ስንክሳር ዘወርኀ ኅዳር 20 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ኅዳር 20

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ሃያ ቀን የሰማዕት ቅዱስ ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት ነው፣ ሁለተኛው የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_አባት_አንያኖስ አረፈ።


ኅዳር ሃያ በዚህችም ቀን የሠራዊት አለቃ የነበረ የሰማዕት ቅዱስ ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት ነው።
የዚህ ቅዱስ አባት ስሙ ዮሐንስ ይባል ነበር። እርሱም ከላይኛው ግብጽ ሰጥብ ከምትባል መንደር ነበር። ወደ አንጾኪያ ከተማም ከሠራዊቱ ጋራ ወሰዱትና በዚያ ኖረ ከዚያች ከተማ መኳንንቶችም ያንዱን ልጅ አገባ እርሷም ጣዖትን ታመልክ ነበር። ባሏ ዮሐንስ የሚያመልከውን ግን አታውቅም ነበር።
ከዚህም በኋላ ይህን ቅዱስ ቴዎድሮስን በወለዱት ጊዜ እናቱ ወደ ጣዖቷ አቅርባ አምልኮትዋን ልታስተምረው ፈለገች አባቱ ግን አስተወው ስለዚህም ተቆጥታ ባሏ ዮሐንስን አባረረችው ሕፃኑ ቴዎድሮስም በእናቱ ዘንድ ቀረ።
አባቱ ዮሐንስም ልጁ ቴዎድሮስን ወደ እውነተኛ መንገድ ይመራው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይና ይማልድ ነበር። ሕፃኑ ቴዎድሮስም በአደገ ጊዜ ጥበብን ተማረ ጌታችንም ልቡን ብሩህ አደረገለት ስሙ አውላኪስ ወደሚባል ኤጲስቆጶስም ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ። እናቱም ታላቅ ኅዘንን አዘነች።
ከዚህም በኋላ ስለ አባቱ በሕይወት እንዳለ ወይም እንደሌለ ጠየቀ ከአገልጋዮቹም አንዱ የአባቱን ሥራ በሥውር ነገረው። ቅዱስ ቴዎድሮስም ጐለመሰ እጅግም ብርቱ ሆነ ንጉሡም የሠራዊት አለቃ አድርጎ ሾመው።
የፋርስ ሰዎችንም ሊወጋቸው በወጣ ጊዜ ይህ ቅዱስ ቴዎድሮስ በረታ የፋርስ ንጉሥንም ልጅ ይዞ ማረከው ከእርሱም ጋር ምሥራቃዊው ቴዎድሮስ ነበር የፋርስንም ሠራዊት አሳደዱአቸው።
ከጥቂት ወራቶች በኋላም የፋርስና የበርበር ስዎች በሮማውያን ላይ ተነሡ። ብዙ ከተሞችንም አጠፉ ዲዮቅልጥያኖስም በሰማ ጊዜ እጅግ ፈራ ቴዎድሮስንም ጠርቶ ምን እናድርግ ሠራዊትህን ሁሉ የጦር መሣሪያህንም ሁሉ ይዘህ ወደ ሰልፍ ውጣ አለው።
ቅዱስ ቴዎድሮስም እንዲህ ብሎ መለሰለት አንተ የጦር መሣሪያህን ወስደህ ለአሽከሮችህ ስጣቸው እኔ ክብር ይግባውና በፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ርዳታ እተማመናለሁና የጦር መሣሪያ አልሻም እኔም ብቻዬን ወደ ጦርነቱ እሔዳለሁ ከወታደሮችም አንድ እንኳ ከእኔ ጋራ አልወስድም። በእጄ ውስጥ ያለ ይህ ጦር የተቀመጥኩበትም ፈረስ የበቃኛል ከእኔ ጋራ የሚወጣ ፈጣሪዬ እርሱ ይረዳኛልና። ንጉሡም እነሆ ጠላቶቻችን ወደእኛ ቀርበዋልና የወደድከውን አድርግ አለው።
በማግሥቱም ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደ ሰልፍ ወጣ ንጉሡም የበርበርን ሰዎች ትወጋቸው ዘንድ ምን ኃይል አለህ እነርሱ ብዙ ወገኖች ናቸውና አለው። ቅዱሱም ለንጉሡ እንዲህ ብሎ መለሰለት አንተ ከሠራዊትህ ጋራ በዚህ ቁም እኔም ወደ እነርሱ ብቻዬን እሔዳለሁ በነርሱም ላይ ደሚደርሰውን ታያለህ። እኔ በእግዚአብሔር ኃይል እንደማጠፋቸው አውቃለሁና። ከእነርሱም አንዱ እንኳ ወደቤቱ አይመለስም። ንጉሡም አደነቀ ከእርሱ ጋር ያሉትም አደነቁ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደ ጦርነቱ ብቻውን ሔደ ንጉሡንም ከእርሱ ሩቅ በሆነ ቦታ ተወው። ወደ በርበር ሰዎችም ደርሶ ትዋጋላችሁን ወይስ በሰላም ወደ አገራችሁ ትመለሳላችሁ አላቸው። እነርሱም ከአንተ በቀር ለሰልፍ የመጣ አናይምና ከማን ጋር እንዋጋለን አሉት እርሱም ማንም ከእኔ ጋር እንዲመጣ አልሻም። እኔ ብቻዬን በፈጣሪዬ ኃይል አጠፋችኋለሁ አላቸው።
ምናልባት ውሻ ልታባርር መጥተህ ይሆናል ከፈቀድህ ግን ወደ አንተ ይመጣ ዘንድ ከእኛ ውስጥ አንዱን ምረጥና ሁለታችሁ ተጋጠሙ አሉት።
ያን ጊዜ ቅዱስ ቴዎድሮስ ከፈረሱ ላይ ወረደና ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ እንዲህ እያለ ጸለየ ጣዖታትን እስከ አጠፋቸውና የባቢሎንን ከተማ ዘንዶ እስከ ገደለው ድረስ ነቢዩ ዳንኤልን ያጸናኸው ጌታዬ አምላኬ ሆይ እንዲሁም ዛሬ ከአእኔ ጋራ ሁን በረድኤትህም አጽናኝ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ምስጋና ይገባሀል ለዘላለሙ አሜን።
ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ ጦሩን አንሥቶ በላዩ በመስቀል ምልክት አማተበ በፈረሱ ላይም ተቀምጦ በበርበር ሰዎች ላይ እንዲህ እያለ ጮኸ እንዋጋ ዘንድ ወደኔ ኑ ክብር ይግባውና ለእግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ባሪያው ነኝ እንዲህም እያለ በመካከላቸው ገብቶ የበርበርን ሰዎች አጠፋቸው ከእነርሱም ፈረሰኛንም ሆነ እግረኛን ምንም አላስቀረም የመኳንንቶቻቸውንም ቸብቸቦ ቆርጦ ወደ ንጉሡ አቀረበ። ንጉሡም ተቀበለው ሠራዊቱም ሁሉ ሰገዱለት። የአንጾኪያም ከተማ ሰዎች ሁሉም ወጥተው የበርበርን አገር ማረኩ።
አውኪስጦስ በሚባል አገርም ሰዎች የሚያመልኩት ታላቅ ዘንዶ ነበረ ይበላቸውም ዘንድ በየዕለቱ ሁለት ሁለት ሰዎችን ይሰጡት ነበር ሁለት ልጆችም ያሏት አንዲት ክርስቲያናዊት መበለት ነበረች። እንዲበላቸውም ልጆችዋን ወሰደው ለዘንዶው አቀረቧቸው።
በዚያን ጊዜም ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደዚያ አገር ደረሰ ያች መበለትም በፊቱ ቆመች ልጆቿን ወስደው እንዲበላቸው ለዘንዶው እንዳቀረቧቸው በእርሷ ላይ የሆነውን ሁሉ አልቅሳ ነገረችው።
ክርስቲያን እንደሆነችም ባወቀ ጊዜ በልቡ ይችን ሴት በድለዋታል እግዚአብሔርም ይበቀልላታል አለ። ወዲያውኑም ከፈረሱ ወረደና ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ጸለየ። ከዚህም በኋላ ወደ ዘንዶው ቀረበ የከተማው ሰዎችም ሁሉ ወደርሱ ይመለከቱ ነበር። በጦሩም ወግቶ ያንን ዘንዶ ገደለው። ርዝመቱም ሃያ አራት ክንድ ሆነ የመበለቷንም ልጆች አዳናቸው።
ከዚህም በኋላ አባቱን ይፈልገው ዘንድ ወደ ላይኛው ግብጽ ሔደ አባቱንም አገኘው አባቱም ልጁ እንደሆነ በምልክቶቹ አወቀው ቅዱሱም አባቱ እስከ አረፈ ድረስ በዚያ ኖረ።
ከዚህም በኋላ ወደ አንጾኪያ ከተማ ተመለሰ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስንም ክብር ይግባውና ክርስቶስን እንደካደና ጣዖትን እንደአመለከ ክርስቲያኖችንም ሲአሠቃያቸው አገኘው።
ከዚህም አስቀድሞ የከተማው ሰዎች የሚያመልኩትን ዘንዶ እርሱ እንደ ገደለው የአውኪስጦስ አገር ሰዎች ወደ ንጉሥ ከሰውት ነበርና ስለዚህ ንጉሥ ልኮ አስቀረበው።
ቅዱስ ቴዎድሮስም ወደ ንጉሡ በቀረበ ጊዜ ንጉሡን እንዲህ ብሎ ዘለፈው አንተ የክፉ ሥራ ሁሉ መገኛ የሆንክ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የክብር ባለቤትን ትተህ የረከሱ ጣዖታትን ያመለክ የኃጢአት ልጅ ሆይ ወዮልህ እግዚአብሔርም ፈጥኖ መንግሥትህን ያጠፋታል።
በዚያን ጊዜም ንጉሡ ተቆጥቶ ከመሬት ላይ ጥለው ይገርፉት ዘንድ ወታደሮችን አዘዛቸው። ይህንንም አደረጉበት ደሙም እንደ ውኃ ፈሰሰ። እጆቹንና እግሮቹንም ከግንድ ጋር ቸነከሩት።
በሥቃይም ውስጥ ሳለ ከእግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደርሱ ወረደ እንዲህም አለው ጽና እነሆ የገድልህ ፍጻሜ ቀርቦአል ሥጋህ በውስጡ በሚኖርበትም ቦታ ድንቆችና ተአምራቶች ይገለጣሉ እነሆ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠህ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ፣ ወይም በስምህ የተራበ ለሚያጠግብ፣ የተጠማውን ለሚያጠጣ፣ ወይም ለቤተክርስቲያንህ መባን መጻሕፍትንም ለሚሰጥ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስስለታለሁ። ገድልህንም የሚጽፈውን፣ ወይም የሚያነበውን፣ የሚሰማውን፣ ወይም የሚገዛውን እኔ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ።
ከዚህም በኋላ ብዙዎች ከንጉሥ ሠራዊትና ከሕዝቡ ተሰብስበው በንጉሡ ላይ እንዲህ ብለው ጮኹበት አንተ ከሀዲ እግዚአብሔር ያጥፋህ ከጠላቶቻችን ያዳነንን ኃያልና ጽኑዕ የሆነውን የከበረ ቴዎድሮስን ታሠቃየዋለህና ይህንንም ብለው በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ያን ጊዜም ንጉሥ ተቆጥቶ ሁሉንም አስገደላቸው ሰማዕትም ሆኑ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ።
ከዚህም በኋላ ንጉሡ አዘዘ የብረት ዐልጋም አምጥተው ቅዱሱን በላዩ አስተኙት ከበታቹም እሳትን አነደዱ ቅዱስ ቴዎድሮስም እንዲህ ብሎ ጸለየ አቤቱ ፈጣሪዬ ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ምድጃ እንደ አዳንካቸው አድነኝ። ወዲያውኑም ያ እሳት ጠፋ እንደ ንጋት ጊዜ ቊርም ሆነ።
ከሰማይም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ክብር ይግባውና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል የተሰጠህ ሆይ ጽና በርታ ያን ጊዜም ቅዱሱ ተነሥቶ በንጉሡ ፊት ቆመ እንዲህም አለው ክብር ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አድኖኛልና አንተ ከሀዲ እፈር አለው። የንጉሡም የጭፍራ አለቃ ይህን በአየ ጊዜ ክቡር ቴዎድሮስ ከሚያመልከው ክብር ይግባውና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም ብሎ ጮኸ ርሱንም ራሱን አስቆረጠውና በሰማዕትነት ሞተ።
ቅዱስ ቴዎድሮስንም ብዙ ከአሠቃየውና ማሠቃየቱ ከሰለቸው በኋላ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ ሥጋውንም እንዲአቃጥሉ አዘዘ። በጌታችንም ፈቃድ ከእናቱ ደጅ ወስደው እራሱን ቆረጡ ከእርሱም ደም፣ ወተትም ፈሰሰ ታላቅ እሳትም አንድደው ሥጋውን በውስጡ ጨመሩ እሳቱም ከቶ አልነካውም ። እናቱም ለወታደሮች ብዙ ወርቅ ሰጥታ ሥጋውን ወሰደች በአማሩ ልብሶችም ገነዘችው እስከ መከራው ፍጻሜም በቤቷ ውስጥ አኖረችው።
ከዚያ በኋላም አብያተ ክርስቲያናት ተሠሩለት ስብጥ በሚባል በአባቱ አገርም በተሠራች ገዳም ሥጋውን አኖሩ ከሥጋውም ድንቆችና ተአምራቶች ተደረጉ ታላቅ ፈውስም ሆነ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህችም ቀን ቅዱስ አባት አንያኖስ አረፈ። እርሱም ለወንጌላዊ ማርቆስ ሁለተኛ የሆነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ነው።
የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ አረማውያን ናቸው እርሱም ጫማ ሰፊ ነበር ቅዱስ ወንጌላዊ ማርቆስም ወደ እስክንድርያ አገር መጀመሪያ በገባ ጊዜ እግሩን ተደናቅፎ ጫማው ተቆረጠ እንዲሰፋለትም ወደ ጫማ ሰፊ አንያኖስ ዘንድ ሔደና ጫማውን ሰጠው መስፋትም በጀመረ ጊዜ መስፊያው ጣቱን ወጋው በዮናኒም ቋንቋ አታኦስ አለ ትርጓሜውም አንድ እግዚአብሔር ማለት ነው። ቅዱስ ማርቆስም የእግዚአብሔርን ስም ሲጠራ በሰማ ጊዜ ደስ ብሎት የክብር ባለቤት ክርስቶስን አመሰገነው።
ከዚህም በኋላ አፈር አንሥቶ በምራቁ ጭቃ አድርጎ በአንያኖስ ጣት ላይ አደረገውና በዚያን ጊዜ አዳነው አንያኖስም ከዚህ ድንቅ ምልክት የተነሣ አደነቀ ቅዱስ ማርቆስንም ወደ ቤቱ ወሰደው ስለ ሥራው ስለ አምልኮቱም የመጣውም ከወዴት ቦታ እንደሆነ ጠየቀው።
ቅዱስ ማርቆስም ከብሉያትና ከሐዲሳት መጻሕፍት የአንድ እግዚአብሔርን ህልውና ስለ ዓለሙ ሁሉ ድኅነት የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን፣ መከራ መስቀልንም ተቀብሎ ስለመሞቱ፣ ስለ ትንሣኤውና፣ ስለዕርገቱ፣ ዳግመኛም ለፍርድ ስለ መምጣቱ ይነግረው ጀመረ።
የአንያኖስም ልቡ ብሩህ ሆኖለት በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር ተጠመቀ። የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ በላያቸው ወረደ አዘውትሮ በመጠመድ የሐዋርያ ቅዱስ ማርቆስን ትምህርት የሚሰማ ሆነ የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ሕጓንና ሥርዓቷንም ተማረ።
ቅዱስ ማርቆስም ወደ ሌሎች አገሮች ሒዶ ለማስተማር በፈለገ ጊዜ እጆቹን በአንያኖስ ላይ ጭኖ በግብጽ አገር ለወገኖቹ ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ ሊቀ ጵጵስና ሾመው እርሱም ብዙዎችን አስተምሮ አጠመቃቸው በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው ቤቱንም ቤተ ክርስቲያን አደረጋት እርሷም በስተምዕራብ ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ ያለች ዛሬ የሰማዕት ቅዱስ ሰርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሁና የታወቀች ናት።
ይህ የተመሰገነ አባት አንያኖስም በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages