ስንክሳር ዘወርኀ ኅዳር 21 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ኅዳር 21

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ሃያ አንድ በዚህች ቀን የእመቤታችን የቅድስት_ጽዮን_ድንግል_ማርያም የበዓልዋ ነው፣ ከሮሜ አገር የሆነ ቅዱስ_ጎርጎርዮስ አረፈ፣ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_አባት_ቆዝሞስ አረፈ፣ ቅዱስ_አባት_አባ_ዮሐንስ ዘአስዩጥ አረፈ።


ኅዳር ሃያ አንድ በዚች ቀን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የበዓልዋ መታሰቢያ ነው።
"ጽዮን" ማለት "ጸወን - አምባ - መጠጊያ" ማለት ነው። አንድም በምሥጢሩ "ማሕደረ አምላክ" ማለት ነው። ጽዮን የሚለው ስም በቁሙ ለቅዱስ ዳዊት ተራራና ለኪዳኑ ጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም ለቤተ ክርስቲያንና ለዘለዓለማዊት ርስት ያገለግላል።
እግዚአብሔር ከዘመነ አበው በሁዋላ በጊዜው ለእሥራኤላውያን ክብር፣ ሞገስ፣ አምባ የምትሆናቸውን ታቦተ ጽዮንን በቅዱስ ሙሴ አማካኝነት ሰጥቷቸዋል። (ዘጸ. 31፥18) ከዚያም ለ500 ዓመታት ከእነሱ ጋር በመሆኗ በፈጣሪና በእነሱ መካከል ድልድይ ሆና ኖራለች።
ከዚያም ባለቤቱ ሲፈቅድ በዘመነ ሳባ በቀዳማዊ ምኒልክ (እብነ መለክ-እብነ ሐኪም) አማካኝነት ወደ ኢትዮዽያ መጥታለች። እነሆ በሃገራችን የ3ሺ ዓመት ቆይታዋን ልትደፍን የቀራት ጥቂት ዓመታት ብቻ ናቸው። ጌታ እንደ ፈቀደ ቅዱስ መስቀሉንና ታቦተ ጽዮንን ይዘን ይሔው በቸርነቱ እንኖራለን።
ያም ሆኖ ታቦተ ጽዮንን መስረቅ የሚፈልጉ ብዙ ቀሳጢዎች እንዳሉ እናውቃለን። ግን አንጨነቅም። ምክንያቱም የመጣችውም የምትጠበቀውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነውና እንጸልያለን እንጂ አንጨነቅም። በተለያየ ወሬም ራሳችንን አናማጥንም። ባለቤቱ እንድትሔድ ከፈቀደ ደግሞ ማንም ጉልበተኛ አያስቀራትም።
ታቦተ ጽዮን ብዙ ጊዜ "ጽላተ ኪዳን፣ ታቦተ ሕጉ" እየተባለች ትጠራለች። "ጽሌ" ማለት "ሰሌዳ" እንደ ማለት ሲሆን "ጽላት" ደግሞ በብዙ ቁጥር ነው። "ኪዳን" ደግሞ በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል ያለ "ውል - ስምምነት" ነው።
"ታቦት" ማለት "ማሕደር-ማደሪያ" እንደ ማለት ነው። ሕጉ የተጻፈባቸውን ሰላድው "ጽላት" ስንላቸው የጽላቱ ማደሪያ ደግሞ "ታቦት" ይባላል። ጽላት (ታቦትን) ያመጣ ፈጣሪ ነው። በሐዲስ ኪዳንም ምሥጢርና ሐተታ ቢኖረውም 2 ቦታ ላይ ስለ ታቦት ተጠቅሶ እናገኛለን። (2ቆሮ.6፥16 ፣ ራዕይ.11፥19)
በመጨረሻም ኅዳር ሃያ አንድ ቀን ጽዮን ማርያምን የምናከብርባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን።
✞ ታቦተ ጽዮን (ጽላተ ኪዳን) ለሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ መሰጠቷን እናስባለን።
✞ ታቦተ ጽዮን በምርኮ በሄደችበት በሀገረ ፍልስጤም ዳጎን የተባለ የአህዛብን ጣኦት አድቅቃ በድል የተመለሰችበትን ዕለት በማሰብ።
✞ በዘመነ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በአሚናዳብ ሠረገላ ሁና ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ቅዱሱ ንጉሥ በታላቅ ሐሴት በፊቷ ዘመረ። አገለገለ። ምድራዊ ክብሩን እስኪረሳ ድረስ ለታቦተ አምላክ የተቀኘላት በማሰብ።
✞ ታቦተ ጽዮን ንጉሥ ሰሎሞን ወደ ሠራላት ቤተመቅደስ በክብር የገባችበትን ዕለት በማሰብ፤
✞ የቀደሙ ነብያት ስለእመቤታችን በተለያየ አምሳል ያዩበት ለምሳሌ፦ ነብዩ ዕዝራ በሃገር መንፈሳዊት፣ ሕዝቅኤል በተዘጋች ቤተመቅደስ፣ ዘካርያስ በተቅዋመ ወርቅ ወዘተ ያዩበትን ዕለት በማሰብ፤
✞ ቀዳማዊ ምኒሊክ ከዐሥራ ሁለቱ ነገድ እስራኤል የበኩር ልጅ ጋር ሊቀ ካህናቱን አዛሪያስንና ታቦተ ጽዮንን ይዞ አክሱም የደረሰበትን ዕለት በማሰብ፤
✞ በዘመነ አፄ ባዜን (በ4 ዓ/ም አካባቢ) አማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም ወደ አክሱም ጽዮን በስደት መጥታ ገብታለች። በዚህ ጊዜም 2ቱ ጽዮኖች ሲገናኙ ታላቅ ብርሃን አክሱምን ውጧታልና ይህንንም በማሰብ፤
✞ በአብርሃ ወአፅብሃ ዘመነ መንግስት ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ሆኖ አዋጅ የታወጀበትን በማሠብ፤
✞ አብርሃ ወአጽብሃ በወርቅና በዕንቁ ያሠሩት ባለ አሥራ ሁለት ክፍል ቤተ መቅደስ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ዕለት በመሆኑ፤
✞ በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዮዲት ጉዲት አብያተ ክርስቲያንን ስታቃጥል ታቦተ ጽዮንን ይዘው ወደ ዝዋይ ሀይቅ ከተሰደዱ በኋላ ዘመነ ሰላም ሲጀመር አክሱም በነበሩ ካህናት አስታዋሽነት ከዝዋይ ወደ አክሱም የገባችበት ዕለት በመሆኑ፤
በእነዚህ ምክንያቶች በመላው ኢትዮጵያ በተለይም በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ከፍ ባለ መንፈሳዊ በዓል እናከብራለን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ከሮሜ አገር የሆነ ተአምራትን የሚያደርግ ቅዱስ ጎርጎርዮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት የቀናች ሃይማኖትንም ተምሮ እውነተኛ ክርስቲያን ሆነ። ከዚህም በኋላ የዚህን ዓለም ኃላፊነት የማታልፍ የመንግሥተ ሰማያትንም ኑሮ አሰበ ኀሳቡንም ሁሉ ስለ ነፍሱ ድኅነት አደረገ።
የዚያቺም አገር ኤጲስቆጶስ በኤጲስቆጶስነቱ ሥራ ይራዳው ዘንድ ለመነው እርሱ ግን አልፈቀደም ከውዳሴ ከንቱ የሚሸሽ ሁኗልና ወደ ገዳምም ገብቶ ጽኑዕ የሆነ ተጋድሎንም መጋደል ጀመረ።
የዚያቺም አገር ኤጲስቆጶስ በአረፈ ጊዜ ኤጲስቆጶስ የሚያደርጉት ፈልገው አጡ ስለዚህም ተሰብስበው ሳሉ የመለኮትንም ነገር የሚናገር ጎርጎርዮስ ከእሳቸው ጋር ሳለ ገዳማዊ ጎርጎርዮስን ፈልጋችሁ በእናንተ ላይ ሹሙት የሚል ቃል ከሰማይ ወደ እነርሱ መጣ ።
በበረሀውም ውስጥ በፈለጉት ጊዜ አላገኙትም እየፈለጉትም ብዙ ቀን ኖሩ እርሱ ግን በአቅራቢያቸው ይኖር ነበር። ባለገኙትም ጊዜ በአንድ ምክር ተስማምተው በሌለበት ወንጌል ይዘው በላያቸው ኤጲስቆጶስነት ሾሙት ስሙንም የመለኮትን ነገር በሚናገር በጎርጎርዮስ ስም ጎርጎርዮስ ብለው ሰየሙት።
ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ለቅዱስ ጎርጎርዮስ ተገልጦ ተነሥተህ ወደ እነርሱ ሒድ እነሆ በላያቸው ኤጲስቆጶስነት ሹመውልሃልና ይህም ከእግዚአብሔር የሆነ ነው አለው። ያን ጊዜም ወደ እነርሱ ወረደ የአምላክን ትእዛዝ መተላለፍ ፈርቷልና በአዩትም ጊዜ ወጥተው በታላቅ ክብር ተቀበሉት የሹመቱንም ሥርዓት ፈጸሙ።
እግዚአብሔርም ቊጥር የሌላቸው ብዙዎች ተአምራትን በእጆቹ ገለጠ ስለዚህም ገባሬ መንክራት ጎርጎርዮስ ተብሎ ተጠራ ። ከብዙዎች ተአምራቱም አንዲቱ ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ ከእርሷም ብዙ ዓሣዎችን የሚያጠምዱበት ታናሽ ባሕር ነበረቻቸው አንዱም አንዱ የኔ ናት በማለት እርስበርሳቸው ተጣሉ ስለዚችም ባሕር በመካከላቸው ይፈርድ ዘንድ ወደ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ለመሔድ ተስማሙ እርሱም ከሁለት ተካፍሉ ብሎ አዘዛቸው እንዳዘዛቸውም ባልተስማሙ ጊዜ ስለዚያች ባሕር እግዚአብሔርን ለመነው በዚያንም ጊዜ ባሕሪቱ ደርቃ የምትታረስ ምድር ሆነች በመካከላቸውም ሰላም ሆነ በእጆቹ ስለሚደረጉ ድንቆች ተአምራት ዜናው በሁሉ አገር ተሰማ በጎ አገልግሎቱንም ከፈጸመ በኋላ በሰላም አረፈ ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ቆዝሞስ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃምሳ አራተኛ ነው። ይህም አባት ብዙ መከራና ኀዘን ደረሰበት በዘመኑም በክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ላይ መከራና ችግር ደረሰባቸው በእነዚያም ወራት የክርስቲያን ወገኖችና አይሁዳውያን ልብሳቸውን በሰማያዊ ቀለም እንዲያቀልሙት እንጂ ነጭ ልብስ እንዳይለብሱ የእስላሞች ንጉሥ ጋዕፊር አዝዞ ነበርና።
በዚህም አባት ዘመን ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራት ተገለጡ በአስቄጥስ ገዳም በቅዱስ ሳዊሮስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ነበረች ጐኗም ተገልጦ ከእርሷ ብዙ ደም ፈሰሰ በግብጽ አገር ከአሉ ከሌሎች ሥዕሎችም ከዐይኖቻቸው ብዙ ዕንባ ፈሰሰ ይህም የሆነው በሊቀ ጳጳሳቱና በክርስቲያን ወገኖች ላይ ስለ ደረሰው መከራ እንደ ሆነ በመራቀቅ የሚያስተውሉ አወቁ።
ከዚህም በኋላ ስለእነዚያ የከፉ ወራቶች ፈንታ በጎ የሆኑ ወራቶችን እግዚአብሔር ሰጠው ሁል ጊዜም ምእመናንን የሚያስተምራቸውና የሚያጽናናቸው በቀናች ሃይማኖትም የሚያበረታታቸው ሆነ ። በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበርም ላይ ሰባት ዓመት ከአምስት ወር ከኖረ በኋላ በአምስት መቶ ሰባ አምስት ዓመተ ሰማዕታት ኅዳር ሃያ አንድ ቀን አረፈ ይንሶር በሚባል ዋሻውም ተቀበረ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ቀን ደግሞ የብርሌ የብርጭቆ ሠሪዎች ልጅ የሆነ ከአስዮጥ አገር ቅዱስ አባት አባ ዮሐንስ አረፈ ። ይህንንም ቅዱስ በወለዱት ጊዜ በበጎ ተግሣጽ አሳድገውታል የጥርብ ሥራንም አስተማሩት ከጥቂት ዘመናትም በኋላ አባቱና እናቱ አረፉ። ያን ጊዜ ወደ ቅዱስ አባ ኢስድሮስና ወደ አባ ባይሞን ዘንድ ሒዶ መነኰሰ በጾምና በጸሎት በገድል ሁሉ ተጠምዶ ተጋደለ ዜናውም በራቁ ገዳማት ሁሉ ተሰማ ።
ከዚህም በኋላ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጠለት ወደ ሀገሩ ሒዶ ወገኖቹን የጽድቅን ጎዳና ይመራቸው ዘንድ አዘዘው። ቅዱስ ቊርባንንም ሳይቀበል ከበዓቱ የማይወጣ ሆነ። በአንዲት ዕለትም ሁለት ቅዱሳን አረጋውያን አባ አብዢልና አባ ብሶይ ወደርሱ መጡ ገና ወደርሱ ሳይቀርቡ ከሩቅ ሳሉ ስማቸውን በመጥራት ሳያውቃቸው አባቶቼ ለመምጣታችሁ ሰላምታ ይገባል ብሎ ተናገረ እጅግም አደነቁት አባ ሲኖዳም ከግብጽ አገር እየመጣ ብዙ ጊዜ ይጎበኘው ነበር።
የከዳተኞችም ጠብ በግብጽ አገር ላይ በተነሣ ጊዜ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ የላከው የጦር መኰንን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መጣ። በጸሎቱም ይራዳው ዘንድ ለመነው ቅዱስ ዮሐንስም መስቀሉን አንሥቶ መኰንኑን አይዞህ አትዘን አንተ ጠላቶችህን ድል ታደርጋለህና አለው እንደ ቃሉም ሆነ።
ዳግመኛም በንጉሥ ቴዎዶስዮስ ላይ ጠላት በተነሣበት ጊዜ ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ላከ እርሱም አትዘን አንተ ጠላትህን ታሸንፋለህ አለው ያን ጊዜም ጠላቶቹን አሸነፈ ።
ከዚህም በኋላ በእነዚያ ወራት ንጉሥ ቴዊዶስዮስ የርኲሰትን ሥራ ስለ ሠሩ የአስዮጥን ሰዎች እንዲገድሏቸው ሀገራቸውንም እንዲአጠፉ አዘዘ። ንጉሡም የላከው መኰንን ሳይደርስ የእግዚአብሔር መልአክ ይህን ነገር ለአባ ዮሐንስ አሳወቀው የሀገርም ሰዎች የንጉሡን ትእዛዝ በሰሙ ጊዜ ወደ አባ ዮሐንስ ገዳም ወጥተው ስለ መጥፋታቸው በፊቱ አለቀሱ አባ ዮሐንስም አትጨነቁ አይዟችሁ እግዚአብሔር ያድናችኋልና አላቸው።
መኰንኑም በመጣ ጊዜ ከእርሱ በረከትን ይቀበል ዘንድ ወደ አባ ዮሐንስ ደረሰ አባ ዮሐንስም ንጉሡ ያዘዘውን ሁሉ ነገረው መኰንኑም ሰምቶ ደነገጠ ለቅድስናውም ተገዢ ሆነ ለመኰንኑም ርኩስ መንፈስ ያደረበት የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረው ያድንለት ዘንድ ቅዱስ ዮሐንስን ለመነው በዚያንም ጊዜ ዘይትን ቀብቶ አዳነው።
ከዚህም በኋላ የአስዩጥ ሰዎችን መገደላቸውን እንዲተው ወደ ንጉሥ ይጽፍለት ዘንድ መኰንኑን አባ ዮሐንስ ለመነው መኰንኑም ጽፎ ለአባ ዮሐንስ ሰጠው አባ ዮሐንስም ተቀብሎ ወደ ዋሻው ገባ ወደ ጌታችንም ጸለየ ብርህት ደመናም መጣች ተሸክማም ወደ ንጉሡ አደረሰችው ያን ጊዜም ንጉሥ ከማዕድ ላይ ነበረ ያንንም ደብዳቤ ከወደላይ ጣለለት ንጉሡም አንሥቶ በአነበበው ጊዜ ከመኰንኑ የተጻፈ እንደሆነ በመካከላቸው በአለ ምልክት ተጽፎ አገኘው የተጻፈውም ቃል ስለ አባ ዮሐንስ ልመና ሀገሪቱን ማጥፋትን እንዲተው የሚል ነበር ቀና ባለ ጊዜም ደመና አየ ንጉሡም አደነቀ።
ከዚህም በኋላ ሀገሪቱን ማጥፋትን ስለ አባ ዮሐንስ ይተው ዘንድ መልሱን ለመኰንኑ ንጉሡ ጽፎ ደብዳቤዋን ወደ ደመናው ወረወራት የተሰበሰቡትም እያዩ እጅ ተቀበለችውና ወደ ደመናው ገባች ወዲያውኑ አባ ዮሐንስ በዚያች ደመና ወደበዓቱ ተመለሰና በማግሥቱ ያቺን ደብዳቤ ለመኰንኑ ሰጠው በላይዋም የንጉሡ ፊርማውና ማኅተሙ አለ በአያትና በአነበባት ጊዜ ደነገጠ አደነቀም ስለ ሀገሪቱ ድኅነትም እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደአገሩ ተመለሰ።
የንጉሥ ዘመድ የሆነች የከበረች ሴት ዜናውን በሰማች ጊዜ ከደዌዋ ይፈውሳት ዘንድ ወደርሱ መጣች በጸሎቱም ተፈወሰች። ከዚህም በኋላ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ በሞተ ጊዜ መናፍቁ መርቅያን ነገሠ ። ቅዱስ አባ ዲዮስቆሮስንም አሠቃየው ። የቀናች ሃይማኖትን ስለመለወጡ አባ ዮሐንስ እየዘለፈና እየረገመው ወደ ርሱ ደብዳቤ ላከ ከጥቂት ወራትም በኋላ እግዚአብሔር ቀሠፈው።
ለእርሱም ዕድሜው መቶ ሃያ አምስት ዓመት ሲሆነው ዕረፍቱ እንደ ደረሰ አወቀ እየጸለየም ግምባሩን ምድር አስነክቶ ሰገደ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ ከመቃብሩም ቁጥር የሌላቸው ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራት ተገለጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በጸሎቷ የሚገኝ በረከቷም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋር ይኑር። በቅዱሳኑም ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages