ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 9 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 9

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ዘጠኝ በዚህች ዕለት #የአቡነ_እስትንፋሰ_ክርስቶስ የመነኮሱበት በዓል ነው፣ የከበረ በሶርያ አገር ላሉ መነኰሳት አባት የሆነ ታላቁ #አባ_በርሱማ አረፈ፣ የከበረ #ቅዱስ_ጳውሎስ_ሶርያዊ በሰማዕትነት ሞተ፡፡


የካቲት ዘጠኝ በዚህች ዕለት የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ የመነኮሱበት በዓል ነው፡፡ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ አባታቸው መልአከ ምክሩ እናታቸው ወለተ ማርያም ይባላሉ፡፡ የተወለዱበት ልዩ ቦታው ወሎ ክፍለ ሀገር ዳውንት ነው፡፡ በተወለዱ ዕለት ተነሥተው በእግራቸው ቆመው ሦስት ጊዜ ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ብለው ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል፡፡ የስማቸው ትርጓሜ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ አንድም የክርስቶስ እስትንፋስ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል እየጠበቃቸውና በመንገዳቸው ሁሉ እየመራቸው ነው ያደጉት፡፡ መንፈስ ቅዱስ ልቡናቸውን ብሩህ አድርጎላቸው በ5 ዓመታቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃላትን፣ ብሉያትንና ሐዲሳትን፣ ድርሳናትንም ጠንቅቀው ዐውቀዋል፡፡
በተወለዱ በ14 ዓመታቸው ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ደብረ ሐይቅ ገዳም ሄደው ከባሕር ዳር ቆመው የሙሴን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ባሕሩን አሻግሯቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተዋል፡፡ ለ3 ዓመታት ያህል በኃይቅ ገዳም ለመነኮሳት እንጨት በመልቀምና ውሃን በመቅዳት ለአባቶች መነኮሳት ምግብ የሚሆናቸው ዓሣ ከባህር ውስጥ በማውጣት አገልግለዋል፡፡ አባታችን እስትንፋሰ ክርስቶስ 40 መዓልትና 40 ሌሊት ከጾሙ በኋላ ምንም እህል ሳይቀምሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ለሙሴ በደብረ ሲና እንደሰጠው ለአባታችንም ወደ እርሳቸው መጥቶ ዓሥሩን ቃላተ ኦሪትና ስድስቱን ቃላተ ወንጌል በውስጣቸው የተጻፈባቸው ሁለት ጽላቶችን ሰጥቷቸዋል፡፡ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ከሠሩ በኋላ ዕለቱን ስንዴ ዘርተው፣ ወይን ተክለው፣ ጽድን ወይራንና ግራርን ተክለው በአንዲት ቀን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ዕለቱን አድርሰዋል፡፡ ስንዴውን ለመሥዋዕት ወይኑን ለቍርባን በተአምራት አድርሰዋል፡፡
አባታችን በጸሎት ላይ እንዳሉ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተልኮ መጥቶ አባታችንን በደመና ጭኖ ወስዶ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ፊት አቆማቸው፡፡ ጌታንም በቅዱሳኑ ሁሉ እንዲባረኩ ካደረጋቸው በኋላ መልአኩን ‹‹ወደ ተወለድኩባትና ወደ ኖርኩባት ቦታ ወደ ኢየሩሳሌም አድርሰው›› ብሎት ኢየሩሳሌምን አሳልሞ ሀገራችን መልሶ አምጥቷቸዋል፡፡ አባታችን ሁሉንም የኢትዮጵያን ቅዱሳት ገዳማትን ተዘዋውሮ ሲጎበኙ በሕይወተ ሥጋ የሌሉት የየገዳማቱ ቅዱሳን ሁሉ በአካል ይገለጡላቸው ነበር፡፡ ጎጃም ውስጥ እያስተማሩ፣ እያጠመቁ፣ የታመሙትን እየፈወሱ፣ የዕውራንን ዐይን እያበሩና ሙታንን እያሥነሱ ብዙ ካገለገሉ በኋላ ለዘጠኝ ዓመታት በባሕር ውስጥ ገብተው ቁልቁል ተዘቅዝቀው ለኢትዮጵያ ጸልየው የምሕረት ቃልኪዳን ተቀብለዋል፡፡ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ጌታችን መጥቶ ‹‹ከመነኮሳት ሁሉ ብልጫ ያለህ ወዳጄ ሆይ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ምሬልሃለሁ ከዚህች ባሕር ውጣ›› በማለት በሞት የሚያርፉበትን ቦታ ነግሯቸዋል፡፡
ጻድቁ ወደ ደብረ አሰጋጅ በሚሄዱበት ጊዜ ጸሐይ ልትገባ ስትል ‹‹በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አውግዤሻለሁ ለመስፍን ኢያሱ በገባኦን እንደቆምሽ አሁንም ቀጥ ብለሽ ቁሚ›› ብለው ገዝተው ፀሐይን አቁመዋል፡፡ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስም ደብረ አሰጋጅ ሲደርሱ ፀሐይ አፍ አውጥታ ‹‹አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ እገባ ዘንድ ፍታኝ›› ስትላቸው ‹‹እግዚአብሔር ይፍታሽ›› ባሏት ጊዜ ጠልቃለች፡፡
ጻድቁ ሌላው በእጅጉ የሚታወቁበት አንድ ትልቅ ቃል ኪዳን አላቸው፡፡ በአምላክ ልቡና የሚገኝ፣ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ልቡና የሚገኝ፣ በቅዱስ ሚካኤልና በቅዱስ ገብርኤል ልቡና የሚገኝ እንደ መልክአ መድኃኔዓለም ያለች እጅግ አስገራሚ ጸሎት አለቻቸው፤ እርሷን ጸሎት በጸለዩ ጊዜ እልፍ ነፍሳትን ከሲኦል ያወጣሉ፡፡
ጸሎቷም የመድኃኔዓለምን የሰውነት ክፍሎች በሙሉ እየጠቀሰች እያንዳንዱ የሰውነት ክፍሎቹ የተቀበሉትን ጸዋትዎ መከራዎች ሁሉ ታዘክራለች፡፡ በእያንዳንዱ ክፍልም የጸሎት ማሳረጊያ አቡነ ዘበሰማያት ይደግማሉ፡፡ ንስሓ የገባ ኃጢአተኛ ሰው እንኳን ቢሆን ይህችን የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስን ጸሎት በጸለየ ጊዜ ሺህ ነፍሳትን ከሲኦል እንደሚያወጣ ጌታችን በማይታበል ቃሉ ለአባታችን ነግሯቸዋል፡፡ እያንዳንዱን የመድኃኔዓለምን የሰውነት ክፍሎች በሙሉ እየጠቀሰች መከራዎቹን የምታዘክረውን ይህቺን በአምላክ ልቡና ያለች ግሩም የሆነች ጸሎት ነፍሳትን ከሲኦል አታወጣም ብሎ የሚጠራጠር ቢኖር መንግስተ ሰማያትን አያያትም፡፡ ጻድቁ ታኅሣሥ 8 ቀን ተወልው ሚያዝያ 9 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል በዚህች ዕለትም የምንኩስናቸው በዓል ይከበራል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የከበረ በሶርያ አገር ላሉ መነኰሳት አባት የሆነ ታላቁ አባ በርሱማ አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ሳሚሳጥ ከሚባል አገር ሰዎች ውስጥ ናቸው አንድ በዋሻ ውስጥ የሚኖር ሰው በእርሱ ላይ ትንቢትን ተናገረ ከመወለዱ አስቀድሞ ለአባቱ እንዲህ አለው የትሩፋቱ ዜና በሶርያ ሀገር ሁሉ የሚሰማ ጣዕም ያለው ፍሬ ከአንተ ይወጣል ከእርሱ የሚሆነውንም አስረዳው።
ተወልዶም አድጎ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ በደረሰ ጊዜ ከወላጆቹ ሸሽቶ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ደርሶ በዚያ ስሙ አብርሃም ከሚባል ሰው ዘንድ ተቀመጠ እርሱም ወላጆቹን ስለፈራ ከዚያ ገዳም ሰደደውና ሒዶ በአለት ውስጥ ኖረ በዚያም ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ ወሬውም በሶርያ አገሮች ሁሉ በተሰማ ጊዜ ብዙዎች ደቀመዛሙርት ወደርሱ ተሰበሰቡ የዚያ ቦታ ውኃ ግን እጅግ መራራ ነበር በላዩ በጸለየ ጊዜ ተለውጦ ጣፋጭ ሆነ።
እግዚአብሔርም በእጆቹ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ ከእርሳቸውም በአንዲት ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ከበአቱ ርቆ ሳለ የፀሐይ መግቢያ ሰዓት ተቃረበ የክብር ባለቤት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነው ወደ በአቱም እስቲደርስ ያን ጊዜ ፀሐይን አቆመለት።
በሌላ ጊዜም እንዲህ ሆነ ረዓም የምትባል አገር ነበረች ስዎቿም ከሀዲዎች ናቸው። በላያቸውም ዝናብ ተከለከለ በተጨነቁም ጊዜ ወደ ከበረ አባ በርሱማ መጥተው ለመኑት እርሱም ገሠጻቸው እንዲህም አላቸው ከክህደታችሁ ተመልሳችሁ በእግዚአብሔር ብታምኑ እርሱ ብዙ ዝናብን ያዘንብላችኋል እነርሱም እናምንበታለን አሉት። በዚያን ጊዜ ጌታችንን ለመነውና ብዙ ዝናብ ዘነበላቸው የሀገር ሰዎችም ሁሉ በጌታችን አመኑ።
እንዲሁም ሰዎቿ ከሀድያን የሆኑ ሌላ ሀገር ነበረች እነርሱንም ገሥጾ መክሮ አስተምሮ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መለሳቸው የጣዖቶቻቸውንም ቤቶች አፈረሰ። ይህም ቅዱስ ለራሱ ቦታ አዘጋጅቶ በዚያ ሳይቀመጥ ሃምሣ አራት ዓመት ቁሞ ኖረ ከመትጋት የተነሣ ሲደክመው ከናሱ ግድግዳ ላይ ተደግፎ ያሸልባል በየሰባት ቀንም ይጾማል።
የከበረ አባ ስምዖን ዘዓምድ ሊያየው ወዶ ወደርሱ ላከ የትሩፋቱንና የቅድስናውን ዜና ከብዙዎች ሰዎች ሰምቶ ነበርና እርሱም ወደ አባ ስምዖን መጥቶ እርስበርሳቸው በረከትን ተቀባበሉ ከዚህም በኋላ ወደ ገዳሙ ተመለሰ።
በሶርያ አገርም አስተማረ በፊታቸው ተአምራትን በአደረገ ጊዜ በትምህርቱ ብዙዎች አመኑ። ዳግመኛም ወደ ታናሹ ቴዎዶስዮስ ንጉሥ ሒዶ በቀናች ሃይማኖት አጸናው ንጉሡም ብዙ ገንዘብን ሰጠው እርሱ ምንም ምን አልወሰደም በአንጾኪያም አገር በኤጲስቆጶሳቱ ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዲኖረው ንጉሥ ጻፈለትና ኀቲም ቀለበቱን ሰጠው።
በከሀዲው ንስጥሮስ ምክንያት ሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት በኤፌሶን ከተማ በተሰበሰቡ ጊዜ ከእሳቸው ጋር ይህ ቅዱስ አለ። ከእርሳቸውም ጋር ንስጡርን አወገዘው ዳግመኛም በአንጾኪያ አገር ያሉ መኳንንት መሳፍንት ሹማምንት ሁሉም ይታዘዙለት ዘንድ ንጉሥ ደብዳቤን ጻፈለት እርሱም በጎ ሥራ እንዲሠሩ በሃይማኖት እንዲጸኑ የሚያዝዝ ደብዳቤ በመጻፍ በንጉሥ ኀቲም ቀለበት እያተመ ለሀገሮች ሁሉ የሚልክ ሆነ።
ክፋዎች ሰዎችም ጠሉት በንጉሥም ዘንድ ነገር ሠሩበት እንዲህም አሉት እነሆ አባ በርሱማ እንደ ዓለም ሰው ሁኖ ይበላል ይጠጣል መልካም ልብስንም ይለብሳል ንጉሥም ሰለ አባ በርሱማ የተነገረውን ያረጋግጥ ዘንድ ከባለሟሎቹ አንዱን ላከ።
የንጉሡም ባለሟል ወደ አባ በርሱማ በደረሰ ጊዜ በእርሱ ላይ ከተነገረው ምንም ምን ያገኘው የለም ከዚህም በኋላ ወደ ንጉሥ ወሰደው ንጉሥም ቀድሞ ከሚያውቀው ከመንፈሳዊ ሥራው ልውጥ ሆኖ ያገኘው ነገር የለም ንጉሡም ታላቅ ክብርን አከበረው ወደ ቦታውም መለሰው።
መናፍቁ ንጉሥ መርቅያንም የኬልቄዶንን ጉባኤ በሰበሰበ ጊዜ የንጉሥ አማካሪዎች አባ በርሱማን እንዳያስመጣ ንጉሡን መከሩት እንደማይፈራና እንደማያፍር ለሰው ፊትም እንደማያዳላ ተከራክሮ ረትቶ እንደሚያሳፍራቸውም ስለሚያውቁ ነው።
አንዱን ክርስቶስን ወደ ሁለት የከፋፈሉበት ይህ ጉባኤ በተፈጸመ ጊዜ የከበረ አባ በርሱማ ተጣላቸው ነቀፋቸው ቃላቸውንም በመሻር አወገዛቸው እነርሱም ወደ ንጉሥ ወንጅለው በጽሑፍ ከሰሱት ንጉሡም ልኮ ወደርሱ አስቀረበው ግን በላዩ ስለ አደረ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ ሊቃወመው አልቻለም በሊቁ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ላይ ሰለ አደረገችው ክፋት ንግሥቲቱን ረገማት ከጥቂት ቀንም በቀር አልኖረችም በክፉ አሟሟትም ሞተች።
ከዚህም በኋላ መናፍቃን የሚቃወሙት ሆኑ ምእመናን እንዳይታዘዙለት ወደ ሀገሮች ሁሉ ጽፈው የሚልኩ ሆኑ እነርሱ ግን አልተቀበሏቸውም ለእርሱ መታዘዛቸውንም አልተዉም። ዳግመኛም በጐዳና ሸምቀው ይገድሉት ዘንድ ሁለት መቶ መናፍቃን ሰዎች ከመናፍቃን ኤጴስቆጶሳት ጋር ተስማምተው ወደ እርሳቸው እንዲመጣና በአንድነት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚሔዱ ሁነው ላኩበት መጥቶም አብሮ በተጓዘ ጊዜ ደንጊያዎችን አንሥተው ጣሉበት ደንጊያዎቻቸውም ወደ ራሳቸው የሚመለሱ ሆኑ በፍርሃትም ከእርሱ ሸሹ።
እግዚአብሔርም ከዚህ ዓለም እሥረኛነት ሊአወጣው በወደደ ጊዜ መልአኩን ወደርሱ ልኮ ከአራት ቀን በኋላ ከዓለም እንደሚፈልስ ነገረው በዚያንም ጊዜ በዙሪያው ወዳሉ አገሮች ምእመናንን ያጽናናቸው ዘንድ ረድኡን ላከው እርሱም ሲዞር የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራስ ወደምትኖርበት ቦታ ደረሰና የከበረች የቅዱስ ዮሐንስን ራስ እጅ ነሣት ስለ ከሀዲው ስለ ንጉሥ መርቅያን በማልቀስ ለመነ። እንዲህ የሚልም ቃል ከመጥምቁ ዮሐንስ ራስ ወጣ አባ በርሱማ ወደ እግዚአብሔር ስለ ከሰሰው ያ መርቅያን ሙቷልና አትፍራ። የከበረ አባ በርሱማ ረድኡን ባረከውና በሰላም አረፈ።
ከበአቱም ደጃፍ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን መሰሶ ተተክሎ ታየ። ምእመናንም ሁሉ ከሩቅ አይተው ወደርሱ መጡ አርፎም አገኙት። ከሥጋውም ተባረኩ በላዩም አለቀሱ ከእርሱም ስለመለየታቸው እጅግ አዘኑ እንደሚገባም አየዘመሩና እያመሰገኑ ገንዘው በመቃብር አኖሩት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የከበረ ሶርያዊ ጳውሎስ በሰማዕትነት ሞተ፡፡ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ የሶርያ ሰዎችና በእስክንድርያ ከተማ የሚኖሩ ነጋዴዎች ናቸው ከዚህም በኋላ በእስሙናይን ከተማ የሚኖሩ ሆኑ።
ወላጆቹም ሲሞቱ ብዙ ገንዘብ ተዉለት ከዚህም በኋላ ከሀድያን ነገሥታትና መኳንንት በክርስቶስ የሚያምኑ ምእመናንን እንደሚያሠቃዩአቸውና እንደሚገድሏቸው ሰማ በዚያንም ጊዜ ተነሥቶ ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች በተነ። ከዚህም በኋላ የወደደውን መንገድ ይመራው ዘንድ ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየ ጌታችንም መልአኩን ሱርያልን ላከ እርሱም በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም የሚደርስበትን ሥቃይ ሁሉ ነገረው እነሆ ከአንተ ጋር እንድኖር እንዳጽናናህም እግዚአብሔር አዞኛልና አትፍራ አለው።
በዚያንም ጊዜ ተነሥቶ ወደ እንዴናው ከተማ ሔደ በመኰንኑም ፊት ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ልብሱን አራቁተው ይገርፉት ዘንድ አዘዘ።
ይህንንም አደረጉበት ከዚህም በኋላ በጐኖቹ ውስጥ መብራቶችን አስገብተው ለበለቡት እሳት ግን አልነካችውም መኰንኑም ለጣዖት እንዲሰግድ ብዙ ገንዘብ አመጣለት የተመሰገነ ጳውሎስም ወላጆቼ ሲሞቱ ዐሥራ ሰባት የወርቅ መክሊት ትተውልኝ ነበር። ስለ ክብር ባለቤት ክርስቶስ ፍቅር ትቼ ለድኆች መጸወትኩት ወደዚህ ወደተናቀ ገንዘብህ እንዴት እመለሳለሁ አለው።
መኰንኑም ሰምቶ ብረቶችን በእሳት አግለው በአፉና በጆሮዎቹ እንዲጨምሩ አዘዘ ይህንንም አደረጉበት ሱርያል መልአክም ወርዶ ዳሠሠውና አዳነው ሁለተኛም እባቦችን በላዩ ሰደዱ አልነኩትም ምላሱንም ቆረጡ ጌታችንም አዳነው።
መኰንኑም ወደ እስክንድርያ ከተማ በሚሔድ ጊዜ ከእርሱ ጋር ወሰደው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመርከብ ውስጥ ተገለጠለትና አጽናናው የዚህም ቅዱስ ኤሲ የሚባል ወዳጅ አለው እኅቱ ቴክላም። ጌታችንም ሥጋው ከሥጋቸው ነፍሱ ከነፍሳቸው ጋር እንደሚሆን ነገረው ያን ጊዜ እሊህ ቅዱሳን በእስክንድርያ ከተማ በእሥር ቤት ነበሩ የከበረ ጳውሎስም ወደርሳቸው በደረሰ ጊዜ እርስበርሳቸው ተሳሳሙ በመገናኘታቸውም ነፍሳቸው ደስ ብሏት እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
መኰንኑም ወደ እንዴናው ከተማ በሚመለስ ጊዜ የቅዱስ ጳውሎስን ራስ ቆርጠው ሥጋውን ከጥልቅ ባሕር ወረወሩ የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ ምእመናንም ሥጋውን በሥውር ወስደው በአማሩ ልብሶች ገነዙት በእነርሱም ዘንድ አኖሩት ከእርሱም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages