ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 16 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 16

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ዐስራ ስድስት በዚች ቀን የእስራኤል መሳፍንት አንዱ #ቅዱስ_ጌዴዎን_ኃያል ዐረፈ፣ #የሙሴ_እኅት_ማርያም መታሰቢያዋ ነው፡፡


ታኅሣሥ ዐስራ ስድስት በዚች ቀን የእስራኤል መሳፍንት አንዱ ጌዴዎን ዐረፈ፡፡ ይህም ከነገደ ምናሴ የሆነ የአባቱ ስም ዮአስ ይባላል ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ተገለጠለትና ለእስራኤል ሾመው። የጠዖታትንም መሠዊያ እነሰዲያፈርስ ዛፎችንም እንዲቆርጥ አዘዘው መሠዊያም ለእግዚአብሔር ሠርቶ በዚያ በሰበረው ዕንጨት እንዲሠዋ አዘዘው ሁሉንም እንዳዘዘው አደረገ። እግዚአብሔር የላከው መልአክም ተመለከተው "እስራኤልን ከምድያም እጅ ታድናቸዋለህና ከሠራዊትህ ጋር ሒድ እነሆ ላክሁህ" አለው።
ጌዴዎንም "አድናቸዋለሁ እንዳልክ እስራኤልን በእጄ ታድናቸው እንደሆነ እነሆ እኔ በአደባባይ የተባዘተ ፀምርን እዘረጋለሁ ጠል በምድር ላይ ሳይወርድ በፀምሩ ላይ ብቻ ቢወርድ አድናቸዋለሁ እንዳል እስራኤልን በእጄ እንድታድ ናቸው ያን ጊዜ አውቃለሁ" አለ እንዳለውም ሆነ። ጌዴዎንም በማግሥቱ ማልዶ ሒዶ ያንን ጨመቀው ከዚያ ፀምር አንድ መንቀል ሙሉ ውኃ ወጣ።
ጌዴዎን እግዚአብሔርን "በቊጣህ አትቆጣኝ ዳግመኛ አንድ ጊዜ ልናገር በፀምር ላይ ብቻ ሳይወርድ ጠል በምድር ሁሉ ላይ ይውረድ" አለው። እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት እንዳለው አደረገ። ፀምሩ ብቻ ደረቅ ሁኖ ጠል በምድር ሁሉ ላይ ወረደ። ጌዴዎንንም የእግዚአብሔር መንፈስ ረድኤት አጸናው ነጋሪትንም መታ አብያዜርም በኋላው ሁኖ ደነፋ ወደ ነገደ ምናሴር፣ ወደ ነገደ ዛብሎን፣ ወደ ነገደ ንፍታሌምም መልክተኞችን ላከ ወጥተውም ተቀበሏቸው። ጌዴዎንም ከርሱ ጋር ያሉ ወገኖቹም ሁሉ ሔዱ አሮኤድ በሚባል አገርም ሰፈሩ የመሰድያምና የአማሌቅ ሠራዊትም በእንበሬም ቆላ መሠዊያ ቀኝ ሰፈሩ።
እግዚአብሔርም ጌዴዎንን "እጃችን አዳነችን ብለው እንዳመኩብኝ የምድያምን ሰዎች በእጃቸው መጣል እንደማልችል ካንተ ጋር ያሉ ሕዝብ ብዙ ናቸው" እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው "ከእናንተ የሚፈራ የመመደነግጥ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይመለስ" ብለህ ለሕዝቡ ንገራቸው። ሕዝቡም ከገለዓድ ተመለሱ ከሕዝቡም ሁለት እልፍ ከሁለት ሽህ ተመልሰው እልፍ ሰዎች ቀሩ።
እግዚአብሔር ጌዴዎንን "ገና ብዙ ሕዝብ አሉ ወደ ውኃ አውርደህ በዚያ ፈትናቸው እኔ ይሒዱ የምልህ ሰዎች እነርሳቸው ካንተ ጋር ይሒዱ" አለው ሕዝቡንም ወደ ውኃ አወረዳቸው። እግዚአብሔር ጌዴዎንን "ውሻ በምላሱ ጠለፍ ጠለፍ አድርጎ እንዲጠጣ ከውኃው ጠለፍ ጠለፍ አድርጎ የሚጠጣውን ሁሉ ለብቻው አቁመው ውኃን ይጠጣ ዘንድ በጉልበቱ የተንበረከከውንም ሁሉ ለብቻው አቁመው" አለው። በምላሳቸው ጠለፍ ጠለፍ አድርገው የጠጡ ሰዎች ቊጥራቸው ሦስት መቶ ሆነ የቀሩት ሕዝብ ግን ውኃን ይጠጡ ዘንድ በጉልበታቸው ተንበረከኩ።
እግዚአብሔርም ጌዴዎንን "እንደዚህ በእጃቸው ውኃን በጠጡት በእነዚህ ሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ የምድያምን ሰዎች ወደ ቤታቸው ይመለሱ" አለው። በዚያችም ሌሊት እሊህ ሦስት መቶ ሰዎች መለከትን ነፉ "ይህ የእግዚአብሔር ኃይልና የጌዴዎን ጦር ነው" ብለው ጮኹ። የምድያምም ሰዎች የመለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔር በልባቸው ፍርሀትን አሳድሮባቸው ደንግጠው ሸሹ እግዚአብሔርም ያንዱን ሰይፍ ወዳንዱ ወደ ጓደኛው መለሰ በሠራዊቶቻቸው ሁሉ እርስበርስ መተላለቅ ሆነ መኳንንቶቻቸውን ኄሬብንና ዜብን ነገሥቶቻቸው ዛብሄልንና ስልማናንም ገደሏቸው ከምድያምም ሠራዊት ፈረሰኞችና ጦረኞችን አንድ መቶ ሁለት ሽህ ገደሉ።
ከዚህም በኋላ የምድያም ሰዎች በእስራኤል ፊት ተዋረዱ ዳግመኛም ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም በጌዴዎንም ዘመን ምድር አርባ ዘመን ዐረፈች። ከዚህም በኋላ በዚች ቀን ታኅሣሥ16 በሰላም በፍቅር ዐረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን የሙሴ እኅት ማርያም መታሰቢያዋ ነው፡፡ ይህች እናት የሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴና የሊቀ ካህናቱ ቅዱስ አሮን ትልቅ እህት ስትሆን ወላጆቿ እንበረምና ዮካብድ ይባላሉ:: እሥራኤል ከግብጽ ባርነት እንዲወጡ የእርሷን ያህል አስተዋጽኦ ያደረገች ሴት የለችም::
ከመነሻውም ቅዱስ ሙሴን የጠበቀች: በሕግ በሥርዓት እንዲያድግ ከእናቱ ጋር ያገናኘች: ወገኖቿ ከግብጽ ሲወጡም ሴቶችን የመራች እናት ናት:: ወንድሞቿን ሙሴንና አሮንንም ታገለገላቸው ነበር:: በተለይ እግዚአብሔር ባሕረ ኤርትራን የብስ ሲያደርጋት ከበሮን አንስታ "ንሴብሖ ለእግዚአብሔር" ብላ ፈጣሪዋን አመስግናለች:: (ዘጸ. 15:20)
አንድ ጊዜም "ኢትዮዽያዊቷን ሲፓራን ለምን አገባህ" በሚል ስለ ተናገረችው እግዚአብሔር ተቆጥቶ በለምጽ መቷታል:: (ዘኁ. 12:1) ቆይቶም በቅዱሱ ምልጃ ምሯታል:: ማርያም በመንገድ ሳሉ: ወደ ርስት ሳይደርሱ ዐርፋ ተቀብራለች:: (ዘኁ. 20:1)
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages