አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ዐስራ አምስት በዚህች እለት #ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘአርማንያ ዕረፍታቸው ነው፣ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ #አቡነ_ኤዎስጣቴዎስ_ከፋሌ_ባህር ልደታቸው ነው፣ #የቅዱስ_አቡነ_ሉቃስ_ዘዓምድ ዕረፍታቸው ነው፣ የእኔ ቢጤ የነበሩትና ጽድቃቸውን ማንም ሳያውቅባቸው የኖሩት #የአባ_ቆራይ ዕረፍታቸው ነው፡፡
ታኅሣሥ ዐስራ አምስት በዚህች እለት የአርማንያ አገር ኤጲስቆጶስ አባ ጎርጎርዮስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ የንጉሡን ትእዛዝ ስመተላለፋና ለአማልክት አልሠዋም ስላለ የአርማንያ ንጉሥ ድርጣድስ አሠቃይቶ ጥልቅ ወደ ሆነ ደረቅ ጒድጓድ ውስጥ ጨመረው በዚያ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ። እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበር አንዲቷን አሮጊትም ሁል ጊዜ ምግቡን እነሰድታመጣለት አደረጋት ሕያው እንደሆነም የሚያውቅ የለም።
ንጉሥ ድርጣድስም ቅድስት አርሴማን ለማግባት ሽቶ ነበርና በእርሷ ምክንያት ደናግሎችን ገደላቸው። የእሊህ ደናግልም ሥጋቸው በተራራ ላይ እንደ ወደቀ ነበር ንጉሡም ስለ ገደላቸው ደናግል ይልቁንም ውበቷንና ደም ግባቷን እያሰበ ስለ ቅድስት አርሴማ አብዝቶ የሚያዝንና የሚጸጸት ሆነ።
ከዚህም በኋላ ወገኖቹ ለመኑት እንዲህም አሉት አውሬ ታድን ዘንድ በፈረስ ተቀመጥና ወደ ዱር እንውጣ የልብህም ኀዘን ይወገድልሃል። በዚያንም ጊዜ አውሬ ለማደን በፈረሱ ተቀምጦ ወደ ዱር ወጣ። የሚነክስ ሆነ ወገኖቹንም ነከሳቸው እግዚአብሔርም መልኩን ለውጦ እንደ እሪያ አደረገው ያገኘውን ሁሉ የሚነክሰ ሆነ። እንዲሁም ከቤተ መንግሥት ሰዎች በብዙዎቹ ላይ ሰይጣን አደረባቸው ታላቅ ድንጋጤም ሆነ ይህም ሁሉ የሆነ ስለ ቅዱሳት ደናግልና ስለ ቅድስት አርሴማ ነው።
የንጉሡ እኅት ግን "ጎርጎርዮስን ከጒድጓድ ካላስወጣችሁት ድኅነት የላችሁም" የሚላት ሰው በራእይ አየች ይህንንም ለወገኖቿ ነገረች እርሱ አስቀድሞ በጒድጓድ ውስጥ የሞተ ስለ መሳላቸው ደነገጡ። በዚያንም ጊዜ ወደ ጒድጓድ ሔዱ በሕይወት እንዳለም ያወቁ ዘንድ ወደ ጒድጓዱ ውስጥ ገመዶችን አወረዱና ገመዶቹን እንዲይዝ ወደርሱ ጮኹ እርሱም ገመዶችን ያዘ ስበው አወጡት አጥበውም ንጹሕ ልብስን አለበሱት በበቅሎም አስቀምጠው ወደ ቤተ መንግሥት አደረሱት። በዚያንም ጊዜ በሰማዕትነት ስለሞቱ ደናግል ሥጋ ጠየቀ እነርሱም የደናግሉ ሥጋቸው ወዳለበት መርተው አደረሱት የዱር አራዊትና አዕዋፍ ሳይበሏቸው በደኅና አገኛቸው ያማሩ ቦታዎችን አዘጋጅተው በውስጣቸው ያኖሩዋቸው ዘንድ አዘዘ እንዳዘዛቸውም አደረጉ።
ከዚህም በኋላ ንጉሡን ያድነው ዘንድ ሕዝቡ ለመኑት ንጉሡም ወዳለበት ዱር አደረሱት እርሱም "ከክፉ ሥራህ ትመለሳለህን? ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታምናለህን?" አለው። እሪያ የሆነውም ንጉሥ አዎን እንደሚል ራሱን ዘንበል አድርጎ አመለከተ በዚያንም ጊዜ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ጸለየ ከንጉሡም ላይ በእሪያ አምሳል ሰይጣንን አስወጣው። የንጉሡም አእምሮውና መልኩ እንደ ቀድሞው ተመለሰለት ነገር ግን ዳግመኛ እንዳይታበይ ከእግሩ ላይ የእሪያ ጥፍር አስቀረ ፈጣሪውም ተገዢ ይሆን ዘንድ ዳግመኛም የቤተ መንግሥት ሰዎችን ሁሉንም አዳናቸው ከላያቸውም አጋንትን አስወጥቶ ሰደዳቸው።
ከዚህም በኋላ የአርማንያን ሰዎች ሁሉንም ሰበሰባቸውና ሥርዓትን ሠራላቸው ስምንት ቀንም እንዲጾሙ አዘዛቸው እንዳዘዛቸውም አደረጉ የእግዚአብሔርንም ሕግ እያስተማራቸው ኖረ። ዳግመኛም ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆኑን አስተማራቸው ታላቆችም ታናናሾችም ትምህርቱን ተቀበሉት ለአርማንያ ሰዎች ሃይማኖትን የመቀበላቸው ምክንያት ይህ ነው።
ከዚህም በኋላ የክርስትና ጥምቀትን ያጠምቃቸው ዘንድ ቅዱስ ጎርጎርዮስን ለመኑት እርሱም "እኔ ካህን ስለአልሆንኩ አይገባኝም ነገር ግን የሚያጠምቃችሁን ካህን ይልክላችሁ ዘንድ ወደሮሜ ሊቀ ጳጳሳት መልክተኞችን ላኩ" አላቸው። በዚያንም ጊዜ ከርሱ ጋር ወደ ንጉሥ አኖሬዎስና ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ መልክተኞችን ልከው የአርማንያ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንደተመለሱ አስረዱአቸው ንጉሡም ሊቀ ጳጳሳቱም ሰምተው ደስ አላቸው ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱ ለአርማንያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ይሆን ዘንድ ቅዱስ ጎርጎርዮስን ሾመው ወደ አርማንያን ንጉሥ ወደ ድርጣድስም በክብር ላከው።
ቅዱስ ጎርጎርዮስም ተሹሞ ወደ አርማንያ አገር በደረሰ ጊዜ በመምጣቱ ደስ ተሰኙበት እርሱም የአርማንያን ሰዎች ሁሉንም አጠመቃቸው በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያምም ስም ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠራላቸው ሃይማኖንትም ከአጸናቸውና መልካም ጉዞንም ከፈጸመ በኋላ ታኅሣሥ15 ቀን በሰላም በፍቅር ዐረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ዕለት አጽፋቸውን እንደጀልባ ተጠቅመው የኢያሪኮን ባሕር የተሻገሩት ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባሕር ልደታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ አባታቸው ክርስቶስ ሞዐ ሲሆን እናታቸው ስነ ሕይወት ይባላሉ፡፡ ደጋግ የሆኑ ወላጆቻቸው በሃይማኖትና በምግባር ኮትኩተው አሳደጓቸው፡፡ በአደጉም ጊዜ ከአባ ዘካርያስ እጅ መነኮሱ፡፡ ታላላቅ ቅዱሳን እስኪያደንቋቸው ድረስ በጽኑ ተጋደሎ ሲኖሩ ጌታችን ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር ተገልጦላቸው በንፍሐት መንፈስ ቅዱስን አሳደረባቸው፡፡ ‹‹ከእናትህ ማኅፀን የመረጥኩህ ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ ሆይ ለብዙዎች ወንጌልን ትሰብክ ዘንድ ከኢትዮጵያ እስከ አርማንያ ድረስ መምህር አደረግሁህ፡፡ አንተን የሰማ እኔን ሰማ፣ አንተንም ያልሰማ እኔን ያልሰማ ነው›› ካለቸው በኋላ ወደ ሰማይ በክብር ዐረገ፡፡
አባታችን ቅስናን ከተሸሾሙ በኋላ ወንጌልን መስበክ ጀመሩ፡፡ እነ አቡነ አብሳዲን ጨምሮ ብዙዎችንም አመንኩሰው ደቀ መዛሙርቶቻቸው አደረጓቸው፡፡ እጅግ አስገራሚ ተአምራትን በማድረግ ለብዙ ሕሙማን መድኃኒት ሆኗቸው፡፡ ልጆቻቸውን ሰብስበው ከመናፍቃን ጋር በፍጹም እንዳይቀላቀሉ በመምከር አቡነ አብሳዲን ሾመውላቸው ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ቅዱሳት ቦታዎችን ተሳለሙ፡፡ በመንገዳቸውም የክርስቶስን ወንጌል እየሰበኩ ብዙዎችን ወደ ቀናች ሃይማኖት መለሷቸው፡፡ ወደ አርማንያም ሄደው ወደ ኢያሪኮ ባሕር በደረሱ ጊዜ መርከበኞችን እንዲያሳፍሯቸው ቢለምኗቸው እምቢ አሏቸው፡፡ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ግን አጽፋቸውን በባሕሩ ላይ ዘርግተው በስመ ሥላሴ አማትበው አጽፋቸውን እንደመርከብ አድርገው ልጆቻቸውን ይዘው ባሕሩን ተሻገሩ፡፡ ልጆቻቸውን ‹‹ልጆቼ በልባችሁ ቂምንና ሽንገላን እንዳታኖሩ ተጠበቁ፣ ለእኔ ግን ከእናንተ አንዱ እንደሚጠፋ ይመስላኛል›› አሏቸው፡፡ ይህንንም እንዳሉ ከመካከላቸው አንዱ የቂም በቀል መከማቻ ነበርና ወዲያው ሰጠመ፡፡
አባታችን አርማንያ ደርሰው ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋር ቡራኬን ከተሰጣጡ በኋላ ማስተማር ጀመሩ፡፡ የአርማንያ ሰዎች ሁሉም በሃይማኖት አንድ እስኪሆኑ ድረስ ታላላቅ ተአምራትን እያደረጉ አስተምረው አጠመቋቸው፡፡ አባታችን ጊዜ ዕረፍታቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጦላቸው ታላቅ ቃልኪዳን ከሰጣቸው በኋላ መስከረም 18 ቀን ዐርፈው ሊቀ ጳጳሳቱና ካህናቱ በታላቅ ክብር ገንዘው በሰማዕቱ በቅዱስ መርምህናም ቤተ ክርስቲያን ቀብረዋቸዋል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች እለት በአንዲት ምሰሶ ላይ ወጥተው ከዚያ ሳይወርዱ በላይዋ ላይ ሆነው ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደሉ 45 ዓመት የኖሩት አቡነ ሉቃስ ዘዓምድ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ይኸውም ሀገሩ ፋርስ ሲሆን በመቶ የንጉሡ ጭፍራ ላይ መኰንን ሆኖ ተሹሞ ነበር፡፡ በኋላም ሹመቱን ትቶ ገዳም ገብቶ መነኮሰ፡፡ በምሥራቅ ካሉ ገዳማት ውስጥ በአንዱ ገብቶ ብዙ ዘመን ሲጋደል ኖረ፡፡ ልብሱንም የብረት ልብስ በማድረግ እስከ 6 ቀን የሚጾም ሆነ፡፡ ከዚህም በኋላ ከዓምድ ላይ ወጥቶ በዚያ ላይ ሦስት ዓመት ለጸሎት ቆመ፡፡ የታዘዘ መልአክም መጥቶ ከዚያ ዓምድ ላይ እንዲወርድ ነግሮት በብርሃን መስቀል እየመራው ወስዶ አንድ ገዳም አደረሰው፡፡ በዚያም ብዙ ተአምራት እያደረገ ኖረ፡፡
ከዚህም በኋላ አቡነ ሉቃስ አርምሞ ያዘ፡፡ ከቶ እንዳይናገርም በአፉ ውስጥ ድንጋይ ነክሶ ያዘ፡፡ አሁንም መልአኩ ወደ ቍስጥንጥንያ ዳርቻ ቦታ ይዞት እየመራ ወስዶት በዚያም አንዲት ምሰሶ ላይ ወጥቶ ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ በላይዋ ላይ 45 ዓመት ኖረ፡፡ በዚያም አስደናቂ ተአምራትን እያደረገ ብዙዎችን በመፈወስና ወንጌልን በማስተማር ብዙ ደከመ፡፡ ታኅሣሥ 15 ቀን ካረፈ በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱና ካህናቱ መጥተው በክብር ወደ ቍስጥንጥንያ ከተማ ወሰዱት፡፡ በዚህም ጊዜ በድውያን ላይ ታላቅ ፈውስ ሆነ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች እለት ጻዱቁ አባ ቆራይ ዕረፍታቸው ነው፡፡ እጅና እግር የሌላቸውና የእኔ ቢጤ የነበሩት ጽድቃቸውን ማንም ሳያውቅባቸው የኖሩት አባ ቆራይ ጻድቅ መሆናቸው ካረፉ በኋላ ነው የታወቀው፡፡ ገዳማቸው ትግራይ ተንቤን ውስጥ ይገኛል፡፡ ቅዱሱ በዐፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት በትግራይ ተንቤን አውራጃ አዲ ራእሶት-የራሶች (የታላላቅ ሰዎች አገር) በሚባለው ቦታ የእግርና የእጅ ጣቶች የሌሏቸው አባ ቆራይ ወንበር በምትመስል ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ተገለጡ፡፡
አንድ የአካባቢው ሰው በመንገድ ሲያልፍ አባ ቆራይ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ጸሎት ሲያደርጉ አያቸውና በሁኔታው ተገርሞ ወደ እርሳቸው ጠጋ ብሎ ስማቸውንና የመጡበትን አገር ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም "ስሜ አባ ቆራይ ይባላል፣ አገር ግን የለኝም" አሉት፡፡ እርሱም "እባክዎን ወደ መንደር እንሂድና የጸሎትና ቤት ሠርተንልዎት በዚያ ይቀመጡ" አላቸው፡፡ አባ ቆራይ ግን "ማረፊያዬ ይህቺ ናት፣ ከዚህች ሥፍራ አልነሣም" አሉት፡፡ አባ ቆራይም በዚያው እንደተቀመጡ ዝናቸው በሁሉ ዘንድ ተሰማና ሰዎች መጥተው በተቀመጡበት ድንጋይ ዙሪያ ጎጆ ቀለሱላቸው፡፡
ከዚህም በኋላ መንደርተኞቹ በየተራ በምግብ ሊረዷቸው ዕጣ ተጣጥለው ወደየቤታቸወ ሄዱ፡፡ በመጀመሪያ ተራ የደረሰው ሰው ከአንድ ሰዓት በኋላ ምግብ ይዞ ቢመለስ የአባ ቆራይ ጎጆ በብርሃን ተሞልታ አገኘ፡፡ ወደ ጎጆዋም ሲጠጋ ነበልባሉ እየፈጀው አላስቀርበው አለ፡፡ እርሱም በድንጋጤ ወደ መንደሩ ተመልሶ ለአካባቢው ሰው ነግሮ ሁሉም ተሰብስበው መጡ፡፡ መንደርተኛውም ካህናትን ይዘው ብዙ የምሕላ ጸሎትና እግዚኦታ ካደረሱ በኋላ እግዚአብሔር ወደ ጎጆዋ እንዲገቡ ፈቀደላቸውና ገቡ፡፡ ነገር ግን አባ ቆራይን በሕይወት አላገኟቸውም፡፡ አስክሬናቸውን ብርሃን ከቦት አገኙት፡፡ ከአስክሬናቸው አጠገብ "የአባ ቆራይን አስክሬን ከዚህች ጎጆ ውስጥ እንድትቀብሩት፤ ወደ ሌላ ቦታ ወይም ቤተ ክርስቲያን ወስደን እንቀብራለን ብላችሁ እንዳታስቡ፡፡ ነገሩን በድፍረት ብትፈጽሙት በሀገሩ ላይ እግዚአብሔርን ቁጣ ታመጣላችሁ" የሚል ትእዛዝ በብራና ተጽፎ ተገኘ፡፡ በዚሁ ትእዛዝ መሠረት የአሀሩ ሕዝብ ተሰብስቦ አባ ቆራይን ታኅሣሥ 15 ቀን እዚያው ቀበሯቸው፡፡
ከጥቂት ዘመናት በኋላ ባልና ሚስት የሆኑ ሰዎች መቆምም ሆነ መራመድ የማይችል ድውይ ልጃቸውን ይዘው ወደ ጸበል ሲሄዱ መሸባቸውና በአካባቢው ማደሪያ ሲፈልጉ የአባ ቆራይ ጎጆ ክፍት ሆኖ ታያቸውና ልጃቸውን ይዘው ሄደው ገቡ፡፡ ድውይ ልጃቸውን በአባ ቆራይ መቃብር ላይ ቢያስተኙት የኤልሳዕን አጥንት እንደነካውና ፈጥኖ እንደተነሣው ሙት ይህ ድውይ ልጅም በአባ ቆራይ መቃብር ላይ እንዳረፈ ወዲያው አፈፍ ብሎ በመነሣት እንደ እንቦሳ ጥጃ መዝለል ጀመረ፡፡ ወላጆቹም እልልታቸውን አቀለጡት፡፡ ወላጆቹም በነጋ ጊዜ ወደ መንደርተኛው ሄደው የተደረገላቸውን ተአምር ተናገሩ፡፡ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ የአባ ቆራይ በዓል በአካባቢውና አጎራባች ቦታዎች ሁሉ ዘንድ መከበር ጀመረ፡፡ የዕረፍታቸውም በዓል ታኅሣሥ 15 ቀን ሆነ፡፡
አባ ቆራይ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለይተው እንደ ቅዱስ አልዓዛር (ሉቃ. 16፡19-35) ለዚህ ዓለም ውዳቂ መስለው ለታላቅ ክብር የበቁ ጻድቅ አባት ናቸው፡፡ ዛሬም ልብሳቸውንና አካላቸውን ብቻ እያየን የምንንቃቸው ሰዎች እንደ አባ ቆራይ ያሉ ቅዱሳን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከልዑል እግዚአብሔር በቀር ማንም ማንንም የሚያውቅ የለም፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment