ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 16 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 16

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ዐሥራ ስድስት በዚችም ዕለት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም አማላክን ለወለደች #ለእመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም በዓልን ያደርጋሉ፣ የመጥምቁ ዮሐንስ እናት የከበረች #ቅድስት_ኤልሳቤጥ አረፈች፣ ጻድቁ ንጉሥ #አፄ_ገብረ_ማርያም የእረፍት ቀናቸው ነው ፣ የጻድቅና #ቅዱስ_ንጉሥ_ነዓኩቶ_ለአብ መታሰቢያው ነው፣ #አቡነ_መልከ_ጼዴቅ ዘሚዳ ልደታቸው ነው፡፡


የካቲት ዐሥራ ስድስት በዚችም ዕለት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም አማላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓልን ያደርጋሉ። በዚች ዕለት መታሰቢያዋን ለሚያደርግ ስሟን ለሚጠራ ለድኆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳንን ተቀብላለችና።
ይህችም የከበረች እመቤታችን ልጅዋ ንጹሕ ሥጋዋን ተዋሕዶ ከብቻዋ ኃጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ ፈጽሞ ስለእኛ መዳን ወዶ ያደረገውን መከራ ተቀብሎ ሙቶ ተነሥቶ ከዐረገና በአባቱ ዕሪና ከተቀመጠ በኋላ እርሷን እናቱን ማርያምን በደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ዘንድ ትቷት ነበር እነሆ ልጅሽ እርሱንም እነሆዋት እናትህ ብሎ አደራ እንዳስጠበቀው።
ከዚያንም ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ማርያም ትጸልይ ዘንድ ያለ ማቋረጥ ወደ ልጅዋ መቃብር ሁል ጊዜ ስትሔድ ኖረች ይኸውም ጎልጎታ ነው።
አይሁድም በአዩዋት ጊዜ ቍጣንና ቅናትን ተመልተው በድንጊያ ሊወግሩዋት ወደዱ እግዚአብሔርም ከዓይናቸው ሠወራት ከዚህም በኋላ ዳግመኛ መጥታ በዚያ እንዳትጸልይ ተማክረው ከመቃብሩ ዘንድ ጠባቂዎችን አኖሩ እርሷ ግን በየዕለቱ መሔድን አላቋረጠችም ጠባቆችም አያይዋትም የልጅዋ የጌትነቱ መጋረጃ ሠውርዋታልና መላእክትም መጥተው ያገለግሏታል ጌታችንም ዘወትር ይጐበኛታል የምትሻውንም ይፈጽምላት ነበር።
ከዚህም በኋላ መላእክት ወደ ሰማይ አሳረጓትና የጻድቃንን ማደሪያዎች አሳዩዋት አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብም ወዳሉበት አደረሱዋት ከአዳም ጀምሮ እስከዚያ ዕለት በአካለ ነፍስ ያሉ አባቶች ሁሉ አንቺን ከሥጋችን ሥጋን ከዐፅማችን ዐፅምን ለፈጠረልን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የአምላክ ልጅ ከአንቺ ሰው በመሆኑ በአንቺ ድህነት አግኝተናል ከጥፋትም የሕይወት ወደብ ሆነሽልናልና እያሉ ሰገዱላት።
ከዚያም ወደ ተወደደ ልጅዋ የእሳት መጋረጃ ወደተተከለበት ወደ ጌትነቱ ዙፉን አደረሷት ጌታችንም እጇን ይዞ ወደ ውስጠኛው መጋረጃ አስገብቶ ከጌትነቱ ዙፋን ላይ አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጣት ያዘጋጀላትንም ዐይን ያላየው ጆሮ ያልሰማው በሰው ልቡና ያልታሰበ ተድላ ደስታን ሁሉ ነገራት።
ከጌትነቱ ዙፋንም በታች የእስራኤል ንጉሥ አባቷ ዳዊትን የነቢያትና የመላእክት ማኀበር እንደ ግድግዳ ከበውት በመሰንቆ ሲያመሰግን አየችው እንዲህም ይላል ልጄ ስሚ በጆሮሽም አድምጪ ወገንሽን የአባትሽንም ወገን ርሺ ንጉሥ ደም ግባትሽን ወዷልና እርሱም ጌታሽ ነውና።
ዳግመኛም የሥቃይን ቦታ ያሳዩዋት ዘንድ መላእክት ከዚያ ውሰዷት ለሰይጣንና ለሠራዊቱ በእርሱ ጐዳና ለሚጓዙ ሁሉ ወደተዘጋጀ ወደጨለማው ዳርቻ አደረሷት እመቤታችን ማርያምም ወዮልኝ ወደዚያ እንዳይመጡ ለሰው ልጆች ማን በነገራቸው አለች መልአኩም አመቤቴ ቡርክት ማርያም ሆይ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ይኖራልና ለአንቺም ከአንቺ በኋላም በቃል ኪዳንሽ ለሚታመኑ አትፍሪ አላት ከዚህም በኋላ ወደ ቦታዋ መለሷት።
ከዚያንም ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ድንግል ማርያም ስለ ኋጥአን እጅግ እያዘነች ኖረች እንደ ዛሬይቱም የካቲት ዐሥራ ስድስ ቀን በጎልጎታ ቦታ ቁማ ወደ ልጇ እንዲህ ብላ ለመነች ልጄ ሆይ በእግዚአብሔር አባትህ በክርስቶስ ስምህ ከአንተ ጋርም ህልው በሆነ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ አማፅንሃለሁ ዓለም ሁሉ ሊሸከምህ የማይችል ሲሆን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በተሸከመችህ ማሕፀኔ አማፅንሃለሁ ልጄ ሆይ ያለ ሕማም ያለ ድካም ከእኔ በመውጣትህ በመወለድህ በአሳደጉህ ጡቶቼ በሳሙህ ከንፈሮቼ በአቀፋህ እጆቼ ከአንተ ጋር በተመላለሱ እግሮቼ አማፅንሃለሁ ። በውስጡ በተኛህበት በረት በተጠቀለልክበት ጨርቅ አማፅንሃለሁ የምወድህ ልጄ ሆይ በልቡናዬ ያለውን ሁሉ ትፈጽም ዘንድ የልመናዬን ቃል ሰምተህ ወደእኔ ትመጣ ዘንድ ወዳንተ ፈጽሜ እማልድሃለሁ።
የብርሃን እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲህ ብላ በጸለየች ጊዜ እነሆ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወረደ ከእርሱም ጋር አእላፍት መላእክት አሉ በዙሪያውም ሁነው ያመሰግኑታል እርሱም እናቴ ማርያም ሆይ ምን ላድርግልሽ አላት እመቤታችንም ለተወዳጅ ልጅዋ እንዲህ ብላ መለሰችለት ልጄ ወዳጄ ሆይጌታዬና ፈጣሪዬ አለኝታዬና መጠጊያዬ በእናቴ ማሕፀንም ሳለሁ ባንተ ጸናሁ አንተም ጠበቅኸኝ ሁልጊዜም ስም አጠራሬ አንተ ነህ።
አሁንም ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ ቃሌንም አድምጥ እኔ እናትህ እኔም አገልጋይህ የምለምንህ ይህ ነው መታሰቢያዬን ለሚያደርጉ በስሜ አቢያተ ክርስቲያን ለሚሠሩ ወይም የተራቆተውን ለሚያለብሱ የተራበውን ለሚያጠግቡ የተጠማውንም ለሚያጠጡ የታመመውን ለሚጐበኙ ያዘነውን ለሚያረጋጉ የተከዘውንም ደስ ለሚያሰኙ ወይም ምስጋናዬን ለሚጽፉ ልጆቹንም በስሜ ለሚሰይም በበዓሌም ቀን በማኅሌት ለሚያመሰግን አቤቱ ዐይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰውም ልቡና ያልታሰበውን በጎ ዋጋ ስጣቸው በአማላጅነቴም የሚታመነውን ሁሉ ከሲኦል ነጻ አድርገው ከአንተ ጋር የደረሰብኝን ረኃቡንና ጥማቱን መከራውን ሁሉ አስብ አለችው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዳልሽው ይሁንልሽ የሰጠሁሽም ቃል ኪዳን እንዳይታበል በራሴ ማልኩልሽ አላት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን ድንግል ማርያም በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የመጥምቁ ዮሐንስ እናት የከበረች ኤልሳቤጥ አረፈች። ይህች ቅድስት ከኢየሩሳሌም የሆነች የእናቱዋ ስም ሶፍያ ነው እርሷም ከሌዊ ነገድ ከአሮን ወገን ለሆነ ለማጣት ልጁ ናት በዝምድና አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የእናቷ እኅት ልጅ ናት።
ማጣት ሦስት ልጆችን ወለዷልና የታላቂቱም ስም ማርያም ነው እርሷም ወደ ግብጽ በተሰደደች ጊዜ እመቤታችንን ያገለገለች ሰሎሜን ወለደቻት ሁለተኛዋም ሶፍያ ናት እርሷም የዚች የቅድስት ኤልሳቤጥ እናቷ ናት የታናሺቱም ስም ሐና ነው። እርሷም የከበረች ድንግል እመቤታችንን ማርያምን ወለደቻት። ሰሎሜ ኤልሳቤጥ እመቤታችን ማርያም የእኅትማማች ልጆች ናቸው።
ይችንም ቅድስት ኤልሳቤጥ ካህኑ ዘካርያስ አገባት የከበረ ወንጌልም ስለርሳቸው ተናግሯልና እነርሱ ሁለቱም ያለ ነውር ያለ ነቀፋ በእግዚአብሔር ሕግ ጸንተው የሚኖሩ ዕውነተኞች ደጎች ሆኑ።
ኤልሳቤጥም መካን ስለሆነች ወደ እግዚአብሔር የሚለምኑና የሚማልዱ ሆኑ አርጅተውም የመውለጃቸው ዘመን በአለፈ ጊዜ እግዚአብሔር መልአኩን ገብርኤልን ወደ ዘካርያስ ልኮ ጸሎታቸው ልመናቸው እንደ ተሰማ ስለ ዮሐንስ መወለድና ከእርሱ ስለሚሆነው አስረዳው።
ከዚህም በኋላ ይቺ ቅድስት ኤልሳቤጥ መጥምቁን ዮሐንስን ፀንሳ ወለደችው ከሰዎችም የሚደርስባት ሽሙጥ ተወግዶ እጅግ ደስ አላት።
ሕፃኑም በማሕፀኗ እያለ እመቤታችን ድንግል ማርያም ሰላምታ በሰጠቻት ጊዜ እንዲህ ብላ ጮኸች "ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ የማኅፀንሽም ፍሬ ቡሩክ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ እነሆ እንዴት ነሽ ስትይኝ የሰላምታሽን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ልጁ በማሕፀኔ ውስጥ በደስታ ዘለለ።
ከዚህም በኋላ ጌታችንን አየችው በአምላክነቱም አመነች የሚያምኑበትም በመዳናቸው ደስ አላት ዕድሜዋንም በፈጸመች ጊዜ በበረሀ ውስጥ ሳለች አረፈች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች እለት ጻድቁ ንጉሥ አፄ ገብረ ማርያም የእረፍት ቀናቸው ነው፡፡ የላስታ ገሥታት የዘር ሐረጋቸው ከንጉሥ ሰሎሞን ዘር ሲያያዝ የመጣ ነው፡፡ ከ10ኛው እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (920-1253 ዓ.ም ገደማ) በላስታ ቡግና ምድር የነገሡ የላስታ ቡግና ተወላጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ቅዱሳን ነገሥታት የንግሥናቸው መጠሪያ "የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት "ወይም" የላስታ መንግሥት" በመባል ይታወቃል፡፡ ከላስታ (ከዛጉዌ) ነገሥታት መካከል ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ገብረ ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላና ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ እነዚህ አራቱ ነገሥታት እንደ መልከጼዴቅ (ዘፍ14፥18) ክህነትን ከንግሥና፣ ቅድስናን ከንጽሕና ጋር አንድ አድርገው በመያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅድስናና፡ በንጽሕና አገልግለው አልፈዋል፡፡
ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ገብረማርያም በሌላኛው ስማቸው ሐርቤይ እየተባሉ የሚጠሩ ሲሆን የቅዱስ ላሊበላ ታላቅ ወንድም ናቸው፡፡ ታላቁ ጻድቅ ንጉሥ ቅዱስ ነዓኵቶ ለአብን ወልደዋል፡፡ አባታቸው ዣን ስዩም 40ዓመት ከነገሡ በኋላ በ76ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ልጃቸው ገብረ ማርያም ንግሥናውን ተቀብለዋል፡፡ ከእርሳቸው ቀጥሎ ታናሽ ወንድማቸው ቅዱስ ላሊበላ ተወልዶ እንደሚነግስ በትንቢት ተነግሮ ነበር፡፡ ይህን ጊዜ ከላሊበላ ጋር በአባት እንጂ በእናት ይለያዩ ነበርና የበጎ ነገር ጠላት የሆነ ክፉ ሰይጣን የእኅታቸው ክፉ ምክር ተጠቅሞ በወንድማቸው በላሊበላ ላይ በቅናት ክፉ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል፡፡ስለ ንግሥናቸው ሲሉ ምንም እንኳን በወንድማቸው ላይ ክፉ አስበው የነበረና በእኅታቸውም ክፉ ምክር መርዝ የሰጡት ቢሆንም በኋላ በክፉ ሀሳባቸው እጅግ ተፀፅተው "አምላኬንም ወንድሜንም አሳዘንኩ" በማለት ወንድማቸውን ይቅርታ በመጠየቅ ላሊበላን አንግሠውት እርሳቸው መንኵሰው ገዳም ገብተዋል፡፡
ቅዱስ ላሊበላ ካለበት አክሱም ድረስ ሄደው በዕንባና በልቅሶ ይቅርታ ጠይቀው ወደ አገራቸው ሮሐ ከተማ ይዘውት በመምጣት መንግሥታቸውን አስረክበውት ነው የመነኑት፡፡ በምንኵስናም ሆነው በታላቅ ተጋድሎ በጾም በጸሎት በመትጋት እግዚአብሔርን እያገለገሉ እያለ ጌታችን ተገልጦላቸው "ክብሩ እንደ መላእክት የሆነ ታላቅ ልጅ ትወልዳለህና ወደቤትህ ተመለስ" ብሎ ከነገራቸው በኋላ ወደቤታቸው ተመልሰው ቅዱስ ነአኵቶ ለአብን ወልደዋል፡፡
ንጉሥ ቅዱስ ገብረ ማርያም በዘመናቸው ከነበሩት ከእስክንድሪያ ሊቀ ጳጳሳት ከአባ ዳንኤል ጋር መልእክት በመላላክ "ከሀገሬ ሊቃውንት መነኰሳት የሕዝቡን ቋንቋ የሚሰሙና የሚያስተምሩ ጳጳስ ይሹሙልን" በማለት ለእስክንድሪያ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ምንም እንኳን የእስክንድሪያ ሲኖዶስ በወቅቱ ኢትዮጵያ የራሷንልጆች እንድትሾም ስላልፈለጉና በወቅቱ ፈቃደ እግዚአብሔር ስላልነበረ የቅዱስ ገብረ ማርያምን ጥያቄ ንግሥት ዘውዲቱና ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ድጋሚ በመጠየቅ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ቢያደርጉትም መሠረቱን ግን የጣሉት ዐፄ ገብረ ማርያም ናቸው በዘመናቸው ብዙ አብያተ ክርስቲያናትንም ያሠሩ ሲሆን ጊዜ ዕረፍታቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጦላቸው "የእኔን መከራ እያሰብክ ከዓይንህ ዕንባ ሳያቋርጥ በጾም በጸሎት ተወስነህ ስላገለገልኸኝ በአንተ ስም ለተራበ ያበላውን፣ ለተጠማ ያጠጣውን፣ ለታረዘ ያለበሰውን ምሬልሃለሁ" በማለት ትልቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸው በካቲት16 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡ ጻድቁን ንጉሥ ዐፄ ገብረ ማርያምን ሚያዝያ10 ቀን የሚነበበው ስንክሳር በሰፊው ይጠቅሳቸዋል፡፡ ከጻድቁ ከአቡነ ገብረ ማርያም ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የስሙ ትርጓሜ ‹‹እግዚብሔር አብን እናመስግነው›› ማለት ነው። የቅዱስ ላሊበላ የወንድም ልጅ ሲሆን ከ11ዱ የዛጉዌ ነገሥታት ውስጥ 10ኛው ነው። አባቱ ቅዱስ ገብረ ማርያም ሥልጣኑን ለወንድሙ ለቅዱስ ላሊበላ ትቶ በመመንኮስ በበዓት ተወስኖ በጾም በጸሎት ሲጋደል ጌታችን ተገልጾለት ‹‹ክብሩ እንደ መላእክት የሆነ ልጅ ትወልዳለህና ወደቤትህ ተመለስ›› ብሎ አዘዘው። ንጉሡ ገብረማርያምም ‹‹40 ዓመት ስነግሥ ያልወለድኩትን አሁን ዓለም በቃኝ ስል ትወልዳለህ የተባልኩት ልጅ ምን ዓይነት ልጅ ይሆን!›› እያለ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ሚስቱን መርኬዛንም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ካበሰራት በኋላ ነአኵቶለአብ ጌታችን በተወለደበት ዕለት ታኅሳስ 29 ቀን ተወለደ። ቅዱስ ላሊበላም ቀደም ብሎ የተወለደው እንዲሁ በጌታችን የልደት ቀን ታኅሳስ 29 ቀን 1101 ዓ.ም ነው። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ነአኵቶለአብ እንደሚወለድ ቀድሞ ለንጉሥ ላሊበላ ነግሮት ነበርና አሁን ሲወለድ ‹‹ያ የነገርኩህ ሕፃን ተወልዷልና ወስደህ በሃይማኖት አንጸህ አሳድገው›› ብሎታል። እንዳለውም ሃይማኖቱን ጠንቅቆ እያስተማረ በእንክብካቤ አሳደገው። ግብፅ ሄዶ ከአቡነ ቄርሎስ ዲቁናን ተቀበለ። በኋላም ቅስናን ተቀበለ። ቅዱስ ላሊበላ ቤተ መቅደሶቹን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ በሕይወት ሳለ መንግሥቱን ስላወረሰው ከላሊበላ በኋላ ነግሦ ኢትዮጵያን መርቷል። ዕድሜው ሲደርስ መልአኩ ሚስት እንዲያጭለት ለቅዱስ ላሊበላ ነግሮት ሲያጭለት እግዚአብሔርን በድንግልና ማገልገል ይፈልግ ነበርና በዚህም እጅግ ሲያዝን እመቤታችን ተገልጻለት ጋብቻው ከእግዚአብሔር መሆኑን ነግራ አጽናንታዋለች፡፡ ‹‹የጌታህ ፈቃድ ነውና አትዘን ይልቁንም አግባ፣ ክብርህም ከደናግላን አያንስም›› ብላ ስለነገረችው ሚስት ቢያገባም ልክ እንደ ቅዱስ ዲሜጥሮስና ልዕልተወይን ንጽሕናቸውንና ድንግልናቸውን ለመጠበቅ በመማከር በግብር ሳይተዋወቁ ለ25 ዓመታት በድንግልና ሆነው በትዳር ኖረዋል። ምንኛ ድንቅ ነው የአባቶቻችን ጽናትና ተጋድሎ!!! እግዚአብሔርን በንጽሕና ለማገልገል ያላቸው ቁርጠኝነትስ በምን ቃላት ይገለጻል!!! ከዚህ በኋላ መልአክ መጥቶ ቅዱስ ነአኵቶለአብንና ባለቤቱን ‹‹በንጽሕና የተጋባችሁት ልትወልዱ ነው እንጂ ዝም ብላችሁ ልትኖሩ አይደለም›› አላቸው። እነርሱም በዚህ ጊዜ በጋብቻ 25 ዓመታት በድንግልና አብረው ከኖሩ በኋላ አንድ ቀን ብቻ በግብር ቢተዋወቁ እጅግ የሚያምርና የሚያሳሳ ወንድ ልጅ ወለዱ። ጻድቁን ንጉሥ ቅዱስ ነአኵቶለአብን ይበልጥ የምናደንቅበት ነገር የተፈጠረው ከዚህ በኋላ ነው። በመልአክ ትእዛዝ የወለደው ልጁ እጅግ የሚያምርና የሚያሳሳ ቢሆንም ንጉሡ ቅዱስ ነአኵቶለአብ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ የወደፊቱን ያውቅ ነበርና ሱባኤ ገብቶ ‹‹በእኔ እግር ተተክቶ ሲነግሥ ፍርድ አጣሞ አንተንም ሰውንም ከሚበድል ይህን ልጄን ቅሰፍልኝና ሄሮድስ ካስፈጃቸው ሕፃናት ጋር ደምርልኝ›› በማለት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። እንደጸሎቱም ጌታችን በዛሬዋ ዕለት የካቲት 16 ቀን ልጁን በሰላም አሳርፎለት ሄሮድስ ካስፈጃቸው ሕፃናት ጋር ደምሮለታል። በዚህም ጊዜ መኳንንቶቹ፣ መሳፍንቶቹና ሕዝቡ ሁሉ ለልቅሶ ቢመጡ እርሱ ግን በቤተ መንግስቱ በልቅሶ ፈንታ ታላቅ የደስታ ድግስ አድርጎ ስለጠበቃቸው ‹‹የንጉሡ ልጅ ሞተ የተባለው ውሸት ነው›› ብለዋል። ቅዱስ ነአኵቶለአብ ክህነትን ከንግስና ይዘው ኢትዮጵያን ከመሩ ከአራቱ የዛጉዌ ነገሥታት አንዱ ሲሆን በነገሠበት 40 ዓመት ሙሉ ዓርብ ዓርብ ቀን የክርስቶስን ሕማም እያሰበ በዕንቁና በወርቅ በተሸቆጠቆጠው ዘውዱ ፈንታ የእሾህ አክሊልን ደፍቶና በአምስቱ ቅንዋተ መስቀሎች ምሳሌ አምስት ጦር ዙሪያውን ተክሎ እያለቀሰ ይጸልይና ይሰግድ ነበር። ለፍርድም በተቀመጠ ጊዜ ከንግሥና ልብሱ ውስጥ በስውር ማቅ ለብሶና ሰውነቱን በሰንሰለት አስሮ ከላይ ግን በክብር ልብሱ ተሸፍኖና በወርቅ ወንበር ተቀምጦ ይፈርድ ነበር። ፍርድ ሲሰጥም ሁሉንም ነገር በመንፈስ ቅዱስ እያውቅ ነበር።
ይህ ጻድቅና ቅዱስ ንጉሥ በዘመኑ ግብፆች ግብር አንሰጥም ብለው ስላመፁበት የዓባይን ወንዞች በጸሎቱ ወደ ሌላ ቦታ እንዲፈሱ ስላደረገባቸው ግብፆች ከበፊቱ ጨምረው ግብራቸውን አምጥተው ሰጥተውት ግዝቱን አንስቶላቸዋል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ጻድቁ አቡነ መልከጼዴቅ ዘሚዳ ልደታቸው ነው። ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መልከጼዴቅ። አቡነ መልከጼዴቅ በ13ኘው መ/ክ/ዘ መጨረሻ በንጉሥ ዐፄ በእደ ማርያም ዘመነ መንግሥት የነበሩ እደጃቸው የተቀበረውን ሰው አፈር የማያስበሉ እጅግ ድንቅ ቃልኪዳን ያላቸው ታላቅ አባት ናቸው። የአምላካቸውን የክርስቶስን መከራ ለማሰብ ገዳመ ቆሮንቶስን የመሰለ ዋሻ ቆፍረውና በዚያ ገብተው ቀንና ሌሊት ዘግተው በረደኝ ፀሐይ ልሙቅ፣ ጨለመኝ ብርሃን ልይ ሳይሉ በጸሎት ብቻ ዘግተው በመኖር ራሳቸውን በችንካር እያቆሰሉና ጭንቅላታቸውን እያተሉ ትሉን ለሰማይ አእዋፍ ይመግቡ ነበር። እግዚአብሔር ወልድ የተገረፈውን ግርፋት እያሰቡ በየቀኑ እስከ 3ሺህ ድረስ ይሰግዱ ሰውነታቸውንም እንዲሁ ይገርፉ እንደነበር መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል። የክርስቶስን መቸንከር እያሰቡ እጅና እግራቸውን፣ ወገብና ደረታቸውን በብረት ቸንክረው መከራውን ያስቡ ነበር። ጎኑ በጦር መወጋቱን አስበው አጥንታቸው እስኪሰበር ድረስ ጎናቸውን ወጉ። ሐሞትና ከርቤ መጠጣቱን አስበው እርሳቸውም መራራ ይጠጡና አንክርዳድን ይመገቡ ነበር። ሞቱን አስበው ደም እንባን ያነቡ ነበር። በእንደዚህ ዓይነቱ ተጋድሎ የክርስቶስን መከራ እያሰቡ ነቢያን፣ ሐዋርያትን፣ ሰማዕታትን፣ ደናግል መነኮሳትን መስለው ሁሉን እያከናወኑ እያለ የወዳጆቹን መከራ የማይዘነጋ፣ የሰውን የድካሙን ዋጋ ፈጽሞ የማያስቀር አምላክ ሠራዊተ መላእክትን አስከትሎ መጥቶ ‹‹መገረፍህ፣ ስለ እኔ መገረፍ ይሁንልህ፣ የደምህ መፍሰስ ስለ እኔ ደም መፍሰስ ይሁንልህ፣ መቸንከርህም ስለ እኔ መቸንከር ይሁንልህ፣ ሞትህም ስለ እኔ ሞት ይሁንልህ›› ብሎ የሚከተለውን ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል። ‹‹ከዚህ ቦታ መጥቶ የተሳለመውን እምርልሃለሁ፤ ነፍሱ በአንተ ቃልኪዳን የማይማር በአንተ ቦታ ለመሳለምም፣ ንስሓ ለመግባትም ሆነ ለመቀበር አላቀርብብህም፤ መጥቶም የተቀበረውን ሥጋውን አፈር አይበላውም›› የሚል እጅግ ድንቅ ቃልኪዳን ነው መድኃኔዓለም የሰጣቸው። ቃል ኪዳኑንም የሰጣቸው ቅዱሳን መልእክትን፣ ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን፣ ደናግል መነኮሳትን ሁሉ ምስክር አቁሞ እንደሆነ ቅዱስ ገድላቸው ይናገራል።
ይህም ድንቅ ቃልኪዳን ዛሬም በገሀድ እየታየ ነው። እስከ ዕለተ ምጽዓትም ሲታይ ይኖራል። በደጃቸው የተቀበረ ሰው አይበሰብስም። ይህም የሥጋው አለመበስበስ ለሞተው ሰው ለሥጋው አንዳች ረብ ጥቅም ኖሮት ሳይሆን የጻዲቁ ቃልኪዳናቸው እስከ ዕለተ ምፅዓት ድረስ ተፈጻሚ መሆኑንና ምልክትን ለሚሻ ለዚህ ክፉ ዘመን ትውልድ ምልክት ይሆን ዘንድ ነው።
ከአ.አ 225 ኪ.ሜ ርቀት ለመራኛ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የሚዳ አቡነ መልከጼዴቅ ገዳም ተፈጥሮአዊ አቀማመጡ እጅግ አስገራሚ በሆነው ዋሻ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁሉም ነገር በግልጽ ይታያል። ይህም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ በተለይም እኛ ኢትዮጵያውን በኃጢአት ሳንጠፋበት የመዳኛ መንገድ አድርጎ የሰጠን ድንቅ የቃል ኪዳን አባታችን መሆናቸውን ተረድቶና አውቆ በቃል ኪዳናቸው መጠቀም መቻል በራሱ ዕድለኛነት ነው። አቡነ መልከጼዴቅ ጌታችን ዕድሜአቸው ረጅም መሆኑን በምሳሌ እያሳየ ሲነግራቸው ‹‹በዚህ ዓለም መኖር ጥቅሙ ምንድር ነው? ወደ እረፍትህ ውሰደኝ እንጂ›› ብለው ሞታቸውን የለመኑ ቅዱስና ጻዲቅ አባት ናቸው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages