ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 19 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 19

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ዕለት የከበሩ #የአባ_ዝሑራ #የአባ_ባሱራ የእናታቸውም #የኔራ ሥጋቸው የተገኘበት ነው፣ የታላቁ አባት #የአቡነ_አፍቅረነ_እግዚእ እረፍታቸው ነው።


ጥር ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ዕለት የከበሩ የአባ ዝሑራ የአባ ባሱራ የእናታቸውም የኔራ ሥጋቸው ተገኘ።
እሊህ የከበሩ ተጋዳዮችም ጣዖት በሚመለክበት ዘመን ሳብሳ ከሚባል አገር በሰማዕትነት ሞቱ ሥጋዎቻቸውም በሳብሳ አገር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚኖሩ ሆኑ ከንጹሐን ሰማዕታትም ዘመን ከዘጠኝ መቶ አርባ ሰባት ዓመት በኋላ የአፍርንጊ ሠራዊት ግብጽን ከበቧት የድምያጥንም ከተማ ወስደው በዚያ ነገሡ ከርሷ ጋርም በዙሪያዋ ያሉ ታላላቅ ከተሞችን ያዙ።
የኮሞል ንጉሥም ይህም የግብጽ ንጉሥ ነው አፍርንጊያውያንንም ይወጋቸው ዘንድ ከግብጽ ሀገር ሁሉ ብዙ ሠራዊትን ሰበሰበ ሠራዊቱም ሲጓዙ ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትን አፈረሱ ከፈረሱትም ውስጥ አንዲቷ የእሊህ ቅዱሳን ሰማዕታት ሥጋቸው በውስጧ ያለባት ናት። ከሠራዊቱም አንዱ የቅዱሳን ሰማዕታት ሥጋ ያለበትን ሣጥን ወሰደ በውስጡ የሚደሰትበትን የዚህን ዓለም ገንዘብ እንደሚያገኝ አስቦ በከፈተው ጊዜ ከዕንቊ የከበረ የቅዱስንን ሥጋቸውን አገኘ ክብራቸውን ግን አላወቀም ከቤተ ክርስቲያኑ ግድግዳ ላይ ሥጋቸውን በትኖ ሣጥኑን ወስዶ ሸጠው።
ምሕረቱ የበዛ የሚታገሥ ልዑል እግዚአብሔርም ወደ አፍርንጊ ሠራዊት እስከሚደርስ በእርሱ ላይ ታገሠ ጦርነትም በገጠሙ ጊዜ ከሁሉ አስቀድሞ እርሱ ተገደለ ባልንጀሮቹም ምስክር እንደሆኑ ወደ ሀገራቸው በተመለሱ ጊዜ የእግዚአብሔርን ክብር ፈጽመው ሰበኩ እንዲህም አሉ እርሱ አስቀድሞ በሰይፍ ተመታ ራሱንም ተቆረጠ ጐኖቹንም ሠነጣጥቀውት በክፉ አሟሟት ሞተ።
የቅዱሳኑን ሥጋቸውን ያ ሰው በበተናቸው ጊዜ የአንድ ቄስ ሚስት የሆነች አንዲት ምእመን ሴት ቁማ ትመለከት ነበር ከዚህም በኋላ በጭልታ ወደርሳቸው ገብታ ደስ እያላት ወስዳ በመጐናጸፊያዋ ጠቀለለቻቸው እስላሞችንም ከመፍራቷ የተነሣ በቤተ ክርስቲያን ማዕዘን ውስጥ አኖረቻቸው በመጐናጸፊያዋም እንደ ተጠቀለሉ በጡብ ሸፈነቻቸው በዚያም ጡብ ተሸፍነው በዚያች ማዕዘን ውስጥ ሃያ ዓመት ያህል ኖሩ ከቀን ብዛትም የተነሣ ያቺ ሴት ወሬያቸውን ረሳች።
እግዚአብሔርም ለወገኖቹ ጥቅም ይገልጣቸው ዘንድ በወደደ ጊዜ በዚያች ሴት ፊት ሌሎች ሰዎች አስታወሷቸው እርሷም በዚያን ጊዜ አስታወሰቻቸው ለካህናቱና ለምእመናኑ ነግራ ቦታቸውን አሳየቻቸው። ካህናቱም ገብተው ሥጋቸውን አነሡ ያማረች ሣጥንንም ሠርተው በውስጧ በክብር አኖሩዋቸው እንደ ዛሬዪቱም ዕለት በዓልን አደረጉላቸው ሁል ጊዜ በዚች ዕለት በዓል ያደርጉላቸው ዘንድ ስማቸውን በበዓላት ግጻዌ መጽሐፍ እንዲጽፉ የአገሩ ኤጲስቆጶስ አባ ገብርኤል አዝዟልና።
ከዐፅሞቻቸውም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ ከተአምራቶችም አንዲት የታወረች ልጅ ያለቻት ሴት ነበረች ተስፋ ከቆረጠችም በኋላ ከቅዱሳኑ ዐፅም በተማፀነች ጊዜ ዐይኖቿ ተገልጠውላት አየች እሊህንም ሰማዕታት በዚህ ክብር ያከበራቸውን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰገነችው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ካመነኮሷቸው ከሰባቱ ከዋክብት አንዱ የሆኑት ታላቅ አባት አቡነ አፍቅረነ እግዚእ እረፍታቸው ነው።
የመላእክትን ሕይወት በምድር የኖሩ እጅግ የከበሩ ታላላቅ የሀገራችንን ቅዱሳን ማለትም አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባን፣ አቡነ ያሳይ ዘማንዳባን፣ አቡነ ሳሙኤል ዘቆየፃን፣ አቡነ ሳሙኤል ዘጣሬጣን፣ አቡነ ታዴዎስ ዘባልታርዋን፣ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን እና አቡነ ዮሐንስ ዘጉራንቄን አስተምረውና አመንኩሰው ለጽድቅ ያበቋቸው አባት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ናቸው፡፡ እነዚህንም ሰባቱን ቅዱሳን በአንድ ጊዜ ሲያመነኩሷቸው በዚያው ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ገዳሙን በብርሃን አጥለቅልቆት ታይቷል፡፡ ከሰማይም የምስክርነት ድምፅ ተሰምቷል፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ላይ የመነኮሱት እነዚህ ሰባቱ ቅዱሳን ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ እነዚህም ሰባቱ ከዋክብት የጣናን ባሕር በእግራቸው ጠቅጥቀው ተሻግረው ብዙዎቹን ደሴቱ ላይ ያሉ አስደናቂ የጣና ገዳማትን የመሠረቱት ናቸው፡፡ ከእነርሱም ውስጥ ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይን እንደጀልባ ተጠቅመው በእርሱ ላይ ሆነው ወደ ደሴት የገቡ አሉ፡፡ በእግራቸውም እየረገጡ ባሕሩን የተሻገሩ አሉ፡፡ በሌላም ቦታ በየብስ የተሰማሩትም ቢሆኑ መጻሕፍቶቻቸውን በአንበሳ ጭነው የተጓዙ አሉ፡፡
አቡነ መድኃኒነ እግዚእ በደብረ ሊባኖሱ ሐዲስ ሐዋርያ የኢትዮጵያ ብርሃኗ በሆኑት በአቡነ ተክለ ሃይማኖት እጅ ከመነኮሱ በኋላ እርሳቸውም በተራቸው ያስተማሯቸውና ያመነኮሷቸው መነኮሳት ቁጥራቸው በውል አይታወቅም፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ለአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ‹‹ስፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብት ቅዱሳንን›› በመንፈስ ቅዱስ እንደሚወልዱ ትንቢት ተናግረውላቸው ነበር፡፡ የተንቤኑን አቡነ ዐቢየ እግዚእን፣ የዞዝ አምባውን አቡነ አብሳዲን ጨምሮ አባታችን መድኃኒነ እግዚእ ብርሃን ሆነው በጣም ብዙ ቅዱሳንን የለኮሱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን›› ይባላሉ፡፡
አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዛሬ ግሸን ላይ በክብር ተቀምጦ ሀገራችንን ከመዓት እየጠበቀ ያለውን የጌታችንን ቅዱስ መስቀል ካመጡት የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ልጆች ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ ዐፄ ዳዊት በዘመናቸው ረኃብ ስለነተሳ የደብረ ቢዘኑን አቡነ ፊሊጶስን ከገዳማቸው አስጠርተው ‹‹ምን ባደርግ ይሻለኛል?›› ብለው አማከሯቸው፡፡ አቡነ ፊሊጶስም ‹‹የጌታችንን መስቀል ያስመጡ›› ብለው መከሯቸው፡፡ ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም ከኢየሩሳሌም፣ ከቍስጥንጥንያና ከእስክንድርያ መንግሥታት ጋር ተጻጽፈው ዓሥሩን ታላላቅ ቅዱሳን መርጠው ይዘው ሄደው መስቀሉን መስከረም 10 ቀን አምጥተውታል። በጽድቅ ሥራቸውና ተአምራትን በማድረግ በወቅቱ ታዋቂ የነበሩትና ቅዱስ መስቀሉን ያመጡት ዐሥሩ ቅዱሳንም የደብረ ቢዘኑ አቡነ ፊሊጶስ፣ የጣና ደሴቱ አቡነ ኂሩተ አምላክ፣ የጣና ደሴቱ አቡነ እንድርያስ፣ አቡነ በትረ ማርያም፣ አቡነ ዮሐንስ፣ አቡነ ታዴዎስ፣ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ፣ አቡነ ዘካርያስ፣ አቡነ ያሳይና አቡነ ቶማስ ናቸው፡፡
አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ዋሊ፣ አቡነ ያሳይ እና ያፍቅረነ እግዚእ እነዚህ ሦስቱ ቅዱሳን ወደ ጣና አብረው ከመጡና አብረው የተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ አቡነ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ ሲሄዱ አቡነ ያሳይ ማንዳባን ገዳምን አቀኑ፡፡ አቡነ አፍቅረነ እግዚእ ደግሞ ጌታችን ባዘዛቸው መሠረት ጣና ውስጥ በስማቸው የተጠራውን ገዳም አቅንተዋል፡፡
አቡነ ያፍቀረነ እግዚእ ‹‹አፍቅረነ እግዚእ›› እየተባሉም ይጠራሉ፡፡ ይኸውም ‹‹ጌታ አምላክ ወደደን›› ማለት ነው፡፡ ትውልዳቸው ትግራይ አክሱም ሲሆን አባታቸው ገብረ ኢየሱስ እናታቸው አፎምያ የተባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ልደታቸው ሐምሌ 19 ቀን ነው፡፡ አቡነ ያፍቀረነ እግዚእ በገዳማዊ ሕይወታቸው በእጅጉ ይታወቃሉ፡፡ በንጉሥ ዓምደ ጽዮን ዘመን የነበሩ ሲሆን ደራሲና ፈላስፋም ናቸው፡፡ ጻድቁ ደራ ፎገራ ውስጥ ባለ አራር ዓምድ አስደናቂ ገድል አላቸው፡፡ ከደራ ፎገራ ተነሥተው በጣና አድርገው ፈላሾችንና ቅማንቶችን በሚገባ በማስተማርና በማጥመቅ ብዙ ሐዋርያዊ አገልግሎት ፈጽመዋል፡፡
ጻድቁ በወጣትነታቸው ወደ ጣና ባሕር ሄደው መሐምላ፣ ምፅሌና፣ አይፋር በተባሉና በሌሎችም አገሮች ወንጌልን ካስተማሩ በኋላ ወደ ትግራይ ሄደው በዚያ ገዳማቸውን መሠረቱና በዚያው ዐረፉ፡፡ ከጌታችን ጋር አብረው ማኅበር የጠጡ 3 ሺህ ቅዱሳን አክሱም አካባቢ ባለው በአቡነ ያፍቀረነ እግዚእ ገዳም ይከብራሉ፡፡ ገዳምነቱ የአቡነ ያፍቀረነ እግዚእ ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ ግን በገዳማቸው የጻድቁ በዓል መከበር እየቀረ የእነዚህ 3 ሺህ ቅዱሳን ማኅበርተኞች በዓል ነው በድምቀት የሚከበረው፡፡ በገዳሙ ውስጥ የአቡነ ያፍቀረነ እግዚእ ቤተመቅደስ ለብቻ የ3ሺዎቹ ጻድቃን ማኅበርተኞች ቤተመቅደስም ለብቻ ይገኛሉ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages