ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 15 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 15

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ዐሥራ አምስት በዚህች ቀን ከዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነቢይ #ቅዱስ_ዘካርያስ አረፈ፣ ሰብስጥያ በምትባል አገር የሰማዕታት #ቅዱሳን_አርባ_ሐራ_ሰማይ ቤተ ክርስቲያናቸው ተከበረች፣ በገድል ተጠምዶ የኖረ #ቅዱስ_አባ_በፍኑትዮስ አረፈ።


የካቲት ዐሥራ አምስት በዚህች ቀን ከዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ታላቅ ዕውነተኛ ነቢይ ዘካርያስ አረፈ። እርሱም ከሌዊ ነገድ ነው የአባቱም ስም በራክዩ ነው በገለዓድም ወለደው በባቢሎንም ምርኮ ጊዜ ተማረከ ከዚያ ሳለም በላዩ የወረደለትን መለኮታዊ ትንቢትን ተናገረ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ አንደበት ጠቃሚዎች የሆኑ ብዙ ቃሎችን ተናገረ።
ለኢዮሴዴቅም እንዲህ ብሎ ትንቢትን ተናገረ በኢየሩሳሌም እግዚአብሔርን ካህን ሆኖ የሚያገለግል ልጅን ትወልዳለህ ከሚጠትም በኋላ እንደቃሉ ሆነ። ለሰላትያልም ትንቢት ተናገረለት ባረከውም ወንድ ልጅ ትወልዳለህ ስሙንም ዘሩባቤል ትለዋለህ እርሱም በኢየሩሳሌም መቅደስን ይሠራል አለው ዳግመኛም ለፋርስ ንጉሥ ተናገረ የድል ምልክትንም ገለጠለት። ጌታችን በውርንጫዪቱና በታላቂቱ አህያ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መምጣቱ ተናገረ።
ይሁዳም መድኃኒታችንን ክርስቶስን አሳልፎ በመስጠቱ ስለ ተቀበለው ሠላሳ ብር ትንቢት ተናገረ። መድኃኒታችንም በሚሰቀልበት ዐርብ ሌሊት ስለ ሐዋርያት መበተን ተናገረ። በቀትር ጊዜም ስለ ፀሐይ መጨለም ተናገረ። ስለ እስራኤል ልጆች ኀዘንም እንዲህ አለ ያን ጊዜ የወጉትን ያዩት ዘንድ አላቸው ወደ ኀዘንም ይመለሳሉ እንደ ሚወዱትም ያለቅሱለታል ሰው ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን ጽኑ ኀዘንን ያዝናሉ። የትንቢቱም ወራት በተፈጸመ ጊዜ በሰላም አረፈ በነቢያት መቃብርም ተቀበረ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ሰብስጥያ በምትባል አገር የሰማዕታት አርባ ሐራ ሰማይ ቤተ ክርስቲያናቸው ተከበረች።
በስማቸው የተሠራች ቤተ ክርስቲያናቸውን ታላቁ አባት ቅዱስ ባስልዮስ በዚህች ዕለት አከበራት። ስለ እነርሱም ድርሳናትን ደረሰ። በዚህችም ዕለት በዓላቸውን አከበረላቸው። እነዚህም ቅዱሳን በአልፊያኖስ ዘመን ተጋደሉ እርሱም ከንጉሠ ነገሥት ቈስጠንጢኖስ ከመኳንንቶቹ አንዱ ነው። ከአይሁድ አገሮችም በአንዱ ላይ አነገሠው ክርስቲያኖችንም እንዲጠብቃቸውና እንዲያከብራቸው አዝዞት ነበር።
እርሱ ግን ወደዚያ አገር በደረሰ ጊዜ ጣዖትን አመለከ ሰዎችንም ሁሉ ጣዖት እንዲአመልኩ አስገደዳቸው ብዙዎች ምእመናንም ተነሥተው እርሱንና የረከሱ ጣዖቶቹን ረገሙ። በዚያችም ሌሊት እሊህ አርባ ጭፍሮች ወደ መኰንኑ ደርሰው በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም ምስክር ይሆኑ ዘንድ እርስ በርሳቸው ተስማሙ።
በእንቅልፋቸውም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ ለሰውነታቸው ብርታትን ሰጣቸው በጥዋትም ተነሥተው የጭፍራ አለቃ በሆነ በአግሪጎላዎስ ፊት ቁመው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመኑ። በላያቸውም ተቆጥቶ አስፈራራቸው እነርሱ ግን አልፈሩም በደንጊያም እንዲወግሩአቸው አዘዘ። በአቅራቢያቸውም የውሽባ ቤት በአጠገቧ ያለ የውኃ ጒድጓድ ነበረች ከውርጭ ጽናትም የተነሣ ትረጋለች በውስጥዋም ይጥሏቸው ዘንድ መኰንኑ አዘዘ።
በውስጥዋም በጣሉአቸው ጊዜ ከውርጭ ጽናት የተነሣ ሕዋሳታቸው ተቆራረጠ ከእርሳቸውም አንዱ ፈራ ከዐዘቅቱም አውጡኝ ብሎ ወጣ ወደ ወሽባው ቤትም ገባ ፈጥኖም ሞተ ዋጋውንም አጠፋ የፈለገውንም አላገኘም። አርባ አክሊላትም ከሰማይ ሲወርዱ በሠላሳ ዘጠኙ ሰማዕታት ላይም ሲቀመጡ አንዱ አክሊልም በመልአኩ እጅ ተንጠልጥሎ ሲቀር ከወታደሮች ይህን ያየ ከዚያ ተነሥቶ በጌታ አምኖ ልብሶቹንም አውልቆ ቅዱሳን ወደአሉበት ወደ ዐዘቅቱ ወረደ በመልአኩ እጅ ተንጠልጥሎ የቀረውንም አክሊል ወሰደ። እሊህም ጐልማሶች ሰማዕታት በዚያች
ዐዘቅት በነበሩበት ጊዜ እናቶቻቸው ያጽናኗቸውና ያስታግሡአቸው ነበር። እነርሱም ብዙ ጊዜ ቆዩ እንጂ ቶሎ አልሞቱም። ከሀድያንም ጭኖቻቸውን ሊሰብሩ ፈለጉ ፈጥነው እንዲሞቱ እግዚአብሔርም ወዲያውኑ ነፍሳቸውን ወሰደ ጭኖቻቸውን መስበር አልተቻላቸውም። ከዚህ በኋላም በእሳት ሥጋቸውን እንዲአቃጥሉ በተሽከረካሪም ጭነው ወስደው ወደ ባሕር እንዲጥሏቸው መኰንኑ ወታደሮችን አዘዘ። ሲጭኑአቸውም ያልሞተ ሕፃን አገኙና ተውት እናቱም ከሠረገላው ውስጥ ልትጥለው ተሸክማው ሮጠች ወታደሮችም ስለአልሞተ ከለከሉአት ወዲያውኑ በጫንቃዋ ላይ ሙቶ ከቅዱሳን ጋር እንዲሆን ወደ ተሽከርካሪው ጣለችው። ወደ ስብስጥያ ከተማ ጭነው ወስደው በእሳት አቃጠሉአቸው ወደ ባሕርም ጣሉአቸው።
ከዚህም በኃላ በሦስተኛ ቀን ለስብስጥያ አገር ኤጲስቆጶስ ተገለጡለተ። እንዲህም አሉት ወደዕገሌ ወንዝ ሐድ ሥጋችንንም ታገኛለህና አሸክመህ አምጣው ኤጴስቆጶሱም ከካህናት ጋራ በሌሊት ተነሥቶ ወደ ወንዙ ሔዱ የቅዱሳንንም ሥጋቸውን በአንድ ቦታ ተሰብስቦ እንደ ከዋክብት እያበራ አገኙት ከእርሳቸውም አንድ እንኳን አልጐደለም በክብር ተሸክመው ወስደው በመልካም ቦታ በክብር አኖሩአቸው። ዜናቸውም በአራት ማእዘን ተሰማ መታሰቢያቸውንም አደረጉ በዓለም ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ታነፀላቸው ከሥጋቸውም ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚች ዕለት በገድል ተጠምዶ የኖረ አባ በፍኑትዮስ አረፈ። ይህም አባት ከታናሽነቱ መንኵሶ በጾም በጸሎት በስግደትም እየተጋ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ። ያማረ የምንኵስናውን ሥራ በፈጸመ ጊዜ መነኰሳት ከሚኖሩበት ገዳማት ርቆ ወደሚገኝ በረሀ ውስጥ ይገባ ዘንድ የከበሩ ገዳማውያንንም ይጐበኛቸው ዘንድ ለሚያነቧት ጥቅም ትሆን ዘንድ ገድላቸውንም እንዲጽፍ ልዑል እግዚአብሔር አዘዘው።
በዚያንም ጊዜ ለእግዚአብሔር ትእዛዝ ራሱን ዘንበል አድርጎ ወደ ውስጠኛው በረሀ ገባ በመንደር ውስጥ እንደ ሚዞር ሰው በዱር መካከል ዞረ። ከገዳማውያንም ብዙዎችን አገኛቸውና ዜናቸውን ተረድቶ ገድላቸውን ጻፈ ከውስጣቸውም የከበሩ ገዳማውያን ጢሞቴዎስና አቡናፍር አሉ። ይህንንም አባት በፍኑትዮስ ወደ ውስጠኛው በረሀ በመግባቱ ከረኃብ የተነሣ ሥቃይ ደርሶበታል ያለምግብ ሦስት ቀን አድሮአልና።
ከዚህም በኋላ ተርቦ ለሞት ተቃረበ ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ሰውነቱን ሁሉ አፉንም ዳሠሠው ያለ ምግብም ዐሥራ ሰባት ቀን ኖረ። ዳግመኛም ከቶ ሰው ሳያዩ ስድሳና ሰባ ዓመት ከዚያም የሚበዛ የሚያስደንቅ የገዳማውያንን ኑሮአቸውን ተናገረ ወደ ውስጠኛው በረሀ በሚገቡ ጊዜ እነርሱን ስለሚዋጓቸው ከርኵሳን መናፍስትና ከሚያስፈሩ አራዊት ስለሚደርስባቸውም ፈተና ተናገረ። ከዚህም በኋላ በትዕግሥታቸው የሚዘጉላቸው ይሆናሉ አራዊትም እንደ ባሮች ያገለግሏቸዋል ቅዱስ ቍርባንንም እንዴት እንደሚቀበሉ ደግሞ ተናገረ በዕለተ ሰንበት የመድኃኒታችንን ክርስቶስን ሥጋና ደም መላእክት አምጥተው ያቀብሏቸዋልና ከገነትም ፍራፍሬዎችን ይሰጧቸዋል።
ለዚህም አባት ስለ እሊህ ድንቆች ሥራዎች አይቶ ምስክር ሊሆን የተገባው ሆነ ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages