ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 22 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 22

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ሃያ ሁለት በዚች ቀን የሊቀ መላእክት #ቅዱስ_ዑራኤል በዓለ ሲመቱ ነው፣ የከበረና የገነነ የመነኰሳት ሁሉ አባት አባት #ቅዱስ_እንጦንስ አረፈ፡፡


ጥር ሃያ ሁለት በዚህች ቀን ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል በዓለ ሲመቱ ነው፡፡
ኢዮር፣ ራማ እና ኤረር የተባሉ ሦስት የመላእክት ከተሞች አሉ፡፡ እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክት ከፈጠራቸው በኋላ በነገድ 100 በአለቃ 10 አድርጎ በሦስቱ ሰማያት አስፍሯቸዋል፡፡ ኢዮርን በ4፣ ራማን በ3፣ ኤረርንም በ3 ከፍሎ ነው በዐሥሩ ከተማ ያሰፈራቸው፡፡
በዚህም መሠረት ኢዮርን ላይና ታች አድርጎ በ4 ከተማ ከፍሏታል፡፡ በእርሷ ያሉትን መላእክትን በ40 ነገድ 4 አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያው ነገድ ‹‹አጋእዝት›› ይባላሉ፡፡ አለቃቸው ሣጥናኤል ነበር፤ እርሱም የመላእክትን ሁሉ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያሳርግ ነበር፡፡ ከክብሩ ሲዋረድ ቅዱስ ሚካኤል በምትኩ ተሹሞበታል፡፡ ሁለተኛው ነገድ ‹‹ኪሩቤል›› ይባላሉ፡፡ እነርሱም መንበረ ሥላሴን ይሸከማሉ፡፡ የቀሳውስት አምሳል ናቸው፡፡ አለቆቻቸው ገጸ ሰብና ገጸ አንበስ ናቸው፡፡ በሦስተኛው ከተማ በኢዮር ያሉት ሱራፌል ይባላሉ፡፡ የዲያቆናት አምሳል ናቸው፡፡ በትንቢተ ኢሳያስ በምዕራፍ 6 ላይ የተገለጹትና ኢሳያስን ከለምጹ እንዲፈወስ ያደረጉት ናቸው፡፡ አለቆቻቸው ገጸ ላህምና ገጸ ንስር ናቸው፡፡ (በነገራችን ላይ ‹‹ከሩቤል›› ወይም ‹‹ሱራፌል›› የሚባሉ የግለሰብ መጠሪያ ስሞች ስህተት ናቸው፡፡ አንደኛ እነዚህ ስሞች የብዙ መላእክት መጠሪያን የሚወክሉ ናቸው፡፡ ለአንዱ ሲሆን ‹‹ኪሩብ፣ ሱራፊ›› ይባላል፡፡ ‹ኪሩቤል› ወይም ‹ሱራፌል› ማለት ግን የብዙ ቁጥራቸው መጠሪያ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የቅዱሳን መላእክትን ስም እንዳለ በቁሙ ወስዶ ለግል መጠሪያ ስም ማዋል ተገቢ አይደለም፡፡ ‹‹ወለተ ሚካኤል፣ ክንፈ ገብርኤል….›› እየተባሉ ይሰየማሉ እንጂ ቀጥታ ‹ሚካኤል›፣ ‹ገብርኤል› እያሉ ሰዎችን መሰየም ስህተት ነው፡፡ 4ኛው ከተማ በኢዮር ያሉት ኃይላት ይባላሉ፡፡ የእሳት ሰይፍ ይዘው በሥሉስ ቅዱስ ፊት የሚቆሙ ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት የዛሉና የደከሙ ክርስቲያኖችን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ አለቃቸውም ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡)
ዳግመኛም እግዚአብሔር በራማ ያሉትን መላእክት በ30 ነገድ በ3 አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ‹‹አርባብ›› ይባላሉ፡፡ የሥላሴ እልፍኝ አስከልካዮች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን መንበር በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ሁለተኞቹ በራማ ከተማ ያሉት ‹‹መናብርት›› ይባላሉ፡፡ ለእግዚአብሔርን እጅግ ቅርብ የሆኑ ናቸው፡፡ የመብረቅ ጋሻቸውን የእሳት ጦራቸውን ይዘው የሥላሴ ጋሻ ጃግሬዎች ሆነው በተጠንቀቅ ይቆማሉ፡፡ የሰውን ችግር ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ፡፡ መዝ. 88፡6፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሦስተኞቹ በራማ ከተማ ያሉት ‹‹ሥልጣናት›› ይባላሉ፡፡ መላውን ፍጥረት ለመጠበቅ ሥልጣን የተሰጣቸውና የምጽአት ዕለት አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው፡፡ ዳን. 12፡1፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ሱርያል ነው፡፡
ዳግመኛም እግዚአብሔር በኤረር ያሉትን መላእክት በ30 ነገድ በ3 አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ‹‹መኳንንት›› ይባላሉ፡፡ የስላሴ የእሳት ባለ ቀስት ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ልዩ ጠባቂዎች ናቸው፤ በተለይ በአደጋ ጊዜ ሎጥን እንዳዳኑት ፈጥነው ይደርሳሉ፡፡ በዕለተ ምጽዓት የሰውን ሁሉ ዐፅም ሰብስበው ለትንሣኤ ዘጉባኤ ያበቃሉ፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ሰዳካኤል ነው፡፡ ሁለተኛዎቹ ‹‹ሊቃናት›› ይላሉ፡፡ የሥላሴ የእሳት ፈረሶች ናቸው፡፡ በእሳት ፈረስ ይመላለሳሉ፡፡ እነዚህም 24ቱ ካህናተ ሰማይ ሲሆኑ አለቃቸው ቅዱስ ሰላታኤል ነው፡፡ በኤረር ከተማ የሰፈሩት ሦስተኛዎቹ ‹‹መላእክት›› ይባላሉ፡፡ ፍጥረትን ሁሉ የሚጠብቁ ናቸው፡፡ አለቃቸው ቅዱስ አናንኤል ነው፡፡ በእነዚህ የማይጠበቅ ፍጥረት የለም፡፡ ከአዝርእት ጀምሮ ሁሉን ይጠብቃሉ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ 7 መላእክትን አየሁ›› (ራዕ. 8፡2) እንዳለ ሊቃነ መላእክት በቁጥር 7 ናቸው፡፡ እነርሱም፡- ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ቅዱስ ራጉኤል፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቅዱስ ፋኑኤል እና ቅዱስ አፍኒን ናቸው፡፡ ‹‹ዑራኤል›› የሚለው ስም ‹ዑር› እና ‹ኤል› ከሚሉ ሁለት ቃላት የተመሠረተ ስም ነው፡፡ ‹‹ዑራኤል›› ማለት ትርጉሙ ‹‹የብርሃን ጌታ፣ የአምላክ ብርሃን›› ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዑራኤል ከ7ቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ በመብረቅና በነጎድጓድ ላይ የተሾመ መልአክ ነው፡፡ በመሆኑም መጽሐፈ ሄኖክ እንደሚገልጸው መባርቅት ለጥጋብና ለበረከት እንዲበርቁ ነጎድጓድም ለሰላም እንዲሆን ያሰማራል፡፡ ምሥጢረ ሰማይንና ሰማያዊውን ዕውቀት ሁሉ ለሄኖክ የገለጸለት መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ የፀሐይን፣ የጨረቃን፣ የከዋክብትንና የሰማይ ሠራዊትን ብርሃንን የሚመራው ይኸው ገናና መልአክ ነው፡፡ መጽሐፈ ሄኖክ 28፡13፡፡
መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ በተሰቀለ ጊዜ ክቡር ደሙን በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ በብርሃነ መነሳንስ በዓለም ላይ የረጨው ይኸው ገናና መልአክ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ ዕውቀት ተሠውሮበት ለነበረው ለኢትዮጵያዊው ሊቅ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በእመቤታችን ትእዛዝ ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ ‹‹ዑራኤል የተባለ መልአክ ሊረዳኝ መጣ፡፡›› መጽሐፈ ዕዝራ 2፡1፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር የሕይወትና የይቅርታ ዝናም በምድራችን ላይ ያዘንብ ዘንድ እንዲሁም የእርሻችንን አዝመራ በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ ለምግብነት እንዲበቃ ከፈጣሪ ዘንድ ምሕረትን የሚለምን መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በመልአኩ አማላጂነት እጅግ ብዙ ድርሰቶችን የደረሱት መልአኩ ጽዋ ሕይወትን ካጠጣቸው በኋላ ነው፡፡ በመጀመሪያም አባ ጊዮርጊስ የተወለዱት በቅዱስ ዑራኤል አብሳሪነት ነው፡፡ በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ የተመሠረቱ አብዛኞቹ ቅዱሳት ገዳማት በቅዱስ ዑራኤል መሪነት ነው፡፡ ድርሳኑ ላይ የማይጠቅሳቸው የሀገራችን የከበሩ ቅዱሳት ገዳማትና ቅዱሳን ነገሥታት የሉም፡፡
የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክን ከልጇ ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስትሰደድ መንገድ እየመራ ወደ ግብጽ እና ወደ አገራችንን ኢትዮጵያ ያመጣቸው ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ እመቤታችንን ከተወደደ ልጇ ጋር በደመና ጭኖ መላ ኢትዮጵያን ካስጎበኛት በኋላ ቅድስት አገራችንን ለእመቤታችን የዓሥራት አገር እንድትሆን ያደረገው መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል በዓመት 3 ዓበይት በዓላት አሉት፡፡ ጥር 22 በዓለ ሲመቱ ነው፡፡ መጋቢት 27 የጌታችንን ክቡር የሆነ ወርቀ ደሙን ለዓለም የረጨበት ነው፡፡ ሐምሌ 22 ቀን ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የዕውቀትን ጽዋ ያጠጣበት ዕለት ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችህ ቀን በግብፅ አገር ከአቅማን ከተማ የከበረና የገነነ የመነኰሳት ሁሉ አባት በገዳም ለሚኖር እንደ ኮከብ የሚያበራላቸው አባት እንጦንዮስ አረፈ።
የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ንፁሀን ክርስቲያን ናቸው እርሱም ከታናሽነቱ ጀምሮ ተንኮል ሽንገላ በልቡ ውስጥ የለውም ከወላጆቹም ጋር ወደ ቤተክርስቲያን ሂዶ በቆረበ ጊዜ ከህፃናት ጋር በመጫወት ከቶ አይሳሳቅም ነበር።
ጥቂት በአደገም ጊዜ ራሱን ዝቅ አድርጎ ለወላጆቹ ይታዘዝ ነበር ሰባት አመትም በሆነው ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መፃህፍትን ተማረ ያን ጊዜም የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት አባ ቲዎናስ የተሾመበት ዘመን ነበር የእንጦንዮስንም ወሬውን ሰምቶ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣው ባረከውና ስለርሱ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ ይህ ህፃን በእግዚአብሄር ፊት ታላቅ ይሆናል ዜናውም በአለሙ ሁሉ ይወጣል እጁንም በላዩ ጭኖ ዲቁና ሾመው።
ከዚህም በኃላ ወላጆቹ በሞቱ ጊዜ ታናሽ ብላቴና እኅት ትተውለት ነበር።ከሰባት ወርም በኃላ እንደ ልማዱ ወደ ቤተ ክርስቲያን በሄደ ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ ፍቅር በልቡ አደረበትና በኀሳቡ በአለም የሚሰራውን ሁሉ አባቶቻችን ሀዋርያት ሁሉን የአለምን ስራ ትተው ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ተከተሉት በሀዋርያት ስራ መፅሀፍም እንደተፃፈ ጥሪታቸውን እየሸጡ የሽያጩንም ዋጋ በሀዋርያት እግር ስር ያኖሩትን አሰበ እግዚአብሄር በሰማያት ያዘጋጀላቸው ዋጋቸው ምን ያህል ይሆን አለ ይህም ኀሳብ በልቡ ውስጥ የሚመጣ የሚወርድ ሆነ።
ከዚህም በኃላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደ የክብር ባለቤት ጌታችን በከበረ ወንጌል ለባለፀጋው የተናገረውን ሰማ እንዲህ ሲል ፍፁም ትሆን ዘንድ ከወደድክ ሂድ ጥሪትህን ሁሉ ሸጠህ ለድኆች ስጥ በሰማይም ላንተ ድልብ አድርገው መጥተህም ተከተለኝ።
ከእግዚአብሄርም ዘንድ ይህን ልዩ ኀሳብ አግኝቶ ይህ ቃል ስለርሱ እንደተነገረ አሰበ በዚያንም ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን ወጣ ለአባቱም ያማረ ሰፊ ምድር ነበረው ለአገሩም ሰዎች ሰጣቸው ለርሱ የተውለትንም ጥሪታቸውን ሁሉ ሸጦ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጣቸው እኅቱንም ወስዶ ከደናግል ገዳም አስገባት።
በዚያንም ወራት የምንኩስና ስርአት አልተገለፀም ነበር እግዚአብሄርንም ለማገልገል የሚሻ ከመንደር ጥቂት ወጣ ብሎ ብቻውን በመቀመጥ በፆም በፀሎት ተወስኖ ይጋደላል የከበረ እንጦንዮስም እንዲሁ አደረገ ሰይጣናትም በስንፍናና በዝሙት ጦር የሚዋጉት ሆኑ በህልሙም የሴት ገፅ በማሳየት አብራውም እንደምትተኛ ያደርጓታል።
ከዚህም በኃላ በባህር ዳርቻ ወዳለች የመቃብር ቤት ሂዶ በዚያ የሚኖር ሆነ በላዩ በአደረ በእግዚአበሄርም ረድኤት በተጋድሎ በረታ ምግቡንም ከዘመዶቹ ወገን ያመጡላት ነበር ሰይጣናትም ሲጋደል አይተው ቀኑበት ታላቅ ዱብደባንም ደብድበው ጥለውት ሄዱ ዘመዶቹም ሲመጡ እንደ ሞተ ሆኖ ወድቆ አገኙት ተሸክመውም ወደ ቤተ ክርስቲያን ወሰዱት ጌታችንም አዳነው በነቃም ጊዜ ወደ ቦታው ተመልሶ ይጋደል ዘንድ ተጋድኖውን ጀመረ።
በዚያንም ጊዜ ሰይጣናትን ወደርሱ ሲመጡ አያቸው በአራዊት አምሳል በአንበሶችና በተኩላዎች የተመሰሉ አሉ በእባቦችና በጊንጦችም የተመሰሉ አሉ ያስፈሩትም ዘንድ አንዱም አንዱ በላዩ ተነሳሱ እንጦንዮስም በእኔ ላይ ለእናንተ ስልጣን ካላችሁ ከእናንተ አንድ ያሸንፈኝ ነበር ብሎ ዘበተባቸው ወዲያውኑ እንደ ጢስ ተበተኑ በሰይጣናት ላይ ድልን እግዚአብሄር ሰጥቶታልና ሰይጣናትም ከሚያመጡበት መከራና ስቃይ አረፈ።
ምግቡንም በአመቱ ሁለት ጊዜ ያበስላል በፀሀይም ያደርቀዋል ወደበአቱም ማንም እንዲገባ አያሰናብትም የሚሻውም ሁሉ በውጭ ይቆምና ድምፁን ይሰማል እንጂ ሀያ አመትም እንዲህ ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ በገደል ተጠምዶ ኖረ።
ከዚህም በኃላ ፍፁም የሆነ እግዚአብሄርን መፍራትንና አምልኮቱን ለሰዎች ወጥቶ ያስተምር ዘንድ እግዚአብሄር አዘዘው ስለዚህም ወደ ፍዩም አገር ወጥቶ ብዙዎች ደቀ መዛሙርትን ሰብሰቦ አስተማራቸው በእግዚአብሄርም ህግ አፀናቸው ደቀ መዛሙርቶቹ በውስጣቸው የሚኖሩባቸው ብዙዎች ገዳማት ተሰሩለት።
ስለ ሀይማኖትም ስደት በሆነበት ወራት በሰማእትነት መሞት ወዶ ወደ እስክንድርያ ሀገር ሄዶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመነ ከቶ አልያዙትም በክርስቶስም ስም የታሰሩ እስረኞችን በመጎብኘት ቢአረጋጋቸውና ቢአፅናናቸውም አልያዙትም መኮንኑም እንደማይፈራ ባየው ጊዜ ከፍርድ አደባባይ ውስጥ እንዳይታይ አዘዘው እርሱ ግን ሁልጊዜ መታየቱን አለተወም እንዲአሰቃየውና በሰማእትነትም እንዲሞት የሚያስቆጣውን ነገር ይናገረው ነበር መኮንኑም በእርሱ ላይ ምንም ክፉ ነገር አላደረገም አምላካዊት ኃይል ከልክላዋለችና።
ሊቀ ጳጳሳት ጴጥሮስ ለሰማእታት ፍፃሜ ሆኖ የመከራው ወራት ከአለፈ በኃላ እንጦኒ ወደ ገዳሙ ተመለሰ ይህም በአምላክ ፍቃድ ሆነ የሚለብሰውም ማቅ ነበር በዘመኑ ሁሉ ገላውን በውኃ አልታጠበም ብዙዎች በሽተኞችም ወደርሱ ይመጣሉ በላያቸውም ሲፀልይ ይድናሉ።
ብዙዎች ህዝቦችም ትምህርቱን ሊሰሙ ወደርሱ ሲመጡ በአያቸው ጊዜ ብቻውንም ይኖር ዘንድ እንዳልተውት አይቶ ከእርሱ ስለሚደረገው ነገር ልቡ እንዳይታበይ ፈራ እነርሱ ወደሚያውቁት ቦታ ወደላይኛው ግብፅ ይሄድ ዘንድ ወዶ ወደ ባህሩም ወደብ ደርሶ መርከብ እየጠበቀ ተቀመጠ ከሰማይም ወደርሱ ቃል መጣ እንዲህም አለው እንጦንዮስ ሆይ ወዴት ትሄዳለህ ከዚህስ ምን ትሻለህ አለው እርሱም ብዙዎች ወደእኔ ስለሚምጡ እንደምፈልገው ለብቻ መኖር አልተቻለኝም ስለዚህም ወደ ላይኛው ግብፅ እሄድ ዘንድ ወደድኩ አለ ያም ቃል መልሶ እንዲህ አለው ወደ ላይኛው ግብፅ ብትሄድ ድካምህ ደግሞ እጥፍ ይሆናል ብቻህን መኖር ከወደድክ ግን የሶስት ቀን ጎዳና ያህል ወደ ውስጠኛው በረሀ ተጓዝ።
በዚያንም ጊዜ በዚያች ጉዳና ሊጓዙ የሚሹ የዓረብ ሰዋችን አያቸው ወደ እርሳቸውም ሒዶ አብረሮአቸው ይሔድ ዘንድ ለመናቸው እነርሱም በደስታ ተቀበሉት ወደ አንድ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ እስከሚደርስ የሦስት ቀን ጉዳና ተጓዘ በዚያም የጠራና የቀዘቀዘ ውኃ አለ ዳግምም የሰሌን የተምር ዕንጨቶች መቃቃዎችም በብዛት አሉበት እንጦኒዮስም ያንን ቦታ ወደደው ዓረቦችም ምግቡን የሚያመጡለት ሆኑ ብዙዎች የከፋ አራዊትም ነበሩ በጸሎቱም እግዚአብሔር አስወገዳቸው ወደዚያም ቦታ ከቶ አልተመለሱም። አንዳንድ ጊዜም ወደ ባሕሩ ዳርቻ በመውጣት ደቀ መዛሙርቶቹን ጉብኝቶና አረጋግቶ በበረሀ ወስጥወደአለው ቦተው ይመለሳል ።
ከዚህም በኋላ በጸድቁ ንጉሥ ቁስጠንጢስዘንድ ዜናው በተሰማ ጊዜ በጸሎቱያስበው ዘንድ ንጉሡ አየለ መነዉ ደብዳበ ጻፈለት የከበረ እንጦንዮስ ግን ወደ ንጉሥ ደብዳቤ ዘወር አላለም ለወገኖቹ እንዲህ አላቸውእንጂ የንጉሠ ነገሥት ክርስቶስ ደብዳቤ እንሆበላያችን ይነበባል ወንድሞችም እንዲህ ብለው ለመኑት ይህ ንጉሥ የክርስቲያንን ወገኖች የሚወድ ጻድቅ ሰው ነው ደብዳቤ ጽፈህ ልታጽናናው ይገባል ከዚህም በኃላ እያፅናናውና እየባረከው ፃፈለት።
ዳግመኛም በአፍርንጊያ ንጉስ ዘንድ ዜናው በተሰማ ጊዜ ወደ ከበረ እንጦንዮስ እንዲህ ብሎ ፃፈ ወደ እኛ መጥተህ በእኛ ላይ በአገራችንና በሰራዊታችን ላይ በረከትን ታሳድር ዘንድ ስለ ጌታችን ክርስቶስ መከራዎች እኔ ወዳንተ ፈፅሜ እማልዳለሁ።
የከበረ እንጦንዮስም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ ቁሞም እንዲህ ብሎ ፀለየ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እለምንሀለሁ በአፍርጊያ ውስጥ ወዳለ ወደ በርኪኖን አገር እንድሄድ ፈቃድህ ከሆነ ምልክትን ግለጥልኝ ነገር ግን ያንተ ፈቃድ ይሁን ይህንንም ባለ ጊዜ ብርህት ደመና መጣች በዚያችም ሰአት ተሸክማ ወደ አፍርንጊያ አገር አደረሰችው ንጉሱም ደስ አለው ህዝቡና ሰራዊቱም ሁሉ በሽተኞችንም አቀረቡለትና ሁሉንም ፈወሳቸው የፅድቅና የህይወትንም መንገድ እያስተማራቸው ከእነርሱ ዘንድ ስድስት ወር ኖረ።
በእሁድም እለት ያቺ ብርህት ደመና ተሸክማ ወደ ገዳሙ ታደርሰውና ከልጆቹ ጋር ተገናኝቶ ያረጋጋቸዋል በማግስቱም ዳግመኛ ተሸክማ ወደ አፍርንጊያ አገር ትመልሰዋለች። ከዚህም በኃላ በእግዚአብሄር ፈቃድ በደመና ተጭኖ ወደ ገዳሙ አንደኛውን ተመለሰ።
በአንዲት እለትም ስንፍና መጣበት እንዲህ የሚለውም ቃል መጣ ታይ ዘንድ ወደ ውጪ ውጣ በወጣ ጊዜም መልአኩን አየው በላዩም የምንኩስና ልብስ አለ መታጠቂያ ቅናት የመስቀል ምልክት ያለው ቀሚስ በወገቡም አስኬማ በራስ ቁር አምሳልም በራሱ ላይ ቆብ አለ እርሱም ተቀምጦ ሰሌን ይታታል ከዚያም ተነስቶ ይፀልያል ዳግመኛም ተቀምጦ ሰሌኑን ይታታል በየሰአቱም እንዲህ የሚል ቃል ወደርሱ መጣ እንጦንዮስ ሆይ እንደዚህ ስራ አንተም ከሰንፍና ከሰይጣናት ጦርነት ታርፋለህ ያንን ያየውንም ተቀብሎ እንዲሁ አስመስሎ የሚሰራ ሆነ ከዚያችም እለት ወዲህ ስንፍናና የሰይጣናት ወጊያ አልመጣበትም።
የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ ተገልፆ አረጋግቶታል አፅንቶታልም። አሁንም እንዲህ አለው የመረጥሁህ እንጦንዮስ ሆይ በእውነት እነግርሀለሁ እኔን ስለመውደድህ በዚች በረሀ ውስጥ ብቻህን በመጋደልህና በማገልገልህ ስለ ድካምህ ስምህን ክፍ ከፍ አደርጋለሁ ስልጣንህንም በአለም ዳርቻ ሁሉ ከፍ አደርገዋለሁ።
ገዳማትንና አድባራትንም መነኩሳትን የተመሉ ሆነው ቅኖች የዋሀን ፃደቃን እንደሚኖሩባቸው አደርጋቸዋለሁ ይልቁንም ያንተ ገዳማት እነርሱ እስከ ፍፃሜ ይኖራሉ።
መታሰቢያህንም የሚያደርገውን ሁሉ ለድሆች ምፅዋትን ለቤተክርስቲያን መባ በስምህ የሚሰጠውን ሁሉ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስሳለሁ ከቶ ስቃይን አያያትም በውስጡ ስጋህ የሚቀበርበትንም ገዳም እጅግ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ በውስጡም እንደ መላእክት የሆኑ ደጋጎች መነኮሳት እንዲኖሩበት አደርጋለሁ ከእነርሱም እስከ አለም ፍፃሜ አለቃ የሚሆን አይታጣም የምድር ነገስታት መሳፍንትና ሹማምንት ለገዳምህና ፍለጋህን ለሚከተሉ ልጆችህም እጅ መንሻ ተሸክመው እንዲመጡ አደርጋለሁ ጌታችንም ይህንን ከተናገረው በኃላ ከእርሱ ዘንድ ወደ ሰማያት በታላቅ ክብር አረገ አባ እንጦኒም ፈፅሞ ደስ አለው።
ከዚህም በኃላ ስለ ቤተክርስቲያን መፍረስ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ መናፍቃን በላይዋ ይሰለጥናሉ ከዚህም በኃላ ወደ ቀድሞው ስርዓቷ ትመለሳለች ዳግመኛም ስለ መነኮሳት እነርሱ እጅግ እንደሚበዙ ገዳሞቻቸውንና አድባራቶችን በመተው ወርደው ከአለማውያን መካከል በከተማዎችና በቦታዎች ውስጥ እንደሚኖሩ ስለ አለም ፍፃሜም ትንቢት ተናገረ። ይህም አባ እንጦንዮስ አባ መቃርስን አስኬማንና የምንኩስና ልብስን ያለበሰው ያረጋጋውና ያፅናናው ከእርሱ የሚሆነውንም ያስረዳው ነው ደቀ መዝሙሩና ልጁ ስለሆነ።
ከዚህም በኃላ የገዳማውያን አለቃ ወደሆነ ወደ አባ ቡላ ሄደ እርሱም ለስጋው ያሰበና በሀዋርያዊ አትናቴዎስ ልብስ የገነዘው ነው።እረፍቱም እንደቀረበ በአወቀ ጊዜ በትሩን ለልጁ ለአባ መቃርስ ምንጣፉን ለአባ አትናቴዎስ የፍየል ሌጦ ዐጽፉን ለልጁ ለኤጲስቆጶስ ለአባ ስራብዮን እንዲሰጡ ልጆቹን አዘዛቸው።
ከዚህም በኃላ ከምድር ላይ ጋደም አለ ነፍሱንም በእግዚአብሄር እጅ ሰጠ ወደርሱም ሁሉም የመላእክት ማኅበር መጥተው በክብር በምስጋና ፍፁም ተድላ ደስታ ወዳለበት ዘላለማዊ እረፍት ተቀብለው አሳረጉት።
ስጋውን ግን ልጆቹ እንዳዘዛቸው ሰወሩት እርሱ የቅዱሳን ሰማእታትን ስጋቸውን የሚገልጡትን ይገስፃቸው ነበርና ስለ እነርሱ ስጋ ብዙ ገንዘብ እስከመቀበል ደረሰው አለማዊ ጥሪት ያደርጉታልና።
ይህም የከበረና የተመሰገነ አባት እንጢንዮስ እስከ መልካም ሽምግልና ደረሰ እጅግም አረጀ ግን ወደ ወደደውም ክርስቶስ እስከ ሄደ ድረስ መልኩ አልተለወጠም ብርታቱ ፅናቱም መላው እድሜው መቶ ሀያ አመት ነው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን መላእክት ጸሎትና ምልጃ ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages