አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
የቅዱስ ሰርጊስ ሰማዕት ቤተክርስቲያን የከበረችበት ነው፣ ቅዱስ ሐዋርያ በርተሎሜዎስ የልደቱና በእልዋህ አገር ላደረገው ተአምር መታሰቢያው ነው፣ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ከሚስቱ ጰጥሪቃ ከአምስት ወር ልጁም ከደማሊስ ጋር በሰማዕትነት ያረፈበት
ኅዳር ዐሥራ ዘጠኝ በዚች ቀን ሩጻፋ በሚባል አገር የሰማዕት ሰርጊስ ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት ነው።
ንጉሥ መክስምያኖስም ወደ ሶርያ አገር ወደ አንጥያኮስ በላካቸው ጊዜ ቅዱስ ባኮስን ከውኃ በማስጠም በጥቅምት ወር በአራተኛ ቀን ገደሉት። ቅዱስ ሰርጊስን ግን አሥሮ በወህኒ ቤት አኖረው።
ከዚህም በኋላ በእግሮቹ ውስጥ ረጃጅም የብረት ችንካሮችን ቸንከረው ከፈረሰኞች ጋር ሩጻፋ ወደሚባል አገር እንዲወስዱት መኰንኑ አዘዘ።
ሲወስዱትም ያስሮጡት ነበር ደሙም በምድር ላይ እንደ ውኃ ይፈስ ነበር በጐዳናም አንዲት ድንግል ብላቴና አገኘ ከእርሷም ዘንድ ውኃን ጠጣ ሥጋዬን ትወስጂ ዘንድ እስከ ሩጻፋ ተከተይኝ አላት እርሷም ራራችለት ለጒልምስናውም አዘነችለትና ተከተለችው።
አንጥያኮስም እንዲህ ብሎ ጽፏልና ሰርጊስ ትእዛዜን ተቀብሎ ለአማልክት ካልሠዋ ራሱን በሰይፍ ይቁረጡ። እርሱም ለቅዱስ ሰርጊስ ወዳጅ ነበርና ስለርሱም ይችን ሹመት አግኝቷት ነበርና በዚያንም ጊዜ ወታደሩ በጥቅምት ዐሥር የቅዱስ ሰርጊስን ራስ ቆረጠው ያቺም ብላቴና ቀርባ ከእርሷ ጋር በነበረ የፀጕር ባዘቶ ከአንገቱ የፈሰሰውን ደሙን ተቀበለች። የስደቱም ወራት እስከ አለፈ ድረስ ሥጋውን ጠበቀች።
ከዚህም በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያንን አነፁለት ዐሥራ አምስት ኤጲስቆጶሳትንም ሰብስበው አከበሩዋት በዚች ቀን ሥጋውንም በውስጧ አኖሩ ከእርሱም ድንቅ ተአምር ተገለጠ በእምነት ከእርሱ ለሚወስዱ ሁሉ በሽተኞችን የሚፈውሳቸው ሽታው እጅግ ጣፋጭ የሆነ የሽቱ ቅባት ከሥጋው የሚፈስ ሁኗልና።
በዚህችም ዕለት ጌቶቻችን ከሆኑ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት የአንዱ የቅዱስ ሐዋርያ በርተሎሜዎስ የልደቱ መታሰቢያው ነው፤ ደግሞም እልዋህ በሚባል አገር አስተምሮ ብዙዎችን እግዚአብሔርን ወደማወቅ ለመለሰበት መታሰቢያው ነው።
ለዚህም ሐዋርያ ሒዶ ያስተምር ዘንድ እልዋህ በሚባል አገር ዕጣው ወጣ። እርሱም ከጴጥሮስ ጋር በአንድነት ሔደ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አስተማሩ ልባቸውንም የሚያስደነግጥ ድንቆች ተአምራትን በፊታቸው ከአደረጉ በኋላ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መለሷቸው።
ከዚህም በኋላ ወደ ከተማው ውስጥ ገብቶ ያስተምር ዘንድ ምክንያት አደረገ ቅዱስ ጴጥሮስም እንደ ባሪያ ሸጠው። ባለ ጸጋ ለሆነ መኰንንም በወይን አትክልት ውስጥ የሚያገለግል ሆነ ድንቅ ተአምርን በማድረግ የተቆረጡ የወይን ቅርንጫፎች በሠራተኞች እጅ ላይ ሳሉ አፈሩ። የአገረ ገዥውም ልጅ በሞተ ጊዜ ከሞት አሥነሣው የሀገር ሰዎችም ሁሉ አመኑ እግዚአብሔርንም ወደ ማወቅ ተመለሱ።
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በርበር ወደሚባል አገር ሔዶ ያስተምር ዘንድ ሐዋርያ በርተሎሜዊስን አዘዘው እንዲረዳውም ሐዋርያ እንድርያስን ከደቀ መዝሙሩ ጋር ላከለት። የዚያች አገር ሰዎች ግን እጅግ የከፉ ስለሆኑ በፊታቸው ድንቆች ተአምራቶችን እያደረጉላቸው ሐዋርያትን አልተቀበሏቸውም።
ጌታችንም ሰውን ከሚበሉ አገር አንዱን ገጸ ከልብ ይታዘዝላቸው ዘንድ በሚያዙት ሁሉ ትእዛዛቸውን እንዳይተላለፍ አዘዘው። ሐዋርያትም ወደዚያች አገር ሁለተኛ ይዘውት ገቡ የሀገር ሰዎችም ሐዋርያትን ይበሏቸው ዘንድ ነጣቂዎች የሆኑ አራዊትን አወጡ። ያን ጊዜም ያ ገጸ ከልብ በአራዊቱ ላይ ተነሥቶ እየነጠቀ በላቸው ይህንንም ገጸ ከልብ ከመፍራት የተነሣ ከሰዎች በድንጋጤ የሞቱ ብዙዎች ናቸው።
የሀገር ሰዎች ሁሉም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ከሐዋርያትም እግር በታች ሰገዱ የሚሉአቸውን ሁሉ የሚያደርጉ ታዛዦች ሆኑ። ሐዋርያትም ቤተ ክርስቲያን ሠርተውላቸው ካህናትንም ሹመውላቸው ከእነርሱም ዘንድ ወጥተው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ሔዱ።
ሐዋርያ በርቶሎሜዎስም እግዚአብሔርን የማያውቁ ሰዎች ወደሚኖሩት በባሕር ዳርቻ ወዳሉ አገሮች ሔዶ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰበከላቸው በፊታቸውም ተአምራትን አደረገ ሁሉም የጌታችን በሆነች በቀናች ሃይማኖት አመኑ።
ሐዋርያ በርቶሎሜዎስም ከዝሙት ርቀው ንጹሐን እንዲሆኑ ሰዎችን የሚያዝዝ ሆነ። ንጉሥ አግሪጳም ስለርሱ በሰማ ጊዜ በከበረ ሐዋርያ በርቶሎሜዎስ ላይ እጅግ ተቆጣ። በማቅ ከረጢት ውስጥ እንዲአደርጉትና አሸዋ ሞልተው ከባሕር እንዲጥሉት አዘዘ። እንዲሁም ይህን አደረጉበት ምስክርነቱንና ተጋድሎውንም በዚች ዕለት ፈጸመ።
በዚችም ዕለት ቅዱስ ቴዎፍሎስ ከሚስቱ ጰጥሪቃ ከአምስት ወር ልጁም ከደማሊስ ጋር በሰማዕትነት አረፈ።
ይህም ቅዱስ እግዚአብሔርን በመፍራትና በአማረ አምልኮ ያደገ ነው ሰዎች ሒደው ቅዱስ ቴዎፍሎስ ክርስቲያን መሆኑን ለመኰንኑ ለአንቲጳጦስ ነገሩት መኰንኑም በዜውስ ጣዖት ቤት ሳለ ወደርሱ ያመጡት ዘንድ አዘዘ።
ቅዱሱንም በአቀረቡት ጊዜ አንተ ከወዴት ነህ ሃይማኖትህስ ምንድን ነው አለው። እርሱም የክብር ባለቤት ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን የማምን ክርስቲያን ነኝ አለ መኮንኑም በክፉ አሟሟት እንዳትሞት ለአማልክት ሠዋ አለው ቅዱሱም ክብር ይግባውና ከጌታዬ ከኢየሱስ በቀር ለረከሱ አማልክት አልሠዋም አለው።
መኰንኑም የሆድ ዕቃው እስቲታይ ሰቅለው ይሠነጣጥቁት ዘንድ አዘዘ እርሱ ግን በጌታችን ኃይል ስለተጠበቀ ምንም ምን አልደረሰበትም ሁለተኛም እሳትን አንድደው ከውስጡ እንዲጨምሩት አዘዘ ቅዱሱም በእሳት መካከል በጸለየ ጊዜ እሳቱ ተበተነ ምንም ምን ሳይነካው ከእሳት ውስጥ ወጣ።
መኰንኑም ይህን አይቶ በረኃብ እንዲሞት አሥረው አጽንተው ይጠብቁት ዘንድ አዘዘ ከስምንት ቀንም በኋላ ሚስቱ ጰጥሪቃ ሕፃኗን ተሸክማ መጣች ምስክርም ሁኖ በክርስቶስ ስም ይሞት ዘንድ አጽናናችው።
መኰንኑም ለቅዱስ ቴዎፍሎስ ምግብ የሰጠው እንዳለ ብሎ ሊመረምር ሔደ የእሥር ቤቱንም ደጅ በከፈተ ጊዜ ጣፋጭ የዕጣን መዓዛ ተቀበለው ቅዱስ ቴዎፍሎስንም በተነጠፈ መቀመጫ ላይ ተቀምጦ ሦስት መላእክት ማርና ወተት ሲመግቡት አገኘው በአየውም ጊዜ ደንግጦ ወደኋላው ተመለሰ።
በማግሥቱም ቅዱስ ቴዎፍሎስን ወደ አደባባይ እንዲአመጡት አዘዘ እርሱም ሚስቱ ተከትላው መጣ መኰንኑም ዲዮስ ለሚባል አምላክ ሠዋ አለው። ቅዱሱም እኔ ዓለምን ሁሉ ለያዘ ለእውነተኛው አምላክ ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለሌላ አልሠዋም አለ።
በዚያንም ጊዜ ለአንበሳ እንዲጥሉት መኰንኑ አዘዘ አንበሳውም ሩጦ እግሮቹን ሳመ። ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ አቆሰለው ተጋድሎውን በዚህ ፈጽሞ ነፍሱን ሰጠ። ቅዱስት ሚስቱ ጰጥሪቃም ሥጋውን አንሥታ ከሣጥን ጨመረች መኰንኑም እርሷንም ወደ አደባባይ አምጥተው ለአንበሳ እንዲሰጧት አዘዘ። ሕፃኑም አንበሳውን በአየው ጊዜ ሣቀ የአምስት ወርም ልጅ ሲሆን አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አምናለሁ ብሎ ተናገረ ይህንንም ብሎ በአንበሳ አፍ ከእናቱ ጋር ተበላ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment