ስንክሳር_ዘወርኀ_ታህሣሥ 12 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታህሣሥ 12

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ዐስራ ሁለት #የአቡነ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ ዐረፉ፣ #ቅዱሳን_አንቂጦስ እና #ቅዱስ_ፎጢኖስ በሰማዕትነት ዐረፉ፣ #ዳግማዊ_ቂርቆስ የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ልጅ ብሔረ ብፁዓን የገባበት ነው፡፡


ታኅሣሥ ዐስራ ሁለት በዚህች ዕለት ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የሥሉስ ቅዱስን መንበር ያጠኑ አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ዋሊ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ጻድቁ የተወለዱት በአክሱም ጽዮን ነው፡፡ ነገዳቸው የአክሱም ገበዝ ከነበረው ከጌድዮን ነው፡፡ የአባታቸው እስጢፋኖስና እናታቸው አመተ ማርያም ምግባር ሃይማኖታቸው የቀና ትሩፋት ተጋድሏቸው የሰመረ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ገና በ12 ዓመቱ ማይ ሹም በተባለው ባሕር ገብቶ ሲጸልይ ባሕሩ በብርሃን ተከቦ ይታይ ነበር፡፡ ከባሕሩም ወጥቶ ወደ ቤተክርስቲያን ገብቶ እያለቀሰና እያዘነ ሲጸልይ ካህናቱ ‹‹ይህ ሕፃን የእኛ ኃጢአት እየታየው? ወይስ ምን ኃጢአት ኖሮበት ነው እንዲህ የሚያዝነውና የሚያለቅሰው?›› እያሉ ያደንቁና ይገረሙ ነበር፡፡
አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ እናቱ አመተ ማርያም ቤተሰቧንና ቤት ንብረቷን ትታ ከመነኮሰች በኋላ እርሱም ካልመነኮስኩ በማለት አባቱ እስጢፋኖስን ቢለምነውም እምቢ ስላለው በራሱ ፈቃድ ከአንድ ሽማግሌ ጋር ወደ አባ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ደብረ በንኰል ገብቶ መነኮሰ፡፡ በዚያም ነፍሱን ‹‹ነፍሴ ሆይ! እነሆ ለክርስቶስ ታጨሽ፣ የቅዱሳንን ቀንበር እንሆ ተሸከምሽ፣ የመላእክትን ንጽሕና ትጠብቂ ዘንድ ዛሬ በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ሁሉ ፊት ቃልኪዳን ገባሽ፣ ቃልኪዳንሽን ብትጠብቂ መላእክት ይደሰቱብሻል፣ ባትጠብቂ ግን አጋንንት ይዘባበቱብሻል…›› እያለ ብዙ መከራን በራሱ ላይ በማብዛት ሰባት ዓመት በዚያች ገዳም ኖረ፡፡ እህልም አይቀምስም ነበር ይልቁንም የሚሰጡትን እንጀራ ለሕጻናትና ለውሾች እየሰጠ አሠር ይመገብ ነበር፡፡
ዳግመኛም በሌላ ጊዜ ቅጠልን እየቀቀለ እስከ አምስት ቀን ከድኖ ያስቀምጠዋል፣ እስከሚተላም ድረስ ይጠብቀውና ያን ይመገባል፡፡ ኩስይ የምትባል ከሣር ሁሉ የምትመርን ሣር ምግቡ አደረገ፡፡ በኋላም አባቱም ልጁን ሳሙኤልን ተከትሎ ወደ እርሱ መጥቶ በአባ እጅ መነኮሰ፡፡ ለአባቱም መምህር ሆኖት እያገለገለው ያስተምረው ነበር፡፡ በሌላም ጊዜ 17 ዓመት ከተቀመጠባት ወይና በምትባል ቦታ ሲኖር ከውኃ በቀር ምንም ሳይቀምስ 12 ዓመት ተቀምጧል፡፡ ለ50 ዓመትም ያህል ሣር፣ ቅጠል፣ የዛፍ ሥርና ፍሬን እነዚህንና የመሳሰሉትን እየበላ ኖረ እንጂ እህል የሚባል አልበላም፡፡
ወጥቶም ወደ ዋሻ እየገባ ብዙ ጊዜ 40 ቀንና 40 ሌሊት በጾም በጸሎት እየኖረ እንቅልፍም እንዳያሸንፈው እስከሚነጋ ድረስ ሳይቆም ሳይተኛ እንደቆመ በጽኑ ተጋድሎ ተቀመጠ፡፡ ትልቅ ጉድጓድ ቆፍሮ በውስጡ እየገባ ሳይቀመጥ ሳይተኛ ሰውነቱ እንደ እንጨት እስኪደርቅ ድረስ በጾም በጸሎት በእጅጉ ይተጋ ነበር፣ በዚህም ወቅት ጌታችን ተገልጦለት ሰውነቱን በሙሉ ምራቁን ስለቀባለትና አውራ ጣቱን ስላጠባው ከዚህ ጊዜ በኋላ ርሀብና ጥሙ ጠፍቶለት ሰውነቱም ታድሶለታል፡፡ ዳግመኛም በአፉም ድንጋይ ጎርሶ፣ እግሩንም ታስሮና ማቅ ለብሶ ወደ ባሕር እየገባ ይጸልይ ነበር፡፡
አባታችን አባ ሳሙኤል በሕይወተ ሥጋ ሳለ እጅግ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን አድርጓል፡፡ እንደሙሴ ባሕርን የከፈለበት ጊዜ አለ፤ በልዑልም ዙፋን ፊት እየቀረበ ከቅዱሳን መላእክት ጋር የሚያመሰግንበት ጊዜ አለ፣ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም ጋር ሆኖ የሚያጥንበት ጊዜ አለ፤ በሰማያዊት ኢየሩሳሌምም ሆኖ ከእነ ቅዱስ ጴጥሮስና ከሁሉ ቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታት ጋር በአንድ ላይ ማዕድ የሚቀርብበት ጊዜ አለ፤ በእጆቹ የያዛቸው መጻሕፍቶቹ ምንም ሳይርሱ ትልቅ ወንዝን በውስጡ እያቋረጠ የሚሻገርበት ጊዜ አለ፤ እመቤታችንንም ሲያመሰግናት ከምድር ወደ ላይ አንድ ክንድ ያህል ከፍ የሚልበት ጊዜ አለ፤ በቤትም ውስጥ ሆኖ ምስጋናዋን ሲጀምር የቤቱ መሠረት እየተናወጠ ዝናብ እንደያዘ ደመና ቤቱ ከምድር ከፍ ብሎ የሚቆምበት ጊዜ አለ፤ መንፈስ ቅዱስም በብርሃን ክንፍ እየወሰደው ወደተለያዩ ገዳማት ያደርሰውና ሥጋ ወደሙን እንዲቀበል ያደርገው ነበር፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም የሁልጊዜ ጠባቂው ነውና በሁሉ ነገር ይራዳውና እንደ ጓደኛም ያማክረው ነበር፡፡ በአንዲት ዕለትም በጎዳና ሲጓዝ ወንዝ መልቶበት አገኘው፡፡ አባታችንም መጻሕፍቶቻቸውንና እሳት በእጃቸው እንደያዙ በወንዙ ውስጥ ለውስጥ ውኃውን አቋርጠው ሲሻገሩ መጻሕፍቶቻቸው አልራሱም በእጃቸው የነበረው እሳትም አልጠፋም ነበር፡፡
አባታችን ሊያስቀድሱ ወደ በተ መቅደስ በሚገቡ ጊዜ ሰማያዊ ኅብስትና ጽዋ ይወርድላቸው ነበር፡፡ የእመቤታችንንም ውዳሴዋን ሲደግሙ ክንድ ከስንዝር ያህል ከምድር ከፍ ይሉ ነበር፡፡ እመቤታችንም እየተገለጠች ንጹሕ ዕጣንንና የሚያበራ እንቁን ሰጥታቸዋለች፡፡
ቅዱስ አባታችን ለክቡር ሥጋ ወደሙ እጅግ ትልቅ ክብር አላቸው፡፡ በቤተክርስቲያን አስቀድሰው ሁሉም ሥጋ ወደሙን ተቀብለው ወደ ቤታቸው ሲወጡ ከአራቱ መነኮሳት ውስጥ አንዱ አስታወከ፣ በቤተክርስቲያንም ዳርቻ ተፋው፡፡ ያዩትም ሁሉ ደንግጠው ቆሙ፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ብፁዕ ሳሙኤል ግን ሁሉንም በአፉ ተቀበለው፣ በምላሱም መሬቱን ላሰው፡፡ ይህን ጊዜ ከሰማይም ‹ሳሙኤል ሳሙኤል› የሚልን ድምጽ ሰማና ወደላይ ባንጋጠጠ ጊዜ ሰባቱ ሰማያት ተከፍተው አየ፡፡ ከላይ ያለው ያ ቃልም መለሰ፡- ‹በሰው ፊት እንዳመሰገንኸኝና ፈጽሞም እንዳከበርከኝ የባልንጀራህን ትውኪያ ትቀበል ዘንድ እንዳላፈርህ እኔም እንዲሁ አከብርሃለሁ፤ በሰማያት ባለው በአባቴም ፊት በመላእክት ማኅበር አመሰግንሃለሁ› አለው፡፡›› ሌሎቹም ቅዱሳን እነ አቡነ ተክለሐዋርያትም እንዲሁ ለሥጋ ወደሙ ክብር ሲሉ የቆረበ ሰው ሲያስመልሰው የዚያን ሰው ትውኪያ ይጠጡት እንደነበር በቅዱስ ገድላቸው ላይ በሰፊው ተጠቅሷል፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ለክርስቶስ ያላቸው ክብር እስከዚህ ድረስ ነው፡፡
አንድ ቀን አባታችን በገዳም ውስጥ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይጎበኘው ዘንድ ወደ እርሱ መጣ፡፡ ከእርሱም ጋር ተቀምጦ ‹ወዳጄ ሆይ! ሰላምታ ይገባሃል፡፡ አንተ ግን ከትንሽነትህ ጀምሮ አገለገልኸኝ፣ ምን አደርግልህ ዘንድ ትወዳለህ?› አለው፡፡ ትሑት ሳሙኤልም ‹የነፍሴ ወዳጅ ጌታዬና አለቃዬ ሆይ! መልካም ሀብት ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና ምሕረትህንና ብሩህ ፊትህን ታሳየኝ ዘንድ እሻለሁ› አለ፡፡ ጌታችንም ‹አገልጋዬ ወዳጄ ሆይ! የፈለግኸውን እሰጥሃለሁ፣ ዳግመኛም ያልፈለግኸውንም እጨምርልሃለሁ› አለው፡፡ አባ ሳሙኤልም ‹ጌታዬ ሆይ! አንዲት ልመናን እለምንሃለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ኃጢአቴን አይ ዘንድ እወዳለሁ፡፡ የሌላውን ኃጢአት ግን አታሳየኝ› አለው፡፡
አባ ሳሙኤልን የዱር አራዊትም ሁሉ ይገዙለት ነበር፡፡ ታላቅ የሆነ ዘንዶ፣ ነብር፣ ጅብ፣ ቶራህ፣ ዝሆን፣ አንበሳና ሌሎችም የዱር አራዊት ሁሉ እየመጡ እግሩን እየላሱት ወደ ቦታቸው ይመለሱ ነበር፡፡ አንበሶቹንም እሾህም በወጋቸውና እግራቸው መግል በያዘ ጊዜ በመርፌ እያነቆረ ያድናቸው ነበር፡፡ ስንጥርም ሲወጋቸው ወደ እርሱ እየመጡ ያሳዩትና ያወጣላቸው ነበር፡፡ አንበሳም አጋዘንን ገድሎ ሲበላ ሲያየው ‹‹አንዴ ዞር በልልኝ ቆዳዋን ለልብሴ እፈልገዋለሁ›› ባለው ጊዜ ይለቅለት ነበር፡፡ እንዲሁም አንበሳው ለአባታችን ምግብም ትሆነው ዘንድ ጅግራን እየያዘ በሕይወት ሳለች ያመጣለት ነበር፡፡ አባታችንም ከገዳም ወጥቶ መሄድ በፈለገ ጊዜ አንበሶችን እንደ ፈረስና በቅሎ ይጋልባቸዋል፣ መጻሕፍቶቹንም ይጭንባቸዋል፤ መንታ የወለደች አንበሳም ብትኖር ልጆቿን እየታቀፈ በየተራ ያጠባቸው ነበር፡፡
ወደ ደብረ ዋሊም በሄደ ጊዜ ጌታችን ተገልጦለት በዕለቱ የእመቤታችን በዓል ስለነበር እንዲቀድስ ነግሮት ከሰማይ ኅብስትና ጽዋ መጥቶለት ቅዱሳን ሐዋርያት በቀኝ በግራ እየተራዱት ሲቀድስ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ ኅብስቱንና ጽዋውን ጋርዶታል፡፡ ጌታችንም ቦታዋንና በዚያ ያሉትን መነኮሳት ሁሉ ልጆቹ ይሆኑ ዘንድ አስራት አድርጎ ሰጠው፡፡ ዋልድባ የተመሠረተው በቀደምት ጥንታዊያን አበው ቢሆንም አባ ሳሙኤል ሲገቡበት ምድረ በዳ ሆኖ ጠፍቶ ቋያ በቅሎበት የወባ ትንኞች መፈልፈያ ሆኖ ነበር፡፡ አባታችን ግን የተበታተኑትን መነኮሳት ሰብስበው ዋልድባን እንደገና አደራጅተውና አድሰው አቀኑት፡፡ የተባሕትዎ ኑሮንም አጠናከሩበትና ገዳሙን የመናንያን አበው መሰብሰቢያ አደረጉት፡፡ አባታችን ዋልድባን እንደ ሞሰብ አንስተው አስባርከዋታል፡፡
አባ ሳሙኤል ጊዜው ደርሶ ከማረፉ በፊት ቅዱስ ሚካኤል ነሐሴ 16 ቀን ወደ ገነት ነጥቆ ወስዶ ከዕረፍቱ በኋላ ከልጆቹ ጋር የሚኖርበትን ሥፍራ አሳይቶታል፡፡ በገነት ያሉ ቅዱሳንን ሁሉ ካሳየው በኋላ በእግዚአብሔርም ዙፋን ፊት ቀርቦ ምስጋናና ቃልኪዳንን ተቀብሎ ወደ በዓቱ ተመልሶ ታኅሣሥ 12 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፎ ነፍሱን ጌታችን በእጆቹ ተቀብሏታል፡፡
መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ የገባላቸው ልዩ ቃልኪዳን፡- ‹‹መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም ወደ ገነት ነጥቆ ወስዶ በዚያ ያሉ ቅዱሳንን ሁሉ መኖሪያቸውንና ክብራቸውን አሳየኝ፡፡ ‹እነሆ የተጋድሎህን ሥራ ፈጽመሃልና አንተም ወደተዘጋጀችልህ ትመጣ ዘንድ ጊዜህ ቀርቧል› ብሎ ጌታዬ የሰጠኝን መኖሪያዬን አሳየኝ፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ልዑል ዙፋን ወደ አርያም አደረሰኝ፡፡ በዚያም በክብሩ ዙፋን በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ተወዳጅ ወልድን አየሁት፡፡ በዚያም እመቤታችን ማርያምን ከተወዳጅ ልጁዋ ቀኝ አየኋት፡፡ የብዙ ብዙ ቅዱሳን መላእክትና ጻድቃን ሰማዕታት ሁሉ በየወገናቸው ‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ፍጹም አሸናፊ እግዚአብሔር የክብር ምስጋና ሰማያትንና ምድርን መላ› እያሉ በፊቱ ይዘምሩ ያመሰግኑ ነበር፡እኔም በአምላኬ ፊት ሰገድኩ፡፡ ተወዳጅ ወልድም ተናገረኝ፣ እንዲህም አለኝ፡- ‹ወዳጄ ሳሙኤል ሆይ! ሰላምታ ይገባሀል፣ ደስ ይበልህ፡፡ በጥቂቱ የታመንህ ባሪያዬ ሆይ በብዙ እሾምሃለሁ፡፡ እኔን በመውደድ ብዙ ደክመሃልና የመስቀሌንም መከራ በመሸከም እኔን መስለሃልና እኔም በመንግሥቴ መልካም የሆነውን የድካምህን ዋጋ እሰጥሃለሁ፡፡ እነሆ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የተካከለ መቀመጫህንና አክሊልህን አዘጋጀሁልህ፣ ዕድል ዕጣህም ከአሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ሐዋርያቶቼ ጋር ነው፡፡ አፅምህ በተቀበረበት፣ የገድልህ መጽሐፍ በተነበበት፣ መታሰቢያህ በተደረገበት፣ ሥፍራ ሁሉ ምሕረትና ድኅነት ይሁን፡፡ በጸሎትህ የሚታመነውን፣ መታሰቢያህን የሚያደርገውን ሁሉ ለአንተ አሥራት ሰጥቼሃለሁ፡፡ ስለ እኔ የተቀበልከውን ድካም ሁሉ ዛሬ ያገኘኸውን የአንዲት ቀን የደስታ ልክ አይሆንም፡፡››

ዳግመኛም በዚህች ቀን ወንድማማቾቹ ቅዱሳን አንቂጦስ እና ቅዱስ ፎጢኖስ በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡ ከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ መእመናንን የሚያሠቃይባቸውን የማሠቃያ መሣሪያዎች ለሕዝቡ እያሳየ ሲያስፈራራ የጸኑንም ሲገድል ቅዱስ አንቂጦስ በሕዝቡ መሐል ቆመና ንጉሡን ስለከንቱ እምነቱ ዘለፈው፡፡ ንጉሡም ይዞ ብዙ ካሠቃየው በኋላ በሕዝቡ ፊት ለተራበ አንበሳ ሰጠው፡፡ ነገር ግን አንበሳው ቅዱስ አንቂጦስን ፊቱን አሻስቶ ሲተወው በማየቱ ንጉሡ ሰይፉን መዞ ሊሰይፈው ሊሄድ ሲል መንቀሳቀስ ተሳነው፡፡ ከዚህም በኋላ ሰውነትን ቆራርጦ ወደሚጥል መንኮራኩር ውስጥ ከተተው ነገር ግን ሰማዕቱን ጌታችን ፍጹም ጤነኛ አድርጎ አስነሣው፡፡
ንጉሡ ዳግመኛ ቅዱስ አንቂጦስ እርሳስ ካፈሉበት ትልቅ ጋን ውስጥ ቢጨምረውም የታዘ መልአክ ከጋኑ ውስጥ ነጥቆ አውጥቶ በንጉሡ ፊት አቆመው፡፡ ይህን ጊዜም ወንድሙ ፎጢኖስን አንጢቆስን አቅፎ ካሳመው በኋላ ንጉሡን ‹‹አንተ ከዳተኛና ጎስቋላ ንጉሥ ወንድሜን ታሸንፈው ዘንድ አይቻልህም አምላኩ ይጠብቀዋልና›› አለው፡፡ ንጉሡም የሚያደርግባቸውን ነገር እስኪያስብ ድረስ ቅዱሳኑን ወንድማማቾቹን እጅና እግራቸውን አሳሥሮ ወህኒ ቤት ጨመራቸው፡፡
በማግሥቱም አውጥቶ ሰውነታቸውን ጥፍር ባለው ብረት ሰነጣጠቃቸው፡፡ ወደ አደባባይም አውጥቶ በድንጋይ አስወገራቸው፡፡ ከብዙ ግርፋትም በኋላ በቁስላቸው ላይ ጨው ጨምሮ ካሠቃያቸው በኋላ እሳት ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ነገር ግን አሁንም እሳቱ እንደቀዝቃዛ ጠል ሆነላቸው፡፡ ንጉሡም ይህን ባየ ጊዜ ነበልባሉ ከፍ ብሎ እስኪታይ ድረስ እሳት አስነድዶ ከዚያ ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ቅዱሳኑም ከእሳቱ ውስጥ ሆነው በመስቀል ምልክት አማትበው ረጅም ጸሎት ካደረጉ በኋላ ቅድስት ነፍሳቸውን ለእግዘኢብሔር አሳልፈው ሰጡ፡፡ የሥጋቸውም በድን ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት ድረስ ከእሳቱ ፍሕም ላይ ነበር ነገር ግን የራሳቸው ፀጉር እንኳን አልተቃጠለችም ነበር፡፡ ምእመናንም ቅዱስ ሥጋቸውን ወስደው በክብር አስቀመጡት፡፡ ከሥጋቸውም ብዙ አስደናቂ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡

#ዳግማዊ_ቂርቆስ (የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ልጅ)
በዚህችም ቀን ዳግማዊ ቂርቆስ የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ልጅ ብሔረ ብፁዓን የገባበት ነው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፡- ብፅዕት ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ከአገልጋዮቿ መካከል አንዷ ምግባሯ የከፋ ነበርና በጣም ስላበሳጨቻት በዚያች አገልጋይ አፍ ውስጥ የእሳት ትንታግ ጨመረችባት፡፡ ያም የእሳት ትንታግ እስከ ጉሮሮዋ ዘለቀና አገልጋይዋን ገደላት፡፡ በዚህ ጊዜ ብጽዕት ክርስቶስ ሠምራ ደንግጣ ወደ ሌላ ክፍል ገባችና ኃጢአቷን ለእግዚአብሔር እየተናዘዘች እጅግ በጣም አዝና ጥፋቷ እንደ ጸጸታትና እግዚአብሔር አምላክም በእጇ የሞተችውን አገልጋይዋን ከሥጋዋ አዋሕዶ ቢያሥነሳላት ያላትን ገንዘብና ሀብት ትታ ባላት ዘመኗ ሁሉ አገልጋዩ እንደምትሆን ብጽዓት (ስዕለት) አደረገች፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቷን ሰምቶ አገልጋይዋን ከሞት አሥነሳለት፡፡ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ‹‹ልመናዬን ቸል ያላለ ቸርነቱንም ከእኔ ከባሪያው ያላራቀ አምላክ ይክበር ይመስገን›› ብላ በታላቅ ምስጋና እግዚአብሔርን ካመሰገነች በኋላ አስቀድማ የገባችውን ቃል አስባ ልብሰ ምንኩስናዋን አዘጋጀች፡፡ ሕፃን ልጅዋንም ይዛ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደች፡፡ ስትሄድም በልስላሴና በእንክብካቤ የኖረ እግሯ ከመንገዱ ብዛት ከእንቅፋቱም የተነሳ ፈለግ ሲያወጣ ሥጋውን እየቆረጠች ስትጥለው ደሟ መሬት ለመሬት እየፈሰሰ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ደረሰችና አስቀድማ ያዘጋጀችውን ልብሰ ምንኩስናዋን ለብሳ ከሴቶች ገዳም ገባች፡፡
ቅድስት እናታችን ይዛው የተሰደደችውን የ3 ዓመቱ ሕፃን ግን ወንድ ስለሆነ ከደጅ ላይ አስቀምጣው ስለገባች ሕፃኑ አምርሮ አለቀሰ፡፡ በዚህም ጊዜ ከመነኮሳይያቱ አንዲቷ ‹‹ሕፃኑ ሲያለቅስ ከሚያድር›› ብላ ወደ በአዓቷ ልታስገባው ስትል የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሕፃኑን ነጥቆ ወስዶ በገነት አስቀመጠው፡፡ እርሱም ታኅሣሥ 29 ቀን ተወልዶ በ3 ዓመቱ ታኅሣሥ 12 ቀን ብሔረ ብፁዓን ገብቷል፡፡ እጅግ አሳዛኝ ገድሉ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ይገኛል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት አና ጻድቃን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages