሥር በዚች ቀን ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የእልፍዮስ ልጅ #ሐዋርያው_ቅዱስ_ያዕቆብ በሰማዕትነት ሞተ፣ የንጉሥ ኑማርያኖስ ልጅ #የከበረ_ዮስጦስ በሰማዕትነት ሞተ፣ በገድል የተጠመደ #አባ_ኤስድሮስ አረፈ፣ የፋርስ ሀገር ኤጲስቆጶስ #አባ_ፌሎ በሰማዕትነት ሞተ።


የካቲት ዐሥር በዚች ቀን ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የእልፍዮስ ልጅ የከበረ ሐዋርያ ያዕቆብ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ሐዋርያ በብዙ ሀገሮች ውስጥ ከሰበከ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ ወደ ምኲራብም ገብቶ የክብር ባለቤት የጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት በግልጥ አስተማረ። ከእርሱ ለሚሰሙትም ሁሉ ብዙ ተአምራትን አደረገ። ንጹሕ በሆነ ልቡናም በእግዚአብሔር አመኑ። ራሳቸውንም አጸኑ። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም በልቡናው አሰበ፡፡ እንዲህም አለ። ሕዝቡ ከእርሱ ሰምተው እንዴት ያምናሉ አለ። እርሱም ሕዝቡ ወደተሰበሰቡበት ወደ ምኩራብ ገባ። ከአይሁድም የተቀመጡ የተሰበሰቡ ብዙ ሰዎችን አገኘ። በፍጹም ታላቅ ደስታ ያስምራቸው ዘንድም በመካከላቸውም ገባ። ለሁሉም በቃሉ ማስተማሩን አበዛ። ያለመፍራትም ሃይማኖቱን ገለጠ። አንድ ለሆነው ለእግዚአብሔር ልጅ ምስክር ሆነ። "የሕይወት ቃል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ አምላክ ነው። በእውነትም የእግዚአብሔር ልጅ ነው። እርሱ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ከአብ ጋር ነበርና። እርሱ በአብ አለ፤ አብም በእርሱ አለ። እርሱ የአብ ቃል ነው። እርሱ ሰውን በአርአያችንና በምሳሌያችን እንፍጠር አለ። እርሱ በሰማይ አለ። እርሱ ከአባቱ ጋር አለ። እርሱ በኪሩቤል ሰረገላ ይቀመጣል። ሱራፌልም ያመሰግኑታል። እርሱ በድንግል ማርያም ማሕፀን የተወሰነ በልዕልና በገናንነቱ ሥልጣን ነው። እርሱ ድንግል ማርያም የወለደችው ጌታችን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሰው የሆነ አምላክ ነው"። አንድ ሰው ስንኳን ሳይፈራ በተሰበሰቡት መካከል የሐዋርያው ምስክርነት ይህ ነበር። በእውነት አንድ ለሆነው ለእግዚአብሔር ልጅ ልደትም ምስክር ሆነ። እርሱ ነበርና። በሞቱም፣ በትንሣኤውም፣ ወደ አባቱ ወደ ሰማይ ስለማረጉም ምስክ ሆነ። ለተሰበሰቡትም በክርስቶስ ስለማመን አስተማራቸው።
የተሰበሰቡትም የሐዋርያውን ትምህርት በሰሙ ጊዜ ከእርሱ ጋር ካለው ከአባታቸው ከሰይጣን የተነሳ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ላይ ፈጽመው ተቆጡ። ሁሉም ተሰብስበው ተቀመጡ። የተሰበሰቡት ሁሉ ደሙን ፈለጉ። ነገሩን የሰሙትም የተባረከ ሐዋርያን ያዙት። ከንጉሥ ከቀላውዴዎስም ወሰዱት። የሐሰት ምስክሮችንም በእርሱ ላይ አስነሡ። ለንጉሡም "ይህን ጥፋተኛ ሰው በሀገሩ በአውራጃው ይዘናል" አሉት፤ "እኔ የእግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ነኝ ይላቸዋል። ለንጉሡ እንዳይገዙም ይከለክላል" አሉት። ስለተባረከው ሐዋርያ ይህን ነገር በሰማ ጊዜም እስከሚሞት ድረስ በድንጋይ ይወግሩት ዘንድ አዘዘ። አይሁድንም እግዚአብሔር ረገማቸው። ንጉሡ አይሁድን እንዳዘዛቸውም በድንጋይ ወገሩት። ከዚህ በኋላ ቡሩክ የሚሆን የእልፍዮስ ልጅ የሐዋርያው የቅዱስ የያዕቆብ ምስክርነት የካቲት ዐሥር ቀን ሆነ። በኢየሩሳሬም ቤተ መቅደስ ተቀበረ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የንጉሥ ኑማርያኖስ ልጅ የከበረ ዮስጦስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ በጦር ሜዳ እያለ እኅቱ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስን አግብታ ንጉሥም አደረገችው ከጦርነትም በተመለሰ ጊዜ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ዲዮቅልጣኖስ ክዶ አገኘውና እጅግ አዘነ።
የሀገሩም ሰዎች በአዩት ጊዜ ወደርሱ ተሰብስበው ዲዮቅልጥያኖስን እኛ እንገድለዋለን አንተም ጌታችን በመንግሥትህ ዙፋን ላይ ትቀመጣለህ አሉት እርሱ ግን ይህን ስለአልፈለገ እንዳይገድሉት ከለከላቸው ከምድራዊት መንግሥት ሰማያዊት መንግሥትን መርጧልና።
ከዚህም በኋላ ወደ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ቀርቦ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ ንጉሡም ፈርቶታልና ጌታዬ ዮስጦስ ሆይ ይህን ታደርግ ዘንድ ያስገደደህ ማነው አለው የከበረ ዮስጦስም በምስክርነቴ ደሜን እንዳፈስ ካልጻፍክ ሕዝቡን በአንተ ላይ አስነሥቼ ከመንግሥትህ እንደማስወጣህ የክብር ባለቤት ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ነው ብሎ ማለ።
በዚያንም ጊዜ ንጉሡ ፈርቶ ከሚስቱ ከታውክልያ ከልጁ ከአቦሊ ጋር ወደ ግብጽ አገር እንዲወስዱአቸው አዘዘ የእስክንድርያንም ገዥ አብዝቶ እንዲሸነግላቸው ምናልባት ልባቸው ቢመለስ እንዳያሳዝናቸውም አለዚያ እያንዳንዱን እንዲለያያቸው አዘዘው።
ወደ ግብጽ አገርም በደረሱ ጊዜ ከእርሳቸው ጋር የንጉሥ ደብዳቤ አገልጋዮችም አሉ የእስክንድርያም ገዥ በአያቸው ጊዜ እጅግ ፈራ ሊሸነግለውም ጀምሮ ቅዱስ ዮስጦስን ጌታዬ እንዲህ አታድርግ ክብርህ ይሻልሃል አለው የከበረ ዮስጦስም ነገር አታብዛ አለው መኰንኑም ፈርቶ ቅዱስ ዮስጦስን ወደ ላይኛው ግብጽ ወደ እንዴናው ከተማ ሰደደው ልጁ አቦሊን ወደ ሀገረ ብስጣ ሚስቱ ታውክልያን ወደ ሀገረ ፃ ላካቸው ከአገልጋዮቹም የሚአገለግሏቸው አንዳንድ ሰጣቸው የከበረ ዮስጦስንም በእንዴናው ከተማ ብዙ ከአሠቃዩት በኋላ ራሱን ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ ከሥጋውም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ ለበሽተኞችም ታላቅ ፈውስ ሆነ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት በገድል የተጠመደ ምሁር የሆነ የአለሙ ሁሉ መምህር አባ ኤስድሮስ ፈርማ ከሚባል አገር አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ በምስር አገር የከበሩ ባለጸጎች ናቸው ለእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳትም አባ ቴዎድሮስና አባ ቄርሎስ ዘመዶች ናቸው ከእርሱም በቀር ልጅ የላቸውም መንፈሳዊ ትምህርትን ሁሉ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት ሁሉ አስተማሩት ግልጽ አድርጎ አጠናቸው ጠበቃቸውም ዳግመኛም የዮናናውያንን የፍልስፍና ትምህርት የከዋክብትን አካሔድና ዓለምን መዞራቸውን ተማረ በእውቀቱና በጥበቡም ከብዙዎች ከፍ ከፍ አለ በገድልም የተጠመደ ትሑትና የሚተጋ ሆነ።
በሀገሮችም ያሉ ሰዎች ስለርሱ በሰሙ ጊዜ በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ይሾሙት ዘንድ ተማክረው ከኤጲስቆጶሳቱ ጋር ተስማሙ። በሌሊትም ወጥቶ ሸሸ ወደ ፈርማ ገዳም ደርሶ በዚያ መነኰሰ ከዚያም ወጥቶ ወደ አንዲት አነስተኛ ዋሻ ገብቶ ብቻውን በውስጧ ብዙ ዘመናት ኖረ ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትንም ደረሰ ከእርሳቸውም ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንት የደረሳቸው አሉ የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍቶችን ብሉያትና ሐዲሳትን ተረጐመ።
የመጻሕፍቶቹም ቁጥራቸው ዐሥራ ስምንት ሺህ ነው እሊህም ድርሳናት ተግሣጻት ጥያቄዎችና መልሶች ወደ ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት የተላኩ መልእክቶች ናቸው ወደ ምእመናንም ወንዞች ውኃዎችን እንደሚያፈልቁ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ የሚያፈልቃቸው ሆኗልና።
ይህንንም በጎ ሥራውን ሲፈጽም መልካም ጉዞውንም አከናውኖ ወደ በጎ ሽምግልና ደርሶ እግዚአብሔርንም አገልገሎ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የፋርስ ሀገር ኤጲስቆጶስ አባ ፌሎ በሰማዕትነት ሞተ። ይህንንም ቅዱስ ለእሳት እንዲሠዋ ለፀሐይም እንዲሰግድ የፋርስ ንጉሥ አዘዘው እምቢ በአለውም ጊዜ ታላቅ ሥቃይን አሠቃይቶ ራሱን በሰይፍ ቆረጠው በመንግሥተ ሰማያት የሰማዕትነትን አክሊል ተቀበለ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages