ስንክሳር_ዘወርኀ_ታህሣሥ 13 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታህሣሥ 13

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ዐስራ ሦስት በዚህች ቀን #ሊቀ_መላእክት_ቅዱስ_ሩፋኤል ቅዳሴ ቤቱና ተአምር ያደረገበት ዕለት ነው፣ ታላቁ አባት #አባ_መቃርስ_ገዳማዊ ዓመታዊ የዕርገታቸው መታሰቢያ ነው፣ መነኮስ #አቡነ_አብራኮስ_ገዳማዊ ዕረፍታቸው ነው፣ የሰማዕት #ቅዱስ_በጽንፍርዮስ ዕረፍቱ ነው፡፡


ታኅሣሥ ዐስራ ሦስት በዚህች ቀን በዚህች ዕለት ፈታሄ ማህጸን ሊቀ መልአክት ቅዱስ ሩፋኤል ቅዳሴ ቤቱና ተአምር ያደረገበት ዕለት ነው፡፡ ሰማያውያን ከሆኑ ከመላአክት አለቆች ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል ቀጥሎ 3ተኛ ነው፡፡ "ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል፡፡ ጦቢት 12፡15፡፡ ሩፋኤል የሚለው የስሙ ትርጓሜ ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል መልአከ የሰላምና የጤና መልአክ ይባላል፡፡ በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ሆነ ቁስል ይፈወስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ “በሰው ቁስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” መጽሐፈ ሄኖክ 6፡3፡፡
ቅዱስ ሩፋኤል የሰው ልጆች ከተያዙበት የኀጢአት ቁስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የማይለይ መልአክ ነው፡፡ “በበሽታ ሁሉ ላይ በሰው ልጆችም ቁስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡” በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል፡፡ ሄኖክ 10፡13፡፡ ለሴቶች ረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ በማኅፀን ላለ ችግርና ሴት በፀነሰችበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም፡፡ ሕፃኑ ዐርባ ቀን ሞልቶት በማሕፀን እያለ ማለትም በሥላሴ አርአያ መልኩ መሳል ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል አይለየውም፡፡ በመውለጃቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀላል፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነት ያለን ረቂቅ ርኩስ መንፈስ ያውቃል፡፡ አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በወለተ ራጉኤል ጭን ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሠቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል ጦቢት 3፡8-17፡፡
ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው” ሄኖክ 3፡5-7፡፡ በዚህ መሠረት ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሄኖክ 2፡18፡፡ ሰማያዉያን መዛግብት በእጁ የሚጠብቃቸው እግዚአብሔር እንዳዘዘዉ የሚከፍታቸዉ የሚዘረጋቸዉ ይህ ታላቅ መልአክ ነዉ፡፡
የምህረትና የረድኤት መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ከሥራዎቹ አንፃር በተለያየ ስም ይጠራል፡፡ "ፈታሄ ማህጸን" ይባላል-እናቶች ሲወልዱ ምጥ እንዳይበዛባቸዉ የሚራዳ መልአክ ስለሆነ አያሌ ክርስቲያኖች ማርገዛቸዉን ካወቁ ጀምሮ ድርሳኑን በማንበብ መልኩን በመድገም ጠበሉን በመጠጣት ሰዉነታቸዉን በመቀባት ይለምኑታል፡፡ እንደ እምነታቸዉ ጽናት ይደረገላቸዋል፡፡ ዳግመኛም "ዐቃቤ ኖኀቱ ለአምላክ" ይባላል-ሰማያዉያን መዛግብት በእጁ የሚጠበቅ ስለሆነ ነው፡፡ ዳግመኛም "መራሔ ፍኖት" ይባላል-ጦቢትን በቀና መንገድ መርቶታልና ነው፡፡ እንዲሁም "መላከ ክብካብ" ይባላል-ጦቢያና ሣራን ያጋባ ጋብቻቸዉን የባረከ በመሆኑ ነው፡፡
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ያደረገው ተዓምር ይህ ነው፡፡ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል በዓል እስኪፈፀም ድረስ በከበረ ሊቀ ጳጳስ አባ ቴዎፍሎስ ዘመን በምድረ ግብጽ ውስጥ ከእስክንድርያ ውጭ በታናፀች አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በአንድነት ተሰበሰቡ፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን ከአሳ አንበሪ ላይ የታነፀች ነበር፡፡ ነገር ግን በወደቡ አጠገብ ከነበረ ግዙፍ አንበሪ ጀርባ ላይ መታነጿን ቀድሞ ያነጿት ሰዎች ቢሆኑ ከካህናትም ቢኾን ያወቀ አልነበረም፡፡
ያ አንበሪም የቤተክርስቲያኑ ህንጻ በከበደው ጊዜ ፈጽሞ ተንቀሳቀሰ፡፡ ከአሸዋማው መሬት ላይ በባህሩ ዳርቻ የታነፀች ይህች ቤተ ክርስቲያንም ከመሰረቷ አናወጻት፡፡ ያን ጊዜ ትልቁም ትንሹም ወንዱም፣ ሴቶችም፣ የተሾሙ ዲያቆናት፣ ካህናት፣ ሕዝቡም ሁሉ ደነገጡ ታወኩ፡፡ አሣ አንበሪው ግን መንቀሳቀሱን አልተወም፡፡ በመንቀሳቀሱም የቤተ ክርስያኗ ሕንፃ እኩሌታ ይሰነጠቅ ዘንድ ጀመረ፣ ምድርን ተናወፀች፣ ንጉስና፣ ሊቀ ጳጳሳቱም፣ ካህናቱም፣ ዲያቆናቱም፣ ህዝቡም፣ ሁሉም ካሉበት በባህሩ ወደብ ከተሰራች ከዚህች ቤተ ክርስቲያን መናወጥ የተነሳ ፍርሃት መንቀጥቀጥ በላያቸው ወረደ፡፡ ያ አንበሪ ግን በባህሩ ውስጥ ወደፊት መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗም በጀርባው ላይ ነበረች፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የሉትም ሁሉ ያ አሳ አንበሪ ወደ ባሕሩ ውስጥ ሊያሰጥመን ነው ሲሉ አሠቡ፡፡ ያን ጊዜም በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ስዕል ፊት በጽኑ አለቀሱ፡፡ በአንድ ቃልም "ገናናው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ሆይ ርዳታህ ፈጥኖ ይደርስልን ዘንድ በቅድስት ቤተክርስቲያን ወደተሰበሰብን ወዳጆችህ ተመልከት" እያሉ ይጸልዩ ጀመር፡፡ ያንጊዜም የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ከሰማይ ወርዶ ያችን ቤተክርስቲያን በብሩሃት ክንፎቹ እንደደመና ጋረዳት፡፡ በእጁ በተያዘ የብርሃን በትረ መስቀሉ ያን ኣሣ አንበሪ ወገቶ "በኢየሱስ ክርስቶስ ሃይል ከቦታህ ሳትንቀሳቀስ እስከትውልድ ፍፃሜ ዘመን ለዘለአለም ትኖር ዘንድ አዝዝሃለሁ" አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ሊቀመላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያኗን ከነመዓዘኗ ከግርግዳዎቿ ከመሠዊያዋ በውስጧ ተተክለው ካሉት ሁሉ ጋር ከጀርባው ላይ እያለች ያንን አሳ አንበሪ ወግቶ በያዘበት ብርሃናዊ በትረ መስቀሉ ወደቀድሞው የባሕሩ ወደብ ጎተተው፡፡ ያንጊዜም ግንቡ ቦታውን ሳይለቅ እርስ በእርሱ ተጣበቀ፡፡
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል አሣ አንበሪውን በቀድሞ ሥፍራው ያቺን ቤተክርስቲያን በቀደመ መሠረቷ ላይ አጽንቷቸዋልና፡፡ ሊቀመላእክት ቅዱስ ሩፋኤልም አዳኝ የሆነ የጌታው የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ጠርቶ ከሞት እንዳዳናቸው ሁሉም አስተዋሉ፡፡ በድንቅ ተዓምራቱ የዳኑ ንጉሡና ሕዝቡም ሁሉ በሊቀመላእክቱ ቅዱስ ሩፋኤል ላይ አድሮ ድንቅ ተዓምራቱን ስለገለጸላቸው የቅዱስ ሩፋኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ የዚህች ቤተክርስቲያን ታሪክም በዓለም ሁሉ በየአውራጃዎቹም ተሰማ፡፡ የቅርብም የሩቅም ሰዎች ሁሉ ተሰብስበው ታላቁ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል የለመኑትን ሁሉ ያደርግላቸው ዘንድ የነገሩትን ያማልዳቸው ዘንድ በውስጧ ይጸልያሉ፡፡ በዚችም ቤተክርስትያን ብዙ ውስጥ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተደረጉ፡፡ ታኅሣሥ 13 ቀንም ተአምራቶቹ ከተፈጸመባቸው ዕለታት አንዷ ናት፡፡ ቅዳሴ ቤቱም በዚሁ ዕለት ተከናውኗል፡፡

ዳግመኛም በዚህች እለት ታላቁ አባት አባ መቃርስ ገዳማዊ ዓመታዊ የዕርገታቸው መታሰቢያ ነው፡፡ ይኸኛው መቃርስ ዕረፍቱ መጋቢት 27 ከሚውለው ከታላቁ መቃርስ ይለያል፡፡ በመቃርስ ስም የሚጠሩ ከ8 በላይ ሌሎች ቅዱሳንም አሉ፡፡ ታኅሣሥ 13 ቀን የዕርገቱ በዓል የሆነው መቃርስ ግን ቆቅ ይመገብ የነበረው መቃርስ ነው፡፡ እርሱም በልጅነቱ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እየተማረ አደገ፡፡ የዓለምን ከንቱነት ተመልክቶ ዳግመኛም የኃጥአንንና የጻቃንን ዋጋቸውን አይቶ ወደ ገዳም ገብቶ መነኮሰ፡፡ ከመነኮሰም በኋላ የ10 ቀን መንገድ ተጉዞ ኩዕንትና ቆቆች ውኃም ካለበት ተራራ ላይ ደረሰ፡፡ እንዲህም አለ፡- ‹‹ለምግቤ ኩዕንትን ወደ መልቀም ብሰማራ የስግደቴና የጸሎቴ ሥራ ይቋረጣል፣ በዚህም ተራራ ላይ ብቸኛ ነኝና ሰብስቦ የሚያስገባልኝ የለም፡፡ ሥጋ አትብላ ያለውስ የባልንጀራችንን ሥጋ በሐሜት የምንበላውን አይደለምን? ሌላ ምግብ እንደሌለኝ ፈጣሪዬ ያውቃል›› ብሎ ከዚያች ዕለት ወዲህ ለምግቡ ቆቅ የሚያጠምድ ሆኖ በእግዚአብሔር ፈቃድ በየቀኑ አንድ አንድ ቆቅ የሚያዙለት ሆነ፡፡ በየቀኑም አንድ አንድ ቆቅ እየተመገበ ውኃ እየጠጣ ፈጣሪውን እያመሰገነ በታላቅ ተጋድሎ ሆኖ የሰውን ፊት ሳያይና ከማንም ጋር ሳይነጋገር ብዙ ዘመን ኖረ፡፡
ከቍስጥንጥንያ ከተማ የመጣ አንድ መነኩሴ ዋሻ ሲፈልግ አባ መቃርስ ደግሞ ቆቅ ሲያጠምድ አየውና ለሐሜት ቸኩሎ ወደ ቍስጥንጥንያ ተመልሶ ሄዶ ለሊቀ ጳጳሳቱ ‹‹ቆቅ እያጠመደ ሥጋ የሚበላ መነኩሴ አገኘሁ፣ እርሱም በሕዝብ ዘንድ ሊያስነቅፈን ነው›› ብሎ ነገረው፡፡ ሊቀ ጳጳሳቱም ከአንድ ሌላ መነኩሴ ጋር ድጋሚ እንዲያረጋግጡ ላካቸው፡፡ እነርሱም ገና ከበዓቱ ሳይደርሱ አባ መቃርስ ቆቅ ሊያጠምድ ሄደና ያለወትሮው በአንዲት ወጥመድ ሦስት ቆቆችን ተያዙለት፡፡ ሌላ ጊዜ በቀን አንድ ብቻ ነበር የሚያዝለት ዛሬ ግን እግዚአብሔርም ለሚመጡት እንግዶችም ጭምር ሲያዘጋጅላቸው ነው ያለወትሮው ዛሬ ሦስት ሆነው የተያዙለት፡፡
አባ መቃርስም ሁለቱን መነኮሳት ሲያያቸው ሁለቱ ተጨማሪ ሆነው የተያዙለት ቆቆች የእንግዶቹ መሆናቸውን ዐውቆ ጌታችንን አመሰገነው፡፡ እነርሱ ግን ማዕድ ሠርቶ እስካቀረበላቸው ድረስ በመቃርስ ላይ ይጠቋቆሙበት ነበር፡፡ አባ መቃርስም ምግብን አዘጋጅቶ ሲጨርስ የራሱን ድርሻ አንዷን ቆቅ አስቀርቶ ሁለቱን ለእንግዶቹ አቀረበላቸው፡፡ እርሱ በልቶ ጨርሶ ቀና ሲል እንግዶቹ መነኮሳት እንዳልበሉ ተመለከተና ‹‹አባቶቼ ለምን አልበላችሁም?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹እኛ መነኮሳት ስለሆንን ሥጋ አንበላም ትኅርምትም አለን›› አሉት፡፡ አባ መቃርስም ‹‹እሺ ተውት›› አላቸውና እነዚያን አብስሎ በገበታ ላይ ለምግብነት ያቀረባቸውን ሁለት ቆቆች ሦስት ጊዜ በእስትንፋሱ እፍ ቢልባቸው ሕይወት ዘርተው በረሩና ወደ ጫካ ሄዱ፡፡ እነዚያ መነኮሳትም እጅግ ደንግጠው ‹‹ማረን ይቅር በለን፣ ቅዱሱን የእግዚአብሔር ሰው በከንቱ አምተንሃል›› ብለው እግሩ ሥር ሲወድቁ ‹‹እግዚአብሔር የሁላችንን በደል ይቅር ይበለን›› አላቸው፡፡
ሁለቱ መነኮሳት ወደ ቍስጥንጥንያ ተመልሰው ለሊቀ ጳጳሳቱና ለሕዝቡ ያዩትን ነገር መሰከሩ፡፡ ሊቀ ጳጳሳቱም እጅግ ተደንቆ ወደ ንጉሡ ደብዳቤ ጽፎ ‹‹በምድራችን ጻድቅ ሰው ተገኝቷልና አንተም ና ሄደን በረከቱን እንቀበል›› ብሎ መልእክት ላከበት፡፡ ንጉሡም እሺ ብሎ ከሠራዊቱ ጋር ተነሥቶ ከካህናቱ ጋር ወደ አባ መቃርስ ዘንድ ሄዱ፡፡ ወደ ገዳሙም በቀረቡ ጊዜ አባ መቃርስን ወደ ብሔረ ሕያዋን ያደርሰው ዘንድ መልአክ አንሥቶ በክንፎቹ ተሸክሞት ሲያርግ አዩት፡፡ እነርሱም ‹‹የእግዚአብሔር ቅዱስ ሆይ ባርከን፣ የምንድንበትንም አንዲት ቃል ንገረን›› አሉት፡፡ አባ መቃርስም ‹‹ከሐሜትና ከነገር ሥራ አንደበታችሁ ይከልከል፤ ካህን ብዙ ባይማር ትዕቢትና መታጀር ባልመጣበት ነበር፣ መነኩሴም ትኅርምት ባያበዛ ባልተመካም ነበር፡፡ እርስ በእርሳችሁ ተፋቀሩ፡፡ እግዚአብሔር አድሮባችሁ ይኑር›› አላቸው፡፡ ይህንንም ከተናገራቸውና ከባረካቸው በኋላ ከዐይናቸው ተሰወረ፡፡ ይህም ዕርገቱ ታኅሣሥ 13 ቀን የተፈጸመ ነው፡፡

ዳግመኛም በዚህች ቀን መነኮስ አቡነ አብራኮስ ገዳማዊ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ይኽም ቅዱስ ዕድሜው 20 ዓመት በሆነው ጊዜ የዚህን ዓለም ኃላፊነት ተረድቶ የነፍሱን ድኅነት ሽቶ መንኩሶ ገዳም ገባ፡፡ በዚያም በታላቅ ተጋድሎ ሲኖር ሰይጣን በቅናት ተነሳስቶበት ብዙ ፈተናዎችን አመጣበት ነገር ግን ቅዱስ አብራኮስ ጽኑ በሆነው መንፈሳዊ ተጋድሎው ሰይጣንን ድልነሣው፡፡ ሰይጣንም በተደጋጋሚ መሸነፉን አይቶ የፈተናውን ዓይነት ለወጥ አድርጎ በሰንፍና ሊጥለው ፈለገ፡፡ እናም ሰይጣን በግልጽ ፊት ለፊት ተገልጦ ቅዱስ አብራኮስን ‹‹እነሆ ከዚህ ዕድሜህ ሌላ 50 ዓመት ቀረህ›› አለው፡፡ ቅዱስ አብራኮስም ሰይጣን በስንፍና ሊጥለው ያመጣበት ፈተና መሆኑን ዐውቆ በተራው ሰይጣን ላይ ተራቀቀበት፡፡ እንዲህም አለው፡- ‹‹አሁንስ ልቤን አሳንከው፣ እኔ ሌላ መቶ ዓመት እኖር ዘንድ ስላሰብኩ ቸል ብያለሁ ነገር ግን አንተ እንዳልከው 50 ዓመት ከሆነ የምኖረው ከቀድሞው እጅግ አብዝቼ እጋደል ዘንድ ይገባኛል›› አለው፡፡ ሰይጣንም ይህን ጊዜ አፍሮ ከእርሱ ሸሸ፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ አብራኮስ ጽኑ የሆነ ተጋድሎውን በገድል መጠመዱን አብዝቶ ከ70 ዓመት ተጋድሎው በኋላ በሰላም ዐረፈ፡፡

በዚህች እለት የሰማዕት ቅዱስ በጽንፍርዮስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይኽም ቅዱስ አባት ዓለምን ንቆ በመመንኮስ በታላቅ ተጋድሎ ይኖር ነበር፡፡ የሚያገለግለውም በምስር አገር በወንዝ ዳር ባለች በሊቀ መላእክት በቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ስለቀናች ተዋሕዶ ሃይማኖቱም ከእስላሞች መሳፍንት ጋር ተከራከረ፡፡ የጌታችንም የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነቱን ገለጠላቸው፡፡ እስላሞችም ባፈሩ ጊዜ በእርሱ ላይ ተቆጡ፡፡ ከዚህም በኋላ እስላሞች አባ በጽንፍርዮስን ይዘው በእጅጉ አሠቃዩት፡፡ በመጨረሻ ራሱን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን መልእክት አና ጻድቃን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages