አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ዐስራ አራት በዚህች እለት #ቅዱስ_መርምህናም እና እኅቱ #ቅድስት_ሣራ በሰማዕትነት ዐረፉ፣ መኑፍ ከሚባል አገር #ቅዱስ_ስምዖን በሰማዕትነት ዐረፈ፣ #የቅድስት_ነሳሒት ለዕረፍቷ ነው፡፡
ታኅሣሥ ዐስራ አራት በዚህች እለት ቅዱሳን መርምህናምና እኅቱ ሣራ አርባ አገልጋዩቹ በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡ የዚህም ቅዱስ አባት የአቶር ንጉሥ የተቀረጹ ስማቸው ቤል አጵሎን የሚባሉ ጣዖታትን የሚያመልክ ነው እናቱ ግን ክርስቲያን ናት። ይህም ቅዱስ መርምህናም ወደ ዱር ሒዶ አራዊትን ያድን ዘንድ እንዲፈቅድለት አባቱን ለመነው በፈቀደለትም ጊዜ ወደ እናቱ ሒዶ "አራዊትን ለማደን ወደ በረሀ እሔዳለሁ" አላት እናቱም "የሰማይና የምድር አምላክ እግዚአብሔር በላይህ በረከትን ያሳድር" አለችው።
ከዚህም በኋላ ከአርባ ፈረሰኞች አገልጋዮቹ ጋር ወጥቶ ሔደ መቅሉብ ወደሚባል ተራራም ደርሶ በዚያ አደረ። በሌሊትም የእግዚአብሔር መልአክ ጠራው እንዲህም አለው "መርምህናም ሆይ ተነሥተህ ወደዚህ ተራራ ላይ ውጣ ስሙ ማቴዎስ የሚባል ቅዱስ ሰው ታገኛለህ እርሱም የሕይወትን ነገር ይነግርሃል" ሲነጋም ወደ ተራራው ወጣ እንደ በግ ጠጉር ለብሶ አባ ማቴዎስን አገኘው መርምህናም በአየው ጊዜ ፈራ ቅዱስ አባ ማቴዎስ "ልጄ ሆይ ወደ እኔ ቅረብ እኔም የእግዚአብሔር ፍጥረቱ የሆንኩ እንዳንተ ሰው ነኝ" አለው። መርምህናምም "ከአባቴ አማልክቶች በቀር አምላክ አለን?" አለው አባ ማቴዎስም የክርስትና ሃይማኖትን ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክርስቶስን ህልውና በተለየ አካሉ ሰው መሆኑንና መከራ ተቀብሎ መሞቱን መነሣቱን ወደ ሰማይ ማረጉንም የፍርድ ቀንም እንዳ ለጻድቃን በጎ ዋጋ ለኃጢአተኞች ቅጣት እንዳለ አስተማረው።
መርምህናምም "ከራስዋ እስከ እግርዋ ለምጽ የያዛት እኅት አለችኝ የአምላክህን ስም ጠርተህ በጸሎትህ ብታድናት እኔ አምንበታለሁ" አለው አባ ማቴዎስም "እኔ አድናታለሁ ና በአንድነት እንውረድ" አለው ከተራራው በወረዱ ጊዜ አባ ማቴዎስን በመንገድ ትቶ ቅዱስ መርምህናም ወደ እናቱ ሒዶ ሁሉን ነገራት እኅቱንም በሥውር ወደ አባ ማቴዎስ ወሰዳት አባ ማቴዎስም ወደ እግዚአብሔር ጸለየና ምድሪቱን አመሳቅሎ መታት በዚያን ጊዜ ውኃ መንጭቶ እንደ ባሕር ሆነ ወደ ባሕሩም አውርዶ እጁን በራሳቸው ላይ አድርጎ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው አሽከሮቹን አርባ ሰዎችንም ሥጋውንና ደሙንም አቀበላቸው ወዲያውኑ ሣራ ከለምጽዋ ነጻች።
ከዚህም በኋላ አባ ማቴዎስ ስለ ከበረ ስሙ በላያቸው የሚመጣውን መከራ በሚቀበሉ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን እንዲጸኑ መከራቸው ከዚህም በኋላ በላያቸው ጸለየና በፍቅ አንድነት አሰናበታቸው። ቅዱስ መርምህናምም በመጣ ጊዜ ወደ እናቱ ቤት ገባ ወደ አባቱ ወይም ወደ አማልክቶቹ አልሔደም አባቱም ሰምቶ ተቆጣ ወደ አማልክቶቹ ቤትም እንዲጠሩት አዘዘ ቅዱስ መርምህናም ግን ከእኅቱና ከሠራዊቱ ጋር ስሟ ቅሳር ወደ ምትባል ተራራ ሒዶ ከላይ ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ።
አባቱም በሰማ ጊዜ ከልብሰ መንግሥትና ከዘውድ ጋር መኳንንቱን "የመንግሥቴን ሥልጣን ተረከብ ብሎሃል" እንዲሉት ላካቸው እርሱ ግን በቊጣ ተመለከታቸውና "እኔ ክብር ይግባውና የጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጽሞ የማይጠፋ መንግሥት እሻለሁ" አላቸው። የአቶር ንጉሥ አባቱም በዚያን ጊዜ ተቆጣ ልቡ ፈርቶ ይመለስ ዘንድ አገልጋዮቹን በፊቱ እንዲገድሏቸው ካልተመለሰ ግን እርሱንም እኅቱንም እንዲገድሉ አዘዘ። ቅዱስ መርምህናምም ሰምቶ የተመኘውን ይሰጠው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ "ጸሎትህን ሰማሁ ልብህ የወደደውንም ሰጠሁህ" የሚል ቃል ከሰማይ መጣ። ከዚህም በኋላ የቅዱሳኑን ራሳቸውን በሰይፍ ቆረጡና ከጒድጓድ ውስጥ ጣሏቸው ሥጋቸውንም ያቃጥሉ ዘንድ ብዙ ዕንጨቶችን ሰበሰቡ ግን አላገኙአቸውም እግዚአብሔር ሠውሮዋቸዋልና።
ወዲያውኑ ንውጽውጽታ ሆነ ፀሐይም ጨለመ ወታደሮችም ፈርተው ሸሹ ሰይጣንም በአቶር ንጉሥ በሰናክሬም ላይ አድሮ አሳበደው እንደእሪያም ጮኸ የቅዱስ መርምህናምም እናት አይታ ወደ አባ ማቴዎስ ልካ አስመጣችውና የንጉሡን ነገር ነገረችው እርሱም በዘይት ላይ ጸልዮ ቀባው ሰይጣንም በእሪያ አምሳል ከርሱ ወጣ። በዚንም ጊዜ ንጉሥ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ ከቤተ ሰቦቹና በሚገዛው አገር ካሉ ሰዎች ሁሉ ጋር ተጠመቀ።
ከዚህም በኋላ አምላክን በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ ገንዘብንም ለድኆችና ለችግረኞች እንዲበትኑ አዘዘ ሁሉንም እንዳዘዛቸው አደረጉ። የቅዱስ መርምህናምም እናት ከከበሩ ደንጊያዎች አርባ ሣጥኖችን አሠራች የልጅዋ ጭፍራ የነበሩ የእነዚያን አርባ ሰማዕታት አጥንቶቻቸውን አሰብስባ በየአንዳንዱ ሣጥን ጨመረቻቸው ለልጆቿም ብርሌ ከሚመስል ዕንቊ ሁለት ሣጥን አሠርታ በውስጣቸው አድርጋ በሠራችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖረቻቸው ከሥጋቸውም ታላላቅ የሆኑ ቊጥር የሌላቸው ተአምራት ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች እለት መኑፍ ከሚባል አገር ቅዱስ ስምዖን በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ እርሱም በእስላሞች ዘመን ከመሳፍንቶቻቸው ከአንዱ ጋር ተከራከረና ቅዱስ ስምዖን ረትቶ አሳፈረው ያም እስላም ወደ መሳፍንቱ አለቃ ሒዶ "ይህ ስምዖን የእስላሞች ሃይማኖት ያቃልላል" ብሎ ወነጀለው ስለዚህም ይዘው በጽኑዕ ሥቃይ አሠቃዩት ከዚያም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ዕለት የውሲም ኤጲስቆጶስ አባ ያዕቆብ ስርሷ የተናገረላት የሮሜ ንጉሥ ልጅ ቅድስት ነሳሒት ዐረፈች፡፡ እንዲህም አለ በአንዲት ዕለት አምላክን በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያለሁ የገዳሙን ደጅ ሰው ሲያንኳኳ ሰማሁ ተነሥቼም ወደ በሩ ሔድኩ ያረጀ ዓጽፍ የለበሰ ፊቱንም የተሸፋፈነ ሰው አየሁ "ከወዴት መጣህ? ወዴትስ ትሔዳለህ?" አልሁት። "ከአባ መቃርዮስ ገዳም መጣሁ በዚች ሌሊት ከዚህ ገዳም አድሬ ቊርባንን መቀበል እሻለሁ" አለኝ። ያን ጊዜ ቀዳሚት ሰንበት ነበረች እኔም "ፊትህን ካላሳየኸኝ አልከፋትልህም" አልሁት እርሱም "ፊቴን ማየት አትሻ ፊቴ በኃጢአቴ የጨለመ ነውና ፊቴንም ለሚያይ የከፋች ሥራዬ ትታየዋለች" አለኝ። በከለከልኩትም ጊዜ ወደ ዱር ሊመለስ ወደደ እኔም ተርቦ ወይም ተጠምቶ እንደሆነ ብዬ በልቤ አሰብኩ ስለዚህም ከፈትኩለትና ወደ ማደሪያዬ አስገባሁት መብልንም አመጣሁለት እርሱም "ከነገ ከቊርባን በኋላ በቀር እኔ አልበላም" በማለት እምቢ አለኝ።
ከዚህም በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባና በጨለማ ቦታ ቆመ ከዚያ ያሉ መነኰሳትም እስከ አደነቁ ድረስ የዳዊትን መዝሙር ሲያነብ ድምፁን እንደ መላእክት ድምፅ ሁኖ ሰማሁት በነጋም ጊዜ በእግሮቹ ላይ ተቀመጠ ምንም ምን ማንበብ አልሻም። እኛ ግን ይጸልይልን ዘንድ ልንለምነው ቀረብን እርሱም "አባቴቼ ሆይ በበደሌ ብዛት ፊቴን ያጨለምኩ ስሆን ስለ እናንተ እንዴት እጸልያለሁ" አለን። ቊርባንንም በምናሳርግ ጊዜ በእግሩ ቁሞ የቅዱስ ጳውሎስን መልእክት፣ የሐዋርያትንም መልእክትና የሐዋርያትን ሥራ ማንበብ ጀምረ በአራተኛም ጊዜ በመሠዊያው ፊት ቁሞ የቅዱስ ዮሐንስን ወንጌል ማንበብ ጀመረ በፊቱም ላይ የተከናነበውን ልብስ አስወግደ ከፊቱም ብርሃን ገናናነት የተነሣ ሊያዩት አልተቻላቸውም። እኛ ቊርባንን ከተቀበልን በኋላ ቆረበ ከነገሥታት ልጆች ወገንም እንደሆነ ተጠራጠርን መብልንም በአቀረብንለት ጊዜ ከእኛ አልተቀበለም ነገር ግን ሰይጣን በእነርሱ ከሚያስትባቸው ሴቶችን ከማየት እንርቅ ዘንድ መከረን።
ሮማዊ የሆነ አንድ ደግ ጻድቅ አረጋዊ መነኵስ ነበር እርሱም "አባቴ ያዕቆብ ሆይ ይቺ ከነገሥታት ልጆች ውስጥ የሆነች ሴት ናት ስለዚህም እንዳትታወቅ ፊቷን ከሰው ትሠውራለች" አለኝ። ከዚህም በኋላ ሥራዋን ከእኔ ሳትሠውር እንድትነግረኝ በክርስቶስ ስም አምላት ዘንድ ወደርሷ ሔድሁ። ግን አላገኘኋትም ከአምስት ወርም በኋላ ከንጉሥ አባቷ ዘንድ የተላኩ ብዙ ሰዎች እርሷን እየፈለጉ መጡ። እነርሱም ቤተሶቦቿ ከተኙ በኋኋ በሌሊት እንደወጣች እነርሱም እርሷን ሲፈልጉ ዐሥራ ሁለት ዓመት እንደሆናቸው ሥራዋን ነገሩን። ከዚህም በኋላ መጻተኞች ሰዎች በዚች ቀን እንዳረፈች ነገሩን።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ በጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment