ስንክሳር ዘወርኀ ኅዳር 22 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ኅዳር 22

ቅዱሳን_ቆዝሞስ_ወድምያኖስ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ሃያ ሁለት በዚች ቀን ቅዱሳን ቆዝሞስና ድምያኖስ ወንድሞቻቸውም አንቲቆስ ዮንዲኖስ አብራንዮስ በሰማዕትነት አረፉ። እሊህም ድዮማ ከምትባል ከተማ ስለ እግዚአብሔር ልጅ የታነፀች ግምብ ከአለችበት አረምያ ከምትባል አገር ናቸው።


እናታቸውም ቴዎዳዳ እግዚአብሔርን የምትፈራና የምትራራ መጻተኞችንና ዶኆችን የምትወዳቸው የምትረዳቸው ናት አባታቸውም ከሞተ በኋላ ልጆቿን እያስተማረች አሳደገቻቸው። እሊህም ሁለቱ ቆዝሞስና ድምያኖስ የሕክምና ጥበብን ተምረው በሽተኞችን ያለ ዋጋ የሚፈውሱአቸው ይልቁንም ድኆችን አብዝተው የሚረዷቸው ሆኑ።
ወንድሞቻቸው ሦስቱ ግን ወደ ገዳም ሒደው መነኰሱ በጾምና በጸሎትም ተጠመዱ። ከአባ አጋግዮስ አደራ በአስጠበቀው በንጉሠ ቊዝ ልጅ ምክንያት ዲዮቅልጥያኖስ ክዶ የረከሱ ጣዖታትን በአመለከ ጊዜ በምእመናን ላይ መከራ ሆነ ገንዘብ ወዳጅ አጋግዮስ ብዙ ወርቅን ተቀብሎ የንጉሠ ቊዝን ልጅ ወደ አባቱ ልኮታልና ከዚህም በኋላ የንጉሠ ቊዝን ልጅ ዲዮቅልጥያኖስ ዳግመኛ ከጦር ሜዳ አግኝቶ ማረከው እርሱንም የንጉሡን ልጅ ሠውሮ አባ አጋግዮስን ጠራው ያንንም አደራ የሰጠውን የንጉሠ ቊዝን ልጅ እንዲአመጣ አዘዘው አጋግዩስም ሙቶ ተቀብሮአል ብሎ በሐሰት ተናገረ በዚያንም ጊዜ በመሠዊያው ፊት አማለው እሳትም ከሰማይ ወርዳ እንደምታቃጥለው ጠበቀ የእሳትም መውረድዋ በዘገየ ጊዜ ወርቅን በእሳት አቅልጦ አጠጣውና አቃጠለው ስለዚህም ከወርቅና ከብር የተሠሩ ጣዖታትን አመለከ።
ቆዝሞስና ድምያኖስ በሀገሩ ሁሉ ስለ ክርስቶስ እነርሱ እንደሚያስተምሩ ዲዮቅልጥያኖስ በሰማ ጊዜ ወደርሱ እንዲአቀርቧቸው አዘዘ በደርሱም ጊዜ ለአገረ ገዢው ለሉልዮስ እንዲአሠቃያቸው ሰጠው። እርሱም በብዙ ሥቃዮች ማሠቃየትን ጀመረ በእሳት የሚያቃጥልበት ጊዜ አለ በግርፋት የሚገርፍበትም ጊዜ አለ ሦስት ወንድሞችም እንዳሏቸው ሰምቶ እነርሱንም ወደርሱ አስመጣቸውና አምስቱንም በመኰራኲር ውስጥ እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ። ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ጨመሩዋቸው በውስጡም ሦስት ቀኖችና ሌሊቶች ኖሩ ያለ ጥፋትም በጤንነት ወጡ ዳግመኛም ከብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ከበታቻቸው እሳትን አነደዱ እግዚአብሔርም ያለ ጥፋት ጠበቃቸው።
መኰንኑም እነርሱን ማሠቃየት በሰለቸ ጊዜ ወደ ንጉሥ መለሳቸው ንጉሡም ዳግመኛ ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው ቴዎዳዳ እናታቸውም የምታስታግሣቸው ንጉሡንና የረከሱ ጣዖቶቹን የምትረግም ሆነች።
በዚያንም ጊዜ አንገቷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትንት አክሊልንም ተቀበለች ሥጋዋ ግን በምድር ላይ ወድቆ ነበር ቆዝሞስም እንዲህ ብሎ ጮኸ የዚች አገር ሰዎች ሆይ ይችን አሮጊት መበለት ሥጋዋን አፈር አልብሶ ይሠውራት ዘንድ ከውስጣችሁ ርኅራኄ በልቡ ያደረበት የለምን የህርማኖስ ልጅ ቅዱስ ፊቅጦርም በሰማ ጊዜ ተደፋፍሮ ሥጋዋን ገንዞ ቀበራት።
ንጉሡም እነርሱን ማሠቃየት በሰለቸ ጊዜ ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። ከመከራውም ዘመን በኋላ ቤተ ክርስቲያን ተሠርታላቸው ሥጋቸውን በውስጧ አኖሩ ከእርሳቸውም ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራት ተገለጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages